Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢረቻ ከልዩነት ባሻገር ያለ አንድነት የሚገለፅበት የምሥጋና፣ የእርቅና የሠላም በዓል ነው

0 972

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢረቻ ከልዩነት ባሻገር ያለ አንድነት የሚገለፅበት የምሥጋና፣ የእርቅና የሠላም በዓል ነው

ኢብሳ ነመራ

ኦሮሞዎች በየዓመቱ የሚያከብሩት የዘንድሮ የኢሬቻ በዓል መስከረም 21 በክልል አቀፍ ደረጃ በቢሾፍቱ ከተማ አርሰዲ ሃይቅ ወይም ሆረ አርሰዲ ላይ ይከበራል። ኢረቻ ኦሮሞዎች ክረምት አልፎ ወደጸደይ ብርሃን የሚደረገውን ሽግግር የሚያከብሩበት አውደ ዓመት ነው። አሮጌው ዓመት አብቅቶ ለአዲሱ አቀባበል የሚደርገብት፣ የአዲስ ዓመት ብስራት ዕለት ነው። ኦሮሞዎች በዚህ ዕለት ክረምቱን አዝንቦ ምድሩን አረንጓዴ ላለበሰው፣ ወንዞችን በውሃ ለሞላው፣ ምንጮችን ላፈለቀ፣ ከብቶች እንዲረቡና እንዲፋፉ ላደረገ ምሉዕ በኩለሄ ዓምላክ (Waaqa) ምስጋና ያቀርባሉ። ኢረቻ የምስጋና ቀን ነው።

የአዲስ ዓመትና የምስጋና ዕለት የሆነው ኤሬቻ የእርቅM በአል ነው ነው። የተጣሉ ሰዎች ሳይታረቁ ወደኢሬቻ አይሄዱም። ቂም ተይዞ ወደኢሬቻ አይኬድም። ኢረቻ የተጣሉ የሚታረቁበት ቂም የሚሽርበት በዓል ነው። በሃዘን ወደኢሬቻ አይኬድም። ወደኢሬቻ የሚኬደው በዓመtu ያጋጠመ ሃዘንን ለአሮጌው ዓመት ትቶ በተስፋና በደስታ ነው። ኤሬቻ የሚካሄድበት መልካ በሰውና በምሉዕ በኩለሄ ዓምላክ መሃከል ያለ ግንኙነት ብቻ የሚገለጽበት ስፍራ ነው።

የኢረቻ መልካ ሁሉም የኦሮሞ ልጆች በመሃከላቸው ያለውን የጎሳ፣ የሃይማኖት፣ የአመለካካት ልዩንት ጥለው የአንድ አባት ልጆች መሆናቸውን የሚገልጹበት የአንድነት ስፍራ ነው። በኢሬቻ በዓል ላይ ዓምላክን ከማመሰገንና ደስታን ከመግለጽ ውጭ የግል ወይም ቡድናዊ ፍላጎት መግለጽ ነውር (admalee) ነው።

የኢረቻ በዓል በአባ መልካዎች፣ ቃሉዎች፣ አባገዳዎች የሚመራ በአል ነው። ኢረቻ የመንግስት በዓል አይደለም። ይህን መነሻ በማደረግ በቅርቡ የሁሉም የኦሮሚያ አካባቢዎች አባገዳዎች የጋራ ሸንጎ የሆነው የአባ ገዳዎች ህብረት በኦዳ ቡልቶም ሸንጎ ተቀምጦ የዘንደሮውን ኢረቻ በምን አይነት አኳኋን እንደሚከከብሩ መክሮ አቋም ይዟል።  የአባገዳዎች ህብረት የዘንድሮ ኢሬቻ መስከረም 21 ቀን 2010 ዓ/ም እንደሚከበር አውጆ፣ በዓሉን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለማክበር አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቋል። ህብረቱ የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል አከባበር የሚያስተባብሩ 300 ወጣቶች (foollee) መመረጣቸውን አስታውቋል። የአባገራዎቹ ህብረት በበዓሉ ላይ የጦር መሳሪያ የታጠቀ ፖሊስ እንደይገኝ መወስኖ፣ ይህንንም ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስታውቆ ተቀባይነት ማግኘቱን አስታውቋል። የኢሬቻ በዓል በሚከበርበት ስፍራ ሀገሪቱንና ክልሉን የሚያስተዳድረውን ፓርቲ ጨምሮ የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ዓርማ እንዳይያዝና እንዳይውለበለብ መወሰኑንም አስታውቀዋል። ህበረቱ የኢረቻ መልካ የፖለቲካ መድረክ ከመምሰል በፀዳ መልኩ የኦሮሞ ባህልን በማንፀባረቅ መከበር እንደሚኖርበት አሳስቧል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፖሊስ ያለ ምንም ትጥቅ ከዳር በመሆን በዓሉን ለማክበር ከመጡት ጋር ተቀላቅለው ስርቆትና የመሳሰሉ ወንጀሎችን ለመፈፀም የሚንቀሳቀሱ አካላትን የመከላከል ስራ እንደሚሰራም ተገልጿል። በበዓሉ ላይ የሚሳተፉ ሰዎችን የመፈተሽ ስራ የሚሰሩት በአባ ገዳዎች የተመረጡት 300 ወጣቶች እንዲሆኑ ተወስኗል። በ2009 ዓ/ም በኢሬቻ በዓል ላይ ህይወታቸው ላለፉ ሰዎች በቆመው የመታሰቢያ ሀውልት ላይ ከተፃፈው ጽሁፍ ጋር ተያይዞ ቅሬታ በመቅረቡ ጽሁፉ ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ መወሰኑም ተገልጿል።

እንግዲህ፣ ኢረቻ የህዝብ በዓል በመሆኑ በአባገዳዎችና አባ መልካዎች እንዲመራ መደረጉ መልካም ነው። ኢሬቻ ቀደም ሲል እንደተገለጸው የምስጋና፣ የእርቅ፣ የሰላምና የደስታ፣ የአንድነት በዓል በመሆኑ ከዚህ መነፈስ ውጭ የሚከናወን ማንኛውም ድርጊት ለኦሮሞዎችና ለባህላቸው ካለ ንቀት የመነጨ ተደርጎ ነው የሚወሰደው።

ኢረቻ ለክፍለ ዘመናት ሲከበር የቆየ በዓል ነው። ባለፉት ስርአቶች እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህላዊ እሴቶች እውቅና ተነፍጎት፣ ያለባህሪው ክፉ ዓመል ተለጥፎበት ተደፍቆ ቆይቷል። ይህም ሆኖ በየአካባቢው መለካዎች ላይ ሲከናወን ቆይቷል፤ ደብዛውን ማጥፋት አልተቻለም። የኢረቻ በአል አንሰራርቶ አደባባይ የወጣው ባለፉ ሁለት አስር ዓመታት ነው። ይህ በየአቅጣጫው ማንነቱን የሚገልጹ እሴቶቹን ለማጥፋት በመንግስት ደረጃ ዘመቻ ሲካሄድበት ለኖረው የኦሮሞ ህዝብ ታላቅ ድል ነው።

በዚህ መሰረት በተለይ ባለፉ አንድ ተኩል አስርት ዓመታት ኢረቻ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ላይ በክልል አቀፍ ደረጃ ሲከበር ቆይቷል። ከዚህ በተጨማሪ በሁሉም የኦሮሚያ አካባቢዎች በሚገኙ መልካዎች በተመሳሳይ ስሜት ሲከበር ቆይቷል። ይሁን እንጂ በተለይ ባለፈው ዓመት በክልል አቀፍ ደረጃ በቢሾፍቱ የተከበረው በዓል እንቅፋት ገጥሞታል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚያስታውሰው፣ የእንቅፋቱ መነሻ ምክንያት የምስጋና፣ የእርቅ፣ የሰላም፣ የአንድነት በዓል የሆነው የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓል ከዚህ ውጭ የፖለቲካ መደረክ ለማድረግ የሞከሩ ተደራጅተው የገቡ ቡድኖች ያካሄዱት ህገወጥና ጸያፍ እንቅስቃሴ ነው። እነዚህ ቡድኖች ገሚሶቹ ጃዋር መሃመድን በመሳሰሉ ውጭ ሃገር በሚንቀሳቀሱ ፌደራላዊ ሥርአቱን ለማፍረስ የሚፈልጉ ቡድኖች በማህበራዊ ሚዲያ ባካሄዱት ቅስቀሳ ያደራጇቸው ነበሩ። በሃገር ውስጥ ህጋዊ ሆነው በሚንቀሳቀሱ፣ አመቺ አጋጣሚ ያገኙ ሲመስላቸው ግን ወደህገወጥነት የመሄድ ዝንባሌ ባላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የተደራጁም ቡድኖች እንደነበሩ የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ። በበዓሉ ታዳሚዎች መሃከል ሲውለበለቡ የነበሩ የፓለቲካ ፓርቲዎች ዓርማዎች ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። በዚህ በዓል ላይ የኦነግንና የኦፌኮን አርማ እያውለበለቡ በበዓሉ ታዳሚዎች መሃከል የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች እንደነበሩ ተመልክተናል።

ይህ ብቻ አልነበረም። የእነዚህ ቡድኖች አባላት የበዓሉ ዋነኛ መገለጫ የሆነው ምርቃትና ምስጋና በአረጋውያንና በአባገዳዎች የሚቀርብበት መድረክ ላይ በመውጣት ከአባገዳዎች እጅ ማይክራፎን በመንጠቅ አዋኪ የተቃውሞ ቅስቀሳ ማካሄዳቸውን ተመልክተናል። ይህን ተከትሎ ከበዓሉ ታዳሚዎች መሃከል በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ ሲሰራጭ በነበረው ቅስቀሳ የተደናገሩ የተወሰኑ ወጣቶች የተቃውሞ ቅስቀሳውን ተከትሎ በእጅ ምልክትና በጩኸት የበዓሉን መንፈስ ቀየሩት። በዚህ አኳኋን ኦሮሞዎች ለምሉዕ በኩለሄ አምላካ ምስጋና ለማቅረብ የታደሙበት በዓል ወደ የፖለቲካ ተቃውሞ ትዕይንትነት ተቀየረ። ይህ ጸያፍ ተግባር ነው።

ጸያፍ የሚያደርገው ተቃውሞ ማሰማቱ አይደለም። ዜጎች የፈቀዱትን አመለካካት የመያዝ፣ የማራመድ፣ አቤቱታዎችን የማሰማት፣ ተቃውሞዎችን በማንኛውም ሰላማዊ መንገድ የመግለጽ ህገመንግስታዊ መብት አላቸው። ድርጊቱን ጸያፍ የሚያደረገው ከልዩነት በላይ ያለ የኦሮሞዎች አንድነት በሚገለጽበት የምስጋና፣ የእርቅና የሰላም መግለጫ በሆነው የኢረቻ መልካ ላይ መካሄዱ ነው።

ይህ ያለቦታው የተካሄደ ተቃውሞ ታዳሚዎችን አስደንግጦ ነበር። እናም መልኩን የቀየረው መልካ ላይ ላለመገኘት ከስፍራው መሸሽ ይጀምራሉ። ቦታው ለአደጋ ጊዜ መውጫነት አመቺ ስላልነበረ በተለይ በስፍራው አንድ አቅጣጫ የነበሩ ተዳሚዎች ወደኋላ ሲገፉ በስፍራው የነበረ ጥልቅ የወሃ መውረጃ ቦይ ውስጥ ወድቀው ተረጋገጡ፤ በተደረመሰ አፈር ታፈኑ። በዚህ ሁኔታ በበዓሉ ላይ ለመሳተፍ በዓሉን በሚመጥን አኳኋን ደምቀው የወጡ ሃምሳ ያህለ ኮረዶች፣ ጉብሎች፣ ጎልማሶች ህይወታቸውን አጡ። ይህ እጅግ የሚያሳዝን አጋጣሚ ነበር።

በኢረቻ በአል ላይ ህይወታቸውን ያጡ ዜጎች ጉዳይ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ያሳዘነ፣ ሃዘኑ እስካሁንም ከልብ ያልወጣ ቢሆንም፣ ሁከቱን ለጠነሰሱት ለጃውር መሃመድና የኤርትራን መንግስት የትርምስ ስትራቴጂ ለማስፈጸም ለሚራወጡ ተላላኪዎች ግን ሲሳይ ነበር። በይፋ ይታይ የነበረውን የሟቾች ቁጥር በብዙ እጥፍ እያባዙ፣ የሞቱበትንም ምክንያት እያዛቡ ሲነዙ የነበረው ውዥንብር ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል።  

ያም ሆነ ይህ፣ የባለፈ ዓመት አሳዛኝ አጋጣሚ መቼም መደገም አይኖርበትም። አባገዳዎች የኤረቻ በዓል አከባበርን አስመልከቶ በልዩ ሁኔታ የመከሩትና በመገናኛ ብዙሃን ቀርበው ስለበዓሉ ምነነትና ስለአከባበሩ ማብራሪያ የሰጡት፣ በአሉ ከዓላማው ውጭ እንዳይወጣ ያሳሰቡትና የጥንቃቄ እርምጃ የወሰዱት ለዚህ ነው። በአጠቃላይ የኢረቻ በአል ከልዩነት በላይ ያለው የኦሮሞ አንድነት የሚገለጽበት የምስጋና፣ የእርቅና የሰላም በዓል ነው። በመሆኑም ኢረቻ በዚህ መነፈስ እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ይወጣ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy