Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመስከረም 7ቱ ህዝበ ውሣኔ

0 410

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአማራና ቅማንት ህዝቦች ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ህዝበ ውሳኔ ሲደረግ፤

ዜና ሐተታ

ህዝበ ውሣኔ በአንድ አገር ወይም ክልል አግባብ ባለው አካል የተወሰነ ጉዳይ ሲሆን፤ አከራካሪ እና ህዝብ በእራሱ ድምጽ ጉዳዩን መለየት እንዳለበት የሚያስፈልግበት ጉዳይ ሲኖር የሚሰጥ የዜጎች ድምጽ ነው። በውሳኔው መሰረት የህዝብን ፍላጐት ለመለካት ወይም ለመወሰን ድምጽ አሰጣጥ እንዲካሄድ ይደረጋል። ትናንትና በአማራ ክልል በሚገኙ ስምንት ቀበሌዎች 21 ሺ 125 የሚሆኑ ዜጎች አስተዳደራዊ ወሰናቸውን ለመወሰን ህዝበ ውሳኔ አድርገው ነበር።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈጉባዔ አቶ ይርሳው ታምሬ እንደሚገልፁት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ህዝበ ውሳኔ በወሰን እና በማንነት ጉዳዮች እንዲሁም በተለያዩ የህዝቡን አብላጫ ድምጽ ማረጋገጥ ሲያስፈልግ በተለያዩ ጊዜያት ተግባራዊ መደረጉን ያስታውሳሉ። አሁንም በአማራ ክልል የህዝቡን ውሳኔ ያስፈለገው አስተዳደራዊ ጉዳይ በመኖሩ የአብዛኛውን ጥያቄ መመለስ የሚያስችል ህዝበ ውሳኔ መደረጉን ይናገራሉ።

እንደ አቶ ይርሳው ገለጻ፤ በአማራ ክልል የቅማንት የማንነት ጥያቄ ቀደም ባሉ ጊዜያት የተመለሰ ነው። የራስ አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ ደግሞ በአማራ እና በቅማንት ህዝቦች በአንድነት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ወደ የትኛው የአስተዳደር አካባቢ መካለል እንደሚፈልጉ ለመወሰን የህዝበ ውሳኔ አስፈላጊ ሆኗል። ጉዳዩን በህዝበ ውሳኔ እንዲመለስ ማድረጉ ህብረተሰቡ በየትኛው አስተዳደር ለመካለል ያለውን ፍላጎት ያሳያል። በመሆኑም የህዝበ ውሳኔው ውጤት ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር የሚነሱ ጥያቄዎችን እንደሚፈታ ይጠበቃል።

ውጤቱ ምንም ይሁን ምን የአብላጫው ድምጽ እንደሚከበር ሁሉ በአካባቢው ላይ የሚኖሩ አነስተኛ ድምፅ ያላቸው ዜጎች መብታቸው እንደተከበረ ይቀጥላል። በህዝቦቹ መካከል ቁርሾ እና ጠላትነት ቀድሞም ያልነበረ በመሆኑ መተሳሰብና አብሮ መኖሩ ወደፊትም የሚቀጥል ይሆናል። ምርጫ የማይከናወንባቸው አራት ቀበሌዎችም በቀጣይ የህብረተሰቡ ፍላጎት እና ውይይት መሰረት ባደረገ መልኩ በቀጣይ ውሳኔ እንደሚሰጥባቸው ነው የጠቆሙት።

«ህዝበ ውሳኔው በአግባቡ ከተፈጸመ ችግሩን በመሰረቱ ይፈታል የሚል እምነት አለኝ» የሚሉት አፈጉባዔው፤ በህዝቦች መካከልም ያለውን መፈቃቀርን መከባበርን የበለጠ ያጠናክራል። አስተዳደራዊ በሆነ መንገድ እናንተ ወደ እዚህ ሁኑ እናንተ ወደዚያኛው አካባቢ ተካለሉ ብሎ መወሰን በህዝቦች መካከል የሚፈጥረው ቅሬታ እንደሚኖር ይጠቁማሉ። ምርጫው ለህዝቡ ከተተወ እና በህዝቡ ድምጽ የሚወሰን ከሆነ ግን ቅሬታ የማይፈጥር አሰራር እንደሚሆን ያስረዳሉ። ከምርጫ ሥርዓቱ ከማንነት ጋር የተያያዘ የምርጫ ሥርዓት በመሆኑ ከህዝቡ ውጤቱ በኋላ የተመዘገበው አሃዝ እና ውጤቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረብ እንደሚያስፈልግ የአገሪቷ ህግ እንደሚያዝ ይናገራሉ። ፌዴሬሽን ምክር ቤቱም ውጤቱን ሲያጸድቀው የህዝቡ ውሳኔ ተግባራዊ እንደሚደረግ ይገልፃሉ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ እንደሚገልፁት ደግሞ፤ የአማራ ና የቅማንት ህዝቦች ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው 12 ቀበሌዎች ድምጸ ውሳኔ በማድረግ ጉዳዩን ዕልባት ለመስጠት የቅድመ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸው ይታወቃል። የፌዴራል ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው ጊዜ ሰሌዳ መሰረት የድምጽ አሰጣጡ ሥነሥርዓት ትናንትና ተካሂዷል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል ህዝበ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው የታቀዱ ቀበሌዎች ቁጥር 12 ነበር። ከዚህ ውስጥ ግን አራቱ ቀበሌዎች ተጨማሪ ውይይት ያስፈልገናል የሚል ጥያቄ ስላቀረቡና ጥያቄያቸው ተቀባይነት በማግኘቱ በቀጣይ ጊዜያት ጉዳያቸው እንዲታይ ተደርጓል።

እንደ ዶክተር ነገሪ ገለጻ፤ ህዝበ ውሳኔ የሚደረገባቸው ቀበሌዎች ስምንት ሲሆኑ፣ በእነዚሁ አካባቢዎች ህብረተሰቡ በተረጋጋ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ላይ እንዲቆይ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል። የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ አካላትን በቦታው በማሰማራት ከምንጊዜውም በላይ የህብረተሰቡ ደህንነት የተረጋጋ እንዲሆን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጸሐፊና የጽህፈት ቤቱ ዋና ኃላፊ አቶ ነጋ ዲፊሳ በበኩላቸው፤ ህዝበ ውሳኔው ህዝቦች በራሳቸው ድምጽ የሚፈልጉትን መምረጥ እንደሚችሉ ማሳያ እንደሚሆን ይናገራሉ። በስምንቱ ቀበሌዎች የሚደረገው ህዝበ ውሳኔ የዴሞክራሲን የአብላጫ ድምጽ የሚያከብር በመሆኑ ህብረተሰቡ የሚበጀውን ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ዕድል እንደሚሰጥ ያስረዳሉ። በመሆኑም ከምርጫ ውጤቱ በኋላም የተረጋጋ እና ሰላማዊ የሆነ እንቅስቃሴ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ነው የሚጠቁሙት።

እንደ አቶ ነጋ ገለጻ፤ በኢትዮጵያም ሆነ የተለያዩ አገራት የህዝበ ውሳኔዎች ማከናወን የተለመደ ዴሞክራሲያዊ አሰራር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። የህዝቡን ውሳኔ በተመለከተ ለሚነሱ ማንኛውም ችግሮች ከአካባቢ የፍትህ አካላት ጀምሮ እስከ መደበኛ ፍርድ ቤቶች ድረስ ቅሬታ ማቅረብ የሚቻል በመሆኑ ጉዳዩ ህጋዊ መስመር ይዞ የተጓዘ መሆኑን ይናገራሉ። ለዘመናት በመተማመን ላይ ለተመሰረተው እና ሰላማዊ ለሆነው የአካባቢው ህብረተሰብ እንደቀደሙ ጊዜያቶች ሁሉ ጨዋነቱን ባስመሰከረ አርቆ አሳቢነት የምርጫ ውጤቱንና ሂደቱን መከታተል እንደሚገባው ይናገራሉ።

ዛሬ የህዝበ ውሳኔው ድምፅ አሰጣጥ ማለዳ 12:00ጀምሮ የተከናወነ ሲሆን ። ማምሻውን አቶነጋ በስልክ በሰጡን መረጃ መሰረት ምርጫው በሰላማዊ መንገድ ተጠናቋል። ከ20ሺ በላይ መራጮች ድምፅ ሰጥተዋል። በነገው ዕለትም በ24ቱም ምርጫ ጣቢያዎች ጊዜያዊ ውጤት ይፋ ይደረጋል። የፊታችን መስከረም 15 ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ይጠበቃል።

ጌትነት ተስፋማርያም

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy