ዘላቂ መፍትሄ የማበጀት ጉዳይ ጊዜ አይሰጠው
ብ. ነጋሽ
በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎቸ አዋሳኝ አካባቢዎች ተቀስቅሶ የነበረው ግጭት ባለፈው ሳምንት ጋብ ብሏል። እሁድ መስከረም 7፣ 2010 ዓ/ም የሁለቱ ክለሎች ርዕሳነ መስተዳድር በጋራ መግለጫ ከሰጡ በኋላ ሁኔታዎች የመረጋጋት መልክ እየያዙ ነው። እርግጥ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (OBN) ረቡዕ መስከረም 10 ባሰራጨው ዜና ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተነሱ ታጣቂዎች ጭናክሰን ላይ በሰነዘሩት ጥቃት ህይወት ማጥፋታቸውን፣ አካል ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን፣ ቤቶች ማቃጠላቸውን አስታውቋል። ከዚህ በኋላ ግን በሁለቱም በኩል የተሰማ ግጭትና ጉዳት የለም።
የፌደራልና የአርብቶ አደር አካባቢዎች ልማት ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ ሃሙስ መስከረም 11፣ 2010 ዓ/ም በሰጡት መግለጫ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝና በሁለቱ ክለሎች ርዕሳነ መስተዳደር መገለጫ መሰጠቱን ተከትሎ ሙሉ በሙሉ ቆሟል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 6፣ 2010 ዓ/ም በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ዙሪያ ከሁለቱ ክልሎች የተውጣጡ የሃገር ሽማግሌዎችን፣ የሐይማኖት አባቶችንና አባ ገዳዎችን እንዲሁም የሁለትን ክልሎች ርዕሳነ መስተዳደር ማነጋገራቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቱ ላይ በሰጡት መግለጫ፣ ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም የፌዴራል መንግሥት ሕገመንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ አፋጣኝ እርምጃዎችን ይወስዳል ብለዋል። የሐይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ሰላም የማስፋኑ ሂደት ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
የአካባቢዎቹን ሰላምና ፀጥታ ወደነበረበት ለመመለስ በሁለቱ ክልሎች የሚገኙ ዋና ዋና መንገዶች በፌደራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ክትትል ሥር እንዲሆኑ፣ የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች የሕዝቡን ሰላም የመጠበቅና የማረጋጋት ሥራ እንዲሰሩ፣ አካል በማጉደልና የሰው ሕይወት በማጥፋት የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር እንዲያውሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ማዘዛቸውንም አስታውቀዋል። ግጭት በተቀሰቀሰባቸው የሁለቱ ክልሎች ድንበር አካባቢዎችና የግጭቱ ቀጠናዎች የፌዴራል መንግሥት ማንኛውንም የጦር መሣሪያ ወይም ትጥቅ የማስፈታት እርምጃ እንደሚወስድም አስታውቀዋል። በሁለቱ ክልሎች መካከል የሰብዓዊ መብት በመጣስ የሰው ሕይወት ያጠፉ የፀጥታ ኃይል አባላትም ይሁኑ ሌሎች አካላት በሕግ አግባብ እርምጃ እንዲወሰድባቸው እንደሚደረግም አስታውቀዋል። ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሰብአዊ መበት ጥሰትን እንደሚያጣራም አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚሲስትሩ የሁለቱን ክለሎች ርዕሳነ መስተዳድር፣ አባገዳዎችና የሃገር ሽማግሌዎች አነጋግረው መግለጫ ከሰጡ በኋላ፣ የፀጥታ ኃይሎች ባልደረሱባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው በመስጋት ከቀዬአቸው እየወጡ የነበሩ ነዋሪዎችን የማረጋጋት ስራ መሰራቱንም የፌደራልና የአርብቶ አደር አካባቢዎች ልማት ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ተናግረዋል። አቶ ከበደ እንዳስታወቁት ከሁለቱ ክልሎች ህዝቦች ጋር ውይይት በማካሄድ የማረጋጋት ስራ እየተሰራ ነው። በቀጣይ ህዝቡን የሚያቀራርቡ የሰላም ኮንፈረንሶች ይካሄዳሉ።
በሌላ በኩል ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው እሁድ መስከረም 7፣ 2010 ዓ/ም ምሽት ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕስ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳና የኢትዮጵያ ሶማሌ ርዕስ መስተዳድር አቶ አብዲ መሃመድ ኡመር በሰጡት መግለጫ፣ ሰሞኑን በክልሎቻቸው አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት ሁለቱን ህዝቦች እንደማይወከል ተናግረዋል። አቶ ለማ መገርሳ፣ በግጭቱ የደረሰው ጉዳቱም ሀዘኑም የሁለቱም ክልሎች የጋራ ጉዳትና ሀዘን ነው ብለዋል። አቶ አብዲ መሃመድ ኡመርም፣ ከሁለቱም ወገን በግጭቱ መክንያት ለሞት የተዳረጉትም ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉትም ዜጎች ወንድሞቻችን ናቸው፤ ሀዘኑም ያገራችን ነው ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል።
አቶ ለማ ድርጊቱን በማንኛውም መስፈረት የኦረሞ እና ሶማሌ ህዝብን እንደማይወክል በማንሳት አውግዘውታል። አቶ አብዲም ድርጊቱን የፈፀሙት ግለሰቦች የኦሮሞንም፣ የሶማሌንም ህዝብ አይወክሉም በማለት ድርጊቱን እኩይ ምግባር ብለውታል።
ከላይ የተጠቀሰው የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መሰተዳድር በግጭቱ ዙሪያ የሰጡት መግለጫ ግጭቱ የህዝብ እንዳልሆነ የተሰጠ ምስክርነት ነው። በሁለቱም ክልሎች የሚኑሮ የግጭቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎች በሰጡት አስተያየት፣ አብሮን የሚኖረው የኦሮሞ ወይም የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ በድንገት ተነስቶ ጥቃት አደረሰብን ሲሉ አልተደመጡም። እርግጥ በተለይ መስከረም 2 እና 3 በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጸሙ ጥቃቶች፣ የህዝብ ግጭት የሚመስል ባህሪ ነበራው። ይህም ቢሆን ግን በማህበራዊ ሚዲያ ውስጡ ውስጡን ሲቀሰቀስ ቆይቶ በተወሰነ ደረጃ መሪ ኖሮት በተደራጀ ሁኔታ የተካሄደ እንጂ ድንገተኛ የህዝብ ቁጣ ያስከተለው ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም።
የት ምን አይነት አደጋ እንደሚፈጠር ባይታወቅም ብዙዎቻችን በአዲስ አመት መግቢያ ዕለት ማግስት ከባድ ሁከት ሊቀሰቀስ መታሰቡን ጭምጭምታ ሰምተን ነበር። በተለይ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይህ መረጃ ነበራቸው። ወደቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ደውለው ያስጠነቀቁም ነበሩ። ይህ ሁኔታ መስከረም 2 እና 3 የተካሄደው የህዝብ ለህዝብ ግጭት ባህሪ የታየበት ክስተት አሜሪካ የተጠነሰሰ፣ ሃገር ቤት ባሉ ወኪሎች የተመራ ሊሆን እንደሚችል እንድንጠራጠር አድርጎናል። እስካሁን ባለው መረጃ ግን ይህ አካል ማን እንደሆነ በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም።
በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው አሁን ሁኔታዎች ተረጋግተዋል። በሁለቱም ክልሎች የተፈናቀሉትን የማረጋጋትና የመደገፍ ስራ እየተከናወነ ነው። የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ሰሞኑን እንዳስታወቀው፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በነበረው ግጭት የተፈናቀሉ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል። ኮሚሽኑ ከተለያዩ አካላት የተውጣጡ ተወካዮችን የያዘ ኮሚቴ አቋቁሞ ወቅታዊ ምላሽ፣ የማገገሚያና መልሶ የማቋቋም ተግባራትን እያከናወነ ነው። በፌደራልና አርብቶ አደር አካባቢዎች ልማት ሚኒስቴር የሚመራው ይህ ኮሚቴ የጸጥታ አካላት፣ የኢኮኖሚ ልማት መስሪያ ቤቶችና የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት የተካተቱበት ነው።
ኮሚቴው ግጭት የመከላከል፣ ለተፈናቀሉ ዜጎች ፈጣን ምላሽ የመስጠትና መልሶ የማቋቋም ስራ የሚያከናውን ነው። በሐረር ከተማና በጅግጅጋ አካባቢ ለሚገኙ በርካታ ተፈናቃዮች የተጠናከረ ድጋፍ እየተደረገ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ በኦሮሚያ በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉትን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም የህዝብ ድጋፍ እየተሰባሰበ ነው። እስካሁን የክልሉ የመንግስት ሰራተኞች፣ ባለሃብቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በመለገስ ላይ ይገኛሉ። ድጋፉን ለማሰባሰብ የተደራጀው ኮሚቴና የክልሉ መንግስት ሌሎች ክልሎችም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
በአጠቃላይ ግጭቱን ለማብረድና በግጭቱ ሳቢያ ለጉዳት የተጋለጡ ዜጎችን ለመደገፍ በመንግስትና በህዝብ እየተወሰደ ያለው የአሰቸኳይ ጊዜ እርምጃ ተገቢና የሚደነቅ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ አይደለም። እንዲያውም በወዲያና በወዲህ በሁለቱ ክልሎች የችግሩ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ለመርዳት የሚደረገው ቅስቀሳ፣ ከግጭቱ ቀጠናዎች ውጭ የሚኖረውም ህዝብ ወገኖቼ ተበድለዋል በሚል ስሜት ቅሬታ እንዲያድርበትና እንዲያኮርፍ ሊያደርግ ስለሚችል ጉዳዩ በጥንቃቄ መያዝ አለበት። እነዚህ ሁለት ህዝቦች የተለያየ ሃገር ዜጎች ሳይሆኑ በአንድ ፌደራላዊ መንግስት ስር ያሉ የጋራ ሃገር ባለቤቶች በመሆናቸው አካሄዱ የሁለት የተለያዩ ህዝቦች ጉዳይ በማይመስል አኳኋን መያዝ አለበት። ግጭቱንና ግጭቱ ሊያስከትል የሚችለውን መቃቃር ለዘለቄታው የመፍታት እርምጃ ከዚህ ነው የሚጀመረው።
ከዚህ ባለፈ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ተግባር እንደሚከናወን የሚጠበቅ ቢሆንም፣ እስካሁን ጎልቶ የታየ እንቅስቃሴ የለም። የሁለቱንም ክልሎች ህዝቦች ያሳተፈ ችግሩን የፈጠሩና የመሩ አካላትን አንጓሎ ማውጣት የሚያስችል የሰላም ኮንፈረንስ መካሄድ አለበት። የሰላም ኮንፈረንሱ ለሚዲያ ፍጆታ ያህል የሚካሄድ ሳይሆን የችግሩን አሳሳቢነት የሚመጥን መፍትሄ አመንጪ መሆን ይኖርበታል።
ለሰው ህይወት መጥፋትና መፈናቀል ምክንያት የሆነውን ግጭት የጠነሰሰውና የመራው ማንም ይሁን ማን፣ ይህን ያደረጉት አካላት እድሉን ያገኙት የፌደራልና የክልሎቹ መንግስታት ሃላፊነታቸውን በወቅቱ ባለመወጣታቸው መሆኑ መቼም መዘንጋት የለበትም። የፌደራል መንግስትና የሁለቱ ክልሎች መንግስታት በህዝበ ውሳኔ የተረጋገጠውን የሁለቱን ክልሎች ወሰን ለአስራ ሁለት ዓመታት ያህል መሬት ላይ እንዲካለል ሳያደርጉ መተኛታቸው ችግሩን ለፈጠሩ ሰዎች እድል መስጠቱ መታወቅ አለበት። በቀጣይ በ1997 ዓ/ም የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ መነሻ በማደረግ በሁለቱም ወገን ከህዝብ ጋር በመወያየትና ህዝብን በማሳተፍ ወሰን የማካለሉ ሥራ መጠናቀቅ አለበት። ይህ ካልሆነ አመቺ ጊዜ ጠብቆ ለግጭት መቀስቀሻነት መዋሉ አይቀሬ ነው። እናም እየተወሰዱ የሚገኙት የአስቸኳይ ጊዜ ግጭት አስወጋጅና የግጭት ጉዳት መከላከያ እርምጃዎች መልካም መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ዘላቂ መፍትሄ የማበጀቱ ጉዳይ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም።