Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሥርዓቱ ከፋፋይ አስተሳሰቦችን አይቀበልም!

1 504

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሥርዓቱ ከፋፋይ አስተሳሰቦችን አይቀበልም!

                                                             ታዬ ከበደ

ኢትዮጵያ የምትከተለው የፌደራል ሥርዓት አንድ የጋራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብን በህዝቦች ፍላጎት ላይ ተመስርቶ እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው። ሥርዓቱ እንደ እገሌ የሚባለው ዘር ከዚህ ድንበር ማለፍ የለበትም የሚል ከፋፋይ አስተሳሰብን የሚቀበል አይደለም። በህዝቦች መፈቃቀድና ፍላጎት ላይ የተመሰረተች አገርን እውን ለማድረግ የሚተጋ ህዝብ በከፋፋይ ኋላ ቀር አስተሳሰቦች መጠመድ ሊኖርበት አይገባም።   

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በፍላጎት ላይ በተመሰረተ ሁኔታ አዲስ ሀገር ሆና ተደራጅታለች፡፡ ይህ ደግሞ የህዝቡን ማህበራዊ ሁኔታ፣ ቋንቋ፣ ባህል ከግምት ያስገባ ነው፡፡ ለዜጎችመ በጣም ምቹና ተስማሚ አደረጃጀት ነው፡፡ ስርዓቱ ዜጎች በራሳቸው ሙሉ ፍላጎትና ፈቃደኝነት ላይ ተመስርተው የመሰረቱት እንደመሆኑ መጠን የመቻቻል፣የመፈቃቀድና የአብሮነት እንጂ የሁከትና የግጭት መንስኤ ሊሆን አይችልም።

እንደሚታወቀው ሁሉ ግጭቶች በየትኛውም ሁኔታ ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ግጭት መፈጠር የለበትም ሊባል አይችልም፡፡ በየትኛውም ማህበረሰብ መስተጋብራዊ ግንኙነት ውስጥ  ግጭት መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ዋናው ጉዳይ እንዴት አድርገን ልናረጋጋቸው እንችላለን የሚለው ነው፡፡ ግጭቶች በራሳቸው መጥፎ አይደሉም፡፡ መጥፎ የሚያደርጋቸው አስተሳሰባችን ነው፡፡

ለውጥን መሰረት ባደረገ አስተሳሰብ ከተቃኘ፣ ግጭት የለውጥ መነሻ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ፌዴራሊዝም የግጭት መነሻ ነው የሚባለው አመለካከት መሰረት የሌለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት መቻቻልን ያመጣና በሂደትም በመጎልበት ላይ ያለ ነው፡፡ ምክንያቱም የስርዓቱ አወቃቀር ብዝሃነትን እንደ ውበት አድርጎ የሚነሳ በመሆኑ ነው፡፡ በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነትን በማጠናከር የመቻቻል መንፈስ እንዲዳብር ተደርጎ በህዝቦች ስለተዋቀረ ነው፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያ በምትከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት አያሌ ድሎችን ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ሕዝቦቿም የውጤቶቹ ተቋዳሽ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ይሁንና የቀድሞው ሥርዓት ተመልሶ ይመጣ ዘንድ ጨለምተኞቹ ሠላሙን አግኝቶ ኑሮውን ለመለወጥ የሚጣጣረውን ዜጋ ወደ ኋላ ለመጎተት የማይቀበጣጥሩት የለም፡፡

አስተማማኝነቱን በተግባር በማረጋገጥ ላይ የሚገኘውን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማጥቆር ሥራ የተጠመዱት እነዚህ ፅንፈኛ ኃይሎች የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን እድገትና አንድነት ሠላም ነስቷቸው የማይወረውሩት የአሉባልታ ድንጋይ የለም።  

እርግጥ ህዝቦች የዘመናት ጥያቄዎቻቸውን በመለሰው ህገ መንግስት መብቶቻቸውን ቢያጣጥሙም ውጣ ውረዶቹ ግን አልቀሩም፡፡ በተለይም ጨለምተኞችና ፅንፈኞች  ‘የፌዴራሊዝም ሥርዓት በኢትዮጵያ ተግባራዊ ከሆነ ሀገሪቱ ወደማያባራ ጦርነት ውስጥ ትገባለች፤ ሀገሪቱም የመበታተን አደጋ ይገጥማታል፣ ህዝቦቿም በየጎራው ተከፋፍለው እርስ በርሳቸው ይጨራረሳሉ’ የሚል ልቦለድ ድርሰት በመከተብ ማርታቸውን እንዳጧጧፉት የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በወቅቱ የሀገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃን ብዙ ደሰኮሩ፤ የፖለቲካ ተንታኞች ተብዬዎችም ብዙ ቀበጣጠሩ፤ ፅንፈኞችም ‘ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ለሀገሪቱ አይበጅም’ ሲሉ ብዙ አራገቡ፡፡

እርግጥ በወቅቱ ጨለምተኞቹና ፅንፈኞቹ በሀገሪቱ የተዘረጋው ፌዴራላዊ ሥርዓት ህዝቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠፍቷቸው አልነበረም— የቀድሞው ሥርዓት ናፋቂ ከሆኑት ኃይሎች ጋር በመሰለፍ ማቀንቀኑን መርጠው እንጂ፡፡ ግና ጨለምተኞቹና ፅንፈኞቹ ያሻቸውን ቢሉም መንግሥትና ህዝቡ በውዠንብራቸው ሳይዘናጉ ብዝኃነታቸውን ውበታቸው በማድረግ አንድነታቸውን አጠናክረው ለጋራ ዕድገት መረባረቡን መረጡ፡፡

በዚህም በሀገራችን ዕውን እየሆነ ያለው ሥርዓት በማህበራዊ መስተጋብሮች ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል አብሮ ለመጓዝና የማንነት ልዩነቶችን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሣሪያ መሆኑን አስመስክረዋል፡፡ ይህ አብሮነትም ዜጎች የጋራ ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ሥርዓቱ የጎላ ሚና እንደሚጫወት እምነትን አስይዞ በአዲስ የአስተሳሰብ መንፈስ ወደ ልማት ጎዳና መትመም ችለዋል፡፡

እናም ሥርዓቱ እነዚህን ሁሉ ውጣ ውረዶችን አልፎ ሰላምን ዕውን ያደረገ፣ ልማትን ያረጋገጠና በዚህም የህዝቦችን ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነትን ዕውን ያደረገ እንዲሁም ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የዴሞክራሲ ባህል ግንባታን መገንባት የቻለ ሆኗል፡፡ ምንም እንኳን ሥርዓቱ እነዚህን ውጣ ውረዶችን ተሻግሮ ሀገራችንንና ህዝቦቿን ዛሬ ላይ ላሉበት አስተማማኝ ቁመና ቢያበቃትም ቅሉ፤ አሁንም ተግዳሮቶችን እያስተናገደ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱት እነዚህ ተግዳሮቶች መሰረት ያደረጉት የህዝቡን ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙ ጉዳዩችን ቢሆኑም፤ ሀገራችን እየተከተለችው ባለው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አማካኝነት የተመዘገበው ድል በማይዋጥላቸው የውስጥና የውጭ ፅንፈኛና ፀረ-ሰላም ኃይሎች መጠለፉ እውነት ነው፡፡

የህዝቦች ጥያቄዎች በፅንፈኞችና ሀገራችንን ሁሌም በሚያስደነግጣቸው አንዳንድ የውጭ ሃይሎች መጠለፉም በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ውስጥ ሁከትና ግጭት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል፡፡

ያም ሆኖ ተግዳሮቶቹን መፍታት የሚቻለው በሥርዓቱ ብቻ ነው። እርግጥ ሀገራችን ውስጥ እየተተገበረ ያለው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ትናንት ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውን ውጣ ውረዶችን እየፈታና ችግሮችን እያረመ የመጣ በመሆኑ እነዚህ ተግዳሮቶች ይፈታል ብዬ አምናለሁ፡፡

ዛሬ ሥርዓቱን ተግዳሮቶቹ እየፈተኑት ቢሆኑም፤ የችግሮቹ አራማጅ ኃይሎች የዘመናት ጥያቄያቸውን በህገ መንገስቱ ያረጋገጡት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባለመሆናቸው፤ ከመንግስት ጋር ሆነው በሥርዓቱ አማካኝነት ተግዳሮቶቹን እንደሚፈቷቸው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

ትናንት ዜጎች በልማት አጀንዳ ተሳታፊ ስላልነበሩ ህይወታቸውን የሚለውጥ ሀብት የማፍራትና ከአገሪቱ ሀብት በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት አልነበራቸውም፡፡ የሕብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓቱ አንዱ መሠረታዊ እምነት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል በመሆኑ ይህ እንዲረጋገጥና ህገ መንግስታዊ ዋስትና እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡

ባለፉት መንግሥታት በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የኖረውን የተዛባ ግንኙነት በመፋቅ አዲስ ኢትዮጵያዊ ማንነት ለመገንባት የሚያስችሉ የማንነቶች እኩልነት ማረጋገጥ፣ ሁሉም ዜጎች ኢትዮጵያን በመገንባት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ፣ በአካባቢ ጉዳዮቻቸው ላይ ወሳኝ የሚሆኑበትን የራስ አስተዳደር ማረጋገጥ በአጠቃላይ ከአገሪቱ ልማት ተመጣጣኝ ጥቅም እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል፡፡

የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማንነቶች አዲስ የእኩልነት መንገስ መክፈቱንነና እንደ ማረጋገጫ መሣሪያ ስለተወሰደም በዚህ አወቃቀር አዲስ የእኩልነት ግንኙነትና የጋር ህልውና እንዲመሠረት ተደርጓል፡፡ በዚህም የአዲሲቷን ኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል የመወሰን ሥልጣን ባለቤት መሆን እንዳለባቸው በወኪሎቻቸው አማካይነት ይፋ አድርገዋል፡፡

የአገራችን ሀዝቦች በፌዴሬሽኑ ምሥረታ ወቅት የገቡትን ቃል በአፈፃፀም ሂደት እንዳይዛነፍ የመጠበቅ ኃላፊነት የሚሰጣቸውን ህገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን ህዝቦች እውን አድርገዋል፡፡ ይህም በመከባበር፤ በመተማመንና በመተባበር በእኩልነት አብሮ ለመኖር የሰላም ዋስትና ሆኗል፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ የሚገኝ አገርና ህዝብ ደግሞ ለከፋፋይ አስተሳሰቦች የሚረታ አይሆንም፡፡

 

 

 

  1. ethiopia yegnanat says

    “ግጭቶች በራሳቸው መጥፎ አይደሉም፡፡”

    አየህ የአንተ ከንቱነትና ደካማ አስተሳሰብ እንድሁም የእውቀትህ ጥግ በዚህች ዐረፍተ ነገር ላይ ያልቃል፡፡ “ግጭቶች በራሳቸው መጥፎ አይደሉም፡፡” ከግጭት የባሰ ምን መጥፎ ነገር ሊኖር ይችል ይሆን???? ነው ይሄ የምታዩት እተከሰተ ያለው ደም አፋሳሽ ግጭት ከትራጄዲ ድራማ ለይታችሁ አታዩትም???

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy