Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአንድነታችን መገለጫ!

0 248

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአንድነታችን መገለጫ!

                                                      ደስታ ኃይሉ

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ባንዲራ የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በህገ መንግስታቸው ላይ አንድ የጋራ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ለመገንባት የገቡት ቃል ማረጋገጫ ነው። ሁሉም የአገራችን ህዝቦች በአንድነት ሆነው በድህነት ላይ የተባበረ ክንዳቸውን የሚያሳዩበት መገለጫቸው ጭምር በመሆኑ ዜጎች በባንዲራው ስር ሆነው ድህነትን እየተዋጉ ነው።

ህዳሴያቸውን ለማረጋገጥም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ባንዲራ ስር ከትመዋል። ድህነትን ለመዋጋት በባንዲራው ስር የሚገኙት የሀገራችን ህዝቦች ባለፉት አስር ዓመታት ውጤት እያገኙ ነው። በባንዲራው ስር በመሆናቸው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ትሩፋቶች ተጠቃሚ ሆነዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ዜጎች ስለማደግና ስለመሻሻል እንጂ እንዳፉት መንግስታት ስለ አስተማማኝ ሰላም እጦት፣ በድህነት ስለመራቆትና ስለ መብት ጥሰቶች ማሰብ ዋነኛ ጉዳዩች አይደሉም። ባለፉት አስር ዓመታት በተከናወኑ ስራዎች እነዚህ ስኬቶች የአንድነታቸው መገለጫ እየሆኑ ነው።

ያለፉት ጨቋኝና አምባገነን ስርዓቶች የሀገራችንን ህዝብ በእጅጉ ጎድተውታል፡፡ ስርዓቶቹ ለስልጣናቸው ሲሉ የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎቶች በማፈን የራሳቸውን ወንበር ሲያደላድሉ ኖረዋል። የህዝቡን ተስፋ አሟጠው በመውሰድ ተስፋ ቢስ አድርገውታል።

ስልጣንን በዘር ግንድና በኢ-ዴሞክራሲያዊ መንገድ ተቆናጠው ህዝቡን አላላውስ ብለውት በድህነት አረንቋ ውስጥ እንዲዳክር ከማድረጋቸውም በላይ፣ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ አንገቱን ደፍቶ እንዲሄድ ማድረጋቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።

ለሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መራር ትግል ምስጋና ይግባውና ዛሬ ይህ ታሪክ ዳግም ላይመለስ ጓዙን ጠቅልሎ ተሰናብቷል። ህዝቦች በራሳቸው ፈቃድ ተስማምተው ባፀደቁት ህገ መንግስት ሰላማቸውን፣ ልማታቸውንና ዴሞክራሲያቸውን ያለ ገደብ እያጣጣሙት ነው። ይህ ተግባር የአገራችን ህዝቦች በባንዲራው ስር ሆነው ያጣጣሙት ያሉት ዘርፈ ብዙ ተግባር የእነርሱው መስዋዕትነት ውጤት ነው።

ህገ መንግሥቱ የህዝቦች የዘመናት ትግል ውጤት ነውና፤ ይህን የህዝቦችን የዘመናት ትግል ግምት ውስጥ በማስገባት ነበር ህገ መንግሥቱም ሊረቀቅና ሥራ ላይ ሊውል የቻለው፡፡ የኢትዮጵያ ባህል፡ ቋንቋ እና ታሪክ ማለት የኢትዮጵያ ህዝቦች ባህሎች፡ ቋንቋዎች እና ታሪኮች ተደምረው የሚፈጥሩት ነው፡፡ ይህ እውነታ በልዩነት የሚስተናገደው በፌዴራሊዝም ሥርዓት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታም አንድነትን እያረጋገጡ ነው፡፡ ይህ የህዝቦች ጥቅል አውነታ የመጣው በባንዲራው ስር መሆኑ አይካድም፡፡ ባንዲራው ደግሞ የህገ መንግስቱ ውጤት ነው፡፡

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ ሶስት ላይ ባንዲራውን አስመልክቶ ባንዲራው ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሃል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በመሃሉ ብሔራዊ አርማ (ኮከቡና ጨረሮቹ) እንደሚኖሩት በግልፅ ተቀምጧል። የኢትዮጵየያ ህዝቦች ህገ-መንግስቱን ተከትሎም በዚህም በ1988 ዓ.ም. በቁጥር 16/1988 “የሰንደቅ ዓላማና አርማ አዋጅ” እንዲወጣ አድርገዋል።  

ታዲያ ይህን ዕውነታ በሚገባ የተገነዘቡት የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች የሰማዕታቱን አደራ ተቀብለው በተለይም ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በሰንደቅ ዓላማው ጥላ ስር ተሰባስበው አያሌ ሀገራዊ ተግራትን ፈፅመዋል። ዙሪያ መለስ ዕድገትን እያስመዘገቡም ዛሬ ላይ መድረስ ችለዋል። ሰንደቅ ዓላማውን የማንነታቸው መገለጫ በማድረግም በአንድነትና በእኩልነት ዘልቀዋል።

የኢፌደሪ ሰንደቅ ዓላማ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብዝሃነት መገለጫ ነው። አደሲቷ ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም ሃይማኖቶችና ቋንቋዎች የሚገኙባት ናት። ባለፉት ዓመታት ይህን ልዩነት እንደ ጥንካሬ በመውሰድ የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት የተፈጠረው ብሎም ብጥብጥና ሁከት ውስጥ እንዳትገባ ማድረግ የተቻለው ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚችልና ዘለቂና ቀጣይነት ያለው ልማት ማረጋገጥ ስለተቻለ መሆኑ እሙን ነው። ለዚህም ደግሞ ዋስትናው ህገ-መንግስቱ ነው።

እርግጥ በህገ-መንግስቱ ሳቢያ ሁሉም ዴሞክራሲያዊ መብቶች (የግልና የቡድን) በተቀናጀ መልኩ አንዱ የሌላውን በሚደግፍ አኳኋን ተመልሰዋል። በዚህም ብዝሃነትን ለማስተናገድ ችግር የነበሩ በርካታ ጉዳዩች ሊመለሱ ችለዋል። ይህም የአገሪቱ ልማት ላለፉት 16 ዓመታት ያለ አንዳች ሳንካ ፈጣንና ተከታታይ በሆነ መንገድ እንዲቀጥል አድርጓል።

እርግጥ ባለፉት ዓመታት ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ትሩፋት ሊገኝ የቻለው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግስት እየተመሩ ብዝሃነታቸውን የጥንካሬያቸው ምንጭ አድርገው በሰንደቅ ዓላማው ስር ተሰባስበው ሌት ተቀን በመስራታቸው ነው።

በአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ልዩነቱን የጥንካሬው መሰረት አድርጎ በመቁጠር በባንዲራው ስር ተጠልሎ ድህነትን ለማሸነፍ ላለፉት 10 ዓመታት በፅናት ታግሏል። የትግሉ ባለቤትም ሆኗል።

በባንዲራው ስር በመሆን በአንድነት ብዝሃነቱ የድሉ ምንጭ እንጂ የልዩነቱና የመፋለሱ ምክንያት እንዳልሆነ ላለፉት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዓመታት በተግባራዊ ክንዋኔው ያረጋገጠው ይህ ህዝብ፤ ነገም ይህን ጥንካሬውን አጠናክሮ መቀጠሉ አጠያያቂ አይሆንም።

ይሁንና ከዚህ የህዝቡ ፍላጎት ውጪ በሆነ መንገድ በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገፆች ፀረ-ሰላም ሃይሎችና እዚህ ሀገር በተጨባጭ በመምጣት ላይ ያለውን ለውጥ የማይፈልጉ የውጭ ሃይሎች በሰልፍ ሰበብ የሀገራችን ባንዴራ ለማኮስመን ጥረት እያደረጉ ነው። ሆኖም የሚሳካላቸው አይሆንም። ምክንያቱም የህዝቦች አንድነትና እኩልነት የሆነውን መሰረታዊ ጉዳይ አለመቀበል በመሆኑ ከህገ መንግሰቱ ጋር ስለሚጋጭ ነው። ከህገ መንግስቱ ጋር የሚጋጭ ደግሞ መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ሁሉም ያውቀዋል። የህገ መነግሰተ ባለቤት ከሆኑት የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር መጋጨት ብቻ ነው።

የኢፌዴሪ ባንዲራ የሀገራችን ህዝቦችና ሃይማኖቶች አንድነትና እኩልነት መገለጫ በመሆን ዜጎች በስሩ ተሰባስበው ዛሬ ላይ ለተገኘው ሁለንተናዊ ለውጥ መሰረት ነው።

ስለ አገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት ሲነሳ፤ ጉዳዩ አንድነት ፈጣን ልማትንና የጋራ ተጠቃሚነትን ከማስገኘት አኳያ ያለው ፋይዳም ከግምት ውስጥ ገብቶ ነው። ሌላ ምንም ዓይነት ምክንያት ኖሮ አይደለም። ይህ በመሆኑም የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መገለጫ ባንዲራው መሆን ችሏል። በዚህም ሳቢያ ባንዲራውን አለማክበር ህገ መንግስቱን መቃወም መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ግንዛቤ ተወስዷል።

በየትኛውም አገር ውስጥ በቡድንም ይሁን በአገር ደረጃ ከአንድነት ውጪ የሚከናወን ምንም ዓይነት ነገር የለም። አንድነት ሲኖር ፈጣን ልማትና የተሻለ አቅም መፍጠር ይቻላል። አንድነት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የህዝቦች ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ የሚችለው እኩልነትና መፈቃቀድ ሲኖሩ ነው። ይህ አንድነት የሚገለፀው ደግሞ በባንዲራው ጥላ ስር መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy