Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመረጃ ነፃነትና ህገ መንግሥቱ

0 292

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመረጃ ነፃነትና ህገ መንግሥቱ

ዳዊት ምትኩ

በኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ማንኛውም ዜጋ የመንግሥትን መረጃ የማግኘትና የማሰራጨት መብት ተከብሮለታል። ሚዲያዎች ያለምንም ቅድመ ምርመራ በነፃነት መረጃ የመሰብሰብና የማሰራጨት መብት የተከበረላቸው ከመሆኑም በላይ፤ ይህን መብት የተጎናፀፉት በፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ነው።

ሚዲያዎች ህገ መንግሥታዊ ከላላ ያላቸው በመሆኑም ስራዎቻቸውን ከማናቸውም አካል ነፃ ሆነው እያከናወኑ ነው። ይህ ህገ መንግስታዊ መብት ይበልጥ እንዲጎለብትም በመንግሥትም ይሁን በግል ሚዲያዎች በኩል ያሉ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት ከሚዲያዎቹ ጋር በመቀራረብ በመስራት ላይ ይገኛል።

እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ላይ “አመለካከትንና ሃሳብን በነፃነት የመያዝና የመግለፅ መብትን” በደነገገበት አንቀፅ 29 ላይ በሰባት ንዑሳን የተዘረዘሩ ወሳኝ ጉዳዩችን ይዟል። እነርሱም ማንኛውም ሰው የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ እንደሚችል፣ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ሃሳቡን በነፃነት የመግለፅ መብት እንዳለው፣ የፕሬስና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የስነ ጥበብ የፈጠራ ነፃነት መረጋገጡን ብሎም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሃሳቦችና አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ፕሬስ በተቋምነቱ የአሰራር ነፃነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የህግ ጥበቃ እንደሚደረግለት የሚገልፁ መብቶች ናቸው።

እንዲሁም በመንግስት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ሚዲያዎች የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችላቸው ሁኔታ እንዲመሩ እንደሚደረግ ብሎም በዚህ አንቀፅ ስር የተጠቀሱት መብቶች ገደብ ሊጣልባቸው የሚችለው የሃሳብና መረጃ የማግኘት ነፃነት በአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትል በሚችለው አስተሳሰባዊ ውጤት ሊገታ አይገባውም በሚል መርህ ላይ ተመስርተው በሚወጡ ህጎች ብቻ መሆኑንና ማንኛውም ዜጋ ከላይ በተጠቀሱት መብቶች አጠቃቀም ረገድ የሚጣሉ ህጋዊ ገደቦችን ጥሶ ከተገኘ የህግ ተጠያቂ ሊሆን ይችላል የሚሉት ገዳዩች በመተግበር ላይ የሚገኙ መብቶች ናቸው።

ታዲያ እነዚህ ሃሳብን በነፃነት የመያዝና የማሰራጨት የህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች ሃሳብን  እንደ ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ መብቶች መብት ብቻ አይደሉም። ህገ መንግስቱን መሰረት አድርገው በሚወጡ አዋጆችና ህጎች ገቢራዊ የሚሆኑም ናቸው። ይህም አንድ መብት እስከተሰጠ ድረስ፤ በዚያኑ ልክ መብቱን ህጋዊ በሆነ መንገድ ለማስፈፀም ገደብ ሊጣልበት እንደሚችል የሚያስረዳ እውነታ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ አገር ውስጥ የሚሰጡ መብቶች ከግዴታዎች ጋር የተቆራኙ ናቸው። ሁለቱን ለያይቶ መመልከት አይቻልም።

ያም ሆነ ይህ ግን እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው የኢፌዴሪ መንግስት ገደቦችን ለማስቀመጥ ሲል፣ ሃሳብን በነፃነት የመያዝና የመግለፅ መብቶችን የመገደብ አካሄድን አይከተልም። እንደ ጀማሪ ዴሞክራሲያዊ ሀገር ካለማወቅ አሊያም ከተለያዩ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ እሳቤዎች በመነሳት መብቱን በአግባቡ የመጠቀም ሁኔታ ላይኖር እንደሚችል ስለሚገነዘብ፤ የዴሞክራሲ አንድ እሴት በሆነው መቻቻል አማካኝነት ሆደ ሰፊ በመሆን የሚፈጠሩ ችግሮችን የማስተማርና የማሳወቅ መንገዶችን ተከትሎ ለመፍታት ጥረት አድርጓል፤ እያደረገም ነው። ለነገሩ መንግስት ይህን የሚያደርገው ለማንም ብሎ አይመስለኝም—የሀገራችን ዴሞክራሲ እንዲሰፋና እንዲጠልቅ ካለው ፅኑ ፍላጎት በመነሳት እንጂ።

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ላይ ሃሳብን በነፃነት ከመያዝና ከመግለፅ ጋር ህገ መንግስታዊ ከለላና ዋስትና ካለው መብት ውስጥ፤ ማንኛውም ሰው የመሰለውን ሃሳብ የመያዝ መብት አንዱ ነው። ይህ መብት በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውሰጥ የሰው ልጅ ያሻውን ዓይነት አስተሳሰብ የመያዝ መብቱ የህግ ከለላና ዕውቅና ያለው መሆኑን ይገልፃል። ሃሳብን መያዝ፤ ሳይተገብሩ የራስ ሃሳብን መያዝና አቋም መውሰድን እንዲሁም አግባብ በሆኑ ህጋዊ ማዕቀፎች ውስጥ ሃሳብን በነፃነት መተግበር የሚያሳይ ፅንሰ ሃሳብ ነው።

ፅንሰ ሃሳቡ የሰው ልጅ ይጠቅመኛል ወይም ይበጀኛል የሚለውን አስተሳሰብ መያዝና መተግበር እንደሚችል የሚያስረዳ ነው። በዚህ ፅንሰ ሃሳብ ውስጥ ሃሳብን መያዝ እና መግለፅ የተሰኙ ሁለት ጉዳዩች አሉ። ምናልባትም እነዚህ ሁለቱም ጉዳዩች በተናጠል አሊያም በአንድነት ሊገለፁ ይችላሉ። በተናጠል ሲገለፁ አንድ ሰው የመሰለውን ሃሳብ ይዞ ምንም ዓይነት ተግባራዊ ውሳኔ ላይወስድ የሚችልበትን ነባራዊ ዕውነታን ያመላክታሉ። በአንድነት ሲገለፁ ደግሞ፤ አንድ ሰው የመሰለውን ሃሳብ መያዝ ብቻ ሳይሆን፣ በተግባርም ሃሳቡን በፈለገው መንገድ እንዲያራምድ የሚያስችለውን አውድ ይፈጥሩለታል። ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነትም ሊኖርበት አይችልም።

በአገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ የሰው ልጅ አንድን ሃሳብ ስለያዘ አሊያም የያዘውን ሃሳብ በፈለገው የመገናኛ መንገድ ስለገለፀ ሊጠየቅ አይችልም፤ ይልቁንም ህጋዊ ከለላ አግኝቶ እንዳሻው ሊገልፀው ይችላል። ይህም ፌዴራላዊ ስርዓታችን ካለፉት ስርዓቶች ምን ያህል የተለየና ዜጎችን መብቶቻቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ ህጋዊ ከለላ የሚሰጥ መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል።

የሀገራችን ህዝቦች ተስፋቸው ከሰላም፣ ከልማትና ከዴሞክራሲ ጋር የቶራኘ ነው። ለዘመናት አንገታቸውን ሲያስደፋ የነበረውን ድህነትን ድል ለመንሳት ቆርጠው ተነስተዋል። ይህን መከወን እንደሚችሉም ባለፉት 26 ዓመታት ገደማ ተጨባጭ ውጤቶችን ማየት ችለዋል። አዎ! የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች የአስተማማኝ ሰላም፣ የፈጣንና ተከታታይ ዕድገት እንዲሁም ስር በመስደድ ላይ የሚገኝ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባለቤቶች ሆነዋል—በእነዚህ ጥቂት ዓመታት። ከአፍሪካ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃርም፤ ብዙዎቹ የአህጉሪቱ ሀገራት ማሳካት ያልቻሏቸውን መሰረታዊ የለውጥ ሂደቶችን ተራምደዋል።

ዛሬ የተለያዩ አፍሪካዊ ወንድሞቻችን ከሀገራችን ስኬታማ ውጤቶች ተሞክሮ እየወሰዱ ነው። ከመሰንበቻው ለሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ሀገራችን የመጡት የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ኤለን ሰርሊፍ ጆንሰንን በምሳሌነት ማንሳት የምችል ይመስለኛል። ፕሬዚዳንቷ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከሀገራችን በኢንዱስትሪና በሌሎች የልማት ዘርፎች ልምድ ለመቅሰም እንደምትፈልግ ተናግረዋል።

በእኔ እምነት ይህ ሁኔታ ከሁለትዮሽ ግንኙነቱ ባሻገር፤ ሀገራችን ያለችበትን ትክክለኛ ቁመና የሚያሳይ ነው። እናም ፕሬስ እንደ ማንኛውም የዴሞክራሲ ተቋም የሀገራችን ህዝቦች ዕውን እያደረጉ ያሉትን ሁለንተናዊ ለውጦች ሊደግፍና ችሮችንም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ሊጠቁም የሚገባ ይመስለኛል። የማንኛውም ሀገር ፕሬስ የሚሰራው በሀገሪቱ ፖለቲካል ኢኮኖሚ አውድ እንደመሆኑ መጠን፤ እዚህ ሀገር ውስጥ የሚከናወኑ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ተግባራትን በመደገፍና ህፀፆችን ነቅሶ በማሳየት የህዝቦችን ከድህነት የመውጣት ተስፋ ምሉዕ ሊያደርግ ይገባል።  

      

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy