Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አቅዶ የሚያሳካ ብቻ ሳይሆን በፈተናም የማይናወጥ ሥርዓት

0 360

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አቅዶ የሚያሳካ ብቻ ሳይሆን በፈተናም የማይናወጥ ሥርዓት

ኢብሳ ነመራ

የሁለተኛ ሚሊኒየም ሁለተኛውን አሥርት (decade) ሰሞኑን ተቀብለናል። የሁለተኛው አሥርት መግቢያ የሆነውን 2010 ዓመተ ምህረት የአሥርት ለውጥ መሆኑ የሚፈጥረውን ስሜት በሚመጥን ሁኔታ ነው የተቀበልነው፤ በመንግሥት ደረጃ በተዘጋጁ የተለያዩ ሁነቶች። የአንድ አሥርት ዘመን መሻገራችን ያለፉ አሥር ዓመታት ጉዟችንን እንድናስታውስ ይቀሰቅሰናል። ያለፉ አሥር ዓመታት ጉዟችን በስኬት የታጀበ የመሆኑን ያህል ያልታሰቡ ብርቱ ፈተናዎችም ያጋጠሙበትም ነበር። ያለፉ አሥርት ዓመታት ስኬቶች ላይ ብዙ ተነግሯል። በጽናት የታለፉት ፈተናዎች ላይ ግን ብዙ የተባለ አልመሰለኝም። በመሆኑም በዚህ ጽሁፍ የዛሬ አሥር ዓመት ሦስተኛውን ሚሊኒየም ከተቀበልን በኋላ እንደሃገር ካጋጠሙንና ከታለፉ ፈተኛዎች መሃከል ዋና ዋና ያልኳቸውን ጥቂቶቹን ለማስታወስ ወድጃለሁ። የአንድ ሥርዓት ጥንካሬ የሚለካው አቅዶ በደረሰባቸው ስኬቶቹ ብቻ ሳይሆን ሳይናወጥ ባለፋቸው ድንገተኛ ፈተናዎችም ጭምር ነው።

ባለፉት አሥርት ዓመታት እንደሃገር ገጥሞን ከነበረው ፈተና ውስጥ በቃሚነት የሚጠቀሰው በአየር መዛባት ምክንያት የተከሰተ ድርቅና ድርቁ ያስከተለው የምግብ እጥረት ችግር ነው። በ2003 ዓ/ም በተለይ የሃገሪቱ ምስራቃዊ ቆላማ አካባቢዎች በከፍተኛ ድርቅ ተመትተው ነበር። ይህ ምስራቅ አፍሪካን የመታ ድርቅ ከዚያ ቀደም አካባቢውን ከመቱ ድርቆች ሁሉ የከፋ እንደነበረ ተነግሯል። ድርቅ ለኢትዮጵያ እንግዳ ባይሆንም ይህን በ2ኛው ሚሊኒየም የመጀመሪያ አስርት መግቢያ ላይ ያጋጠመ ድርቅ በተለይ የድርቁን ተጽእኖ በመከላከል ረገድ መንግስት የነበረው ድርሻ ከዚያ ቀደም ከነበሩት ልዩ ያደርገዋል።

ይህ ድርቅ በተከሰተበት ወቅት ኢትዮጵያ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በስመዘገበችው ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ሳቢያ የመጠባበቂያ የእህል ክምችት  የቻለችበት ነበር። የ2003 ዓ/ም ድርቅ ሲከሰት፣ የኢፌዴሪ መንግስት ሁኔታውን ለእርዳታ ሰጪ መንግስታትና ለጋሽ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አሳውቆ እርዳታው እስኪቀርብ እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። ከዚያ ቀደም ሆኖ በማያውቅ ሁኔታ በቂ የመጠባባቂያ የእህል ክምችት ስለነበረ፣ ከዚህ ክምችት በብድር በመውሰድ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ማቅረብ ችሏል። በኋላ የውጭ እርዳታ ሲደርስ የመጠባባቂያ የእህል ክምችቱ ወደነበረበት እንዲመለስ ተደርጓል። በኢትዮጵያ የድርቅ ተጽእኖ ታሪክ በራስ አቅም ቀድሞ እርዳታ ማቅረብ ሲቻል ይህ የመጀመሪያው ይመስለኛል።

ድርቁ ግን ሃገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የማቅረብ አቅም ስላላት ብቻ በዛው አልቀረም። በ2007 ዓ/ም የስርጭት አድማሱን አስፍቶ በብዙ የሃገሪቱ አካባቢዎች አጋጠመ። ምስራቃዊ የአማራና የኦሮሚያ አካባቢዎች፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ የአፋር፣ የደቡብ አንዳንድ አካባቢዎች፣ የድሬደዋ የገጠር ቀበሌዎች በዚህ የድርቅ ተጽእኖ ስር ወድቀው ነበር። ይህ ኤል ኒኖ የተሰኘው የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው ድርቅ ከዚያ ቀደም ከተከሰቱት ሁሉ የከፋ ነበር።

የ2007 ዓ/ም ድርቅ መጀመሪያ የተከሰተው የበልግ ዝናብን በመጠንም በስርጭትም እንዲቀንስና እንዲዛባ በማድረግ ነበር። የኢፌዴሪ መንግስት የበልግ ምርት ከሚሰበሰብበት የ2007 ዓ/ም ሰኔ ወር ማብቂያ ጀምሮ ነበር በድርቁ ምክንያት የምግብ እጥረት ማጋጠሙን ይፋ ያደረገው። በበልግ የዝናብ ስርጭት መዛባት ሳቢያ ሰኔ 2007 ዓ/ም ላይ ለምግብ እጥረት የተጋለጡት ዜጎች ቁጥር 2 ነጥብ 9 ሚሊየን ብቻ ነበር። በነሃሴ ወር በድርቅ ሳቢያ የአስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ወደ 4 ነጥብ 3 ሚሊየን ከፍ አለ። ጥቅምት 2008 ዓ/ም መግቢያ ላይ ለምግብ እጥረት የተጋለጡ የአስቸኳይ ግዜ እርዳታ ፈላጊዎቹ ቁጥር 8 ነጥብ 2 ሚሊየን ደረሰ።  ታህሳስ ላይ ይፋ በተደረገው መረጃ መሰረት የአስቸኳይ ግዜ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር 10 ነጥብ 2 ሚሊየን ደረሰ። ይህ በሃገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነበር።

ይሁን እንጂ የኢፌዴሪ መንግስት ይህን ከባድ ፈታና መወጣት ችሏል። ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብና ተያያዥ አቅርቦት የሚውል ከ16 ቢሊየን ብር በላይ በጀት በመመደብ በእርዳታ አሰጣጥ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ ይዞ የአስከፊውን የድርቅ ተጽእኖ ወቅት መሻገር ችሏል። በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት ሰንደቃላማ የታተመባቸውን የእርዳታ እህል ቀረጢቶች ለመመልከት የበቃነው በዚህ የድርቅ ተጽእኖ ወቅት ነበር።

የ2008 ዓ/ም በልግና ክረምት የዝናብ ስርጭት የተስተካከለ ስለነበረ 2009 ዓ/ም ጥር ላይ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ጠባቂዎች ቁጥር ወደ 5 ነጥብ 6 ሚሊየን ዝቅ አለ። ይሁን እንጂ በተለይ ጥርና ታህሳስ አካባቢ ባልተለመደ ሁኔታ የተከሰተ ውርጭ ሰብል ላይ ጉዳት በማድረሱና መሰል ያለተጠበቁ ምክንያቶች መጋቢት 2009 ዓ/ም ላይ የእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ወደ 7 ነጥብ 78 ሚሊየን አሻቅቦ ነበር። ነሃሴ 2009 ላይ ይህ አሃዝ ወደ 8 ነጥብ 5 ከፍ ብሏል። አሁን እስከታህሳስ ድረስ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የሚደረግላቸው ዜጎች ቁጥር 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ነው። እስካሁን ባለው መረጃ ከእነዚህ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ጠባቂዎች መሃከል 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎች በዓለም የምግብ ፕሮግራም አማካኝነት እርዳታ ሲቀርብላቸው፣ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ገደማ ዜጎች የካቶሊክ የእርዳታ ድርጅት በሚያስተባብራቸው የለጋሽ ተቋማት የሚረዱ ናቸው። ቀሪዎቹ በኢትዮጵያ መንግስት የሚረዱ ናቸው።

በ2ኛው ሚሊኒየም የመጀመሪያ አስርት ሃገሪቱን የገጠማት ድርቅ ከባድ ፈተና ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። መንግስት አስከፊው ድርቅ ለአንድም ሰው ህይወት መጥፋትና መፈናቀል ምክንያት ሳይሆን ለመከላከል መቻሉ ደግሞ ፈተናን የመቋቋም አቅሙን ያሳያል።

በመጀመሪያው አስርት ዓመት ሃገሪቱን የገጠማት ሌላው ፈተና ከሃይማኖት አክራሪነት ጋር የተገናኘ ነው። ለሃያ ዓመታት ያህል ውስጥ ውስጡን ሲስፋፋ የቆየው እስላማዊ አክራሪነት 2003 ዓ/ም ላይ አመቺ አጋጣሚ ሲያገኝ ፈንድቶ ወጥቶ እንደነበረ ይታወሳል። በተለይ በአዲስ አበባ ሃወሊያ የሚባል እስላማዊ ድርጅት ውስጥ ተቋማዊ መልክ ይዞ በመውጣት በሌሎች አካባቢዎች ከነበሩ ያልተማከሉ የአክራሪነት እንቅስቃሴዎችና ዝንባሌዎች ጋር በመመጋገብ ሃገሪቱን ለከፋ ፈተና አጋልጧት ነበር።

ተገቢ የሙስሊሙን ማህበረሰብ ጥያቄ ሽፋን አድርጎ ድምጻችን ይሰማ በሚል መለያ ይመራ የነበረው ይህ የአክራሪነት እንቅስቃሴ፣ ከሌሎች ሃገሪቱን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ጋር አጀንዳ በመመጋገብ በተለይ አርብ በሚካሄዱ ሳምንታዊ የጸሎት ስርአቶች ላይ እንዲሁም የአደባባይ የጸሎት ስርአት በሚካሄድባቸው በዓላት ከአንድ ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ የከፍተኛ ሁከት መንስኤ ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል። ይህን የአክራሪነት አስተምህሮ የማይደግፉ የሃይማኖት አባቶች ላይ ግድያ እስከመፈጸም የደረሰ ጥቃት የተሰነዘረበት ሁኔታ እንደነበረም እናስታውሳለን። አንዳንድ ህጋዊ ሆነው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በዚህ የአክራሪነት እንቅስቃሴ ላይ ተለጥፈው ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ባደረጉት ሙከራ ለአክራሪነት እንቅስቃሴው ጉልበት ሰጥተውት እንደነበረ ይታወሳል። አሁን ይህ የአክራሪነት እንቅስቃሴ በተለይ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ባደረገው ጥረት ከሽፎ ሰላም የሰፈነበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን። አሁንም ግን ይህ እንቅስቀሴ ውስጥ ውስጡን መኖሩንና አመቺ አጋጣሚ እየጠበቀ መሆኑን የሚያሳዩ እውነታዎች አሉ።

ባለፈው አስርት ሃገሪቱን የገጠማት ሌላው ፈተና በአዲሲቱ ኢትዮጵያ መስራች አባትነት የሚጠቀሱት መለስ ዜናዊ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሃላፊነት ላይ እያሉ በድንገት መሞት ነበር። ይህ ዜና ብዙዎችን ያስደነገጠ ነበር። ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ማድረግ አይቻል ይሆን ? የሚል ስጋት የተፈጠረባቸው ዜጎችም ቀላል አልነበሩም። በውጭ ሃገር ያደፈጡና የኢፌዴሪን ህገመንግስታዊ ሥርአት ለማፈረስ ያስችላል ብለው ያሰቡትን ማንኛውንም ጉዳይ የሚያራግቡ ቡድኖችም፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሞት ሃገር ለማተራመስ እንደሚያስችል አጋጣሚ ለመጠቀም የሞከሩበት ሁኔታ ነበር። አሁን ፍርድ ቤት የወሰነባቸውን ቅጣት በመፈጸም ላይ የሚገኙት ያኔ ከለንደን ወደኤርትራ እየተመላለሱ ኢትዮጵያን በሽብር ጥቃት የማተራመስ እንቅስቃሴ ሲመሩ የነበሩት ግንቦት 7 የተባለው የኤርትራ ተላላኪ መስራችና መሪ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በአንድ ወቅት ከአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራም (ቪኦኤ) ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የመለስ ሞት ስርአቱን ለማፍረስ መልካም አጋጣሚ ፈጥሮልን ነበር፣ ሳንጠቀምበት አልፈናል . . . በሚል የሰጡትን አስተያየት ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል።

ያም ሆነ ይህ፣ የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ህልፈት መላውን ህዝብ ያስደነገጠና ያሳዘነ ቢሆንም፣ ስርአቱ ከግለሰቦች በላይ ህልውና ያለው መሰረት ላይ መዋቀሩን ባረጋጋጠ የስልጣን ሽግግር ሥርአቱ ሳይናወጥ አሁን ላይ መድረስ ተችሏል።

ሌላው ባለፉ አስር አመታት ከገጠሙን ፈተናዎች ሁሉ የማይረሳው በ2008 ዓ/ም በኦሮሚያና በአማራ እንዲሁም በተወሰኑ የደቡብ ክልል አካባቢዎች ተቀስቅሶ የነበረው ሁከት ነው። ይህ ተገቢ የህዝብን የመልካም አስተዳደር መጓደልና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካካትና ድርጊት የበላይነት እያገኘ መምጣት በህዝብ ላይ የፈጠረው ቅሬታ የቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ ውጭ ሃገር ባደፈጡ የኤርትራ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚዎችና ሌሎች ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚፈልጉ ሃይሎች ተላላኪዎች ተጠልፎ ወደአውዳሚ ሁከትነት ተቀይሮ ነበር። ይህ ሁከት በረደ ሲባል እያገረሸ ለአንድ ዓመት ያህል ለበርካታ ዜጎች ህይወት መጥፋት የመንግስትና የህዝብ ሃብት ውድመት ምክንያት ሆኗል።

በተለይ ባለፈው ዓመት መግቢያ ላይ በቢሾፍቱ አርሰዲ ሃይቅ ላይ የሚካሄደውን ዓመታዊ የኢሬቻ በአል ለሁከት መፍጠሪያነት ለመጠቀም በተደረገው ጥረት በመረጋገጥና ገደል ውስጥ በመውደቅ ከ50 በላይ ሰዎች ህይወት መጥፋቱን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የተሰለፉ ሃይሎች ይህን በማህበራዊ ሚዲያ በተሳሰተ መንገድ በማቅረብ በመላ ኦሮሚያ አውዳሚ ሁከት ቀሰቀሱ። ይህን ሁከት በተለመደው ህግን የማስከበር ስርአት ማረጋጋት ስላልተቻለ ህገመንግስረቱ በሚያዘው መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ።

ከዚህ በኋላ በመላ ሀገሪቱ ሰላማዊ ሁኔታ ሰፍኗል። ይሁን እንጂ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ ማግስት በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች የነጋዴዎች እለታዊ የገቢ ግምትን መነሻ በማደረግ ሁኔታውን በተዛባ ሁኔታ በማቅረብ፣ እንዲሁም ነጋዴውን በማስፈራራት ስራ የማቆም አድማ እንዲያካሂድ በማድረግ ሁከት ለመቀስቀስ ተሞክሯል። ይህም ፈተና ስርአቱን ሳያናውጥ ታልፎ እዚህ መድረስ ተችሏል።

በመጀመሪያው አስርት ዓመት ሃገሪቱን ከገጠማት ውስጥ ሌላው ተጠቃሽ ችግር ድንበርን ሰበብ በማድረግ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ያጋጠሙ ግጭቶች ናቸው። ይህን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሁለቱ ክልላዊ መንግስቶች ስምምነት ላይ የደረሱ ቢሆንም አሁንም፣ ምክንያቱን በግልጽ ለመለየት ባስቸገረ ሁኔታ እያገረሸ ይሄው ሰሞኑን እንደምንመለከተው ወደሁለተኛው የሚሊኒየሙ አስርት ተሸጋግሯል። እንግዲህ፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልለሎች መሃከል የተፈጠረውን ግጭት ይዘን ነው ወደ 2010 የተሻገርነው። ይህን ችግር የኢፌዴሪ ሥርአት እየፈታ ካለፋቸው ከላይ የተገለጹ ችግሮች አኳያ ስንመለከተው መፈታቱ አይቀሬ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም። የሁለቱን ህዝቦች በደም የተሳሰረ አንድነት አጽንቶ በሚያስቀጥል አኳኋን በቅርቡ መፍትሄ እንደሚያገኝ ባለሙሉ ተስፋ ነን።

እንግዲህ የአንድ የመንግስት ሥርአት ጽናትና ጥንካሬ የሚለካው አቅዶ በሚያከናውናቸው ስኬቶቹ ብቻ አይደለም።  ሳይታሰብ የሚከሰቱ ችግሮችን ተቋቁሞ ሳይናወጥ መፍትሄ እያበጀ፣ ለቀጣይ መማሪያ እንዲሆኑ ለታሪክ እየተወ መዝለቅ በመቻሉ ጭምር እንጂ። በዚህ ጽሁፍ የኢፌዴሪ መንግስት ካሳካቸው አንድ ሁለት ብሎ ዘርዝሮ ለማስረዳት የሚያታክቱ ዓለም የመሰከረላቸው ስኬቶች ይልቅ፣ ሳይታሰብ የገጠሙትና ሳይናወጥ ያለፋቸው ፈተናዎች ላይ ያተኮርኩት ለዚህ ነው። የኢፌዴሪ ሥርአት ያቀደውን የሚያሳካ ብቻ ሳይሆን በድንገት በሚገጥሙት ፈተናዎችም የማይናወጥ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy