Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በአዲሱም ዓመት ጥልቅ ተሃድሶው ይበልጥ ይጥለቅ!

0 278

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአዲሱም ዓመት ጥልቅ ተሃድሶው ይበልጥ ይጥለቅ!

ዳዊት ምትኩ

ጥልቅ ተሃድሶ ሂደት ነው። የአንድ ወቅት ጉዳይ አይደለም። ባሳለፍነው ዓመት ህዝቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ መንግስት በጥልቅ ተሃድሶው እየታገዘ ረጅም ርቀት መጓዝ ተችሏል። ይህ መንግስትና ህዝቡ የጀመሯቸው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴዎች በያዝነው ዓመትም ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል። የተሃድሶው እንቅስቃሴ ካለፉት ዓመታት በላይ ይበልጥ መጥለቅ ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ገዥው ፓርቲም ይሁን መንግስት ተሃድሶ የማድረግ ልምድ ያላቸው ናቸው። የዛሬ አስራ አምስትና አስራ ስድስት ዓመታት ገደማ ያካሄዱት የተሃድሶ ንቅናቄ የትግሉ በር ከፋች ነበር።

አምናም ከህዝቡ ጋር በመሆን የተካሄደው የተሃድሶ ትግል ውጤት ማምጣቱን የኢህአዴግ ምክር ቤት በቅርቡ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ላይ ገልጿል። በያዝነው ዓመትም ጥልቅ ተሃድሶው ይበልጥ እንደሚጠልቅ የምክር ተሃድሶውን በያዝነው ዓመት ይበልጥ እንዲጠልቅ ማድረግ ያስፈልጋል።

ጥልቅ ተሃድሶውን ይበልጥ እንዲጠልቅ ማድረግ በአገራችን አውን እየሆኑ ያሉትን የፈጣን ልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቶችን ማጠናከር ነው። ጥልቅ ተሃድሶው በእነዚህ ሂደቶች ውስጥ ያሉትን ማነቆዎች ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመፍታት ያስችላል። በተለይም ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመከላከል ጥልቅ ተሃድሶው ውጤት ሊያመጣ ይችላል። እናም በያዝነው 2010 ዓ.ም በኪራይ ሰብሳቢነት ላይ ይበልጥ ሊዘመትበት ይገባል።

እንደሚታወቀው ሁሉ በየትኛውም ዴክራሲያዊ ሀገር ውስጥ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ነባራዊ ክስተት ነው። ምንም እንኳን በሀገራችንም መንግሥትና ህዝብ በመገንባት ላይ የሚገኙት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ገና ለጋ ቢሆንም፤ እንደ ጀማሪ ዴሞክራሲያዊ ሀገር ከዚህ ነባራዊ ክስተት የፀዳንና ጉድለቶች የሉብንም ብሎ ለመናገር አይቻልም።

የኢፌዴሪ መንግስትና እርሱን የሚመራው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ከህዝቡ ጋር በመሆን በየጊዜው በሚወስዷቸው በርካታ ርምጃዎች የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቦች እየተቀረፉ ቢሆኑም፤ የሚፈለገው የአስተሳሰብ ለውጥ ሙሉ ለሙሉ ተገኝቷል ማለት አይቻልም። እንዲያውም አስተሳሰቦቹ እየገነገኑ ጫፍ ላይ እየወጡ ይመስላሉ። በአመዛኙ ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሙስናን የሚፀየፍና እንደ ነውር የሚያይ የመንግስት ስራ አስፈፃሚን ብሎም ህዝብን በተሟላ ሁኔታ መፍጠር አልተቻለም።

በሰጪም ይሁን በተቀባይ መካከል ያለው አስተሳሰብ አንድና ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል። ይህ የሆነውም ካለፉት ስርዓቶች ይዘናቸው የመጣናቸው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ቅሪት አስተሳሰቦች ብሎም ልማቱ የፈጠራቸው አንዳንድ ሁኔታዎች አስተዋፅኦ ያደረጉ ይመስለኛል።

ፐብሊክ ሰርቪሱ ምንም እንኳን በሀገራችን ውስጥ ለተገኘው ልማት የበኩሉን ድርሻ ቢያበረክትም ከዚህ ነባራዊ የሀገራችን ሁኔታ ውጪ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ስልጣን የህዝብ ማገልገያ ሳይሆን የራስ መገልገያ ሊሆን ችሏል።

ይህን አመለካከት ለመለወጥ ደግሞ በመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ የአስፈፃሚነት ስራን የሚከውኑት የፐብሊክ ሰርቪሱ አካላት በአመለካከት ብሎም በአደረጃጀት ለውጦች ውስጥ እንዲያልፉ ተደርጓል። በተለያዩ ክልሎች ውስጥም በርካታ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርጓል፤ ከደረጃቸውም ዝቅ ብለዋል። በመሆኑም ይህን ሁኔታ በያዝነው ዓመትም ይበልጥ ማስፋት ይገባል።

ማንኛውም ተሃድሶ ያለ ህዝቡ ድጋፍ ግቡን ሊመታ ስለማይችል በአሁኑ ወቅት ሁሉም የህብረተሰቡ ክፍል በቀጥታ በተሃድሶው ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ተደርጓል። በዚህም ህዝቡ ራሱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆኖ ችግሩን ከመግለፅ ባለፈ የማይመጥነውንና የስነ ምግባር ጉድለት አለበት ብሎ የሚያምነውን የመንግስት ስራ ፈፃሚን እየገመገመ ተገቢው እርምጃ የመውሰድ ተግባራት እንዲከናወኑ እገዛ አድርጓል።

በማንኛውም ዴሞክራሲን የህልውና ጉዳይ አድርጎ በሚንቀሳቀስ ሀገር ውስጥ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ቁልፍ ነው። ለነገሩ መልካም አስተዳደር የዴሞክራሲ አካልና መሠረት ነው። ስለሆነም መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታን በግብነት አስቀምጦ መረባረብ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ አያጠያይቅም።

ታዲያ ይህን ዕውነታ በውል የተገነዘበው የኢትዮጵያ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስትም ሃሳቡን ወደ ድርጊት ለመለወጥ በጥረት የታገዙ ጠንካራ እንቅስቃሴዎችን ከጀመረ 26 ዓመታትን አስቆጥሯል። በእነዚህ ዓመታት በርካታ ተግባራቶች ዕውን ቢሆኑም የሚፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት አልተቻለም።

በተለይም በፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የአገልጋይነት መንፈስን የተላበሰ አሰራር አልተፈጠረም። በመሆኑም ይህን የአገልጋይነት መንፈስ ለመፍጠርና በመንግስት ስልጣን ያለመገልገል አመለካከትን ፈር ለማስያዝ ለማስያዝ የተደረገው ጥረት አበረታች ነው። ይህም ስራው ወደፊት እየተጠናከረና የተፈጠሩትን ችግሮች በአስተማማኝ መንገድ ለመፍታት አሁንም ተግቶ መስራት የሚያስፈልግ መሆኑን ያመላክታል።

ርግጥ የመልካም አስተዳደር ስራዎች ከህዝቡ ጋር በቅርበትና በቀጥታ የሚያገናኙ በመሆናቸውና የህዝቡ የእርካታ መለኪያዎችም ስለሆኑ ጥንቃቄ የሚያሻቸው ጉዳዩች ናቸው። ህዝቡ በሚሰጠው እርካታ ተገቢ ያልሆነና ህዝቡን ለምሬት የሚዳርግ ከሆነ ቅሬታ ከመፍጠሩም በላይ፤ የዜጎችን የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚነትን ያደበዝዛል።

መንግስት ለህዝቡ የሚሰጠው አገልግሎት በተገቢው ሁኔታ እንዳይፈፀምና ህዝብ ከመልካም አስተዳደር ትሩፋቶች ተጠቃሚ እንዳይሆን ያደርጋል። ይህ ደግሞ መንግስት የሚሰጠው የመልካም አስተዳደር አገልግሎት በልማትና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲያሳርፍ ያደርጋል።

እነዚህ ዕውነታዎችም የህዝቡን አመኔታ በመሸርሸር ለሁከትና ለብጥብጥ መዳረጋቸው የሚቀር አይመስለኝም። በሁከትና በብጥብጥ ውስጥ የሚኖር ህዝብ ደግሞ ልማትንና ዴሞክራሲን ዕውን ሊያደርግ አይችልም። ከዚህ አኳያ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ የታየው ችግር ተጠቃሽ ነው። እንዲህ ዓይነት ችግሮች ዳግም እንዳይፈጠሩ ደግሞ ተሃድሶ ማድረግ ሁሌም ያስፈልጋል።

በየጊዜው የሚስተዋሉ ችግሮችን እየተከታተሉ ተገቢ ምላሽ መስጠትና ለዚህ የሚሆን መፍትሔ አደራጅቶ በማይቀለበስ መልኩ ለህዝብ ማሳወቅ የአንድ ጊዜ ስራ አይደለም። ሊሆንም አይችልም። ቀጣይነትና ተከታታይነት ያለው ሊሆን ይገባል። በያዝነው አዲስ ዓመት ይህን መሰሉ የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴዎች ሊጎለብቱና ሊያድጉ ይገባል። ምክንያቱም ችግሮችን በተሃድሶው እንቅስቃሴ ውስጥ ሳያሰልሱ መመልከትና ተገቢውን ምላሽ መስጠት በህዝቡ ዘንድ ይበልጥ አመኔታን ስለሚፈጥር ነው።

ቀጣይነት ያለው የተሃድሶ ስራ ልማትን ለማፋጠንና ዴሞክራሲን በፅኑ መሰረት ላይ ለማኖር መደላድልን ይፈጥራል። ልማት ከተፋጠነና ዴሞክራሲው እንዲጎመራ የሚያስችል ምህዳርን በፅኑ መሰረት ላይ የሚያኖር ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረም እንደ አገር የምናስበውን ራዕይ እንድናሳካ ያደርገናል። እናም ይህን አገራዊ ራዕይ ዕውን ለማድረግ በተያዘው አዲሱ ዓመትም ችግሮችን እየፈቱ የጥልቅ ተሃድሶን ጥልቀቶች ይበልጥ ማጥለቅ ወሳኝ ስራ መሆን ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy