Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እውነትም ኢትዮጵያዊያን ከድህነት የከፋ ጠላት የላቸውም!

0 297

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

…እውነትም ኢትዮጵያዊያን ከድህነት የከፋ ጠላት የላቸውም!

 

አባ መላኩ

 

የአገራችን የኅብረተሰብ ክፍሎች ዋነኛ ጠላት ድህነት መሆኑ በግልጽ ይታወቃል። ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በህይወት ዘመናቸው እያሉ የድህነትን አስከፊነት ለመግለጽ ሲሉ “ኢትዮጵያዊያን ጠላታቸውን መውጋት ከቻሉ ከድህነት የከፋ ጠላት የላቸውም።” ብለው ነበር። እውነት አላቸው።

 

ኢትዮጵያ ልማትን ማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ ነው በሚል መረባረብ ከጀመረች ሀያ ስድስት ዓመታት አልፈዋል። ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ ዘርፈ ብዙ የልማት ግንባታ  እየተከናወነ ይገኛል። በአገሪቱ ፍትሃዊ ልማትን እውን ለማድረግና በተለይም ባለፉት ሥርዓታት ትኩረት ተነፍገው የነበሩ አርሶና አርብቶ አደሮች ከዚህ ልማት ተጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ የግብርና ልማትን ማዕከል ያደረገ የልማት ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሰራበት ነው። አርብቶና አርሶ አደሩ ተዘፍቀውበት ከነበረው የከፋ ድህነት ተላቀው የተሻሻለ ህይወት እንዲኖሩ ለማስቻል ቀላል የማይባል ለውጥ ተካሂዷል።

 

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አገር ነች። በአገሪቱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕጋዊ እውቅና አግኝተው የተወከሉ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቁጥርም 75 ደርሷል። የኢትዮጵያ ህዝቦች በተለያየ የሥራ መስክ የተሰማሩ ቢሆንም አብዛኛው ህዝብ የሚተዳደረው በግብርና ነው። ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖርና በግብርና ሥራ የሚተዳደር ነው። በመሆኑም በግብርናው ዘርፍ እየተካሄደ ያለው ልማት የህዝቡን ጥያቄ የመለሰ ሆኗል።

በዚህ ማዕቀፍ ከሚገኙት ህዝቦች መካከል የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር ህዝቦች ይገኙበታል። እነዚህ ህዝቦች በተለይም በአገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ፣ ደቡብ ምሥራቅ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብና ምዕራብ አካባቢዎች የሰፈሩ ናቸው። እነዚህ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደር የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ጠረፋማ አካባቢዎች ናቸው።

በእነዚህ አካባቢዎች ከ15 ሚሊዮን በላይ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደር ህዝብ እንደሚኖር ይገመታል።

 

የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር ህዝቦች ከሌሎች የአገሪቱ ህዝቦች ጋር በንጽጽር ሲታዩ በሁሉም መልክ ተጠቃሚነታቸው የቀነሰ ነው። በአሁኑ ወቅት በመላ ኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት ግንባታ በፈጣን የዕድገት ምህዋር ላይ ይገኛል። የመንገድ፣ የስልክ፣ የመብራትና የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶች ተስፋፍተዋል።

 

በእነዚህ አካባቢዎች ያለው የመሠረተ ልማት ዝርጋት ግን ከቀደሙት ሥርዓታት በተወሰነ ደረጃ ይሻል እንደሆነ እንጂ ከተቀሩት የአገሪቱ ክፍሎች ሲነጻፀር አሁንም ገና ብዙ ይቀረዋል። በተለይ የአርብቶ አደሩ አካባቢ የዝናብ እጥረት የሚያጋጥመው፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የሚያስተናግድና ተደጋጋሚ ድርቅ የሚያጠቃው አካባቢ በመሆኑ ህዝቡ የበለጠ ተጎጂ ሆኖ ለዘመናት ዘልቋል።

በእነዚህ አካባቢዎች ያለውን እውነታ ማየት ይቻላል። በተለይ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን እንመልከት። በአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ያለው የልማት ለውጥ ከሌላው የአገሪቱ ክፍል ካለው በእኩል ደረጃ መጓዝ አልቻለም። እነዚህ አካባቢዎች መሠረተ ልማት በተፈለገው መልኩ ካልተስፋፋባቸው የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።  

 

በአካባቢዎቹ የመሠረተ ልማት አለመስፋፋት ደግሞ የአገልግሎት ተቋማት እንዳይስፋፋ ከፍተኛ መሰናክል ሆኖ ለዘመናት ዘልቋል። የትምህርት፣ የጤና፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ አገልግሎቶች በሚፈለገው ደረጃ አይገኝም። ለመሠረተ ልማትም ሆነ ለአገልግሎት ተቋማት በተፈለገው መልክ አለመስፋፋት ዋናው ምክንያት አካባቢዎቹ በቀደሙት ሥርዓታት ትኩረት ተነፍጓቸው የነበሩ ስለሆነ ነው።

በአገራችን በህዝብ ድምጽ ልማታዊ መንግሥት ከተመሠረተ በኋላ ለአካባቢዎቹ የተለየ ትኩረት በመስጠት የአገልግሎት ተቋማትን ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ ነው። ይሁንና  በሚፈለገው መልክ ከሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ጋር ተጣጥሞ መሄድ አልቻለም።

ለዚህም መሰናክል ከሆኑት ዐበይት ምክንያቶች መካከል የሕዝቡ በተወሰነ ሥፍራ ተረጋግቶ አለመኖሩ ነው። አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩ ህዝብ አንድ የተወሰነ የሚኖርበት ሰፈርም ሆነ መኖሪያ የለውም። የሚተዳደረው በእንስሳት ዕርባታ በመሆኑ የእንስሳት ግጦሽና ውኃን ፍለጋ ወቅትን ተከትሎ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ በመዘዋወር መኖር ግድ ሆኖበት ዓመታት ዘልቀዋል።  

 

በዚህ ሁኔታ የሚኖረው የአካባቢው ማኅበረሰብ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የሚያስችል የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ነድፎ በመሥራት ላይ ይገኛል። የዚህን ህዝብ ችግር በጊዚያዊነት ለመፍታት መንግሥት ከማኅበረሰቡ አኗኗር ጋር የሚጣጣም ማህበራዊ አገልግሎት ማቅረብን ሥራዬ ብሎ ተያይዟል። በዚህ መልክ በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማት ተንቀሳቃሾች ናቸው።

 

አርብቶ አደሩ አንድን ሰፈር ለቆ ወደ ሌላ ሰፈር በሚጓዝበት ወቅት የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትም የሰው ኃይላቸውንና ቁሳቁሳቸውን ይዘው ከአርብቶ አደሩ ጋር አብረው እንዲሄዱና በሚያርፉበት አካባቢም ሆነው አገልግሎቱን ያለማቋረጥ እንዲሰጡ የማድረግ አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራበት ነው። በዚህ መልክ የተወሰነ ርቀት መሄድ ተችሏል።

 

ይህ የመፍትሄ አካል ግን የአርብቶ አደሩን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚችልና የልማት ተጠቃሚነቱን ሙሉ በሙሉ ሊያረጋግጥ የሚችል አይደለም። መፍትሄው በጊዚያዊነት አርብቶ አደሩን ለማገዝ የተወሰደ ነው። ከዚህ አንድ ዕርምጃ ወደፊት በመሄድ ሌላ መፍትሄ ማፈላለግ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም።

እንደሚታወቀው ከ1983 ዓ.ም በኋላ በአገሪቱ በተፈጠረው የሠላም፣ የዴሞክራሲና የልማት አቅጣጫ የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩን ህዝብ ህይወት ለመቀየር የሚያስችሉ የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተነድፈው በመተግበራቸው መሠረታዊ ለውጦች መታየት ጀምረዋል። መንግሥት አገሪቱን ከድህነት አረንቋ ለማውጣት የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ነድፎ በመተግበር ላይ በመሆኑ አገሪቱ በዚህ የዕድገት አስተሳሰብና የዕድገት ምህዋር ውስጥ ገብታለች።

 

በዚህ መልክ የተቀረፀው የኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ የአርብቶ አደሩ ጉዳይ በሰፊው እንዲያካትት በመደረጉ የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮች ተጠቃሚነት በተወሰነ ደረጃ እየተረጋገጠ መጥቷል። የአርብቶና የከፊል አርብቶ አደሩን ህይወት መቀየር የሚያስችል የሥራ እንቅስቃሴ ለማድረግ በልማት ስትራቴጂው ከሰፈሩ ታላላቅ አጃንዳዎች አንዱ አካባቢውን ማልማት ነው። የአርብቶ አደሩ አኗኗር በእንቅስቃሴ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ሁሉንም አርብቶና ከፊል አርብቶ አደር በቀጥታ ወደ አርሶ አደርነት በአንድ ጊዜ መቀየር ስለማይቻል ኑሮውን ለመለወጥ እየተደረገ ያለው ጥረት በሁለት መንገድ የሚፈፀም ይሆናል።

 

አንደኛው አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩ ባለበት ሁኔታ ኑሮውን ማሻሻል እንዲችል ማገዝ ነው፤ ሌላው ደግሞ በዘላቂነት ወደ አርሶ አደርነት እንዲለወጥ ማድረግ ነው። የመጀመሪያውን አቅጣጫ ለማስፈፀም ተንቀሳቃሽ የአገልግሎት ተቋማትን ማስፋፋት ነው። አርብቶ አደሩ ለእንስሳት ግጦሽና ውኃ ፍለጋ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ አብረው የሚንቀሳቀሱ ትምህርትና ጤና ተቋማትን ማስፋፋት ነው። የሰውና የእንስሳት የህክምና ባለሙያዎች በሰፊው በመመደብ አርብቶ አደሩ ጋር እንዲኖሩ እየተደረገ ነው። እነዚህ ባለሙያዎች ከአርብቶ አደሩ ጋር እየተዘዋወሩ እየኖሩ የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለመቀየር ይጥራሉ።

በተመሳሳይ መልኩ ተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤቶች በማዘጋጀትና መምህራንን በመመደብ የአርብቶ አደሩ ልጆች የትምህርት ማዕድ ተቋዳሽ የሚሆኑበት መንገድ ተመቻችቶላቸዋል። መንግሥት የአርብቶ አደሩን ችግር ለመፍታት የወሰደው ርምጃ መጀመሪያ አርብቶ አደሩ ያሉበትን ችግሮች ለይቶ ማውጣት ነበር። በመሆኑም ሦስት ዐበይት ችግሮች ተለይተዋል።

 

የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች በልማት ወደ ኋላ የቀሩ በመሆኑ በህዝቡ የሥራ ባህል አለመዳበር፣ አማራጭ የገቢ ማስገኛ መስኮች አለመኖር፣ ሥር የሰደደ የሥራ አጥነት ችግር መኖሩ ዋናዎቹ ችግሮች ነበር። ሌላው ደግሞ ምንም እንኳን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ለውጦች ቢታዩም አሁንም በአንጻራዊነት ትምህርት ቤቶችና ጤና ተቋማት በሚፈለገው መጠን ባለመስፋፋታቸው ችግሩ አሁንም አለ። አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩ ህዝብ ያልተደራጀና ተበታትኖ የሚኖር መሆኑ የህዝቡን የመሠረተ ልማትና የአገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።

 

በመጀመሪያው አምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እንደተመለከተው የአርሶ አደሩን ችግር በጊዚያዊነት ለመፍታት እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በማጠናከር በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል። በዘላቂነት ኑሮውን መቀየር የሚቻለው ከአርብቶ አደርነት ተላቆ የተረጋጋ ህይወት መምራት ሲችል ነው። የተረጋጋ ህይወት ሊኖረው የሚችለው ደግሞ የራሴ የሚለው ቋሚ መንደርና መኖሪያ ሲኖረው ነው።

 

ይህ ማለት ከአርብቶ አደርነት ወደ አርሶ አደርነት መቀየር ሲችል መሆኑ እሙን ነው። አርብቶ አደሩ ህዝብ ወደ አርሶ አደርነት በመቀየር ከዚያም አርሶ አደሩን ከድህነት ለማላቀቅ እየወሰደ ያለውንና በርካታ የአርሶ አደሮችን ህይወይት በመቀየር በርካቶች ወደ ኢንቨስተርነት መቀየር ያስቻለውን የግብርና ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ በመጠቀም ህይወታቸው ለመቀየር እየተሰራ ነው።

 

ከዚህ ባሻገር በአርብቶ አደርነት የሚኖር ህዝብ ኑሮው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ ተረጋግቶ ስለ ህይወቱ መሻሻል የሚያስብበትና ትምህርትና ሥልጠና የሚወስድበት እድል ይኖረዋል። በመሆኑም የማስፈሩ ዓላማ አንድም ተበታትነው የሚኖሩትን በማቀራረብ ማህበራዊ ቁርኝታቸውን የበለጠ ለማሻሻል ነው። በሌላ መልክ ደግሞ የተረጋጋና የተሻሻለ ህይወት እንዲኖረው ለማድረግ ነው።

 

በመሆኑም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመንደር የማሰባሰብ ሥራ እየተካሄደ ይገኛል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ትላልቅ ልማቶች በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ህዝቡን በመንደር የማሰባሰቡ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል። በተለይም የስኳር ልማት እየተስፋፋባቸው ያሉባቸው አካባቢዎች ይጠቀሳሉ። ለአብነት በኦሞ፣ በወልቃይትና በአፋር እየተገነቡ ባሉ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች በልማቱ ምክንያት ለሚነሱ ነዋሪዎች መንደርን ገንብቶ የማስፈር ሥራ ተከናውኗል። በቤንሻንጉልና በጋምቤላ ክልሎችም አርሶ አደሩ የሚኖረው ተበታትኖ ስለነበር በመንደር የማሰባሰቡ ተግባር ቀጥሏል። ክልሎቹ ነዋሪዎቻቸው ተበታትነው የሚኖሩ በመሆኑ የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ይገኛል። በአርብቶ አደሩ አካባቢ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች የአርብቶ አደሩን አኗኗር በመቀየርና በማሻሻል ረገድ የሚኖራቸው ሚና የጎላ ነው። በርትተን ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል።  በእውነትም ኢትዮጵያውያን ከድህነት የከፋ ምን ጠላት አላቸው!

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy