NEWS

የብአዴን የከፍተኛ አመራር ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ተጀመረ

By Admin

September 26, 2017

የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን/ የከፍተኛ አመራር ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ዛሬ በባህርዳር ከተማ ተጀምሯል።

” እየሰራን እንታደሳለን ፤ እየታደስን እንሰራለን ” በሚል መሪ ሀሳብ ለአምስት ቀናት የሚካሄደው ኮንፍረንስ፥ ያለፉት 26 ዓመታትን የልማት ጉዞ በመዳሰስ የጥልቅ ተሃድሶ ስኬቶችና ተግዳሮቶችን ይገመግማል፡፡

የጥልቅ ተሃድሶ ሂደቱ ተጠናክሮ በሚቀጥልበትና አጠቃላይ አቅጣጫ በሚቀመጥበት ሁኔታ እንደሚመክርም በብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት የገጠር ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዘለቀ አንሉ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በመሪ ድርጅቱ፣ በመንግስትና በመላ ህዝቡ የነቃ ተሳትፎ በየደረጃው የሚገኘውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የተጓዙበት ርቀትም ለኮንፈረንሱ ይቀርባል።

በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች የተገኙ ስኬቶችን በቀጣይ አዳብሮ ለማስቀጠል የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች የጋራ መግባባት ላይ እንደሚደርሱም ይጠበቃል። ከዚህ ባለፈም አሁንም ያልተፈቱ ችግሮችን በቀጣይ ለይቶ እልባት ለመስጠት የተጀመረውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራ አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያም ይመክራል።

ኮንፍረንሱ የ2009 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምን በመገምገም የነበሩ ስኬቶች እንዲጠናከሩና ችግሮች እንዳይደገሙ የሚያመቻች አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎም ነው የሚጠበቀው።

በተለይ አመራሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለይቶ በመፍታት የተያዘውን በጀት ዓመት ሁለንተናዊ ዕቅድ ለማሳካት፥ በተቀመጠ አቅጣጫ ዙሪያ በመምከር የጋራ መግባባት ላይ እንደሚደረስ ይጠበቃል፡፡

አመራሩ በሚያነሳቸው ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ግልጽነትና መግባባት ላይ መድረስ ኮንፍረንሱ የሚመለከታቸው ጉዳዮች መሆናቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።