Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስደትና ኢኮኖሚያዊ አንድምታው

0 263

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስደትና ኢኮኖሚያዊ አንድምታው

                                                         ዘአማን በላይ

ስደት የነባራዊ ሁኔታ ክስተት ነው። ሰው በተለያዩ ሁኔታዎች ከሀገሩ ሊሰደድ ይችላል። ሆኖም አብዛኛው የሚሰደደው የተሻለ ህይወት ፍለጋ ነው። የኢኮኖሚ ሁኔታ አንድን ሰው የተሻለ በተሻለ ሁኔታ ራሴን ለመራበት እችላለሁ ብሎ ወደሚያስበው ቦታ እንዲሰደድ ያደርገዋል። ይህን ሁኔታ ወደ እኛ ሀገር ስንመልሰው የሀገራችን ወጣቶች የሚሰደዱት ኢኮኖሚያቸውን በማሻሻል ራሳቸውን ጠቅመው ቤተሰባቸውን ብሎም ሀገራቸውን ለመጥቀም ነው።

ከእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ወጣቶች የሚሰደዱት በፖለቲካ ምክንያት አይደለም። ወጣቱ በሀገሩ የመኖር ህልውናው አጠራጣሪ የሆነበት፣ እየታፈሰ ወደ ጦርነት የሚማገድበት፣ በሚያራምደው የፖለቲካ አስተሳሰብ ምክንያት እስር ቤት የሚወረወርበት ዘመን ካከተመ 26 ዓመት አልፎታል።

ዛሬ ወጣቱ መንግስት ባዘጋጀለት ምቹ ሁኔታ የስራ ፈጠራ እድሉ ለምልሟል፣ የመኖር ዋስትናው ከፍ ብሏል፣ ጦርነት እያካሄደ ያለው ፊት ለፊቱ ከተጋረጠበትና ሀገራችንን ለዘመናት አንገት ሲያስደፋ ከነበረው ድህነት ጋር ነው። ዛሬ በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በመሳተፍ ሃሳቡን እንደ ልቡ መግለፅ ይችላል። እዚህ ሀገር ውስጥ የፀረ ዴሞክራሲያዊነት መጋረጃ ዳግም ላይከፈት ተከርችሞ ተዘግቷል።

ይህ ሁኔታም የሀገራችን ወጣቶች ስደትን ከመረጡ፣ የሚሰዱበት ምክንያት ምናልባት እግጅ ባልዳበረውና በተለያዩ ምክንያቶች ሁሉነም ወጣቶች በሚገባ መንገድ ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ እንጂ ከፖለቲካ ችግር ጋር የሚያያይዘው አንዳችም ምክንያት የለም። ምክንያቱም የፖለቲካ ችግር ከዛሬ 26 ዓመት በፊት በህዝቦች ሁለንተናዊ ትግል ምላሽ ያገኘ እንዲሁም የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቶች እየጎለበቱ በመምጣታቸው ነው።      

ታዲያ ሀገራችን ውስጥ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ይህ ከሆነ ዘንዳ፤ እዚህ ላይ ወጣቱ በሀገር ውስጥ ሰርቶ ማደግና መለወጥ እንደሚቻል ማስታወሱ ተገቢ ይመስለኛል። ስደትን በምንም ዓይነት ስሌት እንደ መጨረሻ አማራጭ መያዝ ተገቢ ይመስለኝም። በእኔ እምነት እዚህ ሀገር ውስጥ በመንግስት የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በሚገባ ሳይገነዘቡ ፊትን ወደ ውጭ ማዞር ተገቢ ሊሆን አይችልም።

የትኛውም ሀገር ማርና ወተት ከሰማይ እንደ መና የሚዘንብበት አይደለም። ከህይወት ጋር ልዩ ፈተናን መጋፈጥ ይጠይቃል። ውጣ ውረዶች አሉ። ታዲያ በባዕድ ሀገር ውጣ ውረዶችን ከበርካታ ስንክሳሮች ጋር ከማሳለፍ እዚህ ሀገር ውስጥ ባለው ሁኔታ በአነስተኛ ጥረት ራስን መቀየር የሚቻል ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው ወደ ስደት የሚሄዱ ወጣቶች መንስኤያቸው ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንደሆነ ሲገልፁ እናዳምጣለን። በርግጥ ድህነትና ስራ አጥነትን ለመቅረፍ የጥቃቱ ሰለባ የሚሆኑ ወጣቶች ቁጥር በቀላሉ እንደማይገመት የሚታወቅ ቢሆንም፤ የችግሩ መንስኤ ግን ሁሉንም ይወክላል ብሎ መፈረጅ የሚቻል አይመስለኝም። ምክንያቱም ወጣቶቹ ሰርተው መበልፀግ የሚያስችል ገንዘብ እያላቸው ወደ ውጭ የሚያማትሩበት ሁኔታ አግባብ አይመስለኝም።

ርግጥ ማንም ሰው በላቡ ጥሮና ግሮ ህይወቱን ለማሻሻል የማይሻ ሰው አለ ብሎ ለመናገር አይቻልም። ምክንያቱም መላው ህዝባችንና መንግስት ከድህነትና ኋላቀርነት ለመውጣት ከፍተኛ ትግል በማካሄድ ላይ የሚገኙበት ዋነኛው ምክንያታቸው ለዜጎች ብልፅግና እና ኑሮ መሻሻል ስለሆነ ነው።

ታዲያ ዜጎች ድህነትን ለመቅረፍ የሚያደርጉት ተነሳሽነት ትክክል አይደለም ሊባል የማይችል ቢሆንም፤ እዚህ ሀገር ውስጥ መስራት እየቻሉ በህገ ወጥ መንገድ ተታልለው የእነርሱ ሲሳይ መሆናቸው ግን ያሳዝናል። ያስቆጫልም። እናም እዚህ ሀገር ውስጥ ያለውን ሁኔታ ተጨባጭ ሰርቶ የመለወጥ ሁኔታን በአግባቡ ማጤን የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት በሀገራችን የተንሰራፋውን ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ መንቀሳቀስ ሲጀምር፤ ስራ አጥነት መቅረፍ አንደኛው ተግባሩ በማድረግ ነበር።

በዚህም በከተሞች የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራትን በማደራጀት እንዲሁም የብድር አገልግሎት በመስጠት ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ዜጎችም በየሙያቸው በመሰማራት ለሀገራዊው ልማት ከፍተኛ ጉልበትና አቅም መሆን መቻላቸው የትናንት ትውስታችን መሆኑ የሚካድ አይመስለኝም።

ዛሬ በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅተው ከመንግስት፣ ከቁጠባና ብድር ተቋማት ባገኙት ገንዘብ ተጠቅመው ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ባለቤትነት የተሸጋገሩ ዜጎች በርካታ ናቸው። ምን ይህ ብቻ። በሀገራችን ውስጥ እየተገነቡ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ማቀፍ የሚችሉ ናቸው። ይህም ራስን ችሎ ቤተሰብን ብሎም ሀገርን ለመጥቀም የሚያስችል መስክ መሆኑ ርግጥ ነው።

ወጣቶች በአሁኑ ወቅት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የስራ ዕድል በመፍጠር ላይ ይገኛሉ። የአገራችን ወጣቶች የመንግስትን ጥረት በመደገፍና የሀገሪቱን ልማት በማፋጠን ላይ እንደሚገኙ እዚሁ ሀገር ውስጥ ካለነው ዜጎች ባሻገር ሌላ እማኝ ከውጭ መቁጠር የሚያስፈልገን አይመስለኝም። ምክንያቱም እዚህ ሀገር ውስጥ የወጣቱን የስራ እድል ለማስፋት እየተከናወኑ ያሉ ጉዳዩችን ከእኛ ወዲያ ሊያውቅ የሚችል አካል ባለመኖሩ ነው።

ለአብነት ያህልም መንግስት ካዘጋጀው የ10 ቢሊዩን ብር ተንቀሳቃሽ ፈንድ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። ክልሎችም ከተመደበላቸው በጀት እየቀነሱ ለወጣቶች ስራ ፈጠራ ስራዎች እያዋሉ ነው። እነዚህ እውነታዎች ወጣቱን ከስራ ጠባቂነት ወደ ስራ ፈጣሪነት እንዲያዘነብል ያደረጉት ብቻ ሳይሆኑ፣ በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ “ቀጣሪ” ወጣቶችን መፍጠር ችለዋል።

ርግጥ ሁሉም ነገር ምቹና ምንም እንከን የሌለው ነው እያልኩ አይደለም። ጅምሮች ቢኖሩም አሁንም በአገራችን ውስጥ መሰረቱ ባልተናደው የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ ሳቢያ እዚህም…እዚያም ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች ቢሮክራሲው አላላውስ ሊል ይችላል። የመንግስት ስልጣን ህዝብን ማገልገያ መሆኑ ያልገባቸው አንዳንድ የስራ ሃላፊዎች የተግዳሮቶች ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ። ሌላ…ሌላም ችግሮች የወጣቶቹ ሳንካ ሊሆኑ መቻላቸውን ማንም አይክድም።

ሆኖም ወጣቶች እነዚህን ችግሮች ታግለው ማሸነፍ ይኖርባቸዋል። ሁሉንም ነገር ያለ አንዳች እንከን መጠበቅ የዋህነት ነው። እንኳንስ ገና ለሁሉም ጉዳዩች ጀማሪ በሆነችው ሀገራችን ውስጥ ቀርቶ “ሰልጥነዋል” በተባሉት ሀገሮችም ውስጥ ቢሆን ችግሮች መኖራቸው የግድ ነው። እናም ወጣቶች በሚያደርጓቸው የልማት ጉዞዎች ውስጥ የሚያጋጥሟቨቸውን ችግሮች ለመፍታት በቅድሚያ ችግሩ የተፈጠረበትን ነባራዊ አውድ ማጤን፣ ያ ካልሆነ ደግሞ አንድ ደረጃ ከፍ በማለት ችግሩን ለመፍታት መጣር ይኖርባቸዋል። ያኔም የማይፈታ ችግር አለመኖሩን ይገነዘባሉ። ችግሮችን ታግሎ በመፍታት የተፈጠረውን ሁኔታ መለወጥ ይቻላል። ይህም ፊትን ወደ ውጭ ላለማዞርና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶቻችንን እዚሁ ሀገር ውስጥ እንድንፈታ ያስችለናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy