አባይ የፖለቲካ ትኩሳት ማስቀየሻ…
አባይ የፖለቲካ ትኩሳት ማስቀየሻ…
ወንድይራድ ኃብተየስ
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሠረት የሚያደርገው የአገሪቱን ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታና አገራዊ ህልውናን በማረጋገጥ ብሎም በማንኛውም አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባትና ለህዝቦች ጥቅም በጋራ በመሥራት ላይ ነው። ይህ ኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲን መሠረት ያደረገው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ባለፉት አሥርት ዓመታት አገሪቱ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ዕድገት እንድታስመዘግብ በማስቻሉ ከራሷ አልፋ ጎረቤቶቿን መጥቀም እንደቻለች አብነቶችን በማንሳት መጠቃቀስ ይቻላል። ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓትን መተግበር ከጀመረችበት ሁለት አሥርት ዓመታት ወዲህ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት በማስመዝገቧ ዜጎቿ ብቻ ሳይሆኑ ጎረቤት አገሮች ጭምር አገሪቱ ካስመዘገበችው ዕድገት በቀጥታ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ለሁሉም ጎረቤት አገራት ዜጎች እንደሁለተኛ አገር በመቆጠር ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ስደተኞችን ማስጠለል ብቻ ሰይሆን ለስደተኞች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ሙገሳን ተችሯታል። ይህ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ትክክለኛነት ዋናው ማሣያ ተደርጎ ሊታይ የሚችል ውጤት ነው።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በፈጣን ሁኔታ ማደግ ሲጀምር ከጎረቤት አገራት ጋር በንግድ፣ በባህል፣ በሠላም ማስከበር ወዘተ…ትስስሩ እየጠነከረ መምጣት ጀምሯል። አብነት ኢትዮጵያና ጅቡቲ የጠነከረ ግንኙነት በመፍጠር ዛሬ ላይ አንዷ አገር ለሌላኛዋ የህልውና ምንጭ እስከመሆን ተደርሷል። ጅቡቲ የባህር በሯን ለኢትዮጵያ በማከራየት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ስታገኝ፤ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ የተለያዩ የግብርና ውጤቶችን ለጅቡቲ በማቅረብ ተመሳሳይ ጥቅም ማግኘት ችላለች። የተለያዩ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ማለትም ዘመናዊ የመንገድ ግንባታ፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ የአየር በረራ መስመሮች ማስፋፋት፣ የኃይል አቅርቦት ወዘተ…በማካሄድ የሁለቱን አገራት ህዝቦች ግንኙነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጋለች። ከሌሎች ጎረቤት አገሮች ማለትም ከደቡብ ሱዳን፣ ከሱዳን፣ ከኬንያ እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር አካባቢውን በምጣኔ ሀብት የሚያስተሳስሩና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን የመንገድ፣ የኃይል አቅርቦት፣ የአካባቢ ሠላም፣ ንግድ ወዘተ…እንዲስፋፉ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነች።
የኤርትራ ህዝብም ቢሆን ኢትዮጵያ ካስመዘገበችው የምጣኔ ሀብት ዕድገት ተጠቃሚ መሆን የቻለበት ሁኔታዎች እንዳሉ ማየት ይቻላል። አምባገነኑ የኤርትራ መንግሥት በህዝቡ ላይ በሚያደርሰው ከፍተኛ በደል ሣቢያ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኤርትራዊያን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ተሰደዋል። አገሪቱ እነዚህን የኤርትራ ስደተኞች አቅም በፈቀደ ሁሉ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን ለምሣሌ፣ የትምህርት እድልን በተመለከተ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ እንዲማሩ በመፍቀድ አጋርነቷን አሳይታለች።
እነዚህ ሁሉ መልካም ነገሮች የመነጩት ኢትዮጵያ ከምትከተለው የውጭ ፖሊሲ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም። በተመሳሳይ አትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ መሠረት ስትጥል አገሪቱ ያለባትን ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት እጥረት ለመፍታት እንዲቻል እንዲሁም በተመጣጣኝ ክፍያ ለጎረቤት አገሮች ኃይል በማቅረብ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበትን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ነው። ኢትዮጵያ ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች በዓለም አቀፍ ስምምነት መሠረት የሚተዳደሩ መሆናቸውን ከግንዛቤ በማስገባት የህዳሴው ግድብን ለኤሌክትሪክ ኃይል እንጂ ለመስኖ ልማት እንዳልሆነ በተደጋጋሚ አሳውቃለች።
በመሠረቱ ኢትዮጵያ እንደሱዳን ሰፊ የመስኖ መሬት የሌላት ከመሆኑም በላይ የግድቡ ሥፍራ ወደ ሱዳን ጠረፍ የተጠጋ በመሆኑ የህዳሴው ግድብ ለመስኖ ሥራ የሚያገለግል አይደለም። ይህን ጉዳይ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ለሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ አሳውቀዋል። ግብጽና ሱዳን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የ1929 እና 1959 የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን የሚጥስ በመሆኑ እንደማይቀበሉት ሲወተውቱ ቆይተዋል። ኋላ ላይ ሱዳን የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነትና የልማት ፖሊሲዎች መርምራ በመረዳቷ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ከተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች ያገኘችውን ጥቅም በማስላት አቋሟን በማስተካከል ለህዳሴውን የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ድጋፏን እንደምትሰጥ አሳውቃለች። ሱዳን ከኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች በተለይ ከተከዜ የኃይል ማመንጫ ግድብ ከፍተኛ ጥቅም ማግኘት በመቻሏ የኢትዮጵያ የልማት ሥራዎች አካባቢውን ሊጠቅሙ የሚችሉና የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስሩን የሚያሳድጉ መሆናቸውን ስትመለከት ለታላቁን የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትም ድጋፏን በተገኘው መደረክ ሁሉ አረጋግጣለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክትን ይፋ ባደረገበት ወቅት እንደገለፀው አገሪቱ የጀመረችውን ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገት ለማስቀጠል የሚቻለው እየታየ ያለውን ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት ችግር መቅረፍ ሲቻል ነው። የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ በሚያደርገው የመዋቅር ለውጥ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የኃይል አቅርቦት እንደሚያስፈልግ እውነታ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት አካባቢን የማይበክሉ ትላልቅ የውኃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት በመወሰን እንደ ጊቤ ሦስትና ታላቁ የህዳሴ ግድቦች ያሉ ግዙፍ የኃይል ማመንጫዎችን መገንባት ጀመረ። አገሪቱ ከነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የሚመነጨውን ኃይል አቅርቦት ፍላጎቷን ካሟላች በኋላ ለጎረቤት አገራት በተመጣጣኝ ዋጋ የኃይል ምንጭ በመሆን የቀጠናውን ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር ለማሳደግ ጠንክራ እየሰራች ትገኛለች።
ከዚህም ባሻገር አገሪቱ ለጎረቤት አገራት በተመጣጣኝ ዋጋ ከምታቀርበው የኃይል አቅርቦት የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ያስችላታል። እንግዲህ ከስድስት ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ግብፅና ሱዳን በተመጣጣኝ ዋጋ የኃይል አቅርቦት ከማግኘታቸው ባሻገር የህዳሴው ግድብ የወንዙን ሥነ ምህዳራዊ ሁኔታ መጠበቅ ስለሚችል በየወቅቱ የሚዋዥቀውን የወንዙን የውኃ መጠን በማስተካከል ዓመቱን ሙሉ የተመጣጠነ ፍሰት እንዲኖረው ያደርጋል።
ኢትዮጵያ ቀድማ ይዛ የተነሳችው አቋም ሁሉም የአባይ ተፋሰስ አገራት ከወንዙ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ፕሮጀክት ለመገንባት እንጂ፣ ኢትዮጵያ ግብፅን ወይም ሱዳንን ወይም ሌላ አገርን ለመጉዳት አስባ እንዳልሆነ በትልቁ ሊሰመርበት ይገባል። ባለፉት ዓመታት የአባይ ጉዳይ ሳይቀዛቀዝ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ የትኩረት መስክ ሆኖ አልፏል። ሦስቱ አገራት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በተከታታይ ጊዜያት ባደረጓቸው የምክክር መድረኮች ላይ እንደተስተዋለው የግብፅ ተደራዳሪዎች ይዘዋቸው በሚቀርቡት አጓጉል አጀንዳዎች ምክንያት ውይይቶቹ ፈር ሳይዙ የተበተኑበት አጋጣሚ ነበር።
አንዳንድ የግብፅ ፖለቲከኞችና ምሁራን ስለ ህዳሴው ግድብ በቂ መረጃ ሳይኖራቸው ቀርቶ ወይም ሁኔታውን ሆን ብለው አንጋደው ለህዝባቸውና ለዓለም ማኅበረሰብ በማቅረብ ያለባቸውን የፖለቲካ ትኩሳት በአባይ ጉዳይ በመሸፋፈን ለማስቀየሻነት ሲጠቀሙበት የነበረው ጊዜም አልፏል።
ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ለተፋሰሱ አገራትም ሆነ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በቂ መረጃዎችን ስታቀርብ ቆይታለች። ግብጽን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት የተውጣጣ የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲዋቀር ተደርጎ የህዳሴው ግድብ በአካባቢው አገራት ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ካለ እንዲገመገም ፈቅዳለች። ይህ በሆነበት ሁኔታ አንዳንድ የግብጽ ፖለቲከኞችና ምሁራን ስለህዳሴው ግድብ እንዲህ ያለ እርስ በርሱ የሚጋጭ መገለጫ በየሚዲያው የሚሰጡት በቂ መረጃ ሳይኖራቸው ነው ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።
አንዳንድ ግብፃዊያን ፖለቲከኞችና ምሁራን የውስጥ ችግሮቻቸውን በአባይ ጉዳይ ለማድበስበስ ሲሉ የላይኞቹ የአባይ ተፋሰስ አገራት በተለይ ኢትዮጵያ በግብፅ ላይ ጫና እያደረገች እንደሆነ በማስመሰል ሊጨበጥ የማይችል ታሪክ ያኔ ሲያወሩም ተደምጠዋል። በእርግጥ የኢንቴቤው ስምምነት በተፋሰሱ አገራት መካከል ፍትሃዊ የውኃ አጠቃቀም የሚያሰፍን ከመሆኑ በላይ በቀጣይ የቅኝ ገዥ ስምምነቶች ተቀባይነታቸው ያበቃበት የትብብር ማዕቀፍ ሆኗል።
ያም ተባለ ይህ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪን የሚጠይቅ ፕሮጀክት እቅድ ሲነድፍ የፋይናንስ ምንጭ እንደሚሆነው የተማመነው የህዝብ ድጋፍንና የውስጥ ገቢን እንጂ ከውጭ የሚገኝ ብድርንም ሆነ ስጦታን እንዳልሆነ ግንባታው ይፋ በሆነበት ወቅት ቃል በቃል ተነግሯል። እናም ግንባታው ዛሬም ለአፍታ ሳይስተጓጎል የሕዝብ ድጋፍና እገዛ ሳይለየው ቀጥሏል። አባይ ለግብጽ ፖለቲከኞች የፖለቲካ ትኩሳት ማስቀየሻነቱም ታሪክ ሆኖ ያልፋል። …