Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የቱሪዝም ዘርፉ መሰረተ ሰፊ ይሁን

0 1,209

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የቱሪዝም ዘርፉ መሰረተ ሰፊ ይሁን

ብ. ነጋሽ

ከመስከረም 11፣ 2010 ዓ/ም ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የዓለም የቱሪዝም ቀን እየተከበረ ነው፣ ቱሪዝም ለዘላቂ ልማት በሚል መሪ ሃሳብ። የቱሪዝም ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ  ለ38ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ30ኛ ጊዜ ነው በመከበር ላይ የሚገኘው። ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቱሪዝም ዘርፍ ልማት ዕምቅ አቅም ያላት ሃገር በመሆኗ ከቱሪዝም ጋር ለተያያዙ ማናቸውም ሁነቶች ትኩረት መስጠት አለባት። ከዚህ አኳያ የዓለም የቱሪዝም ቀን በኢትዮጵያ መከበሩ ዘርፉ በህዝቡ ዘንድ እንዲታሰብና ትኩረት እንዲያገኝ ከማድረግ ባሻገር፣ ዘርፉን ለማልማት የሚያስችሉ ሃሳቦች እንዲመነጩና መድረክ እንዲያገኙ እድል ይሰጣል። እናም የቱሪዝም ቀን የሃገሪቱን እምቅ የቱሪዝም ልማት አቅም በሚመጥን መልክ መከበሩ ተገቢ ነው። ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀንን በክልሎች በቅብብሎሽ እንዲከበር ማድረጓ ሁነቱ ዘርፉን ለማነቃቃት የለውን ፋይዳ ከፍ ያደርገዋል። የዘንድሮው የዓለም የቱሪዝም ቀን የሚከበረው በኦሮሚያ ነው።

ለመሆኑ ቱሪዝም ምንድነው?  ቱሪዝም በበርካታ የዘርፉ ተመራማሪዎችና ተቋማት የተለያየ ትርጉም ተሰጥቶታል። ይሁን እንጂ በቱሪዝም መሰረታውያን ላይ ሰፊ ስራ የሰሩት ሮበርት ዉድሮው ማክኢንቶሽ እና ቻርልስ አር ጎልድነር የሰጡት ትርጉም የተሻለ ሆኖ ስላገኘሁት በቀዳሚነት ልጠቅሰው ወድጃለሁ።

እነዚህ ሁለት የዘርፉ ተመራማሪዎች የሰጡት ትርጉም ቱሪዝም ከቤታቸው ርቀው ለሚጓዙ ግለሰቡች ወይም ብድኖች ትራንስፖርትን፣ ማረፊያ ስፍራን፣ የምግብና መጠጥ አቅርቦትን፣ መደብሮችን፣ የመዝናኛ አገልግሎት ሰጪዎችን ጨምሮ ሌሎች የመስተንግዶ አቅርቦት ውስጥ ያሉ ድርጊቶች፣ አገልግሎቶችና ኢንደስትሪዎች ጥምረት ሥርአት እንዲሁም  ቱሪስቶችን ወይም ሌሎች ጎብኝዎችን ለመሳብና ለመቀበል በቱሪስቶች፣ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ በተቀባይ መንግስታትና ማህበረሰቦች መሃከል ያለ ጥቅል መስተጋብር ነው ይላል።

ይህ ለቱሪዝም ኢንደስትሪ ምንነት የተሰጠ ትርጉም በዘርፉ ውስጥ ያሉት አገልግሎቶችና መሰተጋብሮች ላይ ያተኩራል። ይሁን እንጂ ከቤታቸው ርቀው የሚጓዙ ሰዎች የሚለውን ከመጥቀስ ያለፈ በተለይ ስለቱሪስቶች ማንነት አይናገርም። የቱሪስቶችን ማንነት በተመለከተ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት የዓለም የቱሪስት ድርጅት የሰጠው ትርጉም የተሻለ ሆኖ ስላገኘሁት እጠቅሰዋለሁ። በዚህ ትርጉም መሰረት፣ ቱሪዝም ጎብኚ ተብለው በተለዩ ሰዎች የሚፈጸም ድርጊት ነው። ጎብኚ በመደበኛነት ከሚኖርበት አካባቢ ተነስቶ ቢያንስ ለአንድ ዓመት ቆይታ በዓል ማክበርን፣ ጊዜ ማሰለፍንና መዝናናትን፣ ሥራን፣ ህክምናን፣ ትምህርትን ጨምሮ ለተለያዩ ጉዳዮች ወደሌላ መዳረሻ የሚጓዝ ነው። ይላል።

ሁለቱን የቱሪዝም ትርጉሞች አጣምረን ስናያቸው ቱሪዝም መደበኛ የመኖሪያ አካባቢያቸውን ለቀው ወደሌላ ስፍራ ቢያንስ ለአንድ ዓመት ቆይታ የሚጓዙ ሰዎችንና ለእነዚህ ሰዎች የሚቀርቡ አገልግሎቶችን፣ እንዲሁም ከሚሄዱበት ሃገር መንግስትና ማህበረሰብ ጋር የሚኖራቸውን መስተጋብር አጠቃሉ የያዘ ኢንደስትሪ መሆኑን እንረዳለን።

አንድ ሃገር ወይም ማህበረሰብ ከቱሪዝም የሚያገኘው ገቢ ለተጓዦች ከሚያቀርበው የትራንስፖርት፣ የመቆያ ስፍራ፣ ምግብና መጠጥ፣ ጎብኚች የሚፈለጓቸውን ቁሳቁሶች ከሚያቀርቡ ሱቆች ሽያሽ፣ ወዘተ የሚመነጭ ነው። በመሆኑም አንድ ሃገር ወይም ማህበረሰብ ከቱሪዝም ዘርፍ እንዲጠቀም በቅድሚያ ወደዚያ ሃገር ወይም ስፍራ ቱሪስቶች መጓዝ ይኖርባቸዋል። በሌላ አነጋጋር ለመጓዝ የሚያነሳሳቸው ነገር ሊኖር ይገባል። የቱሪስት መስህቦች የሚባሉት እነዚህ ጉዞ አነሳሽ ነገሮች ናቸው። የቱሪስት መስህቦቹ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሊሆኑ ይችላሉ። የቱሪስት መስህብ በመላው ዓለም የሚገኙ ጎብኚዎች ሊያውቁት በሚችሉበት ሁኔታ በሁሉም ሚዲያና አጋጣሚ ካልተዋወቀ መስህብ ሊሆን አይችልም።

በመቀጠል ለተጓዞች/ቱሪስቶች የተሟላ መሰረታዊና የመዝናኛ አገልግሎት በሚፈልጉት የጥራትና የቅልጥፍና ልክ ማቅረብ ያስፈልጋል። ይህም የተሟላና ደረጃውን የጠበቀ የየብስ፣ የአየርና የውሃ ትራንስፖርት አገልግሎትን፣ ብቃትና ክህሎት ያላቸውን ሰዎች የሚያሳትፍ የማስጎብኘት አገልግሎትን፣ የሆቴልና መስተንግዶ አገልግሎትን፣ የተሟላ የግንኙነት መረብን፣ የህክምና አገልግሎትን፣ የመዝናኛ ትዕይንቶችና ፋሲሊቲዎችን ወዘተ ያጠቃልላል። እነዚህ መሰረታዊ አገልግሎቶች ካልተሟሉ፣ የቱሪስት መስህብ ምን ያህል በመላ ዓለም ቢተዋወቅ ቱሪስቶችን ማርካት፣ የተራዘመ የቆይታ ጊዜ እንዲኖራቸው፣ ደጋግመው እንዲመጡና ሌሎች እንዲመጡ እንዲያነሳሱ ማድረግ አይቻልም።

ሌላው ቱሪዝም ከምንም በላይ ሰላም የሚፈልግ መሆኑ ነው። ህይወቱን ለአደጋ የሚያጋልጥ ጦርነትና ብጥብጥ ያለበትን አካባቢ መጎብኘት የሚመርጥ ቱሪስት የለም። ጦርነትና ብጥብጥን ራሱን የመጎብኘት ፍላጎት ያለው ቱሪስት ያለ አይመስለኝም።

እንግዲህ፣ ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ከኢንደስትሪ ጋር ከተዋወቀች ከግማሽ ክፍለ ዘመነ በላይ ጊዜ ተቆጥሯል። ከሃምሳ ዓመታት በፊት የ13 ወር ጸጋ  በሚል ብራንድ  ከዘርፉ ጋር ለመተዋወቅቀ ዳዴ የጀመረች ቢሆንም የተሟላ ቱሪስቶችን መቀበል የሚያስችል የሆቴልና መስተንግዶ አገልግሎትና የማስጎብኘት አገልግሎት አልነበረም ማለት ይቻላል። በየትኛውም አቅጣጫ ከአዲስ አበባ የወጣ ሰው እየራቀ በሄደ ቁጥር ምግብም ማረፊያም ማግኘት የማይችልበት ሁኔታ ነው የነበረው። ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን ይህ ሁኔታ በእጅጉ ተቀይሯል። አሁንም የኮከብ ደረጃ ያላቸው ሆቴሎች በአዲስ አበባ የተገደቡ ቢሆንም ኮከብ ካላቸው ጋር ተቀራራቢ አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎችን በብዙ የሃገሪቱ ከተሞች ማግኘት ወደሚቻልበት ደረጃ እየተደረሰ ነው።

ከቱሪስት መስህብ አኳያ ኢትዮጵያ በርካታ የተፈጥሮና ታሪካዊ መስህቦች ያላት ሃገር ነች። ይሁን እንጂ በተለይ የተፈጥሮ መስህቦቿን በማስተዋወቅም ይሁን በመጠቀም ረገድ ምንም አልተሰራም ማለት ይቻላል። የኢትዮጵያ ቱሪዝም በታሪካዊ መስህቦች ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ ሁኔታ ከዘርፉ በሚፈለገው ልክ መጠቀም እንዳይቻል ያደረገ ቀዳሚ ምክንያት ነው። እርግጥ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት የሚጨበጡም ሆኑ የማይጨበጡ ቅርሶችን በማስመዝገብ ከአፍሪካ በቀዳሚነት የምትጠቀስ ሃገር ነች።

ኢትዮጵያ 12 ታሪካዊና የተፈጥሮ ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት በዩኔስኮ አስመዝግባለች። እነዚህም፤ የአክሱም ሃውልቶች፣ የላሊበላ አብያተክርቲያናት፣ የጎንደር ፋሲል ቤተመንግስት ግምብ፣ የጢያ ትክል ድንጋዮች፣ የሰሜን ብሄራዊ ፓርክ፣ የኮንሶ ሰው ሰራሽ መልከዓምድር፣ የታችኛው አዋሽና የታችኛው ኦሞ ሸለቆ፣ የመስቀል ደመራ፣ የሲዳማ ፊቼ ጨንበላላ፣ የኦሮሞ የጋዳ ሥርአት ናቸው። ከእነዚህ መሃከል የተፈጥሮ ቅርስ ተብሎ ሊወሰድ የሚችለው የሰሜን ብሄራዊ ፓርክ ብቻ ነው። የታችኛው አዋሽና የኦሞ ሸለቆም ቢሆኑ በሰው ልጅ መገኛነት የተመዘገቡ እንጂ በተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገቡ አይደሉም።

በቀጣይነት በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ በእቅድ ደረጃ የተያዙ ቅርሶችም አሉ። እነዚህም፤ የባሌ ተራራዎች ብሄራዊ ፓርክ፣ የድሬ ሼክ ሁሴን መስጊድ፣ የሶፍ ኦመር ዋሻ፣  የጌዲዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ መልከዓምድር፣ የመልካ ካንቱሬ የአርኪዮሎጂ ስፍራዎች ናቸው። በማይጨበጥ ባህላዊ ቅርስነት ደግሞ የአማራና የትግራይ የሻዳይና የአሸንዳ በዓላት፣ የጥምቀት በዓል ይጠቀሳሉ። ከእነዚህ ሊመዘገቡ ከታቀዱ ቅርሶች መሃከልም ቢሆን የተፈጥሮ ቅርሶች ጥቂት ናቸው፤ የባሌ ተራራዎች ብሄራዊ ፓርክና፣ የሶፍ ኦመር ዋሻ።

ይህ ሁኔታ ሃገሪቱ በተፈጥሮ የቱሪስት መስህብ ልማት ላይ ውስንነት ያላት መሆኑን ያመለክታል። እርግጥ ቱሪስቶችን ለመሳብ መስህቦች በዩኔስኮ መመዝገብ አይጠበቅባቸውም። ቱሪስቶችን መሳብና ማስተናገድ በሚችሉበት ሁኔታ መለማታቸው በቂ ነው። የተፈጥሮ ሃብቶች ለቱሪዝም መስህብነት እንዲውሉ ከመዝናኛ መሰረተ ልማቶችና ፋሲሊቲዎች ጋር መቆራኘት አለባቸው። በሃገራችን ያሉትን የተፈጥሮ ሃብቶች ባለው የመዝናናት ፋሲሊቲ ከመጠቀም አኳያም ቢሆን ችግር አለ። የቱሪስት መስህቦችን የማስተዋወቁ እንቅስቃሴ በተለይ በዩኔስኮ የተመዘገቡት ታሪካዊ ቅርሶች ላይ ብቻ ያተኮረ ነው። ይህ ሁኔታ ሃገሪቱ ከቱሪዝም የምታገኘው ጥቅም ሊሆን ከሚገባው በታች እንዲሆን አድርጓል።

ሃገሪቱ ሰፊ የቱሪስት መስህብ ሊሆኑ የሚችሉ የተፈጥሮ ጸጋዎች ያላት መሆኑ ይፋ እውነት ነው። የተፈጥሮ ጸጋ ለቱሪዝም ልማት ያለውን ፋይዳ ለመረዳት ጎረቤታችን ኬንያን መመልከት በቂ ነው። ኬንያ እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት ማስመዝገብ የቻለች ሃገር አይደለችም። ይሁን እንጂ አሁን አሁን አልሸባብ በሃገሪቱ ባደረሰው ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት ሳቢያ የቱሪስት ፍሰቱ ማሽቆልቆል ቢያሳይም በዓመት እስከ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን በሚደርሱ ቱሪስቶች የምትጎበኝ ሃገር ነች። ኢትዮጵያን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ዓመታዊ ቁጥር እስካሁን 1 ሚሊየን እንኳን እንዳልሞላ ልብ በሉ። ኬንያ በቱሪዝሙ ዘርፍ የተሻለ ስኬታማ መሆን የቻለችው፣ የተፈጥሮ ጸጋዎቿን ከመዝናኛ ጋር አጣምራ በማልማቷ ነው። የኢትዮጵያን ቱሪዝም መሆን በሚገባው ልክ እንዲያድግ ዘርፉ በታሪካዊ መስህቦች ላይ ካለው ጥገኝነቱ ተላቆ የተፈጥሮ ጸጋ መስህቦችንም በማጠቃለል መሰረቱ ማስፋት  ይኖርበታል።    

ያም ሆነ ይህ፣ ኢትዮጵያ በርካታ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ታሪካዊና የተፈጥሮ ቅርሶች ያላት ሃገር ብቻም አይደለችም የመገኛም ሃገር ነች። ኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሰው ልጅ ዝርያ መገኛ ሃገር ነች። ከ3 ሚሊየን ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የሉሲ ወይም የድንቅነሽ ቅሪተ አካል የተገኘው በኢትዮጵያ ነው። ኢትዮጵያ ጣፋጩና ተፈላጊው የቡና ዝርያ – አረቢካ ቡና መገኛ ሃገር ነች። ኢትዮጵያ የጤፍና ሌሎች አዝርዕት መገኛ ሃገርም ነች። የኢትዮጵያ የቱሪዝም መለያ ብራንድ ምድረ ቀደምት ወይም Land of Origines እንዲባል የተወሰነው ለዚህ ነው። ይህም በአግባቡ ከተዋወቀ ሃገሪቱን የቱሪስት ስበት ማዕከል ሊያደርጋት ይችላል።

እንግዲህ የኢፌዴሪ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት መቋቋሙ ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል። በዚህም ሳቢያ የሃገሪቱ ቱሪዝም ባለፉት ሶስት ዓመታት እጅግ ከፍተኛ እድገት ማስመዝገብ ችሏል። ኢትዮጵያ በ2007 በጀት ዓመት ከቱሪዝም 2 ነጥብ 9 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ችላለች። በ2008 በጀት ዓመት ይህ የቱሪዝም ዘርፍ ገቢ ወደ ከ3 ነጥብ 4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ከፍ ብሏል። በ2009 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በሃገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተቀስቅሶ በነበረው አለመረጋጋት ሳቢያ የቱሪዝም ገቢው የ2 ነጥብ 5 በመቶ ቅናሽ አሳይቶ 3 ነጥብ 32 ቢሊየን ዶላር ገደማ ሆኗል። ከአንደኛው ሩብ ዓመት በኋላ ባሉት የ2009 በጀት ዓመት ወራት የነበረው የቱሪዝም ፍሰት ግን ከባለፈው  ዓመት ጋር ተመሳሳይ ነበር።

በአጠቃለይ አሁን ያለው የሃገሪቱ የቱሪዝም እድገት አዝማሚያ ተስፋ ሰጪ ነው። ይሁን እንጂ፣ ሃገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ያህል ጥቅም እንድታገኝ ከታሪካዊ የቱሪስት መስህብ ጥገኝነት ተላቆ በተፈጥሮ ጸጋ መስህቦችም ላይ እንዲመሰረት በማድረግ መሰረቱን የማስፋት ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። የሆቴልና የመስተንግዶ አገልግሎትም በመሰረተ ልማትም በሞያም እንዲጎለብት ማድረግም እንዲሁ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ሃገሪቱ አሁን ያላትን ሰፊ የተፈጥሮ ጸጋ የቱሪዝም መስህቦች ዓለም አቀፍ ደረጃን ከሚያሟሉ መዝናኛ ልማት ጋር በማስተሳሰር እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ስራን ከተፈጥሮ የቱሪስት መስህብ ልማት ጋር በማጣመር የቱሪዝም ዘርፉ በየአካባቢው በስራ እድል ፈጠራ ሁሉንም ተጠቃሚ ማድረግ በሚችልና የሃገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት በሚያሳድግ አኳኋን እንዲያድግ መስራት ያስፈልጋል።  

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy