Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰጠን እውቅና

0 341

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰጠን እውቅና

ዳዊት ምትኩ

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትን በሊቀመንበርነት ማገልገል ጀምራለች። ኢትዮጵያ በፀጥታው ምክር ቤት የተሰጣትን የፕሬዝዳንትነት ቦታ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ተቀብላለች። ይህን ኃላፊነቷንም በስኬት ለመወጣት ጥረት እንደምታደርግ መንግስት ገልጿል።

አገራችን የፀጥታውን ምክር ቤት የፕሬዚዳንትነት መንበርን የተረከበችው ለዓለም ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ላበረከተችው አስተዋጽኦ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሰጣት እውቅና መሆኑ ግልፅ ነው። እውቅናው ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ፣ ለአፍሪካና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰላምና መረጋጋት ጥያቄዎች በተለያዩ ወቅቶች የሰጠችው ቀና እና ፈጣን ምላሽ ውጤት ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ መንግስት ለሀገራችን ሰላምና ልማት እውን መሆን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ሁሉ፤ የጎረቤት ሃገሮች ሰላምና ልማትም እንዲፋጠን ካለው ጽኑ እምነት በመነጨ በጋራ ማደግ ቀዳሚ ምርጫው ነው። ምክንያቱም የሀገራችን ሰላምና ልማት ለአካባቢያችን ዕድገት ድርሻ እንዳለው ሁሉ፤ የአካባቢያችን ሰላምና ልማትም ለሀገራችን ዕድገት መፋጠን የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋጽኦ የላቀ እንደሚሆን በፅናት ስለሚያምን ነው።

ታዲያ በሀገራችን በመካሄድ ላይ ያለው የተፋጠነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እንዲሁም የተጀመረው የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ሀገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ዓላማን የሰነቀና ውጤቱም ለሀገራችንም ሆነ ለአካባቢያችን ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ መሆኑ የሚታበይ አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መንግስት ሀገራዊና አካባቢያዊ ሰላምን ከማስፈን አኳያ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል፡፡

በአካባቢያችንና በአህጉራችን ሰላም እንዲሰፍን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ የመጣው የኢትዮጵያ መንግስት ስኬቶች መካከልም ረጅም ኪሎሜትሮችን የምትዋሰነን በጎረቤት ሀገር ሱዳን የተቀሰቀሰውን ቀውስ ለማርገብ የተካሄደው ጥረትና የተመዘገበው አበረታች ውጤት ተጠቃሽ ነው፡፡

ሱዳን በአፍሪካ ውስጥ በቆዳ ስፋቷ ቀዳሚ ሀገር ስትሆን ለጥ ያለና ውሃ ገብ የሆነው መልከዓ ምድሯ እንዲሁም ሰፊ የተፈጥሮ ሃብቷ ለታላቅ ዕድገት መብቃት የምትችል እንደሆነች ብዙዎቹን ያስማማ ሃቅ ቢሆንም ቅሉ፤ ሀገሪቱ ግን ለበርካታ ዓመታት በዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ለመቆየት ተገዳለች።

በዚህም ለከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ቀውስ ልትዳረግ በመቻሏ ለተቀሰቀሰው አለመረጋጋት እልባት ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ታዲያ ኢትዮጵያም ችግሩን እልባት ለመስጠት የአንበሳውን ድርሻ ተወጥታለች።

የኢትዮጵያ መንግስት በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ያደረገው ጥረት የሚመነጨው ሌሎች ሃይሎች እንደሚሉት ሳይሆን የጐረቤቶቻችን ሰላም ለሀገራቸን የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታችን መፋጠን ካለው ፋይዳ አኳያ እንደሆነ ሊጤን ይገባል፡፡

እኛ ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለመዋጋት የምናደርገው ትግል ሊሳካ የሚችለው ጐረቤቶቻችን ሰላም ሲሆኑ በመሆኑ ነው። እርግጥ የእነርሱ ሰላም መሆን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለእኛ ሰላም መጐልበት ያለው ሚና የላቀ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡

በአገራችን ሰላም ላይ የቅርብ ተጽዕኖ ያላት የሱዳንን ችግር ለመቅረፍ በመንግስታችን የተካሄደው ጥረት ምንጩ ሀገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሰላሟን ዘላቂ ለማድረግ ምንጊዜም ቢሆን ወሳኙ ነገር  በውስጥ የምታካሄደው የፀረ-ድህነትና ኋላ ቀርነት ትግል ሊሳካ የሚችለው ተጋላጭነታችን ሲወገድ ብቻ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በጐረቤቶቻችን ላይ የሚያጋጥም ትርምስንና ቀውስን መፈታት ካልተቻለ ጦሱ ለእኛም የሚተርፍ ስለሆነ ነው፡፡

እንደሚታወቀው በየትኛውም አካባቢ የሚኖር ችግር ዳፋው በአንድ ቦታ ላይ ሳይወሰን እንደ ሰደድ እሳት መስፋፋቱ አይቀሬ በመሆኑ የራሳችንንና የአካባቢያችንን ህዝቦች ጥቅም ማዕከል በማድረግ የመደጋገፍ አቅጣጫን መከተል አስፈላጊነቱ የጐላ ነው። እናም ለዚህ ተግባራዊነትም መንግስታችን ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ተፈላጊውን ሰላም በማስፈን ረገድ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል፡፡

በሱዳንና በደቡብ ሱዳን አማፅያን መካከል የተካሄደው ዘግናኝ ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ትልቁን ድርሻ ለተጫወተው የኢትዮጵያ መንግስት ያላቸውን  ጠንካራ እምነት አሳድረው አገራችን የሰላም ጠባቂነት ሚናዋን እየተወጣች ትገኛለች። ይህም ለአገራችን ታላቅ ድል ነው።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ውስጥ በተለይም በሶማሊያ አሸባሪነትን ለመዋጋት የምታደርጋቸው ጥረቶች ለእውቅናው መገኘት ሌላኛው ምክንያት ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ አገራችን አገራችን አሸባሪዎችን በሶማሊያ ለማስወገድ በፅናት የምትታገልበትን ምክንያት የኢትዮጵያና የሶማሊያ ህዝቦች የረጅም ጊዜ ታሪካዊና ባህላዊ ግንኙነት ያላቸው ከመሆናቸው በላይ፣ እነዚህ ህዝቦች በደም፣ በታሪክ፣ በባህል፣ በቋንቋና በሃይማኖት የተሳሰሩ መሆናቸው ነው።

እርግጥ አንዱ ህዝብ በሌላኛው ውስጥ የህይወት ቁርኝትን ፈጥሯል። ይህ ስር የሰደደ የግንኙነታቸው ትስስርም በየትኛውም ኃይል ሊበጣጠስ የማይችል ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሀገራቱ ያላቸው የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና የሚጋሩት እስከ በሺህዎች ኪሎ ሜትር የሚቆጠር የጋራ ድንበር ለንግድ ግንኙነታቸው አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል።

ኢትዮጵያ ሁሌም ወንድም ከሆነው የሶማሊያ ህዝብ ጎን ናት። የሶማሊያ ህዝብ በአሸባሪዎች እንግልት ሲደርስበት ሁለተኛው ሀገሩ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ ከመሰደድ ውጭ አማራጭ የለውም። ዛሬም ቢሆን አሸባሪው አል ሸባብ በተቆጣጣራቸው ቦታዎች ውስጥ የሚገኙ የዚያች ሀገር ህዝቦች ሀገራችንን እንደ ሌላኛው ሀገራቸው በመቁጠር በስደተኝነት እየተጠለሉባት ነው።

ያም ሆኖ ግን አገራችን ከምትከተለው የሰላምና በጋራ የመጠቀም ፖሊሲ በተጨማሪ፣ ይህ ጠንካራና ለረጅም ጊዜ የኖረ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትም ኢትዮጵያ በሶማሊያ በመሸጉ አክራሪዎችና አሸባሪዎች ላይ ለምትወስደው እርምጃ ተጨማሪ ምክንያት ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል ነው። በእኔ እምነት እነዚህን ሁሉ ተግባሮች እያከናወነች ያለችው ኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤትን በፕሬዚዳንትነት መምራቷ ከምታራምደው የሰላም ፖሊሲ አኳያ አግባብነት ያለው ነው። ይህ እውቅና አገራችን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ያላትን ቦታ የሚያመላክት በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy