Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ባለዘርፈ ብዙ ፋይዳው የቀረጥ ነፃ ማበረታቻ

0 1,100

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አገራት ባለሀብቶችን በመሳብ ልዩ ትኩረት በሰጡባቸው ዘርፎች የኢንቨስትመንት ተግባራትን አከናውነው ለወጣቶች የሥራ ዕድልን በመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት፣ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን ለሚያግዙ የአገር ውስጥም ይሁን የውጭ ባለሀብቶች የተለያዩ ዓይነት የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን በመስጠት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋሉ፡፡

እነዚህ ማበረታቻዎች የተለያዩ ሲሆኑ እንደ ገቢ ግብር እፎይታ፣ የግንባታ፣ የካፒታል ዕቃና የተሸከርካሪ ቀረጥ ነፃ ማበረታቻ መስጠትን እንዲሁም የፋይናንስና የመሬት አቅርቦትን ያካትታሉ፡፡

የኢ...ሪ መንግሥትም ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ማበረታቻዎችን በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲካተቱ እንዳደረገ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ያሳያል፡፡

ይሁን እንጂ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች ያላንዳች አገራዊ ፋይዳ ለባለሀብቶች በነፃ የሚሰጡ ችሮታዎች እንደሆኑ ተደርገው የሚወሰዱበት አግባብ እንዳለ የኮሚሽኑ መረጃ ይገልፃል፡፡ የቀረጥ ነፃ መብት ለባለሀብቶች ከተፈቀዱ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች መካከል ይጠቀሳል፡፡

የቀረጥ ነፃ መብት ለኢንቨስትመንት ማበረታቻነት ለባለሀብቶች ብቻ እንደሚሰጥ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ የዚህ መብት ተጠቃሚዎች ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡ ከባለሀብቶች በተጨማሪ የቀረጥ ነፃ መብት በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለሚካሄዱ የኢንቨስትመንት ሥራዎች፣ ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ለኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶችም የቀረጥ ነፃ መብት ይሰጣል፡፡

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የቀረጥ ነፃ ጥያቄዎች ከሚስተናገዱት የመንግሥት ፕሮጀክቶች መካከል የስኳር ልማት ኮርፖሬሽን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፣ ኢትዮቴሌኮም፣ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሚያከናውኗቸው የልማት ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ፡፡

እነዚህ ተቋማት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የተለያዩ የኃይል ማመንጫ ግድቦችንና ሌሎችን ግዙፍ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ግንባታዎችን ስለሚያከናውኑ፣ ለነዚህ ግንባታዎች የሚያስፈልጉ ማናቸውም የግንባታና የካፒታል እቃዎች እንዲሁም ተሸከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ የሚስተናገዱ ናቸው፡፡ እነዚህ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሚከናወኑ የልማት ተግባራት የአገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር በዘላቂ መልኩ ለማሳካት የሚያስችሉ ምሰሶዎች በመሆናቸው ይህ ዓይነቱ ዕድል መሰጠቱ ለሥራው ቅልጥፍናና ውጤታማነት የላቀ ሚና ይጫወታል፡፡ የግል ኢንቨስትመንቱን ምርታማነትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት በማረጋገጥ ረገድም ሚናቸው የጎላ ነው፡፡

በተለያዩ የዓለም አቀፍና የሁለትዮሽ ስምምነቶች መነሻነት የቀረጥ ነፃ መብት ከሚጠቀሙት ሌሎች አካላት መካከል እንደ አፍሪካ ሕብረት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ያሉ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዲሁም የተለያዩ አገራት ኤምባሲዎች ለድርጅቶ ቻቸውም ሆነ በሕጉ መሰረት የመብቱ ተጠቃሚ ለሆኑ ሠራተኞች ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቧቸው ተሸከርካ ሪዎችና የግል መሣሪያዎች ይገኙበታል፡፡

ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የተገኘ መረጃ እንደሚያ ሳየው፣ እ..አ በ2016 በአገር አቀፍ ደረጃ የተሰጠው ጠቅላላ የቀረጥ ነፃ መብት195 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 82 ቢሊዮን ብር የሚሆነው በግል ባለሀብቶች ወደ አገር ውስጥ ለገቡ ዕቃዎች (የማምረቻ፣ የግንባታ፣ የመለዋወጫ፣ የላቦራቶሪ እንዲሁም ለወጭ ንግድና ከውጭ የሚገቡ የንግድ ዕቃዎችን ለመተካት)፣ 32 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች የተሰጠ እንዲሁም ቢሊዮን ብር ደግሞ ለአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ መሥሪያ ቤቶችና ሠራተኞቻቸው እንዲሁም የዲፕሎማቲክ መብት ላላቸው ግለሰቦች የተሰጡ የቀረጥ ነፃ መብቶች ይገኙበታል፡፡

በሌላ በኩል እንደ ፕሮጀክቱ ዓይነትና ባህርይ ከቀረጥ ነፃ ፈቃድ በተለያዩ የመንግሥት ቤቶች አማካኝነት ይሰጣል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በዋናነት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለሰጣቸው የውጭ ባለሀብቶች፣ የውጭ ባለሀብቶችና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በጋራ ለመሰረቷቸው ፕሮጀክቶችና ድርጅቶች እንዲሁም በውስን ዘርፍ ለተሰማሩ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችና የፌደራል መንግሥት የልማት ድርጅቶች የቀረጥ ነፃ ፈቃድ ይሰጣል፡፡ የክልል ኢንቨስትመንት ቢሮዎች በክልል የኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥተው ለሚንቀሳቀሱ ያገር ውስጥ ባለሀብቶችና የዳያስፖራ ፕሮጀክቶችና ድርጅቶች የቀረጥ ነፃ ማበረታቻ ይፈቅዳሉ፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በካፒታል ሊዝ ሥርዓት በኢንቨስትመንት ቦርድ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ወይም በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ወይም በካፒታል ሊዝ ድርጅቶች በኩል ለአነስተኛ፣ ለመካከለኛና ለትልልቅ ተቋማት ለካፒታል ዕቃዎች የቀረጥ ነፃ ማበረታቻ ይፈቅዳል፡፡ የማዕድን፣ ፔትሮሊየምና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴርም በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች በተመሳሳይ መልኩ የቀረጥ ነፃ ፈቃድ ይሰጣል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የውጭ ንግድ የቀረጥ ማበረታቻ ሥርዓት በሚፈቅደው መሰረት አምራቾች ወደ ውጭ ገበያ ለሚልኳቸው የምርት ውጤቶች እንዲሁም የገቢ ዕቃዎችን ለመተካት ከቀረጥ ሙሉ ለሙሉ ወይም የቀረጥ ቅናሽ በተደረገላቸውን ግብዓቶች አማካኝነት ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ሥራውንም የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በቅንጅት ያስተባብሩታል፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ መንግሥታዊ ላልሆኑና ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተሸከርካሪና በርካታ ዕቃዎች (የፍጆታና የምግብ እቃዎችን ጨምሮከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ይፈቅዳል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተመላላሽ ዲፕሎማቶች ተሸከርካሪና የግል መገልገያ ዕቃዎችን፣ እንዲሁም ለተመላሽ ዳያስፖራዎች ደግሞ የግል መገልገያ ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ፈቅዷል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨትመንት ኮሚሽን የቀረጥ ነፃ ማበረታቻ መስጠት በጀመረባቸው ባለፉት አራት ዓመታት በየዓመቱ በአማካኝ 600 ለሚሆኑ የመንግሥትና የግል ፕሮጀክቶች የማበረታቻ ፈቃድ የሰጠ ሲሆን፣ አብዛኞቹ (60 በመቶ በላይ የሚሆኑትበማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው፡፡ በተለይም ከቀረጥ ነፃ ማበረታቻ ተጠቃሚ የሆኑ ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ባለሀብቶች ቁጥር ባለፉት አራት ዓመታት በሦስት እጥፍ ያደገ ሲሆን፤ ይህም ማበረታቻዎቹ መንግሥት ትኩረት ባደረገበት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሁም የወጭ ንግድ ተወዳዳሪነት ላይ ያላቸውን አዎንታዊ ሚና ያሳያል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በኮሚሽኑ ከተፈቀዱ የቀረጥ ነፃ ማበረታቻዎች ውስጥ አብዛኞቹ (72 በመቶ የሚሆኑትየማምረቻ ዕቃዎችን ወደአገር ውስጥ ለማስገባት የተፈቀዱ ሲሆን፣ ይህም የቴክኖሎጂ ሽግግርን፣ ምርታማነትንና ተወዳዳሪነትን እንዲሁም የኢንቨስትመንት መስፋፋትን በከፍተኛ ደረጃ ያግዛል፡፡ ለማምረቻ ዕቃዎች የሚሆኑ መለዋወጫዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የተፈቀዱ የቀረጥ ነፃ መብቶች በኮሚሽኑ ከተፈቀዱ አጠቃላይ የቀረጥ ነፃ መብት 11.5 በመቶ ድርሻ ይይዛሉ፡፡ በአንፃሩ የግንባታ ዕቃዎችን ለማስገባት የተፈቀዱ የቀረጥ ነፃ መብቶች ድርሻቸው ከ10 በመቶ ያነሰ ሲሆን፣ ከተሸከርካሪዎች ጋር ተያይዞ በኮሚሽኑ የተፈቀደው የቀረጥ ነፃ መብት ከጠቅላላው የቀረጥ ነፃ መብት የሦስት ነጥብ አምስት በመቶ ብቻ ድርሻ አለው፡፡ ይህም በአንዳንድ ዘርፎች ከግንባታ ዕቃዎችና ተሽከርካሪዎች ጋር የተያየዙ ችግሮች እንዳሉ ግልፅ ነው፡፡ ቢሆንም ልማታዊ የሆኑት የቀረጥ ነፃ ማበረታቻዎች ያላቸው አዎንታዊ ገፅታና ሚና መዘንጋት የለበትም፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት 14 ተከታታይ ዓመታት በአማካይ ባለሁለት አሃዝ ዕድገት እንደተመዘገበ ሁሉ የአገር ውስጥና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትም እየጨመረ እንደመጣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ያሳያል፡፡ ለአብነት ያህል አገሪቱ በ2008 .ም ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ያገኘችው የውጭ ምንዛሬ ሦስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፤ በ2009 .ም ማዕድንን ጨምሮ ሦስት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች፡፡

በኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ሥራዎች ስኬታማ የሆኑ የበርካታ አገራት ልምድ እንደሚያመለክተው፣ ለባለሀብቶች የሚሰጡ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች በየዘርፉ ውጤታማና በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁልፍ የሆኑ ባለሀብቶችን ለመሳብና ለማቆየት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ በተለይም የኢንዱስትሪ ዘርፉን የውጭ ገበያ ተወዳዳሪነት በማሳደግ የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘት፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ብሎም የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለመፍጠር ያግዛል፡፡

በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባዔ ባወጣው ሪፖርት እንዳረጋገጠው፣ ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ በአፍሪካ ቀዳሚ ከሚባሉት አገራት መካከል አንዷ መሆን ችላለች፡፡ በተለይም በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያስመዘገበችው ዕመርታ አገሪቷን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከቬትናም ቀጥሎ ትልቋ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንቨስትመንት መዳረሻ አድርጓታል፡፡

በኢንቨስትመንት ፍሰታቸውና ተያያዥ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው የላቁ አገራት ልምድ በመቅሰም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በአሁኑ ወቅት የማበረታቻ ሥርዓቱን ዘርፍ ተኮር እና የአፈፃፀም ደረጃን መሰረት ያደረገ እንዲሆን አስፈላጊውን ጥናት እያካሄደ ይገኛል፡፡ በተለይም ማበረታቻዎችን ከባለሀብቶች ትጋትና ውጤታማነት ጋር በማያያዝ ሂደት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እየተገበረ ያለው የማበረታቻ ሥርዓት እንደመልካም ተሞክሮ ሆኖ የሚጠቀስ ነው፡፡

በአጠቃላይ የኢንቨስትመንት የቀረጥ ነፃ ማበረታቻ ለባለሀብቶች እንዲሁ የሚሰጥ ችሮታ ሳይሆን መንግሥት የኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግ የአገርንና የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚጠቀምበት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስትራቴጂ ነው፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy