Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምክንያታዊነት መጎልበት በአዲሲቷ ኢትዮጵያ   

0 308

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

ምክንያታዊነት መጎልበት በአዲሲቷ ኢትዮጵያ   

አባ መላኩ

ሰሞኑን “የፍቅር ቀን” በሚል መሪ ቃል በአገራችን ያለውን የኃይማኖት የመቻቻልና አብሮነትነ በማስመልከት አንድ በዓል   ተከብሯል።  የአገራችን የኃይማኖት መቻቻል እጅግ ጠንካራና ዘመንን የተሻገረ፣ እጅግ የምንኮራበት የህዝቦች ጥልቅ ፍቅር የሚንጸባረቅበት እሴታችን ነው።  አገራችን  የአንድ ቤተሰብ አባለት  መካከል እንኳን  ሁለት እና ሶስት ዓይነት ኃይማኖቶችን የሚከተሉ  ግለሰቦች  አብረው  የሚኖሩበት  ነው።  እንኳን አሁን ሁሉም የፈለገውን ኃይማኖት በነጻነት መከተልና ማስፋፋት እንደሚችል ህገመንግስታዊ ዋስትና በተሰጠበት  ወቅት ይቅርና  ባለፉት የአጼዎቹ ስርዓት እንኳን  ህብረተሰቡ ተቻችሎና ተከባብሮ ኖሯል። ኢትዮጵያዊያን የኃይማኖት መቻቻልን ለዓለም ማስተላለፍ የሚያስችል   የዳበረ ተሞክሮ ያላቸው  ህዝቦች ነን። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  ይህን ድንቅ ባህላችንን ከለላ በማድረግ  የግል  ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን  ለማሳካት በሚፈልጉ ሀይሎች ምክንያት አንድነት በመሸርሸር  አንዳንድ ጽንፍ የወጡ አካሄዶችን እየተመለከትን ነው።

 

ሴኩዩራሊዝም /የሀይማኖትና የመንግስት መለያየት/ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ጠንካራ ህገመንግስታዊ መርህ ነው። ኃይማኖት በመንግሥት መንግሥትም በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደማይችሉ  የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት በግልፅ ደንግጓል፡፡ የመንግስት አሰራርና ኃይማኖታዊ ስርዓት የተለያዩ መሆናቸውን  በህገመንግስቱ አንቀጽ 11 ላይ፤  በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ኃይማኖታዊ መንግስትም ሆነ መንግስታዊ ኃይማኖት እንደማይኖር በግልጽ  ተደንግጓል። ይሁንና አንዳንድ ኃይሎች ፖለቲካንና ኃይማኖትን ሆን ብለው በመደበላለቅ የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም አልተሳካላቸውም። በተለይ ጽንፈኛው የዳያስፖራ ፖለቲከኛ ይህን ሰይጣናዊ ድርጊት በየማህበራዊ ሚዲያውና በመርዘኛ ሚዲያዎቻቸው ማሰራጨታቸውን ቀጥለውበታል።

 

አክራሪው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች አገራችንን ለማወክ  አንዱ በር ሲዘጋባቸው ሌላውን ሲያንኳኩ አንዱ ካርድ ሲበላባቸው ሌላውን ማፈላለግ ስራቸው አድርገውታል። ለአገርና  ህዝብ  የሚያስቡ አይደሉም።  የብሄር  መከፋፈያና  የግጭት  ታክቲካቸው  አልሆን ሲላቸው፤ ኃይማኖትን ከኃይማኖት ለማጋጨት የማያደርጉት ነገር የለም። ለዚህ ጥሩ አብነት የሚሆኑት አቶ ጃዋር ናቸው። አቶ ጃዋርና ተከታዮቻቸው  የብሄር ካርዳቸው ለሁከት ማነሳሻነት አልሳካ ሲላቸው  የኃይማኖት ካርዳቸውን፣ ይህ አልሆን ሲላቸው ደግሞ ሌላውን ለመጠቀም ከመሯርጥ ተቆጥበው አያውቁም። ሰሞኑን እንኳን አቶ ጃዋርና ተከታዮቻቸው  ባለፈው ዓመት በኢሪቻ በዓል በቀሰቀሱት ሁከት ሳቢያ   ህይወታቸው ላለፈ ወገኖቻችን መታሰቢያ እንዲሆን ለተሰራ ኃውልት የሚሰነዝሩትን አስትያየት ለተመለከተው እውነት እነዚህ አካላት ኢትዮጵያዊ ናቸው፣ እውነት እንወክለዋለነ ለሚሉት አካል ወገንተኛ ናቸው  ያስብላል። በዚህ አይነት የዘቀጠ ተገባር ህዝባዊ ነኝ ማለት አሳፋሪ ነው።     

 

ኢትዮጵያ የበርካታ እምነቶችና የበርካታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አገር ናት።  የኢትዮጵያ ህዝቦች ከብዙዎቹ የዓለማችን ህዝቦች  ቀድመው የክርስትናንም ይሁን የእስልምና እምነቶችን  ከመቀበላቸውም ባሻገር ምዕመናኑ ለዘመናት አብረው ተቻችለው መኖር የቻሉባት አገር ናት። በአዲሲቷ ኢተዮጵያ  ህብረብሄራዊነትን ማስተናገድ የሚያስችል ህገመንግስታዊ ስርዓት እውን ሆኗል።   በርካታ የዓለማችን አገሮች አንድ ኃይማኖት፣ አንድ ብሄር፣ አንድ ቋንቋ ኖሯቸው እንኳን  ለበርካታ ግጭቶች ተጋልጠው ተመልክተናል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የምትሆነው ጎረቤታችን ሶማሊያ ናት።   ሶማሊያ አንድ ብሄር፣ አንድ ቋንቋና ባህል ቢኖራትም  የአስተሳሰብ ብዝሃነትን ማስተናገድ ተስኗት በሁከት ስትናጥ ኖራለች።  እኛ ኢትዮጵያዊያኖች ግን በአገራችን የሚስተዋሉ በርካታ ልዩነቶችን ማስተናገድ የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት በመቻላችን ህዝቦች ተቻችለውና ተከባብረን   በአገራችን ያለውን ልዩነቶች አቻችለንና ተሳስበን  በሰላም መኖር  ችለናል።  

 

አሁን ላይ ዓለም በበርካታ ነገሮች ተቀይራለች። በዓለማችን ጽንፈኝነት እየተስፋፋ መጥቷል። ይሁንና ኢትዮጵያዊያን ዓለም በተለያየ ሁኔታዎች እየተናጠች ባለችበት ጊዜ እንኳን  ለዘመናት ያቆዩዋቸውን  እሴታቸውን ማስቀጠል ችለዋል። ለዚህ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ደግሞ አዲሲቷ ኢትዮጵያ የተመሰረተችበት የኢፌዴሪ ህገመንግስት እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻለል።  ጽንፈኛው የዳያስፖራ ፖለቲከኛ ይህን መልካም የህዝቦች ግንኙነት ለማሻከርና ግጭት በመፍጠር  ድብቅ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ጥረት  ቢያደርጉም ሊሳካላቸው  አይችልም። ምክንያቱም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ  የህዝቦችን መብት ወይም በህዝቦች መካከል አድልዖ ሊፈጥር የሚችል  አሰራር ተቀባይነት  ስለማይኖረው ነው።

 

ድብቅ አጀንዳ ያነገቡ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች  ዓላማቸውን ለማራመድ የትኛውንም መንገድ ከመተግበር እንደማይመለሱ ባለፈው ዓመት በአገራችን ተከስቶ በነበር  ሁከት ተመልክተናል። ጽንፈኛው ኃይል በኢሬቻ በዓል ላይ ምን እንዲከሰት እንዳደረገ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።  ጽንፈኛ ኃይሎች   ኃይማኖትን ለፖለቲካ  ፍላጎታቸው  ማሳኪያያነት ምርጫቸው የሚያደርጉት የኢትዮጵያ ህዝብ ለኃይማኖቱ  ቀናዒ መሆኑን ስለሚያውቁ፤ በቀላሉ  ብናነሳሳውና ሁከት መፍጠር  እንችላለን በሚል  የተሳሳተ  ስሌት  ነው። ይሁንና አሁን ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ማንም እንደፈለገው የሚዘውረው ህዝብ እንዳልሆነ በተግባር አሳይቷል።

 

አሁን ላይ ምክንያታዊነት በኢትዮጵያ ህዝቦች ዘንድ እየጎለበተ  እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ማንም ጽንፈኛ እየተነሳ እንዲህ አድርግ ወይም እንዲህ አታድርግ ስላለው ብቻ በጅምላ የሚነዳ እንዳልሆነ መታወቅ ይኖርበታል። እንደዳያስፖራ ፖለቲከኞች መርዘኛ መረጃዎች  ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ የምትባል አገር አትኖርም ነበር። ጽንፈኛው አካል ምንም ቢል  ሰሚ ጆሮ እና ተመልካች ዓይን መሳብ አልቻለም፤  ለዚህ ነው ምክንያታዊነት በአገራችን በመንገስ ላይ ነው ያልኩት።  

 

በአገራችን  ምክንያታዊነት እንዲጎለብት ማድረግ የተጀመረውን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና  ልማትን  ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ነው።  የምክንያታዊነት አስተሳሰብ  ሲነግስ ዜጎች  መብታቸውን መጠየቅ ብቻ ሳይሆን  ግዴታቸውንም እንዲወጡ ከማድረጉም በላይ  ሌሎችንም እንደራሳቸው  አድርገው ማሰብ ይጀምራሉ።   በጭፍንና ጥልቅ  ጥላቻ ናላቸው የዞረ አሊያም የግል የፖለቲካ ፍላጎታቸውን  በሁከትና በነውጥ  ለማሳካት  የሚፈልጉ ጽንፈኛ አካላትን  አካሄድ  ማጋለጥ  የእያንዳንዳችን አገር ወዳድ ዜጋ  ተግባር ሊሆን ይገባል።  

ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ጸረ ሰላም ኃይሎች  ኃይማኖታዊ ፖለቲካቸው  አልሳካ ሲላቸው የብሄር ፖለቲካ ካባቸውን  ይደርባሉ፤  ይህ ደግሞ አላስኬድ ሲላቸው ሌሎች የጥፋት መንገዶችን ማማተራቸው  መቼም የሚቆም ጉዳይ አይደለም።  የእነዚህ የጥፋት  ኃይሎች  ግብ አገሪቱን በማመስና  የግል ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን ማሳካት ብቻ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በቃችሁ ሊላቸው ይገባል። የህግ የበላይነት የሚረጋገጠው በመንግስት ብቻ ሳይሆን በሁሉም አገር ወዳድ  ዜጋ  ጥረት ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy