Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መብትን መወሰን ህገ መንግስታዊ ነው!

0 467

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መብትን መወሰን ህገ መንግስታዊ ነው!

                                                         ታዬ ከበደ

ህገ መንግስቱን መሠረት የራስን መብት በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ድረስ እውን ሆኗል። ይህ በህዝቦች ሙሉ ፈቃድ የፀደቀ መብትን ህዝቦች ራሳቸው ካልሆኑ ማንም ሊሽረው አይችለም። መብቱ የአገራችን ህዝቦች በመፈቃቀድ ላይ ተመስርተው የራሳቸውን መብት በራሳቸው እንዴት እንደሚወስኑ ከህገ መንግስታቸው ጋር አያይዘው የሚመለከቱበት ነው።

ይህ መብት ሁሉም የአገራችን ህዝቦች በፈለጉበት ወቅት ተግባራዊ የሚያደርጉት ነው። የአማራና የቅማንት ህዝቦች ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው ቀበሌዎች ውስጥ የተካሄደውም ሪፈረንደም ይህን መብት ከማረጋገጥ አኳያ እውን የሆነ ነው።

እርግጥ ይህን መብት አንዳንድ ወገኖች ሀገርን ከመበታተን ጋር በማያየዝ ሲገልፁት ይስተዋለሉ። ግን ሃሳባቸው ፈፅሞ የተሳሳተ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ የየትኛውም ዓይነት ፌዴራሊዝም ዋነኛ ዓላማ በአንድ ሀገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በልዩነታቸው ውስጥ ያለውን አንድነት አቻችሎ በጋራ እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ እናም በውስጧ ከ75 በላይ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን የያዘችው ሀገራችን ከፌዴራሊዝም ውጭ ሌላ ምርጫ ሊኖራት አይችልም፡፡

ስለሆነም እነዚህ ህዝቦች በልዩነታቸው ውስጥ ያላቸውን አንድነት ለማጠናከር እንዲሁም ተፈቃቅደውና ተከባብረው በመኖር የጋራ ቤታቸው የሆነችውን ሀገራችንን ለማልማት ቃል ኪዳን ገብተዋል፡፡ እነዚህ ህዝቦች በራሳቸው ቋንቋ እየተጠቀሙና እየተዳኙ ብሎም ባህላቸውን እያሳደጉ ከፌዴራሉ አንድነት የሚገኘውን የጋራ ጥቅም በመቋደስ የአብሮነት ጉዟቸውን ምቹ አድርገዋል፤ ውጤታማም ሆነዋል፡፡

በአንቀጽ 39 ስር የተደነገገውና የብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል መብትም የሀገራችንን ፌዴራሊዝምን ልዩ ገጽታ የሚያላብሰው የማዕዘን ድንጋይ ነው፡፡

ይህ አንቀፅ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድና በአንድነት መኖር የሚያስችላቸውን ዴሞክራሲያዊ የአንድነት ዕድልንም አብሮ ይሰጣል፡፡ ታዲያ ይህን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለመፍጠር ህዝቦች የእኩልነት መብታቸው መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

በመሆኑም በአንቀጹ አማካኝነት የእኩልነት መብት ማረጋገጫ የሆኑት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ታሪኮች ወዘተ ተከብረዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በፖለቲካዊ አስተዳደር በኩል እኩል የመሳተፍ መብት ያገኙ ሲሆን፤ በልማት ስራው ላይም እኩል ዕድል እዲያገኙና በውጤታቸው መሰረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ተችሏል፡፡

ታዲያ እነዚህን መብቶች ሁሉ ያረጋገጠ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በምን ምክንያት ሊገነጠሉ ይችላሉ? የመብቶቹ ባለቤት በመሆኑም ጥቅሞቹን እያጣጣመ የፌዴራል ስርዓቱን ያጠናክራሉ እንጂ በምን ዓይነት የሂሳብ ቀመር ሊበታተኑ ይችላሉ?

በመሆኑም አንዳንድ ወገኖች በአንቀጽ 39 ላይ ያላቸው የስጋት ምንጭ ቀዳሚዎቹን አሃዳዊ ስርዓቶች ከመናፈቅ የመጣ አሊያም ህገ -መንግስቱን ቀድዶ ለመጣል ከመፈለግ የመነጨ ከመሆኑ በስተቀር እስካሁን ድረስ ያለው ተጨባጭ እውነታ የመበታተን ስጋትን የሚያመላክት አይደለም፡፡

ይህ የሀገራችን ተጨባጭ ሃቅም በመስኩ ምሁራን የተረጋገጠ ነው፡፡ የፌዴራሊዝም ምሁሩ ጆርጅ አንድርሰን እንደሚናገሩት፤ ምንም እንኳን የመገንጠል ጥያቄ ሊኖር የሚችለው በፌዴራል ስርዓቱ ውስጥ ነው ተብሎ ቢታሰብም እስካሁን ድረስ ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚያመላክተው አብዛኛዎቹ አሃዳዊ መንግስታት መበታተናቸውን ነው፡፡ እግርጥም “አራምባና ቆቦ” ስጋት ይሏል እንዲህ ነው፡፡

ያም ሆነ ይህ፤ በፌዴራሊዝም ስርዓታችን ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኘው አንቀጽ 39 የአንድነታችን ዋስትና እንጂ የመለያየታችን ስጋት ሊሆን አይችልም፡፡ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙና ይህ አንቀጽ የሌላቸው ሀገራት በብጥብጥና በሁከት እየታመሱ ያሉትም በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነትን ማምጣት ባለመቻላቸው መሆኑን ካሉበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር መመልከታችንም የዚሁ ውጤት ነው፡፡

በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እምነት፤ በግጭት ውስጥ እየታመሱ ያሉት እነዚያ ሀገራት ይህ አንቀጽ ቢኖራቸው ኖሮ እስካሁን ድረስ የተከሰተው ሰብዓዊና ማቴሪያላዊ ቀውስ ባልተፈጠረ ነበር፡፡

ታዲያ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም የብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ያለምንም ገደብ ያረጋገጠ ቢሆንም ዓላማው በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነትን በሀገሪቱ ላይ ለማምጣት እንደሆነ መገንዘብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡

የምንከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት አባሎቹ የሚናቆሩበትና የሚባሉበት ሳይሆን አብረው በፈቃዳቸው በጋራ የሚያድጉበት ስርዓት መሆኑ ሌላው ልዩ ባህሪው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች በጋራ ተባብረውና ተጋግዘው የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን ተደርጎ የተቀረጸው የፌዴራሉ ስርዓት በህገ – መንግስቱ ላይ በግልጽ መንጸባረቁ የጥንካሬው መገለጫ ነው፡፡

የህገ- መንግስቱን መግቢያ ቆንጥረን ብንወስድ እንኳን “…ጥቅማችንን፣ መብታችንንና ነጻነታችንን በጋራና በተደጋጋፊ ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን…” የሚለው ሃሳብ የፌዴራላዊ ስርዓቱ መገለጫ ህብረ – ብሔራዊነት ብቻ ሳይሆን መተጋገዝም ጭምር መሆኑን አመላካች ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም “መንግስት በዕድገት ኋላ ለቀሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ልዩ ድጋፍ ማድረግ አለበት” የሚለው የህገ – መንግስቱ አንቀጽ 89 (4) የዚህ የመተጋገዝ ፌዴራሊዝም መገለጫ ተደርግ የሚወሰድ መሆኑን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ በጥቅሉ በእነዚህ ጥቅሞች አማካኝነት በተፈጠረው የሀገራችን ፌዴራላዊ ስርዓት መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተዋል፡፡ ምላሾቹም ዘላቂ ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን እውን የሚያደርጉ ከመሆናቸውም በላይ፤ በርካታ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶች፣ ባህሎችና ታሪኮች ያሏቸው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፌዴራሊዝም ስር በመሆን ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸው እንዲጎለብት አስችለዋቸዋል፡፡

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ልዩነታቸው የስጋት፣ የአደጋ ብሎም የጦርነት ምንጭ ሳይሆን በራሳቸው ፈቃድ በመሰረቱት ፌዴራላዊ ስርዓት ጥላ ስር ሆነው በአስተማማኝ የሰላም ጎዳና ላይ መጓዝ ከጀመሩ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ በተለይ ባለፉት 10 ዓመታት የተጎናፀፉት ሰላም የዚህ እውነታ ማሳያ ነው፡፡ በድላቸው ባረጋገጡት አስማማኝ ሰላምም፤ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በህገ – መንግስቱ ዓላማ ጥላ ስር ሆነው የልማት ተጠቃሚነታቸውን በየደረጃው ይበልጥ ዕውን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

እነዚህ ውጤቶች በፌዴራል ሥርዓቱ አማካኝነት ያገኘናቸው ትሩፋቶች እንደመሆናቸው መጠን፤ ፌዴራሊዝም የጦርነት ደመናን ገፍፎ በሰላም መንደር ውስጥ እንድንኖር ብሎም እንዲሁም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን ያረጋገጠልን ነው ማለት እንችላለን፡፡

ስለሆነም የራስን መብት በራስ የመወሰን መብት ማለት የህዝቦች ሉዓላዊ የስልጣን መገለጫ እንጂ አገርን የመከፋፈል ተግባር ፈፅሞ ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ያለው በቀድሞ ስርዓት ናፋቂዎች ህሊና ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ መብት የዲሞክራሲያዊ አንድነታችን ማሳያ እንጂ የልዩነት ማስፊያ ሆኖ ስለማያውቅ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አማራና ቅማንት ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የተደረገው የህዝብ ውሳኔ ህዝቦችን የማይለያይ ይልቁንም ህገ መንግስታዊ መብትን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy