NEWS

በቀድሞ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የሥራ ኃላፊዎች ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው

By Admin

September 24, 2017

አቃቤ ሕግ በቀደሞው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የሥራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ላይ በሁለት መዝገቦች ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መሰረተ፡፡

በመጀመሪያው መዝገብ ቁጥር 204153 የባለስልጣኑ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል፣ የምህንድስና ኦፕሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዶ መሃመድ፣ የእቅድና የአይሲቲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ ንጉሴ እና የባለስልጣኑ ስታፍ አሲስታንት አቶ ገብረአናንያ ፃዲቅ እንዲሁም ሌሎች 5 ያልተያዙ ግለሰቦች እና የግል የግንባታ ተቋራጭ ባለቤቶች በክሱ ተካተዋል።

በሁለተኛው መዝገብ ቁጥር 204154 አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል እና የሃይዚ አይ አይ ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ ዛኪር አህመድ እንዲሁም ያልተያዙ ሌሎች ሁለት ግለሰቦችን ጨምሮ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል የተከሰሱት የተቋሙን ጥቅም እንዲጠብቁና እንዲከላከሉ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው በግል ስራ ከሚተዳሩት አቶ ገምሹ በየነ ጋር የግል ጥቅም ለማግኘትና ለማሰገኘት ባደረጉት የሙስና ወንጀል ነው።

በዚህም ከማይፀምሪ – ዲማ የጠጠር መንገድ ሥራ ፕሮጀክትን ምንም አይነት የአዋጪነትና የዲዛይን ጥናት ሳይደረግ ከግዢ መመሪያው ውጪ በአስፓልት ደረጃ  እንዲሰራ በማድረጋቸው ነው፡፡

ክሱ እ.አ.አ. ሚያዚያ 2009 በብር 258 ሚሊዮን 721 ሺ 412 በጠጠር እንዲሰራ ተወስኖ የመንገዱ ስራ ከተጀመረ በኋላ ከዕቅድ ውጪ ሌሎች ተጫራቾችን ባላሳተፈ፣ ግልጽነትና ፍትሃዊነት በጎደለውና የተጫራቹን የአስፓልት መንገድ የመስራት ብቃት ሳይገመገም  እንዲጀመር ማድረጋቸውን የአቃቢ ህግ ክስ ያስረዳል ።

ኃላፊው ድርጅቱን ያለአግባብ ለመጥቀም መንገዱ ከምህንድስና ግምቱ 8 በመቶ  ወይም ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እያለው ከ183 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ወጪ በማድረግ በአጠቃላይ ወጪው ወደ 462 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲያድግ ማድረጋቸው በክሱ ላይ ሰፍሯል፡፡

መንገዱ ሲሰራም አካባቢውን ከግምት ያስገባ የውሃ ማስተላፊያዎችን ባለማካተቱና መንገዱ በድጋሚ መሰራት ግድ ሲሆንም የኮንስትራክሽን ደርጅቱ ከምህንድስና ግምቱም ሆነ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች ያነሰ 380 ሚሊዮን 244 ሺ 197 ብር በጨረታ አቅርቦ እንደነበር በክሱ ላይ ተተንትኗል፡፡

ቢሆንም በጥቅም በመመሳጠር ተደጋጋሚ ለውጦችን በማዘዝ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜና ወጪ እንዳይጠናቀቅና ተደጋጋሚ የማራዘሚያ ጥያቄ በማቅረብ አጠቃላይ ማጠናቀቂያውን 973 ሚሊዮን ብር በላይ ማድረሳቸውን ነው የሚያስረዳው፡፡

በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ዛይድ ከሁምቦ አርባ ምንጭ ያለው 31 ነጠብ 5 ኪሎ ሜትር የመንገዱ ክፍል ሙሉ በሙሉ በጎርፍ በመወሰዱ የዲዛይን ለውጥ በማድረግ በድጋሚ እንዲሰራ ለስራ አመራር ቦርዱ አቅርበው የደቡብ ዲስትሪክት ዳይሬክተሩ  ኮንትራክተሩ የዝግጁነትና አቅም ችግር እንዳለው አስረድተው ቦርዱም ጨረታ ወጥቶ በሌላ ኮንትራክተር እንዲሰራ ወስኖ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ትዕዛዙን ወደ ጎን ትተው ኮንትራክተሩ እንዲጫረት ፈቅደውለት ከምህንድስና ግምት በጣም ከፍተኛ የሆነ ዋጋ አቅርቦ የሚመለከታቸው አካላት አስተያየት ባልሰጡበትና የቦርዱም ሰብሳቢ ባልፈረሙበት እነዚህ የባለሰልጣኑ የጨረታ ውል ሰጪና አጽዳቂ ኮሚቴዎቹ በ700 ሚሊዮን 537 ሺ 444 አላግባብ ተዋውለው የነበረ ቢሆንም ስራው 780 ሚሊዮን 624 ሺ 634 ብር እንዲፈጅ ተደርጓል በሚል ነው፡፡

በሌላ የክስ መዝገብ ደግሞ አቶ ዛይድ፤ ከሳትኮን ኮንስትራክሽን ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል ተክላይ ጋር በመመሳጠር ግምቱ 23 ሚሊዮን ብር የሆነ አስፓልት ሬንጅ እንዲበደሩ በመፍቀድና ከዚሁ ንብረት ውስጥም የተመለሰው 17 ሚሊዮኑን ብር ሲሆን ቀሪው እስካሁን ገቢ ባለመደረጉ ነው።፡

አቶ ሳሙኤልና የድርጅታቸው የፋይናንስ ኃላፊ አቶ ፍስሀ ታደሰ የተበደሩትን አስፋልት የገዙ በማስመሰል የተጨማሪ አሴት ታክስ ደረሰኝ እንዲቆረጥላቸው የገቢዎች ባለስልጣንን በማሳሳት ደብዳቤ አጽፈዋል፣ የመንገዶች ባለስልጣንንም ባልተገባ የፍርድ ሂደት የጉልበትና የገንዘብ ብክነት እንዲኖር አድርገዋል፡፡

አቶ ዛይድ፤ ዛኪር አህመድ ከተባሉት ግለሰብም ጋር እንዲሁ በመመሳጠር 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት የአስፓልት ሬንጅ በብድር እንዲወስዱ ያደረጉ ሲሆን ተበዳሪው የአስፓልት ሬንጁን መመለስ ባለመፈለጋቸው በህግ አግባብ በገንዘብ የመለሱ ቢሆንም የአስፓልት ሬንጁን በአይነት ባለመመለሳቸው መንግስትን ላልተገባ የግዢ ሂደትና ዕቃውም ለተገዛለት ዓላማ እንዳይውል አድርጓል በሚል ነበር ክሱ የተመሰረተባቸው፡፡

ፍርድ ቤቱ የክስ መቃወሚያና አስተያየትቸውን ለጥቅምት 3 ይዘው እንዲቀርቡና ያልተያዙትም ተይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ አስተላልፏል።