Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የትምክህትና የጥበት ኃይሎችን አስተሳሰብ ለማምከን…

0 341

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የትምክህትና የጥበት ኃይሎችን አስተሳሰብ ለማምከን…

ዳዊት ምትኩ

የአገራችንን ሰላምና መረጋጋት የማይሹ ፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ሃይሎች የሚያራምዷቸው የተሳሰቱ አስተሳሰቦችን በርካታ ናቸው። በተለይም የትምክህትና የጥበት ሃይሎች ለህብረተሰቡ ከአሉባልታና ሰላሙን በበሬ ወለደ ወሬ ከማመስ ውጭ ምንም ዓይነት ተግባር የሚፈፅሙለት አይደሉም።

እነዚህ ሃይሎች በወጣቶች ደም በመነገድ የህብረተሰቡን አጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ የጥፋት ተልዕኳቸውን ለመፈፀም ይጥራሉ። ሆኖም ህብረተሰቡ ድብቅ ፍላጎታቸውን መገንዘብ አለበት። ይህን አስተሳሰባቸውን ለማምከንም ከሁሉም በፊት ቀዳሚ ሚናውን ሊወጣ ይገባል።

የትምክህትና የጥበት ሃይሎች የፖለቲካ ኪሳራ የደረሰባቸው ብቻ አይደሉም። ይህ መንግስት ካልወደቀ ወደ አገር ቤት መመለስ የማይችሉም ጭምር ናቸው። እናም የአገሪቱን ሰላም አይፈልጉም፡፡ የእኩይ ተግባር ጠንሳሽና ደጋፊዎችም ናቸው። በቅርቡ እንደተመለከትነው ሁከት ሁሉ በነውጥ ለውጥ ይመጣ ዘንድ የሚታትሩት እነዚህ አካላት በአገር ውስጥ ተልዕኮአቸውን ለሚያስፈፅሙ ላቸው ሰዎች ከውጭ ገንዘብ ጭምር እየላኩ ብጥብጡ እንዳይረግብ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውም እየተሰማ ነው፡፡

ፌስ ቡክን በመሳሰሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች በመጠቀም ህዝቡን ለማሳሳት ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከጉዳዩ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው ፎቶዎችን ቆርጦና ቀጥሎ መለጠፍ፣ የፈጠራ ወሬና አሉባልታን ማራገብ እንዲሁም ፍፁም ያልሆነን እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ ስራቸው ሆኗል፡፡

በግንቦት ሰባት እና ሌሎች አሸባሪ ቡድኖችና በኤርትራ መንግሥት የሚደገፈው “ኢሳት” የተሰኘው እሳት ጫሪና ቆስቋሽ የቴሌቭዥን ጣቢያም ሌላው ሀሰትና የሽብር ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ህዝቡን ለማወክ ሲጥር መመልከት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ መደበኛ ተግባሩ ነው፡፡ ለቆመለት የትርምስ ዓላማ በውሸት ወሬ አደንቋሪ ሆኗል። ይሁን እንጂ እርሱን የሚሰማው የለም። ተግባሩ የታወቀበት በመሆኑም ህዝቡ ለአሉባልታው አልተፈታም።

ለወገኖቻቸው የማይጨነቁና የማያስቡት እንደ ጃዋር መሐመድ ዓይነት ቅጥረኞች በውጭ አገር በድሎት እየኖሩ፣ በርገራቸውንም እየገመጡ “አስብልሃለሁ፤ ነፃ አወጣሃለሁ…” እያሉ ማንቧረቅን አልተሰላቹም፡፡ ይህን ከንቱ ቅጥፈት መስማት የሰለቸው ህዝብ እየበዛ መምጣቱን ቢገነዘቡ ባልደከሙ ነበር፡፡ እኩይ ተግባራቸው ሲሰናከል ህዝባዊ መንገዱ እንደሚጠራም በተረዱ ነበር፡፡

ተወደደም ተጠላ አገሪቱ ዛሬ ከሰላምና ልማት ሌላ ምንም አጀንዳ የላትም፡፡ ለዚህ ብርታት የሚሆናት ደግሞ ባለፉት ዓመታት እያስመዘገበችው የመጣችው የኢኮኖሚ ዕድገት ነው፡፡

የዓለም የኢኮኖሚ ጠበብቶችም ጭምር ትጋቷን እያደነቁ ምሳሌነቷን የሚጠቅሷት ይህች አገር ሁሌም በተሻለ የዕድገት ግስጋሴ ውስጥ ልታልፍ ቆርጣለች፡፡ ዛሬ እነ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያና የመሳሰሉ አገራት የደረሱበት የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የማትደርስበት አንዳችም ምክንያት አይኖርም።

በእስካሁን ሂደትም ዜጎች የመሰረተ ልማትና የማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚነታቸው በከፍተኛ ደረጃ አድጓል፡፡ በመሰረተ ልማት ማስፋፋት ረገድ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል፣ የጤና ተቋማትንና ትምህርትን ተደራሽ በማድረግ በኩልም የተሰራው ስራ ውጤታማ ነው፡፡

ለዚህ ስኬት የህዝቦች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት መከበርና የአገሪቱ ሰላም መስፈን ዋናውን ስፍራ ይይዛል፡፡ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዕውቅና በማግኘታቸው ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ባስገኘላቸው መብት መሰረት ማንነታቸው ተከብሯል፣ በቋንቋቸው መማር ችለዋል፣ ይህ ደግሞ በጋራ መግባባት ላይ ተመስርተው አገሪቱን ለማልማት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አስችሏቸዋል፡፡ ሆኖም በቀጣይነትም አገሪቱን በማልማት ረገድ የሚቀሩ በርካታ ስራዎች መኖራቸውን መዘንጋት አይገባም፡፡

የአገራችንን ሁሉን አቀፍ እድገት ይበልጥ ለማስቀጠል የትምክህትና የጥበት ሃይሎችን አስተሳሰብ በተገቢው መንገድ መመከት ያስፈልጋል። አስተሳሰቡ የአገሪቱን ለውጦች የማይቀበልና ሁሉንም ጉዳዩች በሃይል ለማስፈፀም የሚፈልግ በመሆኑ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ነው።

የትምክህትና የጥበት ኃይሎች በቅርቡ በጥብቅ የሚያቆራኛቸውን ነገር አግኝተው ፍቅራቸው ጣራ መንካቱን እናስታውሳለን፡፡ ይሁን እንጂ ትምክህትና ጥበት አምሳያዎች ቢሆኑም በአንድነት መስራት ስለማይችሉ አንደኛው ራሱን የበላይ በማድረግ መብት ለሌላኛው ለመስጠት ይሞክራል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ‘የእገሌ ብሔር ልሂቃን’ እያለ ስም በማውጣት በማንነት ጥያቄዎች ላይ ላይ ያላቸውን አስተሳሰብ ጥንብ እርኩሱን ሲያወጣ ይስተዋላል።

ይህ የወል የመተቻቸት በሽታቸውም በጋራም ሆነ በተናጠል ብዝሃነት መለያዋ በሆነች ታላቅ ሀገር እንዳይኖሩ የሚያደርጋቸው ነው፡፡ በአንድ ወቅት “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚል እሳቤ በሽብር በአመፃ አውድማ ላይ ተሰማርተውና በጥፋት ጋብቻ ተጣምረው የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መገለጫ የሆነችውን አገራችንን ለማተራመስ ሞክረው ብዙም ሳይቆዩ አንዱ በሌላኛው ላይ ጣቱን ለመቀሰር በቅቷል፡፡

የትምክህትና የጥበት ሃይል ተግባሩን የሚፈፅምበት መንገድ ይታወቃል። ይኸውም የሆነ አጋጣሚን እንደ ምክንያት ወስዶ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለመቀየር የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው። በሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል በግብር ሰበብ የተነሳውን ጉዳይ መመልከት የዚህ አባባል አስረጅ ነው።

ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ለሰላምና ልማት ወዳዱ ህዝብ ትርፍ ይገኝበታል ከተባለ የሚተርፈው ጉዳት ብቻ መሆኑን በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ የህብረተሰብ ክፍል የሚረዳው ነው፡፡

ታዲያ ምንጊዜም ቢሆን ከሁከትና ከረብሻ የሚገኝ ጥቅም እንደሌለ ማንም የሚያውቀው እውነታ ነው፡፡ ሁሉም እንደሚረዳው ሁከት፣ ትርምስ፣ ብጥብጥና ረብሻ ትርፉ ለሰው ህይወት ማለፍና ለንብረት መውደም በር ከፋች ነው፡፡

እናም በእነዚህ ሃይሎች እኩይ አስተሳሰብ ላለመመራት ችግሩን መመከትና ማምከን ይገባል፡፡ የእሳት አቀጣጣይነት ተግባራቸው መቆም አለበት፡፡ የእነዚህ የጥፋት ሃይሎች መንገድ የሰላም ሳይሆን የሁከት፣ የልማት ሳይሆን የድህነት፣ የነፃነት ሳይሆን የባርነት እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ሳይሆንየፀረ-ዴሞክራሲያዊነት በመሆኑ ልንታገለውና አስተሳሰባቸውንም ልናመክነው ይገባል፡፡ ይህን መፈፀምም በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ተግባር ላይ ያዋለችውን ሁለተኛውን የልማት ዕቅድ በሁለንተናዊ መንገዱ እንዲሳካ ድጋፍ ማገዝ ነው፡፡ ህዳሴያችንን እንዲቀርብ ማስቻልም ነው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy