Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መረጃ የማግኘት መብት

0 415

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መረጃ የማግኘት መብት

                                                          ደስታ ኃይሉ

መስከረም 18 ቀን 2010 ዓ.ም የዓለም የመረጃ ነጻነት ቀን ይከበራል። ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የመረጃ ቀን በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥም ዕለቱ ተከብሮ ይውላል። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ መረጃ ለአስተማማኝ ሰላምና ለዘላቂ ልማት ዋስትና ያለውን የዲሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት ታምኖበት በአዋጅ ተደንግጎ ወደ ስራ ተገብቷል።

በመሆኑም ማንኛውም ሰው የመንግሥትን መረጃ የማግኘት መብቱ በህገ መንግሥት የተረጋገጠለትና ይህም ባለፉት 26 ዓመታት እውን ሆኗል። በተለይ ባለፉት አስር ዓመታት በዚህ ረገድ የተከናወኑት ስራዎች ወሳኝ ናቸው። ምንም እንኳን መረጃ የማግኘት መብት ለሁሉም ዜጎች የተሰጠ ቢሆንም፣ መብቱን በስፋት የሚጠቀሙበት ሚዲያዎች በዘርፉ ተጠቃሚ ሆነዋል።

እንደሚታወቀው ሚዲያ አግባብ ባልሆነና ከራሱ ስነ ምግባር ባፈነገጠ መንገድ ጥቅም ላይ ከዋለ የሚያስከትለውን ችግር ያህል፤ በአግባቡና ስነ ምግባሮቹን ጠብቆ ከሰራ የሚያበረክተው ማህበራዊ ኃላፊነት ከፍተኛ ነው። በተለይም የሚዲያ ሙያ እምብዛም ባልዳበረባቸው እንደ እኛ ባሉ ሀገራት ውስጥ የህብረተሰቡን መሰረታዊ ፍላጎት ተመርኩዞ ሚዛናዊና ትክክለኛ ዘገባዎችን ከሰራ የሚጠበቅበትን ተግባር በበቂ ሁኔታ የሚወጣ ይመስለኛል። እናም እንደ መልካም አስተዳደር ዓይነት ተግባሮችን የማስተማርና የማሳወቅ ብሎም ከህብረተሰቡ የሚነሱ ችግሮችን በመመርኮዝ ተግባሩን ከተወጣ ሀገራዊ ኃላፊነቱን መወጣቱ አይቀርም።

በእኔ እምነት ሚዲያው በቅድሚያ በግርድፉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመንቀስ በፊት በጉዳዩ ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ እንዲያዝ ማስተማር ይኖርበታል። ይህም በተለያዩ ወገኖች መካከል በጉዳዩ ዙሪያ ያለውን የተለያየ አስተሳሰብ በተቻለ መጠን ወደ አንድ ለማምጣት ያግዛል። መልካም አስተዳደር የሂደት እንጂ የአንድ ጀምበር ስራ አለመሆኑን ማስተማር ይገባል።

እንኳንስ እንደ እኛ ያለ የዴሞክራሲ ጀማሪ ሀገር ቀርቶ፤ ተግባሩን ዕውን በማድረግ ከሁለት ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠሩት ምዕራባውያንም ቢሆኑ ዛሬ የደረሱበት የመልካም አስተዳደር አፈፃፀም የተሟላ ነው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም።

በመሆኑም መረጃ በማግኘት መብት ዙሪያ ከግንዛቤ እጥረትና ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ሁሉም ነገር የተሟላ ነው ማለት አይቻልም። ግን ረጅም ርቀት መጓዝ ተችሏል።

መረጃ የማግኘት መብት ሐሳብን ከመያዝና ከመተግበር ጋር የተያያዘ ነው። የሰው ልጅ ይጠቅመኛል ወይም ይበጀኛል የሚለውን አስተሳሰብ መያዝና መተግበር ይችላል። በዚህ ፅንሰ ሃሳብ ውስጥ ሃሳብን መያዝ እና መግለፅ የተሰኙ ሁለት ጉዳዩች አሉ። ምናልባትም እነዚህ ሁለቱም ጉዳዩች በተናጠል አሊያም በአንድነት ሊገለፁ ይችላሉ።

በተናጠል ሲገለፁ አንድ ሰው የመሰለውን ሃሳብ ይዞ ምንም ዓይነት ተግባራዊ ውሳኔ ላይወስድ የሚችልበትን ነባራዊ ዕውነታን ያመላክታሉ። በአንድነት ሲገለፁ ደግሞ፤ አንድ ሰው የመሰለውን ሃሳብ መያዝ ብቻ ሳይሆን፣ በተግባርም ሃሳቡን በፈለገው መንገድ እንዲያራምድ የሚያስችለውን አውድ ይፈጥሩለታል። ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት አይኖርበትም።

ይህም በሀገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ የሰው ልጅ አንድን ሃሳብ ስለያዘ አሊያም የያዘውን ሃሳብ በፈለገው የመገናኛ መንገድ ስለገለፀ ሊጠየቅ አይችልም፤ ይልቁንም ህጋዊ ከለላ አግኝቶ እንዳሻው ሊገልፀው ይችላል። ይህም ፌዴራላዊ ሥርዓታችን ካለፉት ስርዓቶች ምን ያህል የተለየና ዜጎችን መብቶቻቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ ህጋዊ ከለላ የሚሰጥ መሆኑን ያረጋግጣል።

የኢትዮጵያ ህዝቦች ተስፋቸው ከሰላም፣ ከልማትና ከዴሞክራሲ ጋር የቶራኘ ነው። ለዘመናት አንገታቸውን ሲያስደፋ የነበረውን ድህነትን ድል ለመንሳት ቆርጠው ተነስተዋል። ይህን መከወን እንደሚችሉም ባለፉት 26 ዓመታት ገደማ ተጨባጭ ውጤቶችን ማየት ችለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝቦች የአስተማማኝ ሰላም፣ የፈጣንና ተከታታይ ዕድገት እንዲሁም ስር በመስደድ ላይ የሚገኝ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባለቤቶች ሆነዋል። ከአፍሪካ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃርም፤ ብዙዎቹ የአህጉሪቱ ሀገራት ማሳካት ያልቻሏቸውን መሰረታዊ የለውጥ ሂደቶችን ማሳካት ችለዋል። የተለያዩ አፍሪካዊ ወንድሞቻችን ከእኛ የስኬታማ ውጤቶቻቸንን ተሞክሮዎች ወደ አገራቸው በመውሰድ እየተጠቀሙበት ነው።

የማንኛውም ሀገር መገናኛ ብዙሃን (ፕሬስ) የሚሰራው በአገሪቱ ፖለቲካል ኢኮኖሚ አውድ እንደመሆኑ መጠን፤ እዚህ ሀገር ውስጥ የሚከናወኑ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ተግባራትን በመደገፍና ህፀፆችን ነቅሶ በማሳየት የህዝቦችን ከድህነት የመውጣት ተስፋ ምሉዕ ሊያደርግ ይገባል።  

በሕገ መንግስቱ ላይ ሃሳብን በነፃነት ከመያዝና ከመግለፅ አኳያ የተጠቀሰው ሌላኛው ጉዳይ  በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙ መገናኛ ብዙሃንን ይመለከታል። መገናኛ ብዙሃኑ የህዝቡን የመረጃ ፍላጎት ለማርካት ማናቸውንም አስተሳሰቦች እኩልና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማስተናገድ ይጠበቅባቸዋል። ይህም ሃሳብን በነፃነት ለመያዝና ለመግለፅ የተደነገገውን ህገ መንገስታዊ መብት ዕውን እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል።

የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ተጠሪነታቸው ለህዝብ (ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት) እንደመሆኑ መጠን ሁሉንም ወገኖች በእኩልነት የማስተናገድ ህጋዊም ይሁን ሙያ ግዴታ አለባቸው።

መገናኛ ብዙሃኑ ያን ያህል የደረጀ ባይሆንም እስካሁን ድረስ ሁሉንም ወገኖች በማሳተፍና ድምፃቸው እንዲሰማ በማድረግ ረገድ ብዙ ርቀት ተጉዘዋል። ወደፊትም ይህን የዴሞክራሲ መንገድ ይበልጥ በማስፋት የበኩላቸውን ሚና ይወጣሉ ብዬ አምናለሁ።

‘…የሃሳብና መረጃ የማግኘት ነፃነት በአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትል በሚችለው አስተሳሰባዊ ውጤት ሊገታ አይገባውም’ የሚለው መርህ በህገ መንግስቱ ከለላ የተሰጠው ሌላኛው የዜጎች መብት ነው።

ይህ መርህ ዴሞክራሲያዊው መንግስት አንድ ሃሳብ ወይም መረጃ የቱንም ያህል አስተሳሰባዊ ውጤት ቢኖረውም፤ ማንኛውም ዜጋ ባስተላለፈው አሊያም በገለፀው ሃሳብ ወይም በፃፈው ፅሑፍ ተጠያቂ እንደማይሆን የሚያስረዳ ነው። ሆኖም በጋዜጠኝነት ካባ የሀገሪቱን ህገ መንገስትና ህጋዊ አሰራሮችን ወደ ጎን በማለት የሚሰራ ማንኛውም ሰው በህግ ፊት ተጠያቂ እንደሚሆን መዘንጋት አይገባም።

በአሁኑ ወቅት አገራችን ውስጥ መረጃን የማግኘት መብት ህገ መንግስታዊ ነው። የህዝብም ይሁን የግል መገናኛ ብዙሃን ይህን መብት በሚገባ መጠቀም አለባቸው። መብቱን እንዳይነፈጉም ተገቢው የህግ ጥበቃ ተደርጎላቸዋል። እናም ህገ መንገስታዊ መብትተን ግለሰቦችም ይሁኑ መገናኛ ብዙሃን በተገቢው ሁኔታ ሊጠቀሙበት ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy