Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የትምክህትና የጥበት ኃይሎች ጎራ መደበላለቅ

0 318

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የትምክህትና የጥበት ኃይሎች ጎራ መደበላለቅ

                                                         ታዬ ከበደ

የአገራችን አንዳንድ የትምክህትና የጥበት ኃይሎች ጎራቸው እየተደበላለቀ ነው። እሳትና ጭድ በጋራ የማኖር ያህለ አሊያም ውሃን በወንፊት ይዞ የመሄድ ያህል አብሮነት ያላቸው ናቸው። እነዚህ ሃይሎች በድህነት ላይ ታጥቆ የዘመተው ህዝብ ላይ ሽብርና ሁከትን በመፍጠር በአገሪቱ መረጋጋት እንዳይኖራት የማተራመስ ተግባራቸውን በመፈፀም ዓላማቸውን ለማሳካት የማይቧጥጡት የአሉባልታ ዳገት የለም፡፡ የማይለፍፉት የበሬ ወለደ ድርሰት የለም፡፡

እንዲህ ላሉ አሳሳች ተግባራት በቀላሉ የማይረበ ሸውና የማይሸነገለው ሕዝብ ነገሮችን በጥሞና ተመልክቶ ብቸኛ አማራጩን ሰላም ቆንጥጦ መያዝ ተለምዷዊው ባህሪው ነው፡፡ የሰላም ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ጠንቅቆ የሚረዳው የኢትዮጵያ ሕዝብ ልማትን የሙጥኝ ብሎ የእድገትን እርካብ መውጣት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥሯል፡፡

ባለፉት ዘመናት በሰላም እጦት ከተጎዳው ማንነቱ አገግሞ በፈጣን የልማት ጉዞው ስኬትን እያስመዘገበ መሆኑ እንኳንስ በወዳጅ በጠላቶቹም እየተመሰከረለት ነው፡፡ በፌዴራል ስርዓት የምትተዳደረው ይህች አገር በሕዝብ ይሁንታ የማንነቷ ጥንካሬ ከፍ እንዲል ሆኗል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች መብትና እኩልነት ተከብሯል፡፡ ነፃና ሉዓላዊት አገር መሆኗም ተረጋግጧል፡፡

እንደሚታወቀው ሁሉ የመልካም አስተዳደር ችግር ያማረረው የሕብረተሰብ ክፍል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እግረ መንገዱን ብሶቱን እንደተወጣ ማመኑ አይከብድም፡፡ በመንግሥታዊና ሕዝባዊ ተቋማት በመልካም አስተዳደር ችግር የሚማረረው ህዝብ ብሶቱን የገለፀበት መንገድ ተመራጭ ባይሆንም፤ የችግሩ ክብደት ምን ያህል እንደሆነ ግን አሳይቷል፡፡ ያም ሆኖ በአገራችን ውስጥ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በተከሰተው ሁከት የትምክህትና የጥበት ሃይሎች አንድ የመሰለ፣ ግን መቼም ሊገናኝ የማይችል ዓላማ ተስተውሏል፡፡

በወቅቱ እንደተመለከትነው በነውጥ ለውጥ ይመጣ ዘንድ የሚታትሩት እነዚህ አካላት በአገር ውስጥ ተልዕኮአቸውን ለሚያስፈፅሙላቸው ሰዎች ከውጭ ገንዘብ ጭምር እየላኩ ብጥብጡ እንዳይረግብ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውም እየተሰማ ነው፡፡

በግንቦት ሰባት እና ሌሎች አሸባሪ ቡድኖችና በኤርትራ መንግሥት የሚደገፈው “ኢሳት” የተሰኘው እሳት ጫሪና ቆስቋሽ የቴሌቭዥን ጣቢያም ሌላው ሀሰትና የሽብር ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ሕዝቡን ለማወክ መጣሩ አልቀረም፡፡

በአገሪቱ ትንሽ ነገር ኮሽ ባለች ቁጥር “አለን” ለማለት የሚከጅሉት እነዚህ ሃይሎች ለወገኖቻቸው የማይጨነቁና የማያስቡ ግን በውጭ አገር በድሎት እየኖሩ፣ በርገራቸውንም እየገመጡ “አስብልሃለሁ፤ ነፃ አወጣሃለሁ…” እያሉ ማንቧረቅን አልተሰላቹም፡፡ ይህን ከንቱ ቅጥፈት መስማት የሰለቸው ህዝብ እየበዛ መምጣቱን ቢገነዘቡ ባልደከሙ ነበር፡፡ እኩይ ተግባራቸው ሲሰናከል ሕዝባዊ መንገዱ እንደሚጠራም በተረዱ ነበር፡፡

ተወደደም ተጠላ አገሪቱ ዛሬ ከሰላምና ልማት ሌላ ምንም አጀንዳ የላትም፡፡ ለዚህ ብርታት የሚሆናት ደግሞ ባለፉት ዓመታት እያስመዘገበችው የመጣችው የኢኮኖሚ ዕድገት ነው፡፡ የዓለም የኢኮኖሚ ጠበብቶችም ጭምር ትጋቷን እያደነቁ ምሳሌነቷን የሚጠቅሷት ይህች አገር ሁሌም በተሻለ የዕድገት ግስጋሴ ውስጥ ልታልፍ ቆርጣለች፡፡ ዛሬ እነ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያና የመሳሰሉ አገራት የደረሱበት የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የማትደርስበት አንዳችም ምክንያት እንደማይኖር እያረጋገጠች ነው፡፡

በእስካሁን ሂደትም ዜጎች የመሰረተ ልማትና የማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚነታቸው በከፍተኛ ደረጃ አድጓል፡፡ በመሰረተ ልማት ማስፋፋት ረገድ ስኬቶች ተመዝግበዋል፣ የጤና ተቋማትንና ትምህርትን ተደራሽ በማድረግ በኩልም የተሰራው ስራም ውጤታማ ነው፡፡

ለዚህ ስኬት የህዝቦች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት መከበርና የአገሪቱ ሰላም መስፈን ዋናውን ስፍራ ይይዛል፡፡ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዕውቅና በማግኘታቸው ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ባስገኘላቸው መብት መሰረት ማንነታቸው ተከብሯል፣ በቋንቋቸው መማር ችለዋል፣ ይህ ደግሞ በጋራ መግባባት ላይ ተመስርተው አገሪቱን ለማልማት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አስችሏቸዋል፡፡ ሆኖም በቀጣይነትም አገሪቱን በማልማት ረገድ የሚቀሩ በርካታ ስራዎች መኖራቸውን መዘንጋት አይገባም፡፡

የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ አገልግሎት ዘርፎች በዙሪያዋ ካሉት አካባቢዎች ተነጥላ ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበች ትገኛለች፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተማው የባቡር መሰረተ ልማት ዝርጋታ ተጠናቅቆ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የአስፋልት መሰረተ ልማቶችም እየተገነቡ ናቸው፣ በንግዱ ዘርፍም በየጊዜው ለውጦች እየታዩ ናቸው፡፡

የትምክህትና የጥበት ሃይሎች ህዝቡ በተለያዩ ወቅቶች የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የዚህችን አገር ሰላምና እድገት ለማጣረስ ሞክረዋል፤ ባይሳካላቸውም። የዚህችን አገር ሰላምና እድገት ስለማይፈልጉም የትኛውንም አጋጣሚ በመጠቀም ግጭት እንዲቀሰቀስ ምክንያት አነፍናፊዎች ሆነዋል፡፡

እስካሁን በተጓዝንበት ርቀት የአገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ፣ ፈጣን ዕድገት እየተመዘገበበትና የዓለም ህብረተሰብ የመሰከረለትን ልማት ለማስተጓጎል ያደረጉትን እንቅስቃሴ መነሻ አድርጎ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ከአገር ውጭና በአገር ውስጥ የሚገኙ ኃይሎች ትርምስን ዋና አጀንዳቸው አድርገው የአገሪቱ ሰላም እንዲደፈርስ፣ የተጀመረውን ልማትና ዕድገት ለማስተጓጎል በአስገራሚ ሁኔታ ያለ ተፈጥሯቸው ተቀናጅተው ያልወጠኑትና ያልጠነሰሱት ነገር የለም፡፡

ለወትሮው የኦሮሞን ህዝብ እንደ ህዝብ እውቅና ለመስጠት ፍላጎት የሌላቸው የፖለቲካ ሃይሎች ሳይቀሩ ነገሩን ሲያራግቡት ተስተውሏል፡፡ ሆኖም አጋጣሚውን እንደምክንያት ወስዶ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለመቀየር የሚደረግ እንቅስቃሴ ለሰላምና ልማት ወዳዱ የኦሮሞ ህዝብ የተሰወረ አይደለም፡፡ የትምክህትና የጥበት ሃይሎች ምንም ዓይነት ሂሳብ አንድ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

እንደሚታወቀው ጭፍን ጥላቻና ብዝሃነትን አለመቀበል የሁለቱም አስተሳሰቦች መገለጫ ባህርያቸው ነው፡፡ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው እንዲሉ ለሥልጣን ካላቸው ጥማት አንፃር ህዝብን ማፋጀት የዕለት ተዕለት ሥራቸው ነው።

አስተሳሰቦቹ እነማን ናቸው ብላችሁ ከጠየቃችሁ መልሱ ጠባብነትና ትምክህት ሆኖ ታገኙታላችሁ። ዛሬ ላይ የህዳሴ ጉዟችን ዋነኛ እንቅፋቶች መሆናቸው በተግባር የተረጋገጠው እነዚህ ሁለት አጥፊ አመለካከቶች በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየተመዘገበ ያለውን ፈጣን ልማት በማደናቀፍ በድህነት አዘቅት ተዘፍቀን እንድንቀር አልመው የጥፋት ኃይሎችን ሁሉ አስተባብረው የሞት ሽረት ትግል በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

እንደሚታወቀው በትምክህትና ጠባብነት አስተሳሰብ የተጠመቁ ኃይሎች ከሁሉ በላይ የቋንቋ፣ የባህልና የማንነት ብዝሃነትን አጥብቀው ይጠላሉ፡፡ የትምክህት ኃይሉ የእኔ ብሄር ብቻ ልዕለ ኃያል የሆነ፣ ቋንቋዬ፣ ባህሌና ማንነቴ ከሌላው የሚበልጥና የተለየ፣ ሁሌም ለመግዛት የተፈጠ ርኩ ነኝ ብሎ ያምናል፡፡

ከዚህ ጐን ለጐንም ሌላውን ብሔርና ዜጋ ተራና ርካሽ፣ ለመመራት እንጂ ለመምራት ያልተፈጠረ ቋንቋው፣ ባህሉና ማንነቱ የወረደ አድርጐ ይቆጥረዋል፡፡ የህዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነትንም አይቀበልም። ስለሆነም ብዝሃነትን ደፍጥጦ የራሱን አስተሳ ሰብ፣ ቋንቋና ባህል በሌላው ላይ ለመጫን የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡

ይህ ካልሆነ ሀገር ትጥፋ ህዝብም ይለቅ የሚል ህሳቤም የተ ጠናወተው ነው። ዴሞክራሲያዊ አንደነትና ብሄ ርተኝነትን የማይቀበል፣ የህዝቦች አንደነት ሳይ ሆን የግዛት አንድነት የሚያሳስበው ኃይል ነው፡፡ ከህዝብ ይልቅ ተራራና ወንዝ የሚናፍቅ ፀረ ህዝብ አመለካከት የተጠናወተውም ነው፡፡

የዚህ አስተሳሰብ ተቃራኒ የሆነው ጠባብነትን የተላበሰ ኃይል ደግሞ የእኔ እና ለእኔ ብቻ ብሎ የሚያስብ ነገሮችን ሁሉ በጠባብነት መነጽር የሚመዝን የዚህ ዓለም እውነታ የሆነውን ብዘሃነትን ተቀብሎና ተቻችሎ መኖር የእሬት ያህል የሚጎመዝዘው ኋላ ቀር አስተሳሰብ ነው። በጠባብነት ድንበር የታጠረ እንደመሆኑ ከሱ ብሄር ውጪ ያለ ህዝብ በአካባቢው እንዳይኖር ሌላ ቋንቋ እንዳይነገር ይሰብካል፡፡

እንግዲህ በእነዚህ ሃይሎች የጎራ መደበላለቅ ሲፈጠር አንዱ ሌላውን የውሸት ታፔላ ለጥፎ ሊደግፈው ይነሳል፡፡ ሆኖም ተግባሩ ከባዶነት በስተቀር ምንንም የማይወክል መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው የሚገባ ይመስለኛል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy