Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ሐገር መውደድ ማለት ምንድን ነው ትርጉሙ?” (ክፍል ሁለት)

0 936

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ሐገር መውደድ ማለት ምንድን ነው ትርጉሙ?” (ክፍል ሁለት)

አሜን ተፈሪ

 

የድምጻዊ ጌታ መሳይ አበበን “አገር መውደድ ማለት ምንድነው ትርጉሙ?” የሚለውን የዘፈን ግጥም ስንኝ መነሻ አድርጌ የተነሳሁበትን የሀገር መውደድ ምንነት የምገልጽበትን መጣጥፌን ክፍል አንድ የቋጨሁት የጃፓኖችን ጉዳይ አንስቼ፤ በገዛ ጋዜጣቸው ያሉትን አውስቼ፤ የእኛን ደግሞ ይዤ ለመቅረብ ቃል ገብቼ ነበር፤ እናም ክፍል ሁለትን እነሆ!

አዎን! ጃፓኖች ማንኛውም ህዝብ ወይም መንግስት ኃይለኛ ወይም የሚተፈር ይሆን ዘንድ ዘመናዊ ዕውቀት ወይም ጥበብ መያዝ እንዳለበት ተረድተዋል፡፡ ስለዚህ ልጆቻቸውን ወደ ምዕራቡ ዓለም እየላኩ አስተማሩ፡፡ ሐገራቸውን ለማልማት እና ለማሳደግ የሚያስፈልገውን ሐብት ለመፍጠር ተፍጨረጨሩ፡፡ ስለዚህ የዓለምን ገበያ በእጃቸው ጨብጠው ከያዙት ሕዝቦች እና መንግስታት ጋር በመወዳደር ለማሸነፍ ተግተው ሰሩ፡፡ ይህንንም ሲያደርጉ፤ ብልጽግናን የሚፈልጉት የግል ኑሮአቸውን ለማመቻቸት አልነበረም፡፡ ገንዘባቸውን ለጌጥ እና ለምቾት ኑሮ ለማዋል ሳይሆን ሐገርን የሚጠቅም ቁም ነገር ለመስራት እያሰቡ ነበር፡፡

ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ለማምረት ሲያስቡ በዘመኑ ዕውቀት እና ጥበብ ሳይታገዙ የትም እንደማይደርሱ አውቀውት ነበር፡፡ ስለዚህ በአንድ የምርት መስክ ለመሰማራት ሲያስቡ አስቀድመው ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ አገሮች እየሄዱ ነጮች እንደምን አድርገው እንደሚሰሩት ጥበቡን ተምረው፣ ቀድተው፣ ወይም ሰርቀው አሰራሩን በትክክል ካወቁት በኋላ ወደ ሐገራቸው ተመልሰው በተማሩበት መስክ ተሰማርተው ተወዳዳሪ ለመሆን ተፍጨረጨሩ፡፡ በአጭር ጊዜ የዓለምን ገበያ በምርቶቻቸው አጨናነቁት፡፡

ይህን ሲያደርጉ በርካታ የውስጥ እና የውጭ ፈተናዎች ነበሩባቸው፡፡ እነኛን ፈተናዎችም በአስተዋይ መንፈስ እየመረመሩ ለመጓዝ ሞከሩ፡፡ ሮበርት ስታንዲሽ የተባለ አንድ አሜሪካዊ ደራሲ የጃፓን ህዝብ “የብርሃን ዘመን” እያለ በሚጠራው ዘመን፤ ምን ዓይነት ፈተናዎች እንደተጋረጡበት እና ፈተናውን እንደምን ባለ አስተዋይነት እንደ ተሻገሩት ለማሳየት የሚችል አንድ ድርሰት አለው፡፡ ይህም ድርስት “ሦስቱ ሸንበቆዎች” ሲል የሰየመው ነው፡፡

በታሪኩ የተሳለው እና የሐገሩ ደካማነት የቆጨው አባት፤ ልጆቹ የምዕራቡን ዓለም ሥልጣኔ እንዲቀስሙ በማሰብ ወደ ውጭ ይልካቸዋል፡፡ ወደ ውጪ የላካቸው ሦስቱ ልጆቹ በተለያየ መስክ ሰልጥነው ተመለሱ፡፡ ሦስቱም በሰለጠኑበት መስክ ተሰማርተው ትልቅ ሥራ መስራት ጀመሩ፡፡ በየሥራ መስካቸው ከአውሮፓ ነጋዴዎች ጋር ግንኙነት መስርተው ሲሰሩ፤ ጥበብ ያላቸውን የአውሮፓ ሰዎች እየጋበዙ በቤታቸው አሳርፈው እያቆዩ በሥራ እንዲረዷቸው ያደርጉ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ አባትዬው ልጆቹ ከጃፓን ባህል ባፈነገጠ ልማድ ውስጥ እየተዋጡ ይሄዳሉ የሚል ሥጋት አድሮበት ይጨነቅ ነበር፡፡ ልጆቹ ጃፓንነታቸውን እየረሱ የሔዱና ያገራቸውን ጠባይ እና ባህል ትተው የባዕድ ልማድ ያያዙ ስለመሰለው በልቡ ሥጋት አድሮበት ነበር፡፡

ይልቁንም፤ በአገራቸው ልማድ የጨዋና የመኳንንት ልጅ የሆነ ሰው ንግድ በመነገድ ገንዘብ ማግኘት የማይገባው ነውር ስለሆነ ነገሩ ያሳስበው ነበር፡፡ ልጆቹ ገንዘብ በመውደድ የተያዙ እና ነጋዴ በመሆናቸው ቅር የተሰኘው አባት፤ በሞት ወደዚያኛው ዓለም ሲሄድ በልጆቹ ሥራ ሊወቅሱት የሚችሉትን የአባት እና የአያቶችን ቁጣ እያሰበ፤ ለወላጆቹ ምን እንደሚመልስላቸው ግራ ገብቶት ልጆቹን ለመጠየቅ ይወስናል፡፡ አባቶቹ “የሐገርን ፍቅር እና የሐገርን ልማድ ለልጅ ልጆቻችን እንዴት አድርገህ አስተማርካቸው? የጣልንብህን አደራ በምን አኳኋን ፈጸምከው?” ብለው እንደሚጠይቁት አስቦ፤ ለዚህ ጥያቄአቸው ምን እመልሳለሁ? በሚል ጭንቀት፤ ሥጋቱን ለልጆቹ ሊያካፍላቸው ፈለገ፡፡

ይህ ታሪክ ጃፓኖች የአውሮፓን ስልጣኔ በተቀበሉበት ዘመን በአዲሱ እና በአሮጌው ትውልድ መካከል የነበረውን የአስተሳሰብ ግጭት የሚያመለክት ነው፡፡ አባትዬው ባህልን እና ሐይማኖትን መሠረት ያደረጉ ጥያቄዎች እያነሳ ለልጆቹ ብዙ ጥያቄ ካቀረበ በኋላ፤ ሁለቱ ልጆች የአባታቸውን ጥያቄ እርሱን በሚያረካ አኳኋን ሲመልሱለት አንዱ ግን ጥያቄውን በዝምታ ያልፈው ነበር፡፡ ስለዚህ አባትዬው በዝምታ ወደ ቆየው ልጁ አተኮረ፡፡ ቆጣ ብሎም፤ “ተናገር እንጂ! ነው ወይስ አይደለም?” ሲል ጠየቀው፡፡ ልጁም በአክብሮት አንገቱን ወደ መሬት ቀለስ አድርጎ፤

ወንድሞቼ አስቀድመው በነገሩ ሳያስቡበት ነው የመለሱልህ፡፡ እኔ ከመመለሴ በፊት አስባለሁ፡፡ እነርሱም እንደኔ አድርገው አስበው ቢመልሱልህ ኖሮ የሰጡህ መልስ እንዲህ በቶሎ አይመጣላቸውም ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ ለምሳሌ ወንድሜ ሾዢ መርከብ በሚሰራበት ቦታ ለመርከብ መሥሪያ የሚሆነውን ጥሩ ብረት ሲያቀልጥ ከማንኛው የብረት ዓይነት ጋር መቀላቀል እንዳለበት ሲወስን ለአንተ መታዘዝ አይገባውም፡፡ ወንድሜ አኪራ ደግሞ ስለ ዘመናዊው የጦርነት አቅድ ጉዳይ ክርክር ሲያደርግ ላንተ የሚታዘዝዝልህ አይመስለኝም፡፡ እኔም ላቀረብክልኝ ጥያቄ ግልጥ በሆነ አኳኋን እመልስልህ ዘንድ እሞክራለሁ፡፡ ሳልዋሽህ እውነተኛውን ነገር ልነግርህ መፍቀዴ ለአንተ ስላለኝ አክብሮት አንድ ማስረጃ ነው፡፡

….የአንተ አስዋይነት የበለጠ ሆኖ የሚገኝበት አጋጣሚ መኖሩ እውነት ነው፡፡ በጣም ብዙ ነገር አለ፡፡ በዚህ ነገር ምንም ሳለመነታ እታዘዝልሃለሁ፡፡ ነገር ግን እኔና ወንድሞቼ አንተ በማታውቀው ነገር ውስጥ ገብተን እንድንማር ሥራ እንድንለመድ አስበህ ወደ ውጭ አገር የላክኸን አንተ ነህ፡፡ በተማርነው መስክ ውስጥ የራሳችን ዳኞች እኛው ራሳችን ብቻ ነን፡፡ ነገሩ እንዲህ እንዲሆን የማትፈቅድ ብትሆንማ ኖሮ ወደ ውጭ አገር አትልከንም ነበር፤ ሲል መለሰለት፡፡

ከዚህ በኋላ አባትዬው አንድ መሠረታዊ ጥያቄ አነሳ፡፡     

“አሁን የሰበሰብኳችሁ የተከበሩ አባቶቼን ልገናኛቸው ነውና ስለሰጡኝ አደራ የሠራሁትን ልገልጥላቸው ከመሄዴ በፊት እናንተ ተወላጆቻችሁን ወዴት እንደምትመሯቸው ለማወቅ ፈልጌ ነው፡፡ የምትከተሉት እርባና የሌለው ሕይወታችሁ እውነተኛ ዓላማው ምንድን ነው? ፍጻሜውስ ምን ዓይነት ነው?›› ሲል ከሁሉ ታላቅ ለሆነው ልጁ ጥያቄ አቀረበለት፡፡

ልጁም ምላሽ ሰጠ፡፡

…ከመጀመሪያው ጀምሮ ዓላማችን ምን ጊዜም ቢሆን የተዛባ ሆኖ አያውቅም፡፡ ይኸውም ጃፓንን በመሬት ላይ ካሉት አገሮች ሁሉ የበለጠች እና ያየለች ለማድረግ ነው፡፡ አሁንም መልሼ እናገራለሁ፡፡ ዓላማዬ መቼም ቢሆን ከመንገዱ አልተዛባም፡፡ የሥራዬን አካሄድ በኖርኩበት ዓለም ከሚገኙት አስፈላጊ ነገሮች ጋር የተስማማ እንዲሆን አድርጊያለሁ። ሲል መለሰ፡፡

አባትዬውም መልሶ፤

“ልጄ ሆይ አንተ ሳሞራይ (መኮንን) ነህ፤ ይህን ነገር ረስተኸዋልን? ሳሙራይ ሰይፍ እንደታጠቀ ኖሮ፤ ሰይፍ እንደታጠቀ ይሞታል፡፡ እንደ ነጋዴ በገበያ ውስጥ መደብር አቁሞ የንግድ ሥራ አይሠራም፡፡ አንተ ግን ነጋዴ ሆንኽ፤ ከዚህ የባሰ ደግሞ ባለባንክ ብለህ የምትጠራውን ሥራ ትሠራለህ፤ እኔ ግን በወለድ አበዳሪ ብዬ እጠራሃለሁ፡፡ ለገንዘብ ብቻ ከማሰብ በቀር ሌላ አሳብ ሊኖርህ ከቶ አይችልምን?››

አሁንም ልጁ መለሰ፤

አባቴ በእናንተ ዘመን ሰይፍ ይሠራ የነበረውን ሥራ አሁን በኛ ዘመን የሚሠራው ገንዘብ ነው፡፡ ያለ ገንዘብ ደካሞች እንሆናለን፡፡ የዛሬ ዘመን ሰይፎች የሚገኙት በገንዘብ ነው፡፡ የዛሬው ዘመን ሰይፎችም መድፍ፣ ጠብመንጃ፣ መርከብ፣ መኪኖች ይባላሉ፡፡ እነሆ የዛሬ ዘመን ሰይፎች እነዚህ ናቸው፡፡ እኔ በምሰበስበው ሐብት እነዚህን ነገሮች ሁሉ ልንገዛ እንችላለን፡፡ አባቶቼ ይታጠቁ እንደነበረው እኔም ሰይፍ ታጠቅኩ እንጂ ሌላ ምንም ያደረግሁት ነገር የለም፡፡ የተለወጠው ዓለም ነው እንጂ እኔ አይደለሁም›› አለው፡፡ ለሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎችም ተመሳሳይ አርኪ ምላሽ ሰጠው፡፡ በመጨረሻም፤

ልጆቼ ሆይ ይህን ሁሉ ለናንተ መናገሬ ስለ ፈራሁላችሁ ነው፡፡ ለቤተሰባችን ስም እሰጋለሁ፡፡ ለተቀደሰችው አገራችንም እፈራላታለሁ፡፡ ባለፈው ጊዜ መጥፎ ምክሮች ሰጥቻችሁ ይሆናል፡፡ አድርጌው እንደሆን ዓይኖቼ እንደ አሁን ተገልጠው ስላላዩልኝ ነው፡፡ አሁን የመጨረሻ ቃሌ የውርድት ሥራ መስራት፣ ማታለል፣ መሸፈጥ፣ ገንዘብን አለመጠን መውደድ ለእናንተም ሆነ ላገራችሁ ከመጉዳት በቀር አይጠቅማችሁም›› በማለት ተናገረ፡፡

ጃፓኖች ከ1955 ዓ.ም (እኤአ) ጀምሮ የአውሮፓን ጥበብ ለማግኘት ሲሉ፤ ትምህርት ቤቶችን፣ የሙያ ተቋማትን፣ የሳይንስ እና የንግድ ሥራ ዕውቀት የሚገኙባቸውን ድርጅቶች አቋቋሙ፡፡ ጃፓን ከሁሉ ነገር በፊት የሚጠቅማት ኢንዱስትሪ ማቋቋም መሆኑን ተረድታለች፡፡  ይህንም ለማሳከት አስደናቂ ጥረት አድርጋለች፡፡

እንደሚታወቀው የአውሮፓ አገሮች ሊሰለጥኑ የቻሉት፤ አንዳንድ ግለሰቦች እየወጠኑ ባከናወኑት የጥበብ እና የዕውቀት ሥራ ተመርተው ነው፡፡ ይህን ሲያደርጉም እርምጃቸው በዝግታ እየተከናወነ በመሄዱ ብዙ ጊዜ አስፈልጓቸዋል፡፡ ጃፓን ግን እርምጃዋ የተከናወነው በንጉሠ ነገሥቷ እና በመንግስቷ መሪነት እና ተጠባባቂነት ውስጥ ሆኖ በመሆኑ፤ መሪዎቹ ጉልበቷ እንዳይባክን ለማድረግ ሲሉ ማንኛውም ሥራ ከመወጠኑ በፊት ከፍ ባለ ጥንቃቄ እንዲጠና ያደርጉ ነበር፡፡ በመጀመሪያ በውጭ ሠዎች ተደግፈው ሰሩ፡፡ በኋላ የውጭ ሰዎችን በራሳቸው ሰዎች ተኳቸው፡፡ ነጋዴዎች ሁሉ ዋናው ድካማቸውና ጥረታቸው ገንዘብ እየሰበሰቡ እና እየበለጸጉ ለመሄድ ነው ቢባልም፤ ጃፓኖች የተለየ ጠባይ ነበራቸው፡፡ የሐገራቸውን መንግስት እያከሰሩ ለመበልጸግ ሲፈልጉ አለመታየታቸው፣ ገንዘባቸውን ለማይረባ ነገር አለማባከናቸው፣ ለገንዝብ ሲሉ ከጠላት ጋር ሲሻረኩ አለመታየታቸው የጃፓኖች ልዩ ጠባይ ነው፡፡ ጃፓኖች ከግል ኑሮአቸው ይልቅ አብልጠው የሚመለከቱት የመንግስታቸውን ጥቅም እና ዕድገት ስለሆነ አገር የሚያናውጥ የአድማ ሠርተውም አያውቁም፡፡ ሐገር መውደድ ማለት ትርጉሙ እንዲህ ያለ ነው፡፡ እኛስ?

በእኛ በኩል ለሐገራችን ሕዝብ የልማት ጉዞ የሚበጁ እና በሰው ልጆች ሁሉ ዘንድ ድንቅ ተደርገው የሚታዩ እሴቶች በህገ መንግስታችን አስፍረናል፡፡ ህገ መንግስታችን በሰው ልጆች ዘንድ ድንቅ ተደርገው የሚታዩ እሴቶችን የያዘ ሰነድ ብቻ አይደለም፡፡ ሐገራችንን አስሮ ወደፊት እንዳትራመድ ቀይዶ ይዞ ያሰናከላትን ብዝሃነትን የማክበር ችግር ለመፍታት የሚያስችል ፖለቲካ እሴቶችንም የያዘ ሰነድ ነው፡፡ ጥያቄው ግን በዚህ ልክ እያሰብንና እየሰራን ነወይ ነው?

የሐገራችን ህዝብ አንድ ሰው ድሃ ሊሆን በሚችለው መጠን ድሃ ሆኖ የኖረ ህዝብ በመሆኑ፤ ደጋግሞ በሚከሰት ድርቅ እንደ ቅጠል ሲረግፍ የኖረ እና በግፍ አገዛዝ ቀንበር ጎብጦ ዘመናትን የተጓዘ አሳዛኝ ህይወት ሲገፋ የኖረ ህዝብ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ በኋላ ቀርነት ሰንሰለለት ተቀፍድዶ ሲማቅቅ የኖረ ህዝብ ነው፡፡ በቀን ሦስት ጊዜ መብላት ተስኖት የሚገኝ ህዝብ ነው፡፡ ይህን መራራ እውነታ በመገንዘብ እንደ ጃፓኖች በቁጭት በመነሳት ለሥራ መሰለፍ የሚገባው ህዝብ ነው፡፡ እናም ሙሉ በሙሉ እንደጃፓኖችም ባይሆን እንደራሳችን በህገመንግስታችን ያሰፈርናቸውን እሴቶች የተላበስን፤ ለግል ጥቅም ሳይሆን ለሀገር ልማት የምንለፋ በስራችንና በትሩፋታችን እውነተኛውን የሀገር መውደድ ስሜት የምናሳይ፤ ይህንን ሕዝብ ከዚህ የድህነት አረንቋ ለማውጣት የምንተጋ ዜጎች ልንሆን ይገባል!            

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy