Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የስኬትን ካባ የደራረበች ሀገር

0 435

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የስኬትን ካባ የደራረበች ሀገር

                                                  ቶሎሳ ኡርጌሳ

አዲሲቷ ኢትዮጵያ ባለፉት አስር ዓመታት በሁሉም መስኮች በሚያስብል ሁኔታ በስኬት ላይ ስኬትን ደርባለች። ሀገራችን ውስጥ የተለያዩ ፍላጎቶች ቢኖሩም፤ እነዚህ ፍላጎቶች አጣጥማና እርስ በርሳቸው እንዲመጋገቡ አድርጋ በህዳሴ ጎዳናዋ ላይ እየተመመች ነው። እነዚህ ስኬቶች ነገም ይሁን ከነገ በስቲያ ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው ይመስለኛል። ኢትዮጵያ ሊፈጠሩ የሚችሉ ነበራዊ ችግሮችን መፍታት የሚችሉ ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ያሏት ሀገር ናት። በእነዚህ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራችም ባለፉት አስር ዓመታት ጉልህ ተግባሮችን ፈፅማለች።

በተለይም ባለፉት አስር ዓመታት በኢኮኖሚ ዕድገትና በህዝብ ተጠቃሚነት፣ በከተማም ይሁን በገጠር የተፈጠሩ የስራ ዕድሎች፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ እንደ መንገድና ባቡር የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት አውታሮች እንዲሁም እንደ ህዳሴው ግድብ ዓይነትና ግልገል ጊቤ ሶስትን የመሳሰሉ የትላልቅ ግድቦች ግንባታ የንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን…ቀዘተ ተጠቃሾች ናቸው። በእነዚህ ዘርፎች የተገኙት ውጤቶች ኢትዮጵያዊያን ሆኑ ሀገራቸው የስኬት ካባን የደረቡ መሆናቸውን የሚያመላክቱ ናቸው።

ታዲያ በዚህ አጭር ፅሑፍ ላይ ሁሉንም ስኬቶች በማንሳት ማውሳት አይቻልም። ይሁንና ሀገራችን በኢኮኖሚ ዕድገትና በህዝብ ተጠቃሚነት ረገድ የተገኙ ስኬቶችን በጨረፍታ መመልከት የሚቻል ይመስለኛል። ይህን ዘርፍ ተመልክተን ስናበቃም “ከእኔ በላይ ለአሳር” እያለ የሀገራችንን ስኬት በማሳነስ የሚጮኸውን ፅንፈኛውን የትምክህት ቡድን ፍላጎት ለማየት እንሞክራለን።

ኢትዮጰያ ባለፉት አስር ዓመታት ያስመዘገበችው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በአገር ውስጥም ከአገር ውጭ ሰፊ እውቅና እና ተቀባይነትን ያገኘ ነው። ዕድገቱ በሀገራችን ህዝቦች ዘንድ ከፍተኛ መነሳሳትን ፈጥሯል። የተረጋገጠው ዕድገት አርሶ አደሮች፣ የግሉ ዘርፍና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በፍጥነት ማደግ እንደሚቻል ያረጋገጠ ነው። በእነዚህ ዓመታት የተመዘገበው ዕድገት የኢትዮጵያን ገፅታ በመሠረቱ እየተቀየረ እንዲመጣ ያደረገ ነው ማለት ይቻላል።

በዚህም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በተከታታይ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉት ጥቂት የዓለም ሀገራት ተጠቃሽ መሆን ችላለች። ይህ እንዲሁ የተገኘ አይደለም—ሀገራችን የምትከተለው የልማት ስትራቴጂ ውጤት እንጂ።

እንደሚታወቀው በተለያዩ ወቅቶች የሀገራችን ብድር የመሸከም አቅም ደረጃ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ በታወቁ ሶስት ገምጋሚ ድርጅቶች የተገመገመ ሲሆን፤ በዚህም ኢትዮጵያ በእነዚህ ዓመታት ያስመዘገበችውን ሁለንተናዊ ዕድገትና ልማት ያረጋገጠ ሆኖ ተገኝቷል። ይህ ሁኔታም የሀገሪቱ ፈጣን ዕድገት በቀጣዩ የመካከለኛ ዘመንም እንደሚቀጥል ያመላከተ ነው። ሁኔታው ሀገራችን ተስፋ ያላት ባለ ከፍታ ዘመን ባለቤት መሆኗን ያረጋገጠ ብቻ ሳይሆን፤ ሀገራችን በአለም አቀፍ ኢንቨስትሮች እይታ ውስጥ እንድትገባ ያስቻላት ነው።

የተመዘገበው ፈጣን ዕድገት የሀገራችን ኢኮኖሚ በመጠኑ ግዙፍ ከሚባሉ ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት መካከል የሚጠቀስ ነው። ይህ ሁኔታም ለቀጣይ ዕድገት ተጨማሪ አቅም የፈጠረ ነው ማለት ይቻላል። የዜጎች ዓመታዊ አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከተቀመጠው ግብ በላይ አፈፃፀም ተመዝግቧል።

ርግጥ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለችው ፈጣን ዕድገት የዜጐች ተጠቃሚነትን በየደረጃው ያረጋገጠ ነው። ዕድገቱ ሰፊ መሰረት ያለው በመሆኑ አብዛኛው የሀገራችን ህዝብ የተሰማራው ከግብርና ዘርፍ ጋር የተያያዘ በመሆኑ በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።

በዚህም ሳቢያ የድህነት ምጣኔው በገጠርም ሆነ በከተማ ሊቀንስ ችሏል። ይህም ከድህነት ወለል በታች ይኖሩ የነበሩ ዜጎችን ህይወት ትርጉም ባለው ደረጃ መለወጥ የቻለ ነው። የመንግስታቱ ድርጅት ይዞት የነበረውንና ድህነትን በግማሽ መቀነስ እንደሚገባ የተቀመጠውን ግብ ካሰኩ ጥቂት ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ ሆናለች። የድህነት ምጣኔው በፍጥነት እየቀነሰ የመጣው በዋናነት በተመዘገበው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ሳቢያ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ባለፉት አስር ዓመታት ተግባራዊ የተደረገውና አሀንም ድረስ የዘለቀው የልማታዊ ሴፍቲኔት ኘሮግራም ለተገኘው ስኬት የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል። ከዚህ ጎን ለጎንም ዓመታቱ ከፈጣን ዕድገቱ ጋር የተያያዘ ፍትሐዊ የገቢ ክፍፍል እውን የሆነበት ነው። የገቢ ክፍፍሉ ፍትሐዊ ሆኖ መቆየቱ ዕድገታችን በዓይነቱ በጣም ፍትሐዊ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

ምንም እንኳን ሀገራችን ያስመዘገበችው ፈጣን ዕድገትና ፋይዳው ትልቅ ትርጉም ያለው ቢሆንም፤ አሁንም የተለየ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መኖራቸው ግን እውነት ነው። እንደሚታወቀው በእነዚህ ዓመታት የዕድገታችን ዋና ምንጭ የግብርና ዘርፍ መሆኑ ይታወቃል።

የኢንዱስትሪ ዘርፉ ደግሞ ከግብርና ዘርፍ በላቀ ፍጥነት በማሳደግ ለፈጣን ኢንዱስትሪያላይዜሽንና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ መሰረት እንደሚጥል የሚታመንበት በተመዘገበው ፈጣን የኢንዱስትሪ ልማት ለዘላቂ ልማት ዋስትና የሚሰጥ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽንና መነሻ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም በአፍሪካ ቀዳሚ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለመሆን የሚያስችሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች እየተገነቡ ነው።

የፓርኮቹ ግንባታ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ከመሳብ በተጨማሪ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድልን የፈጠረ ነው። በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ የሚገኘው የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ በሙ አቅሙ መስራት ሲጀምር በዓመት አንድ ሚሊዮን ዶላር ሊያስገኝ እንደሞችል ይታመናል። የመቐለው የኢንዱስትሪ ፓርክም ወደ ስራ ሲገባ ለአስር ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ታምኗል። ሌሎች በግንባታ ላይ የሚገኙት ፓርኮችም በተመሳሳይ ሁኔታ የውጭ ምንዛሬ ግኝት የሚፈጥሩና ለበርካታ ዜጎችም ዘላቂ የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል።  

እነዚህ በመጠኑ ለመጠቃቀስ የሞከርኳቸው የኢኮኖሚ ልማትና የህዝብ ተጠቃሚነት በሀገራችን ውስጥ የተረጋገጡ ቢሆኑም፤ ፅንፈኛው ሃይል ግን “ከእኔ ወዲያ ለአሳር” በሚል የትምክህት አስተሳሰብ ሃቁን ለማሳነስ ይሞክራል። ይህ ለይስሙላ “ኢትዮጵያን እንወዳለን” በማለት የሚቀነቀን ዲስኩር ከእውነታው ጋር የሚጋጭ ብቻ ሳይሆን የፅንፈኛውን አካል ማንነት ገሃድ ያወጣ ነው። ምክንያቱም በፅንፈኝነት ተሰልፈው የሀገራችንን ስኬቶች ለማጣጣል የሚሞክሩ ሃይሎች መነሻቸውም ይሁን መድረሻቸው ኢትዮጵያዊነት ሳይሆን የሌሎች ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች መሳሪያ መሆናቸውን እየነገሩን ስለሆነ ነው።

ፅንፈኛው ሃይል ቢመቸው እንኳንስ የኢትዮጵያን ስኬቶች ማጣጣል ቀርቶ የትኛውንም ተግባር ከማከናወን ወደ ኋላ ስለማይል ነው። ምክንያቱም በፅንፈኝነት ማዕበል ከወዲያ ወዲህ የሚላጉት እነዚህ አካላት የሀገራችንን ስኬቶች ቢያውቁም እንዳላወቁ መሆን ስለሚፈልጉ ነው።

ሆኖም ከሁሉም በላይ የስኬቶቹ ተጠቃሚ የሆነው የሀገራችን ሀዝብ ሃቁን ስለሚመለከትና በፅንፈኞች የሚነዙ የአሉባልታ ዲስኩሮችን በሚዛዊነት ስለሚመለከት ለእነርሱ የቁራ ጩኸት ቦታ የሚሰጥ አይደለም። ‘ለምን?’ ከተባለ በፍትሐዊነት እየተጠቀመ ያለው በትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራ ካለው መንግስት እንጂ ከእነርሱ ባለመሆኑ ነው።

ያም ሆነ ይህ ግን ሃቁ ያለው ሀገር ቤት እንጂ በኢትዮጵያ ስም የግል ጥቅማቸውን ለማሳደድ ከተሰለፉ ሃይሎች ጋር አይደለም። ዓለም የመሰከረውንና እውቅና የሰጠውን የኢኮኖሚ ዕድገት ማንም ሊሽረው አይችልም። ሀገራችን የስኬት ካባን ደርባ ነገ ወደ ላቀ የከፍታ ምዕራፍ መሸጋገሯ አይቀሬ መሆኑን ወዳጅም ይሁን ጠላት ሊያውቀው የሚገባ ይመስለኛል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy