በመግባባትና በመነጋገር የማይፈታ ችግር የለም!
በመግባባትና በመነጋገር የማይፈታ ችግር የለም!
ታዬ ከበደ
ስለ ግብር አስፈላጊነትና ጥቅም የማይገነዘብ ዜጋ ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ቢያንስ ግብር መክፈል ለዜጎች የሚሰሩት መሰረተ-ልማቶች ያለ ገንብ እጥረት እንዲካናወኑ ማድረግ መሆኑን ሁሉም ያውቃል። በቅርቡ ከቀን ገቢ ግብር ግምት ጋር ተያይዞ ያለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበር ይታወቃል። ሆኖም መንግስትና የንግዱ ማህበረሰብ በሰከነ ሁኔታ መነጋገር በመቻላቸው ቅሬታዎች ሁሉ ምላሽ በማግኘት ላይ ናቸው።
እስከ ሐምሌ 30 ቀን ድረስ የሚከፍሉት የደረጃ “ሐ” ግበር ከፋዩች ሁሉም ሊባሉ በሚያስችል ሁኔታ የሚጠበቅባቸውን ግብር ከፍለዋል። የደረጃ “ለ” እና የደረጃ “ሀ” ከፋዩችም በተመሳሳይ ሁኔታ በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የሚጠበቅባቸውን ግብር እየከፈሉ ነው። ይህም ከመግባባትና ከመነጋገር ማንኛውንም ችግር መፍታት እንደሚቻል የሚያሳይ ክስተት ነው ማለት ይቻላል።
እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመገንባት አቅዳለች። አገራችን በምታራምደው የፊሲካል ፖሊሲ መሰረት በ2012 ዓ.ም ፍፃሜውን የሚያገኘው የሁለተኛው የዕድገት እቅድ የወጪ በጀትን በሂደት በዋናነት በሀገር ውስጥ ገቢ በመሸፈንና የበጀት ጉድለት ዝቅተኛ እንዲሆን በማድረግ ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ምቹ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ለማስፈን ያለመ ነው።
በመሆኑም ባለፉት ዓመታት የታክስ ፖሊሲዎቹን በተሻለ ሁኔታ በማስተዳደር የመንግስት ገቢ ከፍተኛ ዕድገት እንዲያሳይ ተደርጓል። ሆኖም የታክስ ገቢው እያደገ ከመጣው የመንግስት የወጪ ፍላጎት አንፃር ብዙ የሚቀረው ሆኖ ተገኝቷል። እንዲሁም የታክስ ገቢው ዕድገት እየሳየ ቢመጣም፣ ምጣኔ ሃብቱ ሊያመነጭ ከሚችለው ጋር ሲነፃፃር የሚጠበቀውን ያህል መሻሻል አሳይቷል ተብሎ የሚገመት አይደለም።
ስለሆነም ባለፉት ዓመታት የታክስ ገቢው ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ብዙም ለውጥ ማሳየት አልቻለም። እናም በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የታክስ ገቢው ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 17 በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል። በተለይም ቀደም ባሉት ዓመታት ውስጥ በምንም ዓይነት የተክስ ስሌት ውስጥ ያልነበሩ ነጋዴዎችን ወደ ታክስ ስርዓቱ ማስገባት ይገባል።
የታክስ አስተዳደር መረጃ ሥርዓቱን ይበልጥ ማጠናከርና አሟጦ ጥቅም ላይ ማዋል፣ የታክስ ከፋዮችና የህብረተሰቡ በአጠቃላይ የታክስ ትምህርትና ግንኙነትን ማሳደግ፣ የታክስ ህግን ማስከበር እና የታክስና ገቢዎች መዋቅር ተቋማዊ አቅም ማሳደግ አሁንም ተገቢ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ነው።
በያዝነው የዕቅድ ዘመን የታክስ ስርዓቱን በጥብቅ ዲስፕሊን ተፈፃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው። በተጨማሪም የመንግስት ፋይናንስ አጠቃቀሙ ውጤታማነትን ለማሳደግ፣ የተሟላ ግልፅነትና ተጠያቂነት ለማስፈን፣ ብክነትን ለማስወገድና በጀቱን በቁጠባ ለመጠቀም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ስራው እየተከናወነ ነው። ይህም ከህዝቡ በታክስ መልክ የሚሰበሰበው ግብር እንዳይባክንና ለታሰበለት ዓላማ እንዲውል በጥብቅ የሚሰራበት ይሆናል።
በ2012 ከሚጠበቀው ገቢ ውስጥ 605 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ታክስና ታክስ ካልሆኑ የአገር ውስጥ ገቢዎች የሚሰበሰብ ነው። ይህም አገራችን በዕቅድ ዘመኑ አሳካዋለሁ ብላ ላቀደቻቸው የልማት ስራዎች የሚውል ይሆናል። ይህም ግብር በአገራችን የልማት ውጥንን ለማሳካት ያለውን ድርሻ ያሳየናል።
ከዚህ ውስጥ መንግስት ዕድገትን በማፋጠን ድህነትን ለማስወገድ የሚረዱ የድህነት ተኮር ዘርፎች አወጣዋለሁ ብሎ በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ላይ ለያዛቸው የልማት ፕሮጀክቶች 469 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር እንዲደርስ ያደርገዋል። ይህም ከጠቅላላ የመንግስት ወጪ 64 ነጥብ 7 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ እቅዱ ያመላክታል።
እንግዲህ እነዚህ እውነታዎች የሚያሳዩን ነገር ቢኖር በመንግስት የሚከናወኑት ማናቸውም ስራዎች በዋነኛነት ህዝቡ በሚከፍለው ግብር ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን ነው። እርግጥ ዜጎች ግብር ካልከፈሉ ምንም ዓይነት የልማት ስራዎችን ማከናወን አይቻልም።
በመሆኑም ግብር ካልተከፈለ መንግስት በእርዳታና ብድር ብቻ ለመኖር ይገደዳል። እናም የግብርን አገራዊ ጠቃሚነት ከዚህ አኳያ መመልከት ይቻላል። የመንግስት አገልግሎቶችን በጥራት ለማግኘትም ግብር ወሳኝ ሚና አለው። መንግስት ከዜጎቹ ተገቢውን ግብር ካገኘ ለህዝቡ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች በዚያው ልክ ጥራታቸው፣ ፍትሐዊነታቸው፣ ዴሞክራሲያዊነታቸውና ሁሉን አቀፍነታቸው ከፍ ይላል።
በመሆኑም ሰሞኑን በቀን ገቢ ግብር ትመና ላይ የተነሱት አንዳንድ አላስፈላጊ ሃሳቦችና ተግባሮች ይህን የግብር መክፈልን ጠቀሜታ ያገናዘቡ አይደሉም። እርግጥ በቀን ገቢ ግብር አወሳሰኑ ላይ ችግር ሊኖር ይችላል።
ሆኖም ችግሩን ሌላ ችግር በመፍጠር መፍታት አይቻልም። አሁንም ቅሬታን ለማቅረብ የሚቻልበት አሰራር በመኖሩ ይህንኑ ከመንግስት ጋር በመመካከር ገቢራዊ ማድረግ ይገባል። ማንኛውም ችግር የራሱ መፍትሔ አለው። እናም ከግብር ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሔውን መንግስትና ህዝብ ተመካክረው ሊያስቀምጡ ይችላሉ።
እነዚህን የማሻሻያ እርምጃዎች ይበልጥ ለማጎልበት የፋይናንስ ግኝት ያስፈልጋል። ይህ ግኝት ደግሞ የሚገኘው ከግብር ነው። እናም ግብር መክፈል የዜጎች የውዴታ ግዴታ ይሆናል ማለት ነው። ለዚህ ደግሞ ዜጎች ግብር መክፈል ይኖርባቸዋል።
ከዚህ ጎን ለጎንም በሁለተኛው የዕድገት ዕቅድ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ድርሻ በአሁኑ ወቅት ከሚገኝበት በአራት እጥፍ እንዲያድግ በማድረግ ወደ መጀመሪያው የመካከለኛ ጉዞ መንገድ ለመድረስ ለታለመው ዕቅድ እስከ 18 በመቶ የማድረስ ግብን ይጥላል። ሀገራችን ለያዘችው የመካከለኛ ገቢ ራዕይን ለማሳካትም መደላድል ይፈጥራል።
መዋቅራዊ ለውጡን ገቢራዊ በማድረግ ረገድ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የኤክስፖርት ሚናው ሁነኛ ማሳያ ነው። ዛሬን ከነገ ጋር ብናስተያየው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አሁን ካለው ሁኔታ አኳያ ሲታይ ከጠቅላላው የኤክስፖርት ገቢ ከአስር በመቶ አይበልጥም። ይህን አሃዝ ከፍ ለማድረግ ገንዘብ ያስፈልጋል።
የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዕድገት ሊረጋገጥ የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ እንጂ ለብቻው ተፈፃሚ እንዲሆን ብቻ አይደለም። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ኢንቨስትመንትን ዕውን ከማድረግ አኳያ መቆራኘት ይኖርበታል።
ይህን ዕውን ለማድረግም በአሁኑ ወቅት ያሉትም ይሁኑ በቀጣይ ወደ ስራ የሚገቡት ኢንዱስትሪዎች፤ የቴክኖሎጂ አቅማቸውን፣ ምርታማነታቸውን፣ የጥራት አመራር አቅማቸውን ብሎም ተወዳዳሪነታቸውን በቀጣይነት መገንባት ይችሉ ዘንድ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረግላቸዋል። እነዚህን ድጋፎች ለማድረግ አሁንም ገንዘብ በበቂ ሁኔታ መገኘት ይኖርበታል። እናም ግብር መክፈል የግድ ይሆናል።
ያለንበት ወቅትና ቀጣዩ ጊዜ ደረጃ “ለ” እና “ሐ” ግብራቸውን እየከፈሉና የሚከፍሉበት ወቅት ነው። እንደ ደረጃ “ሀ” ወቅት በቀን ገቢ ግብር ግመታ ላይ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ሆኖም ችግሮቹን ከመንግስት ጋር ተመካክሮ መፍታት እንደሚቻል ከደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዩች መረዳት ይቻላል። እናም ቀሪዎቹ ግብር ከፋዩች በወቅቱ ግብራቸውን በመክፈል ቅሬታም ካላቸው ከተቋቋሙት የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች አማካኝነት መፍታት ይችላሉ። በመነጋገርና በመግባባት የማይፈታ ምንም ዓይነት ችግር የለምና!