Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተስፋ ሰጪውን ትምህርት ከአረም እንጠብቅ

0 303

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተስፋ ሰጪውን ትምህርት ከአረም እንጠብቅ

ብ. ነጋሽ

የ2010 የትምህርት ዘመን ሊጀምር ቀናት ቀርቶታል። በተለይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤቶች፣ ተማሪዎቻቸውን መዝግበው ዝግጅት የጀመሩት በነሃሴ ወር ነበር። የትምህርት ዝግጅታቸው  በ2010 የትምህርት ዘመን የሚቀበሏቸውን ተማሪዎች በመመዝገብ የተወሰነ ብቻ አይደለም። ለተማሪዎቻቸው የመማሪያ መጻህፍትም ሰጥተዋል። ይህ ተማሪዎች አስቀድመው ለትምህርት እንዲዘጋጁ ስለሚረዳ ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው።

እርግጥ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በእረፍት ላይ በቆዩባቸው የክረምት ወራት ሊከናወኑ ይገባቸው የነበሩ የህንጻ ጥገናና መሰል ስራዎች ዘግይተው አሁን ተማሪዎች ወደትምህርት ቤት በሚገቡበት ወቅት መከናወን ሲጀምሮ የሚስተዋልበት ሁኔታ አለ። ለምሳሌ  በአዲስ አበባ በሚገኝ አንድ የመንግስት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከዓመት በፊት ተሰንጥቆ ጉዳት እንዳያስከትል ተዘግቶ የነበረ የመማሪያ ህንጻ የፎቅ መወጣጫ ደረጃ፣ ክረምቱን መሰራት ሲኖረበት አሁን መስከረም ከገባ በኋላ ግንባታው ተጀምሮ ተመልክቻለሁ። በሌሎችም ትምህርት ቤቶች ተመሳሳይ ችግሮች ይስተዋላሉ። ከበጀት አለቃቀቅ ጋር በተያያዘ ያልተመቻቸ ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ቢገመትም፣ ጉዳዩ በትምህርት ሂደት ላይ የሚያስከትለውን ተጽእኖ ታሳቢ በማድረግ የዚህ አይነት ችግሮች የሚስትካከሉበት ሁኔታ በሚቻች መልካም ነው።

ትምህርት የአንድ ሃገርን መጪ እድል የሚወስን ነው። በአንድ ሃገር ውስጥ ያለ የትምህርት ሁኔታ – የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት እንዲሁም በትምህርት ቤት ውስጥ የሚታየው የተማሪዎች ስነምግባር የሃገሪቱን የነገ መድረሻ ያመላክታል። ትምህርት የነገ ሃገር ተረካቢ ትውልድ መገንቢያ መሳሪያ ነው። እናም የአንድ ሃገር የትምህርት ሥርአት ነገ ሃገሪቱ ልትደርስ ያለመችውን ራዕይ እውን ማድረግ በሚያስችል ሁኔታ መቀረጽ ይኖርበታል።

የኢትዮጵያን የትምህርት ሥርአት ከዚህ አንጻር ስንመዝነው የሃገሪቱን መጻኢ የልማትና የእድገት ግብ ታሳቢ ያደረገ ሆኖ እናገኘዋለን። የሃገሪቱ የትምህርት ሥርአትና ተደራሽነት ቀጣይ የእድገትና የልማት እቅድ የሚፈልገውን በየደረጃው የሚገኝ የሰለጠነ የሰው ሃይል በመጠንም በብቃትም ማፍራትን ታሳቢ አድርጓል።

ኢትዮጵያ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ የተመሰረተበትን የግብርና ዘርፍ ምርታማነት በማሻሻል ከተፈጥሮ ጥገኝነት የተላቀቀ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ በማድረግ ለሃገራዊ እድገት ግብአት የሚሆን  የካፒታል ክምችት የመፍጠር እቅድ አላት። ይህ ማለት ግብርናውን በቴክኖሎጂና በምርታማነት ወደየላቀ ደረጃ የማሸጋጋር እቅድ ነው። እንዲሁም በቀጣይ ሰባት አመታት ግብርና ላይ የተመሰረተውን ኢኮኖሚ ወደማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ በማሸጋጋር መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣትና መካከለኛ ገቢ ደረጃ ላይ ለመድረስ አቅዳለች። የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ በአጭርና በግልጽ ቋንቋ ሲነገር ይህን ይመስላል።

ታዲያ የግብርናውን ዘርፍ ወደላቀ ደረጃ ትራንስፎርም ማድረግ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመገንዘብና የመጠቀም ብቃት ያለው አርሶ አደር ይሻል። የዚህ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ስኬት ቢያንስ በቤተሰብ ደረጃ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ያጠናቀቀ የሰው ሃይል እንዲኖር ይሻል። በመሆኑም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ መሆን ይኖርበታል። በዚህ ረገድ እስካሁን ስኬታማ ስራዎች ተከናውነዋል። አሁን ሁሉም ለትምህርት የደረሱ ህጻናት የትምህርት እድል የሚያገኙበት ሁኔታ ተመቻችቷል። በሁሉም የሃገሪቱ አካባቢ ህጻናት በ2.5 ኪሎ ሜትር ርቀት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ማግኘት ይችላሉ።

ከዚህ ጎን ለጎን በተለይ በገጠር የጎልማሶች ትምህርትን ማስፋፋት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ አበረታች ጅምር ቢኖርም የታቀደውን ያህል ስኬታማ ስራ አለመሰራቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በአነስተኛ የአርሶ አደር ማሳ ዘመናዊ ቴክኖሎጂንና ግብአትን በመጠቀም ምርታማነትን የማሳደግ እቅድ ሰኬት ከጎልማሳ አርሶ አደሮች መማር አለመማር ጋር ቀጥታ ግንኙነት አለው። እናም የጎልማሶች ትምህርት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ከግብርና ወደማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ መር ኢኮኖሚ ማሸጋጋር የሳይንስና የቴክኖሎጂ እውቀት ያለው የሰው ሃይል ይሻል። በዚህ ረገድ የሞያና የቴክኒክ ትምህርትን ማስፋፋት ወሳኝ ድርሻ አለው። አሁን በሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች በተለያየ ደረጃ ስልጠና የሚሰጡ የሞያና የቴክኒክ ኮሌጆች ተከፍተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። አሁን በሃገሪቱ ያሉት የሞያና ቴክኒክ ኮሌጆች ቁጥር ከ1 ሺህ 3 መቶ በላይ ደርሷል። እነዚህ ኮሌጆች የሃገሪቱን ኢኮኖሚ መሪነት ድርሻ እየተረከበ የሚሄደው የማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ ዘርፍ የሚፈልገውን በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ የቴክኖሎጂ ባለሞያ መመገብ ይችላሉ።

የሞያና ቴክኒክ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ከዚህ በተጨማሪ በስራ ፈጠራ የማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪው መሰረት የሆነውን አነስተኛና ጥቃቅን የማምረቻ ተቋማት የመፍጠርና የማሳደግ ብቃት ያለው ትውልድ እያፈሩ ይገኛሉ። አነስተኛና ጥቃቅን የማምረቻ ተቋማት የማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ መሰረት ከመሆናቸው ባሻገር፣ በመላ ሃገሪቱ በሚሊየን ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ያስችላሉ።

በቀጣይ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ የሚመራው የማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ የላቀ ቴክኖሎጂ (high-tech technology) ማንቀሳቀስ የሚችል በከፍተኛ ደረጃ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የሰለጠነ የሰው ሃይል ይሻል። ያሀገሪቱ የትምህርት ሥርአት ይህን በከፍተኛ ደረጃ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የሰለጠነ የሰው ሃይል መፍጠር በሚያስችል ሁኔታ ተዘጋጅቷል። ይህም 70 በ30 የሳይንስ/ቴክኖሎጂና የማህበረሰብ ሳይንስ ጥመርታ የተማሪዎች  ቅበላ ሥርአት ነው። ወደሃገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ቅበላ ይህን 70 በ30 ጥመርታ የተከተለ ነው። የዚህ ጥመርታ ዓላማ መጪውን የሃገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅር ለማንቀሳቀስና ለማሳደግ የሚያስችል በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለሞያ ማፍራት ነው። ከዚህ በተጓዳኝ የከፍተኛ ትምህርት በከፍተኛ መጠን ተስፋፍቷል። በአሁኑ ጊዜ በዓመት በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ እስከ 2 መቶ ሺህ ተማሪዎችን አሰልጠነው ማስመረቅ የሚችሉ 44 ዩኒቨርሲቲዎች አሉ።

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ የሃገሪቱ የትምህርትና ስልጠና ሁኔታ አመላካቾች፣ የሃገሪቱን ቀጣይ መዳረሻ ከወዲሁ ያሳያሉ። ይሁን እንጂ አሁንም በትምህርት ጥራት ረገድ አሳሳቢ ችግሮች ይታያሉ። በሚማሩበት የአፍ መፍቻ ቋንቋ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ፣ አራቱን የሂሳብ መደቦች ፈጽሞ የማያውቁ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን መመልከት የተለመደ ነው። አንድ አረፍተ ነገር አስተካክለው መጻፍ የማይችሉ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እንግዳ መሆን ካቆመ ከራርሟል። ያጠኑትን የእውቀት ዘርፍ ጽንሰ ሃሳብ (subject matter) ሳያውቁ በመጀመሪያ ዲግሪ የሚመረቁ በርካቶች ናቸው። የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ መመረቂያ ጽሁፎች ግዢ በይፋ የሚከናወን ለመሆን በቅቷል። ዲግሪ እንጂ እውቀት የሌላቸው በርካታ ዜጎች እየተፈጠሩ ነው። ይህ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሌላው በትምህርቱ ዘርፍ የሚታየው ችግር ከኩረጃ ጋር የተያያዘ የስነምግባር ጉድለት ነው። በተለይ በትላልቅ ከተሞች በመንግስት ትምህርት ቤቶች ከሚማሩት ብዙም ያልተናነሰ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች በሚያስተምሩ የግል ትምህርት ቤቶች ኩረጃ የትምህርት ቤቶቹ ያልተጻፈ ደንብ ለመሆን በቅቷል። በትምህርት ቤቶቹ አመራሮችና መምህራን አማካኝነት የሚፈጸም ያልተጻፈ የመተዳደሪያ ደንብ። በተለይ በ 8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ፣ በ10ኛና 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሃገር አቀፍ ፈተናዎች ላይ የግል ትምህርት ቤቶች የተቀናጀ ኩረጃን ሲያስፈፅሙ ይታያሉ።

በያዝነው ዓመት በበርካታ የግል ትምህርት ቤቶች የ10ኛና የ12 ክፍል ሃገር አቀፍ ፈተና ላይ ጎበዝ መምህራን ተመልምለው ፈተናውን እየሰሩ በፈታኞች በኩል መልስ ለተማሪዎች እንዲደርስ የተደረገበት ሁኔታን ታዝበናል። እነዚሀ ትምህህርት ቤቶች ሁሉም ተማሪዎቻቸው በከፍተኛ ነጥብ እንደሚያልፉ አስቀድመው ያውቁ ስለነበረ ውጤት ከመውጣቱ በፊት የ11ኛ ክፍል ምዝገባ አካሂደዋል። ይህ እጅግ አሳሳቢና አስፈሪ ነው። በአጠቃላይ በመጪው ሃገር ተረካቢ ትውልድ ስነምግባር ላይ የሚያሳርፈው ተጽእኖ አደገኛ ነው። በራሳቸው ጥረት የሚሰሩ ተማሪዎች ላይ የሚያሰድረው አሉታዊ ተጽእኖም ቀላል እንዳልሆነ መታሰብ አለበት። በቀጣይ የትምህርት ቤት አመራሮች፣ መምህራንና ወላጆች በአሳሳቢ ሁኔታ በተለይ በግል ትምህርት ቤቶች እየተስፋፋና ባህል እየሆነ የመጣውን የኩረጃ አረም ለመንቀል መስራት ይጠበቅባቸዋል።

በአጠቃላይ የዘንድሮን የትምህርት ዘመን መጀመር መነሻ አድርገን የተመለከትነው የሃገሪቱ የትምህርት ሁኔታ የመጪውን የሃገሪቱን የላቀ የእድገት ደረጃ የሚያመላክት ተስፋ ሰጪ ነው። ይሁን እንጂ ይህን ተስፋ ሰጪ የነገ ተውልድ ማፍሪያ ትምህርት አረም የወረሰው መሆኑም ሊስተዋል ይገባል። አረሙ መጪውን ሃገር ተረካቢ ትውልድ ሳያቀጭጭ የመንቀሉ ተግባር ጊዜ የሚሰጠው አይደለም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy