Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አሳሳቢው የአየር ንብረት ለውጥና እና ብሄራዊ ዝግጁነታችን

0 761

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አሳሳቢው የአየር ንብረት ለውጥና እና ብሄራዊ ዝግጁነታችን

መዝገቡ ዋኘው

አለማችን ባለፉት አርባና ሀምሳ አመታት ውስጥ በድርቅና በረሀብ የተነሳ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿን አጥታለች፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው ጫና ምክንያት የችግሩ ሰላባ ከሆኑት ሀገራት አንድዋ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ይሄው ዘመን እየቀያየረ የሚከሰተው ከአየር ንብረት ጋር ተያይዞ የሚመጣው ችግር ዛሬም ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎቻችን በድርቅ እንዲጠቁ ምክንያት ሆኖአል፡፡

ድርቁ በተከሰተበት ወቅት ከቀድሞ ግዜያት በበለጠና በተሻለ አቅም የውጭ እርደታ ከመድረሱ በፊት መንግስት ብሔራዊ የኢኮኖሚ እድገታችን ባስገኘው አቅም በመጠቀም በብሔራዊ ደረጃ የታየውን ድርቅ ለመመከት የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት መዋቅርን በመጠቀም ድርቁ በተከሰተባቸው ቦታዎች ሁሉ  በፈጣን ሁኔታ ለዜጎቹ መድረስ ችሎአል፡፡

ምግብ ሕክምና ውሀ መጠለያ ባልተቋረጠ መልኩ እንዲያገኙ አድርጎአል፡፡ አስፈላጊ ሁኖ ከተገኘም ዜጎችን ለመታደግ የተወሰኑ የልማት ፕሮጀክቶችን በማቋረጥ ገንዘቡን ለእርዳታ እንደሚያውለውም ገልጾአል፡፡ ይህ ችግር በኢትዮጵያ ብቻ የተከሰተ ችግር ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተ አሳሳቢ ችግር መሆኑ በቅርቡ አሜሪካንንና ካሪቢያን ደሴቶችን የመታው ኡራካን ሀርቤ አውሎ ንፋስና የባሕር ተምዘግዛጊ ማእበል ያስከተለውን ከፍተኛ ውድመትና ጥፋት የአለም ሕዝብ በገሀድ ያየው ነው፡፡

የአሜሪካ መንግስት ከፌደራል በጀቱ ለተጎጂዎቹ በብዙ ሚሊዮን ዶላር ሲመድብ የካሪቢያን ሀገራት ደሴቶች ደግሞ የአለም ሀገራት እርዳታ እያደረጉላቸው ይገኛሉ፡፡ ከተሞች በውሀ ተጥለቅልቀዋል፡፡መሰረተ ልማቶች ወድመዋል፡፡ ሕንጻዎች ቤቶች ፈራርሰዋል፡፡ የመሬት መደርመስ ደርሶአል፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥ የውሀ ሙላት ደርሶአል፡፡ የሰው ሕይወት አልፎአል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው አደጋ እጅግ የገዘፈ ነው፡፡ ነገ ምን እንደሚፈጠር ለመገመት አልተቻለም፡፡ የአየር ንብረት መዛባት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአለማችን በእጅጉ አሳሳቢው ችግር ነው፡፡ የበለጠ ተጎጂ የሚሆኑት ደግሞ ታዳጊና በኢኮኖሚያቸው ድሀ የሆኑ ሀገራት ናቸው፡፡ የመንግስታቱ ድርጅት 72ኛ ጉባኤ በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ  ከሰሞኑ የተካሄደ ሲሆን የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የአየር ንብረት ለውጥ በቸልታ የማይታለፍ የአለማችን አሳሳቢ ችግር መሆኑን በመግለጽ የአየር ንብረት ለውጥ ጫናዎችን ለመቋቋም አለምአቀፉ ማሕበረሰብ ወሳኝ ሚና ሊጫወት የሚገባው ግዜ አሁን መሆኑን በንግግራቸው ወቅት አሳስበዋል፡፡

ጠቅላይሚኒስትሩ እንደሌሎች ሀገራት ሁሉ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ጫናዎች በየቀኑ ጉዳት እየደረሰባት መሆኑን በ72 የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የገለጹ ሲሆን ይሄም ዛሬ በሚታይ ደረጃ ብዙ ሚሊዮን ዜጎቻችን ለድርቅ ተጋላጭ የመሆናቸውን እውነት ያሳየ ነው፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ በአለማችን ላይ ከፍተኛ ጥፋትና ውድመት እያስከተለ ይገኛል፡፡  የዘመኑ ቴክኒዮሎጂ ሊቆጣጠረውም ሆነ ሊገታው አልቻለም፡፡ የአደጋውን መምጣት ቀድሞ ከማሳየቱ በስተቀር ራሱን የቻለ አደጋውን የሚመክትበት ወይም የሚያስቀርበት አቅም የለውም፡፡ ታዳጊ ሀገራት ብቻ ሳይሆኑ የበለጸጉና በኢኮኖሚ እድገታቸው ጣሪያ ነክተናል የሚሉትም ሀገራት የችግሩ ሰለባ ከመሆን አልዳኑም፡፡

ይህን እውነት በማጉላት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርም ደሳለኝ በሚሊዮን የሚቆጠር የአለም ሕዝብ ሕይወት እየቀጠፈ በብዙ ጥረት የተገኙ የልማት ስኬቶችን እያወደመ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት ስለአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖ የምንጠራጠርበት ጊዜ አይደለም፤ የአየር ንብረት ለውጡ በተጨባጭ የታየ የተጋረጠ አደጋ እንጂ ተረት ተረት አይደለም ሲሉ በመንግስታቱ ድርጅት 72ኛ ጉባኤ ላይ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በተለይ ለአየር ንብረት ለወጥ ምንም አስተዋፅኦ በሌላቸው ሀገራት ላይ በተደጋጋሚ የሚደርሰውን ጫናና ተፅእኖ ለመዋጋት አፋጣኝ ወሳኝ እርምጃ የሚወሰድበት ጊዜ ላይ  ነው የምንገኘው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሀገራችን በተለያዩ ዘመናት የተከሰቱ የተለያዩ ድርቆችን ስትጋፈጥ መኖርዋን በቅርቡ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2015 ያጋጠማትን የኤል ኒኖ አደጋን መቋቋሟን በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር አውስተው አሁንም ቢሆን የአየር ንብረት ለውጡን ጫና እየተጋፈጠች የምትገኝ መሆኑን የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን ተግባራዊ እያደረገች እንደምትገኝ ለመንግስታቱ ድርጅት 72 ጉባኤ  አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በሆነችበት ወር በተለይም ባሳለፍነው ረቡእ ያቀረበችው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ማሻሻያ የውሳኔ ሀሳብ በሙሉ ድምፅ በመጽደቁ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቀድሞ ዘመናት ጀምሮ በተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ግዳጅ ጥሪ መሰረት ሠራዊትዋን በማሰማራት በግንባርም በማሰለፍ በርካታ አለም አቀፍ ግዳጆችን በኮርያ በኮንጎ በሩዋንዳ ብሩንዲ በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ተወጥታለች፡፡ በመወጣትም ላይ ትገኛለች፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ በአለምአቀፉ የሰላም ማስከበር ተልእኮ በርካታ ወታደሮችን በማሰማራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ የምትመደብ መሆንዋን በመግለጽ  ዛሬም ለመንግስታቱ ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልእኮ መሳካት ጠንክራ እንደምትሰራ ገልጸዋል፡፡በአለም አቀፍ ደረጃ ሰላም እና ደሕንነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ጉልህ ሚና እንደምትጫወትም አስምረውበታል፡፡

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ ከሆኑት ዶናልድ ያማማቶ ጋር ተገናኝተው   በሁለትዮሽና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር ማድረጋቸውን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሐን ዘግበዋል፡፡

ዶክተር ወርቅነህ በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለው የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት የበለጠ እንዲሰፋ ኢትዮጵያ ጠንካራ ፍላጎት ያላት መሆኑን ገልጸው ሁለቱ ሀገራት በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን የትብብር እንቅስቃሴ የበለጠ ለማጠናከር ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል፡፡ ዶናልድ ያማማቶ ኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለአሜሪካ ግንኙነት መጠናከር የማእዘን ድንጋይ መሆንዋን ገልጸዋል፡፡ አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር የነበረውን የጠበቀ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በአለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂና ሰለባ ከሆኑት የአለማችን በርካታ ሀገራት ውስጥ  ኢትዮጵያም የዚህ የገዘፈ ችግር ሰለባ ነች፡፡

የአየር ንብረት ለውጡ የሚያስከትለው አደጋ በብዙ መልኩ ነው የሚከሰተው፡፡ ድርቅ፤ ውኃ ሙላት፤ የመሬት መንቀጥቀጥ፤ እጅግ የገዘፈና አናዋጭ አውሎ ንፋስ፤ የባሕሮችና ውቅያኖሶች በሞገድ መናጥና ገንፍሎ ወደ ምድር መፍሰስ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በእኛ አቅምና ደረጃ ዛሬ 9 ሚሊዮን ዜጎች የዚህ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ ሰለባ ሆነዋል፡፡

ኢትዮጵያ አቅምዋ የፈቀደውን ሁሉ ለዜጎችዋ በማድረግ ለይ ትገኛለች፡፡ የአየር ንብረት ለውጡ ነገ ምን አይነት አደጋ ይዞብን ሊመጣ እንደሚችል አይታወቅም፡፡ ብሔራዊ ዝግጁነትን ከሌሎች ሀገራት ልምድ በመማር ማሳደግ ይገባናል፡፡ በተለይም የውህ ሙላትና መጥለቅለቅ ቢከሰት የገነባነው የተዘጋጀንበት ነገር ያለ አይመስልም፡፡ መዘጋጀት አለብን፡፡ የጀልባዎች በብዛት መኖር በየክልሉ አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑን ከአሜሪካን ሀገር የተፈጥሮ አደጋ ተምረናል፡፡

ዘመናዊ አስፋልቶች ወደወንዝነትና ባሕርነት ሲለወጡ ሕንጻዎች መኪኖች ግማሽ ድረስ በውሀ ሲዋጡ መኪኖቹን ተክተው በአስፋልቱ ላይ የሞተር ጀልባዎች እየተንቀሳቀሱ ሕዝቡን ለመታደግ ሲሰሩ  አይተናል፡፡ ትልቅ ትምሕርት ሊሆነን ይገባል፡፡ እኛ ደግሞ የብዙ ታላላቅ ወንዞች ባለቤት ነን፡፡ ሞልተው ድንበር ጥሰው ሲገነፍሉ ማሳና ሰብል ሲያወድሙ ቤቶችን ሲያፈራርሱ ንብረትና እንሰሳትን ጠራርገው ሲወስዱ ዜጎችን ሲያፈናቅሉ ስናይ ኖረናል፡፡

የእኛንም በትክክል ያየው ጠፍቶ እንጂ በተደጋጋሚ የተፈጥሮ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ ሰለባ መሆናችን እውነት ነው፡፡ ለዚህ አይነቱ የተፈጥሮ አደጋ ምን ያህል ዝግጁ ነን? ባለሙያስ አሰልጥነናል ወይ? መሳሪያዎቹስ በየክልሎቹ አሉን? ችግሩ ቢከሰት ወዲያው የምንከላከልበት፣ ፈጥነን የምንደርስበት ዝግጁነት አለን? ብለን ራሳችንን በመጠየቅ  በስፋት መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy