Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰላምም ጦርነትም የሌለበት ጉርብትና ኢትዮ – ኤርትራ

0 675

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዜና ትንታኔ

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሰላምም ጦርነትም የሌለበት ጉዞ በአገራቱ ሕዝቦች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን እየተናገሩ ናቸው። ይህ ጉዞ ካልተቋጨም ጉዳቱ አሁን ካለውም በላይ እንደሚሆን አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤትና ከተቀሩት አፍሪካ አገራት ጋር ባላት ግንኙነት ዙሪያ ምርምር የሚያደርጉትና “ጅቡቲ የጥገኝነት መስፈሪያ” እና “ብላክ ኢትዮጵያ” የተባሉ መጽሐፎች ደራሲ ዶክተር በለጠ በላቸው፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ ባለፉት ዓመታት ሰላምም ጦርነት በሌለበት ሁኔታ መቀጠላቸው በቀጣናው ውስጥ በጦርነት የሚጠባበቁ አገራት ሆነዋል። የኤርትራ መንግሥት ከአሸባሪዎች ጋር በማበርና የግብጽና የሌሎች የኢትዮጵያ ጠላቶች ተላላኪ በመሆን ኢትዮጵያ ለሰላም ከፍተኛ ዋጋ እንድከፍል አድርጓታል። በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣለቃ በመግባት አልፎ አልፎም ቢሆን ችግር እንዲፈጠር አድርጓል።

ኢትዮጵያም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነቷን ተጠቅማ በኤርትራ ላይ ባደረገችው ተጽዕኖ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እንድትገለል አድርጋለች። በዚህም በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ሽያጭና በሌሎች ድርጊቶቿ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብና በቀጣናው አገራት ተአማኒነትን እንድታጣ አድርጓታል።

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር የማነ ዘርዓይ፤ ከጦርነቱ በኋላ በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ ያሉት ወረዳዎችና ከተሞች የጦርነት ቀጣና ተብለው በዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ስለሚታሰቡ ቱሪዝምና ኢንቨስትመንት የማይካሄድባቸው፣ የግብርና፣ የትምህርትና ሌሎች መሠረተ ልማቶችም በሚፈለገው ደረጃ ያልተካሄደባቸው አካባቢዎች ሆነዋል፡፡ የአካባቢው ዜጎችም ሊሰደዱ ተገደዋል።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለጻም፤ የኤርትራ መንግሥት የውክልና ጦርነት ስለሚያደርግ ከአዋሳኝ ክልሎች በተጨማሪ በሶማሌ፣ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ግጭት እንዲፈጠር ሰርቷል። ክፍተቶችን በመጠቀም በውስጥ ጉዳይ ላይ ቢንዚን ያርከፈክፋል። በኢትዮጵያ ላይ ፍላጎት ላላቸው አገራት የጥቃት መሣሪያ ሆኗል። ከአሸባሪዎች ጋርም ግንኙነት በመፍጠር የአገሪቷን ሰላም ለማናጋት ሰርቷል፤ እየሰራም ይገኛል፡፡

ዶክተር በለጠ፤ ሁለቱ አገራት ወደ ጦርነት ባይገቡ፤ ሰላምም አውርደው ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን በአነስተኛ ገንዘብና በቅርበት ትጠቀም እንደነበር፤ በጅቡቲ ወደብ ላይ ያላትን ከፍተኛ ጥገኝነት በመቀነስ በተለይም ለሰሜንና ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ተደራሽና በዝቅተኛ ዋጋ መገልገል ትችልም ነበር ይላሉ። በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በሌሎች ዘርፎችም በመተሳሰር ሁለቱም አገራቱ ተጠቃሚነታቸው ከፍተኛ ሊሆን የሚችልበት ዕድሉ ሰፊ ሊሆን የሚችልበት ነበር ብለዋል።

በሁለቱ አገራት በኢንቨስትመንትና በንግድ አማካሪነት እንደሰሩና በአፍሪካ አርጊዩመንት ድረ ገጽ ላይ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት ሚስተር ቶኒ ካሮል እንደሚሉት ደግሞ፤ አገራቱ ስምምነት ቢኖራቸው ኖሮ ኢትዮጵያ ለመንገድና ባቡር ግንባታ ያወጣቸውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወደ ኤርትራ በመዘርጋት የግንባታ ዋጋዋ ይቀንስላት ነበር። ለሌሎች አገራት የምታቀርበው ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለኤርትራ ታቀርብ ነበር። በሁለቱም አገራት የሚካሄደው የማኑፋክቸሪንግ ምርት በሚዘረጉት መሠረተ ልማቶች የተነሳ ሁለቱም በዝቅተኛ ዋጋ ያመርታሉ፤ ይገበያያሉ፡፡ ሰፊ ኢንቨስትመንት ለማካሄድ ምቹና ተመጋጋቢ አገራት ይሆኑ ነበር።

እርሳቸው እንደሚያብራሩትም፤ ኤርትራ የባህር በር ስላላት ሙሉ በሙሉና በከፊል አምርታ ለኢትዮጵያ በመላክና ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የማኑፋክቸሪንግ እንቅስቃሴ ጋር በመተሳሰር የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል መሆን ትችል ነበር። ዝቅተኛ ዋጋ ያለው የኤርትራ ናቅፋ ከኢትዮጵያ ጋር ባለው የንግድ ትስስር ብቻ ይነቃቃ ነበር። በኢትዮጵያ ንግድ በርካታ ኤርትራውያን ነጋዴዎች ንቁ ተሳታፊ ስለነበሩ ሁለቱም አገራት ተጠቃሚ ይሆኑ ነበር፡፡ ሁለቱም አገራት ከየትኛውም አገር የተሻለ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የመሠረተ ልማት፣ የባህልና ሌሎች ነገሮች ትስስርና ተጠቃሚነት ይኖራቸው ነበር።

የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያስረዱት፣ ኤርትራ ከጦርነቱ በፊት ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው ምርት 67 በመቶ የሚሆነውን ወደ ኢትዮጵያ የምትልክ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያም የምግብ እህል በብዛት ትገዛ ነበር። ከጦርነቱ በኋላ ግን አገሪቱ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ምርት በዓመት ከ15 እስከ 17 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ሊሆን ችሏል፡፡ ከጦርነቱ በፊት በነበሩት ሰባት ዓመታት ብቻ ኢትዮጵያ ለኤርትራ ለወደብ አገልግሎት በአማካይ በዓመት አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ትከፍል እንደነበርና ይህም ከአገር ውስጥ ገቢ 25 በመቶውን ይሸፍናል።

በዚህና በሌሎች ችግሮቿ የተነሳ ኤርትራ ከጦርነቱ በኋላ የኢኮኖሚ እድገቷ ከሁለት በመቶ ያነሰ ሆኗል፤ የግሽበት መጠኑም ከ15 እስከ 18 በመቶ ደርሷል፡፡ ኢትዮጵያም የአሰብን ወደብ በአካባቢው ካሉት አገራት የተሻለ የወደብ አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ታገኝ እንደነበር፤ በሌሎችም ትስስሮች ተጠቃሚ ትሆን እንደነበር ምሁራኑና ድረ ገፆቹ ያትታሉ።

ዶክተር በለጠ ሰላምም ጦርነትም ያልሆነው አካሄድ ለሁለቱም አገራት ስለማያዋጣና የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ተገንዝቦ ፖሊሲውን ለመቀየር አቅጣጫ ማስቀመጡ ጥሩ እርምጃ ነው ባይ ናቸው። የኤርትራ መንግሥት እስኪወድቅ መጠበቅ ያለውን ችግር ማሰቀጠል ነው። አካባቢው በየወቅቱ የሚቀያየር በመሆኑ ችግር ሊመጣ ይችላል። የሁለቱን አገራት ችግር የሚፈታ ሁሉን አቀፍ የሆነ ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣ ሥራ መስራት ይገባልም ይላሉ።

ረዳት ፕሮፌሰር የማነ በበኩላቸው፣ እስካሁን ያለው የኢትዮጵያ ፖሊሲ የኤርትራን መንግሥት ማስወገድ የኤርትራ ሕዝብ ጉዳይ አድርጎ ያስቀምመጣል፤ ይህ አካሄድ ውጤታማ ስላልሆነና መንግሥቱም ካልተቀየረ ሰላም ስለማይኖር የሚወገድበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ይላሉ፡፡ አንደኛው አማራጭ ጦርነት ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከአሁን በፊት በዚያች አገር መንግሥት ላይ የተለያዩ ማዕቀቦች እየተጣሉበት መጥቷል፡፡ ነገር ግን ከኤርትራ መንግሥት ጋር የሚሰሩ አካላት በመኖራቸው በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ አልተሆነም። ዓለም አቀፍ ሕግን እየጣሱ ያንን መንግሥት በሚደግፉ አገራት ላይ ምን ዓይነት አቋም መያዝ አለባትየሚለውንና ይህን ለመስራት የሚያዋጣውን አቅጣጫ በማስቀመጥ መስራት ይገባል ይላሉ።

የቀድሞው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኢታማዡር ሹም የነበሩት ሌተናል ጀነራል ገብረጻደቃን ገብረተንሳይ በበኩላቸው፤ በኤርትራ ላይ የተቀመጡትን ሁለቱን አማራጮች መውሰድን እንደሚቻል አንስተው፤ የዲፕሎማሲው መንገድ እንደማያዋጣ ሲረጋገጥ ወታደራዊ እርምጃ የመጨረሻ አማራጭ መሆን እንዳለበትና የኢሳይያስ አፈወርቂን መንግሥት በማስወገድ የሁለቱን አገራት ሕዘቦች ሰላምና ተጠቃሚነት ማምጣት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ምሁራኑ እንዳሉትም፤ ሁለቱ አገራት ካላቸው መልካምድራዊ አቀማመጥና ጉርብትና ብሎም የባህለና ሌሎች ምስስሎሽ አንጻር ግንኙነታቸው ሰላማዊ ቢሆን ኖሮ አገራቱ ዛሬ በዓለም ላይ በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል ጉርብትና ይመሰርቱ ነበር፡፡ አሁን ያለው ሰላምም ጦርነትም የሌለው አካሄድ የማይገታ ከሆነም የሁለቱም አገራት ሕዝቦች አሁን እያጡት ካለው ጥቅምም በላይ ማጣታቸው አይቀርም፡፡ የሁለቱ አገራት አዳዲስ ትውልዶች በተፈጠሩ ቁጥርም የጠላትነት መንፈስን ይዘው ስለሚያድጉ ጉርብትናው ከወዳጅነት ይልቅ ባለመተማመን መመስረቱ አይቀርም፡፡

አጎናፍር ገዛኽኝ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy