Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከፍታውን” ማሳነስ—ለምን

0 688

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ከፍታውን” ማሳነስ—ለምን?
ዘአማን በላይ
ይህን ፅሑፍ ለማዘጋጀት መነሻ የሆነኝ ከመሰንበቻው የአይጋ ፎረሙ ፀሐፊ አቶ ዘርዑ ሓጎስ ‘የኢትዮጵያ ፈርስት ዳት ኮሙን’ ቢኒያም (ቤን) “ኮሜንተሪ”ን አስመልክተው የሰጡት አጭር አስተያየት ነው። በአስተያየታቸውም የእርሳቸው ምልከታና “የቤን” እይታ አንድ መሆኑን ጠቁመዋል። እንዲያውም ‘የኢትዮጵያ ከፍታ’ የሚለውና የደርጉ ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ መፈክር አንድ ዓይነት መሆኑን ለመግለፅ ሞክረዋል።
የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ የ“ቤን” እና የአቶ ዘርዑ ሃሳብ አንድ በመሆኑ ላይ ምንም ዓይነት ተቃውሞ የለኝም። እንዲያውም “ቤን”ም ሆነ አቶ ዘርዑ በህገ መንግስታችን የተረጋገጠላቸውን ሃሳብን የመያዝና የመግለፅ መብት ከመቀመጫዬ ብድግ ብዬ የማከብር ሰው ነኝ። እንዲሁም በደፈናው ማንንም የምቃወም አሊያም በጭፍን የምነቅፍ ሰውም አይደለሁም። ሆኖም እንደ ሁለቱ ግለሰቦች እኔም ሓሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቴን ተጠቅሜ ስለ ‘ኢትዮጵያ ከፍታ’ ጥቂት ማለት እንዳለብኝም እገነዘባለሁ። የዚህ ፅሑፍ ዓላማም ይኸው ነው።
ርግጥ “ቤን” ባነሳቸውና ለአስር ቀናት በሚቆየው የኢትዮጵያን ሚሌኒየም የመጀመሪያው አስር ዓመት (First decade) የተለያዩ ደጋፊ መልዕክቶችን አስመልክቶ የምስማማባቸውም ሆኑ የማልስማማባቸው ነጥቦች ይኖራሉ። በእኔ እምነት መልዕክቱን ማንም ይበለው ማን ዋናው ጉዳይ ‘የኢትዮጵያ ከፍታ’ እውን መሆኑ አይቀሬነት ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ደጋፊ መልዕክቶቹ በደምሳሳው ሲታዩ፤ ከፊሎቹ በጥናት ላይ ያልተመሰረቱ፣ ስለ ሁነት ፈጠራ (Event Creation) ግንዛቤ ባለው ሰው ወይም ሰዎች ያልተዘጋጁ እንዲሁም ሀገራችን ከምትመራበት ህገ መንግስት አኳያ የተቃኙ ላይሆኑ ይችላሉ። ግና ፅንሰ ሓሳቦቹ በራሳቸው ክፋትን የያዙ አይደሉም።
ስለ ፍቅር፣ ስለ መከባበር፣ ስለ ሰላም፣ ስለ ንባብ…ወዘተ. መነገሩ ምንም ዓይነት ክፋት ሊኖረው አይችልም። ክፋት አለው ብሎ የሚያስብ ሰው ይኖራል ብዬም አላስብም። ችግሩ በፅንሰ ሓሳቦቹ ላይ የተሰጡት አንዳንድ ማብራሪያዎችና የጥልቀት ደርዞች የሚጠበቀውን ያህል ያለመሆን ይመስለኛል። ሁለት ምሳሌዎችን መመልከት እንችላለን—ፍቅርንና መከባበርን። ‘ፍቅር’ ሲባል ‘የምን ፍቅር?’ የሚል ጥያቄን ያጭራል። ርግጥ ፍቅር የእናት፣ የሀገር ወይም የፆታ አሊያም የቁስ፣ የአካባቢ…ወዘተ. ሊሆን ስለሚችል ፅንሰ ሓሳቡ ውስን (Specific) በሆኑ ሀረጎች መገለፅ ይገባው ነበር።
በሌላ በኩልም፤ ስለ መከባበር ሲነሳ በማሳያነት የመከላከያ ሰራዊትና የፖሊስ ሰራዊት ሰላምታ መሰጣጣታቸው ችግር ያለው አይመስለኝም። ምክንያቱም መከላከያም ይሁን ፖሊስ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ያቀፉ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መገለጫዎች ስለሆኑ ነው። አንዳንዶችም እነዚህን ሁለት ህዝባዊ ወገንተኛ ተቋማት “የትንሿ ኢትዮጵያ መገለጫዎች” በማለት የሚጠሯቸው ከዚህ ሀገርን ወካይነታቸው ቁመና በመነሳት ይመስለኛል።
እናም ከእነዚህ ሁለት ማሳያዎች በመነሳትም ሁሉም የአስሩ ቀናት መፈክሮች ‘ትክክል አይደሉም’ ብሎ መፈረጅ የሚቻል አይመስለኝም። ያም ሆኖ ግን መንግሰት እንደ መንግስት ስለ እነዚህ ጉዳዩች ማሰቡ በራሱ ከበጎነት የዘለለ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው ይገባል ብዬ አላስብም—ምናልባት በአፈፃፀምና ማብራሪያ በመስጠት ረገድ ጎልቶ የወጣ ነገር ሊኖር እንደሚችል ሊታሰብ ቢችልም። ሆኖም በጉዳዩ ላይ የሚሰጡ ትችቶች ምናልባትም ‘እኔ እያለሁ፣ ለምን ሌላ?’ ከሚል ፍላጎት የመነጨ ከሆነ የአግባብነት ሚዛኑ ወደ ክፋት የሚያዘነብል ይመስለኛል።
እንደ እውነቱ ከሆነ “መጪው ጊዜ የኢትዮጵያ ከፍታ ነው” ቢባል ቅር የሚለው የሀገሬ ልጅ የሚኖር አይመስለኝም—የራሱ ድብቅ አጀንዳ የሌለው ግለሰብ ወይም ቡድን ካልሆነ በስተቀር። የኢትዮጵያ ከፍታ ጎልብቶ ሰላማችን አሁን ካለው በላይ ይበልጥ አስተማማኝ በመሆኑ፣ ልማታችን እጅግ አድጎ ሁሉም ዜጋ ከፍተኛ ተጠቃሚ ቢሆን፣ ሀገር በቀሉ ዴሞክራሲያችን ስር ሰዶ በህዝቡ ፈቃድ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምፃቸው የሚሰማበት ሆኖ ማየትን የማይመኝ “ጤነኛ” ኢትዮጵያዊ አለ ብዬ አላስብም።
ይህ ማለት ግን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህን ይመኛል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። በሀገራችን የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተሰየሙትን ቡድኖች እንመራለን የሚሉ የኤርትራና የሌሎች የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ለውጥ የማይኙ ሀገራት ባንዳ ሆነው “በሆድ አደርነት” የተሰለፉ ኃይሎች እንዲሁም እንደ ጃዋር መሐመድ ዓይነት የውጭ ምንደኞች ለሀገራችን መፃዒ ለውጥ በጎ ያስባሉ ማለት አይደለም። የሀገራችን ማደግ የእነርሱን የተላላኪነት ጥቅም ስለሚነካ ይህን የህዝቦችን ሁለንተናዊ ለውጥ ሊደግፉት አይችሉም። ‘መንግስት የነካው ነገር ሁሉ ትክክል አይደለም’ ብለው የሚያስቡ አንዳንድ የሀገር ውስጥ ህጋዊ ተቃዋሚዎች ነን ባዩችም ገዥውን ፓርቲ የጎዱ መስሏቸው ሁለንተናዊ ለውጡን ላይደግፉት መቻላቸው የሚገርም አይደለም—ጉዳዩ ከአፈጣጠርና ከማንነታዊ ባህሪ ጋር የሚያያዝ ነውና።
በሌላ በኩልም በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኳቸው የአይጋ ፎረሙ ፀሓፊ አቶ ዘርዑ ሓጎስ የሶስተኛው ሚሌኒየም የመጀመሪያው አስር ዓመት መሪ ቃል የሆነው “መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው” የሚለውንና የሰው በላው የደርግ-ኢሰፓ ስርዓትን “ኢትዮጵያ ትቅደም” አምባገነናዊ መፈክር “አንድ ናቸው” በማለት የገለፁበትን አግባብ ትክከል ነው ብዬ አላስብም። በየትኛው እይታም እንደተመለከቱት አይገባኝም።
እንደሚታወቀው አቶ ዘርዑን ጨምሮ ማንኛውም የደርግ ስርዓትን የሚያውቅ ሰው፤ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የሰላም የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓትን ከሰው በላው የደርግ- ኢሰፓ የግፍ አገዛዝ ጋር ማነፃፀር አግባብ የሚሆን አይመስለኝም። ምክንያቱም የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ‘የከፍታ ዘመን’ በሀገር ውስጥ የዜጎችን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ፣ አሁን ከተገኘው በላይ ፈጣንና ተከታታይ ልማት እውን አድርጎ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል እንዲሁም የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን እጅግ ስር ሰድዶ መሰማት የሚገባቸው አናሳ ድምፆች (Minority Voices) ጭምር የሚሰሙበት እንዲሆን ለማድረግ ከመመኘት የመነጨ ነው። ይህን ደግሞ አቶ ዘርዑም ቢሆኑ በሚገባ የሚገነዘቡት ይመስለኛል። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ “መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው” ማለት 2010 ዓ.ም ማለት አይደለም። ይህ ሀረግ ብዙም ያልራቁ፤ ነገር ግን ዘለግ ያሉ ዓመታትን የሚወክል ይመስለኛል።
ርግጥ ይህ ማለት ደግሞ በ2010 ዓ.ም ተአምር ይፈጠራል ማለት አይደለም። ይህም በሶስተኛው ሚሌኒየም አስር ዓመታት ውስጥ የተገኙ ሁለንተናዊ ስኬቶችን ከመዘከር ባለፈ፤ “መጪው ዘመን”ም (ቀጣዩቹ ያልተራዘሙ ዓመታትም) የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን መሆኑን ለማሰብ ነው።
ታዲያ ይህ የሚሆነው በሀገር ውስጥ በህዝቦች የማይተካ ተሳትፎ የሀገራችንን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እውን ለማድረግ እንዲሁም ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በጋራ ለማደግ በማለም ጭምር ነው—መጪው ዘመን የሀገራችን ከፍታ የሚሆነው። የቀጣናው አውራ፣ የአፍሪካ ተምሳሌትና የዓለም ድምፅ መሆንንም የሚያካትት ጭምር።
እናም ይህ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የከፍታ ዘመን ራዕይ እንደምን ሰው በላ ከሆነው የደርግ ስርዓት “ኢትዮጵያ ትቅደም” ጦር ሰባቂ መፈክር ጋር “አንድ ነው” ሊባል እንደሚችል ሊገባኝ አይችልም። ደርግ “ኢትዮጵያ ትቅደም” ሲል ‘ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር’ በማለት ነው። ወጣቱንና አጠቃላይ ህዝቡን ከሀገራዊ ልማት ተጠቃሚ እያደረገ ሳይሆን፤ ወደ ጠርነት አየማገደው ነው። ከ500 ሺህ ብር በላይ ማንም ዜጋ መያዝ የለበትም ብሎ እጅ ተወርች ጠፍንጎ በመያዝ ዜጎችን እያስመረረ ነው—“ኢትዮጵያ ትቅደም” ይል የነበረው። ስለ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ሳይሆን፤ ስለ ጦርነት፣ እንደ ግመል ሽንት የኋሊት ኢኮኖሚያዊ ግስጋሴንና ፀረ-ዴሞክራሲያዊነትን እያቀነቀነ ነው—ኢትዮጵያ መቅደም አለባት ይል የነበረው።
ደርግ ዴሞክራሲን ሳይሆን ህዝቡን በፀረ-ዴሞክራሲ የአፈና ቀንበር እያረሰበትና በግፍ በትር ቁም ስቅሉን እያሳየ ነበር—“ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለው። ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በል ሲለው ‘በምዕራብ በኩል አንድ ያልፈነዳ ጎማ አለ’ እያለ በመከበብ ስሜት ውስጥ ሆኖ የሀገሪቱ ዜጎች በበርካታ ጉዳዩች ከሚመሳሰሏቸው ወንድምና እህት አጎራባቾቻቸው ነጥሎ ነበር—ስለ ኢትዮጵያ መቅደም ሲደሰኩር የነበረው። ሀገሪቱን በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ የጦርነት አውድማና የድህነት ተምሳሌት ተደርጋ እንድትታይ እያደረገ ነበር—ስለ “መቅደሟ” በደመ ነፍስ ሲናገር የነበረው።
እናም ይህ በተግባር የሀገሪቱ የቁልቁለት ጉዞ መገለጫ የሆነው የደርግ “የኢትዮጵያ ትቅደም” የይስሙላ ዲስኩር፤ በምን ዓይነት የተቃርኖ አስተሳሰብ የዕድገት ተምሳሌት ከሆነችው፣ ለጎረቤቶቿ ሰላም ከምትጨነቀው፣ ሀገር በቀል ዴሞክራሲን ይበልጥ ለማጎልበት እየሰራች ካለችው፣ በሰናይ ምግባሯ የጎረቤቶቿ መጠጊያ ከሆነችው፣ የአፍሪካና የዓለም ድምፅ እስከመሆን ከደረሰችው ከአዲሲቷ ኢትዮጵያ የማይቀር የከፍታው ዘመን እውነታ ጋር “አንድ ነው” እንደተባለ ለማንም ግልፅ አይደለም። እንዲያውም እኔ እስከሚገባኝ ድረስ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለው የደርግ የይስሙላ ተረክ ተቀራራቢ ወይም ተመሳሳይ ትርጓሜ ሊኖረው የሚችለው “ኢትዮጵያ ፈርስት” ከሚለው ሀረግ ጋር ነው። ምናልባት አባባሉ እውነታውን ካለማወቅ የተሰነዘረ ከሆነ፤ በዚህ መልኩ መስተካከል አለበት ብዬ አምናለሁ።
እዚህ ላይ ስለ “መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው” እና “ኢትዮጵያ ትቅደም” አስቂኝ ንፅፅር ገታ ላድርግና መንግስት በመጪው ጷጉሜን 5 ቀን 2009 ዓ.ም ስለሚያጠቃልለው የሁነት ዝግጅት ስለተበጀተው ገንዘብ ጉዳይ ጥቂት ልበል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የተበጀተው ገንዘብ አራት ሚሊዩን ብር ነው። ይህ ገንዘብ የወጣው ከመንግስት ካዝና አይደለም። ገንዘቡ ከልማት ድርጅቶች የተገኘ ነው።
ያም ቢሆን ገንዘቡ ከየትም ይምጣ ከየት ለሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዩች አሊያም ‘ለሰናይ ምግባሮች’ ቢውል የሚለው መከራከሪያ አንድ ነገር ሆኖ፣ የዝግጅቱ መንፈስ ታላቅ ሀገራዊ መልዕክት ከመያዙ አኳያ ለዚህ ጉዳይ ቢውል ተገቢ የማይሆንበት ምክንያት አይታየኝም። ሊሆን የማይችለውን ነገር በመመኘት በደፈናው ‘አንድ ሁነት ገንዘብ ሳይወጣ በነፃ ይሰራ’ ለማለት ካልተፈለገ በስተቀር፤ እንኳንስ የሀገርን አቋም ሊያስተጋባ ለሚችል ጉዳይ ቀርቶ እዚህ ግና ለማይባል ተግባር እንኳን ከዚህ የበለጠ ገንዘብ ሊወጣ ይችላል። እናም ጉዳዩን ከልክ በላይ ማጎን ተገቢ መስሎ አይታየኝም።
ርግጥ ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም። የሃሳብ ብዝሃነትን በምታራምድ ሀገር ውስጥ ስለ ‘አንድ ዓይነት አስተሳሰብ’ ማውራት ያዋህነት ነው። ሆኖም አስተሳሰቦች ሚዛናዊና በልኬታቸው የተሰደሩ መሆን የሚገባቸው ይመስለኛል። ጭፍን ሙግትና የደፈና ጥላቻ ይህችን የጋራችን የሆነችውን ሀገር አንድም ስንዝር ወደፊት ሊያስኬዳት አይችልም።
እናም በርዕሴ ላይ “ከፍታውን” ማሳነስ—ለምን? የሚል ጥያቄ ሳነሳ፤ ወደ አዕምሮዬ በቅድሚያ የመጡት አንድም፤ ነገሮችን በቅጡ ያለማጤን፣ ሁለትም፤ ዝም ብሎ ለትችት ብቻ ሲባል ጉዳዩን ዝቅ የማድረግ ሁኔታ ሊሆን እንደሚችል ገምታለሁ። ያም ሆኖ “መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው” ሲባል እውነታውን ከላይ ከጠቀስኳቸው የነባራዊ ሃቅ ሰበዞች እየመዘዙ መተቸት አሊያም ተገቢ የሆነን ጉዳይ በልኬታው መደገፍ መልመድ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የሚበጅ ይመስለኛል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy