Artcles

ኢንቨስትመንት— ባለፈው የበጀት ዓመት

By Admin

September 20, 2017

ኢንቨስትመንት— ባለፈው የበጀት ዓመት

ዳዊት ምትኩ

በ2009 የበጀት ዓመት በኢትዮጵያ ቀጥተኛ የውጪ ኢንቨስትመንት 20 በመቶ አድገት አሳይቷል። በዚሀም ሶስት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ቀጥተኛ የውጪ ኢንቨስትመንት ወደ አገር ውስጥ መሳብ ተችሏል።

በተለይ አገራችን ለጨርቃ ጨርቅና ለአልባሳት ዘርፎች ትኩረት ሰጥታ መንቀሳቀሷና መንግስትም የውጭ ንግዱን ለማሳደግ እንዲሁም በርካታ የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ በዘርፉ ላይ ተስፋ ሰንቆ በመስራቱ ለውጤቱ መገኘት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ አገራችን የምትከተለው ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብታ ለውጭ ባለሃብቶች በማቅረብ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ችላለች።

መንግሥት የግሉና የመንግሥት የዘርፎች ተዋንያን በፍትሃዊ የገበያ ውድድር የተመሩ ልማታዊ ኢንቨስትመንት የማስፋፋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ገበያው የማይመልሳቸውን የልማት ጥያቄዎች በተጠናና በተመረጠ ሁኔታ መንግሥት በራሱ በቀጥታ የሚሳተፍባቸው አቅጣጫዎች እየተከተለ ነው።

ይህም መንግስት የመሰረተ ልማትና የሰው ሃብት ልማት ኢንቨስትመንት የማስፋፋት ሥራ በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ እንደ ልማታዊ መንግሥት ማከናወን ያለበት ቁልፍ ተግባር እንደሆነ ታምኖበታል የሚካሄድ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

የአገራችን መንግስት በዚህ መልኩ የገበያ ጉድለቱን በማጥበብ የኪራይ ምንጮችን ለማድረቅ እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ፣ የግብርናና የመሳሳሉት ድጋፎች በማድረግ ልማታዊ ባለሃብቶች እንዲበረታቱ እያደረገ ይገኛል።

ይህ ሁኔታም እንደ መሬት፣ ብድርና የመሳሰሉትን ድጋፎችን የግሉ ባለሃብት በቅድሚያ እንዲያገኝ፣ ቀልጣፋና ግልጽ፣ ተገማችና ውጤታማ እንዲሆኑ ብሎም ለልማታዊ ኢንቨስትመንቶች ይበልጥ አዋጪ የሚሆኑበትና የሚስፋፉበት ሁኔታ በየጊዜው እየጎለበተ እንዲሄዱ በማድረግ ላይ ይገኛል።

እርግጥ ለሀገራችን ፈጣን ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ኢንቨስትመንቶች ገበያው ላያስተናግዳቸው እንደሚችል ይታመናል። በመሆኑም ፈጣን ዕድገቱን ሳይቆራረጥ ለማስቀጠል የዚህ ዓይነት የኢንቨስትመንት መስኮች በጥንቃቄ እየተጠኑና እየተመረጡ በቀጥታ በመንግሥት በራሱ ብቻ ወይም ከግሉ ዘርፍ በጋራ እንዲካሄዱ እያደረገ ነው።

አሁንም ግን ከዕድገት ደረጃችን ጋር ተያይዞ ከሚኖረው የገበያ ጉድለት እና ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ጋር ተያይዞ ሊከሰትና ፈጣን ዕድገቱን ሊያስተጓጉል የሚችለው አደጋ ኪራይ ሰብሳቢነት ነው። አደጋውን ለማስቀረት አስቀድሞ የተለየና መፍትሔም የተቀመጠለት ጉዳይ ሆኗል።

በመሆኑም የመሬትና የባንክ አስተዳደር ሥርዓቶቹ እንደታቀደው ልማትን በሚያፋጥንና የህዝብ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የተሟላ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት ሁኔታ መከናወን እንዳለባቸው መንግሥት በፅኑ ያምናል።

ከዚህ በተጨማሪም የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱም ፍትሃዊ ውድድርን የሚያሰፍንና ህጋዊ ያልሆነ ጥቅምን የሚዘጋ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ ማከናወኑንም ቀጥሏል። በዚህም የመንግሥት ተሳትፎ የባለሃብቱን ልማታዊ እንቅስቃሴ የሚያሳድግ መሆኑም በገሃድ እየታየ ነው።

በተለይም ባለፉት 26 ዓመታት መንግሥት ልማታዊ የግል ኢንቨስትመንቶችን በማበረታታትና የኪራይ ሰብሳቢነት አማራጮችን በማጥበብ በግሉ ዘርፍ የማይሰሩ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ሂደት ውስጥ ውስን ሃብቱን መሰረታዊ ችግሮችን በሚፈቱ የልማት ሥራዎች ላይ አውሏል።

የልማት ኃይሎችን በማቀናጀትና በመምራት፣ የህዝብ ተሳትፎን በማጎልበት እና የግል ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለው እንዲሁም ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ዕድገትንና ማህበራዊ ልማትን ማረጋገጥ ችሏል።

ከዚህ ጎን ለጎንም መካከለኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የቴክኖሎጂና የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል። ከእነዚህም መካከል የአቅም ግንባታ፣ የገበያ ትስስርን መፍጠር እንዲሁም የኢንቨስትመንት ክትትልና ድጋፍ መስጠትን ያጠቃልላል። ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል።

ታዲያ መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን በወጭ ንግዱ ለማጠናከር ባከናወነው ተግባር ከምንጊዜውም በላይ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተመልክተናል። ለአብነት ያህል የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ኢንዱስትሪ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ለውጦች ታይተውባቸዋል። ባለፈው ዓመት ለተገኘው ለውጥ እነዚህ ሁሉ ጉዳዩች ወሳኝ ሚና ነበራቸው።

ባለፈው የበጀት ዓመት የተመዘገበው አጠቃላይ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ ዕድገት መመዝገቡ ለሀገራችን መፃዒ ዕድል ትልቅ ብስራት ነው። በተለይ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከበፊቱ የተሻለ ጥረት ለማድረግ የሚመለከተው አካል ሁሉ ቁርጠኝነቱን እያሳየ ይገኛል።

የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ልማትን በማስፋፋት የተፋጠነ ልማትን ለማረጋገጥ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራት ላይ ይገኛል። በመሆኑም ቅድሚያ የተሰጣቸው ዋና ዋና ዘርፎች፣ በተለይም በግብርና ልማት እንዲሁም በኢንዱስትሪ መር አቅጣጫን በቀዳሚነት የገቢ ምርት መተካት ላይ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ ነው።

ምንም እንኳን ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀገራችን በተፈጠረው አለመረጋጋት ሳቢያ በኢንቨስትመንቱ ላይ ጉዳት ቢደርስም መንግስት ተገቢውን ካሳ በመክፈል ጭምር ከፍተኛ ርብርብ አድርጓል። ይህ በመሆኑም አንቨስትመንታችን በተገቢው ፍጥነት እንዲያድግ ያደረገ ነው ማለት ይቻላል።

በወቅቱ በተፈጠረው ሁከት ችግር ደርሶባቸው የነበሩ ባለሃብቶችን በብድር መልክ እንደ አዲስ ከማቋቋም አንስቶ ከውጭ የሚያስገቧቸውን ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ በሆነ መንገድ እንዲያስገቡ በመፍቀድ ጭምር መንግስት ተገቢውን ድጋፍ አድርጎላቸዋል። ይህም በተለይ የውጭ ባለሃብቶች ከዚህ አገር ሳይወጡ ኢንቨስትመንታቸውን እነዲያስፋፉ መሰረት የጣለ ነው።

እነዚህ ሁሉ ተግባራት ባለፈው ዓመት ለተገኘው የ20 በመቶ የኢንቨስትመንት እድገት ወሳኝ ሚና መጫወታቸው አይካድም። በተለይም መንግስት በአገራችን ሁሉም አካባቢዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብቶ ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት በማድረግ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ከመሳብ በተጨማሪ የስራ እድልን መፍጠር መቻሉ ለውጤቱ መገኘት አስተዋፅኦው የላቀ ነው። ያም ሆኖ በያዝነው አዲስ ዓመትም ከ2009 ዓ.ም በላይ የኢንቨስትመንት ግኝትን የምናሰፋበት ሊሆን ይገባል።

እንዲሁም ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትንም የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎችም ካምናው ከፍ ማለት ይኖርናል። ለዚህም መንግስትም ይሁን ህብረተሰቡ የየድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።