Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዋልታና ማገር

0 290

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዋልታና ማገር

                                                          ታዬ ከበደ

የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዛሬ በህገ መንግስቱ ዜጎች ለአዲስ ህይወት ማበብ ተስፋ ሰንቀው፣ በፀና ህብረት ላይ ቆመው፣ እጅ ለእጅ ተያይዘው ኑሮን ማጣጣም ይዘዋል፡፡ ንፁህ አየር መማግ፣ በሰላም ገብቶ መውጣት፣ በነፃነት መንቀሳቀስን ችለውበታል፡፡ ለዚህ መብቃት የተቻለው ደግሞ ሺህዎች በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት ነው፡፡ በውጤቱም በመላ አገሪቱ ሰላም ተገኝቷል፤ የልማት መስመር ተይዟል፤ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በፅኑ መሠረት ላይ እየቆመ ነው፡፡

ላለፉት 26 ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ጥቅሞቻቸውን በማጎልበት አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በአንድነት ተነሳስተዋል፡፡ በብዝኃነት ላይ መሠረቱን የጣለው አንድነት ለህዳሴውም ስኬት መገለጫ ነውና የዜጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ህገ መንግሥት ጠብቆ ለማቆየት ሁሉም በፅናት ቆሟል፡፡ በመላ ኢትዮጵያ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩበት፤ ለዴሞክራሲያዊ አንድነት መሠረት የተጣለበት፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት፤ ውበትና ህብረት የታየበት ብሎም የሥልጣን ባለቤት የተረጋገጠበት፤ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉዞ የተጀመረበት መሠረቱ ይኸው ህገ መንግሥት ነው፡፡

የህገ መንግሥቱ ድሎችና ውጤቶች ከመቼውም በላይ ተስፋፍተው፤ የዜጎች ማንነትና ባህላዊ እሴቶች ጎልተው ወጥተው፤ መልካም ተሞክሮዎችም ይበልጡን ጎልብተው የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ ሆነው እንዲቀጥሉ ዜጎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መርጠው በላኳቸው ወኪሎቻቸው አማካኝነት ህገ መንግሥቱ ፀድቆ ሥራ ላይ ከዋለ ሁለት አሥርት ዓመታትን ተሻግሯል፡፡

በእነዚህ ጊዜያት የክልሎችን እኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል በተለይም በልማትና ዕድገት አፈጻፀም ረገድ በጎ እርምጃዎች ተወስደው መልካም ውጤቶች ታይተዋል፡፡ በህገ መንግሥት በተደነገገው እኩል የመልማት መብት በመጠቀም በሁሉም ክልሎች በተነፃፃሪ ፈጣን የሚባል ልማትና ዕድገት ተመዝግቧል፡፡

ህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት ከአገሪቱ ተጨባጭ ታሪካዊ ሁኔታ በመነሳት በህገ መንግሥቱ ተደንግጎ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡ ሕብረ ብሄራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ ያለፉት አፋኝ መንግሥታት የቀበሩትን የማንነትና የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነት ጥያቄን በአስተማማኝ ደረጃ መመለስ ችሏል፡፡

በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለማስቀጠልና ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ቃል ኪዳን ያሰሩበትን አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በህዳሴው እየተቀላጠፈ ይገኛል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ባልተማከለ አስተዳደር ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ማዕቀፍ ውስጥ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አስችሏል፡፡

በዚህም ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ተሳትፏቸውና በየደረጃው ተጠቃሚነታቸው ጎልብቷል፡፡ አካባቢያቸውንም በማልማት ለአገር ብልፅግናና እድገት ከፍተኛ ደርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ የክልሎችን የእኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አኳያ ደግሞ የልማትና ዕድገት አፈጻፀም በክልሎች እኩል ተጠቃሚነት እየተፈፀመ መሆኑን የሚያረጋግጥ እውነታ ነው፡፡

የክልሎችን የእኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አንፃር ልማታዊው መንግሥት ግልፅ የሆኑ ምጣኔ ሀብታዊ ህጎችን፣ የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ነድፎ በየአካባቢው ተጨባጭ እቅድ እየተመነዘሩ የሚፈፀሙበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በአፈጻፀም ሂደት የተገኙ በጎ ልምዶችም እየተቀመሩ በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎችና ለምልዓተ ሕዝቡ የሚደርስበት ስልቶች ተቀይሰዋል፡፡

የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመተግበር ዙሪያ የሚያጋጥሙ ማነቆዎች የሚለዩበትን የአሠራርና የአደረጃጀት ጥያቄዎች ካለፉት ልምዶች በመነሳት እንዲፈተሹና እንዲስተካከሉ በማድረግ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የላቀ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ ይገኛል፡፡

በህገ መንግስቱ የስልጣን ምንጭ ማዕከላዊ መንግስት ሳይሆን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መሆናቸው ተገልጿል። ለራሳቸው በቂ ስልጣን አስቀርተው ለጋራ ጉዳይ የሚያስፈልግ ስልጣንን ለማዕከላዊ መንግስት ቆርሰው ሰጥተዋል። ታዲያ እዚህ ላይ ኢፌዴሪ ህገ-መንግስት ልየ ባህሪያት ያሉት መሆኑን መገነዘብ ያሻል።

ህገ መንግስቱ የብሔሮች የብሔረሰቦችና የህዝቦች እንደ መሆኑ መጠን፤ የህገ-መንግስት የበላይነትን ለማረጋገጥ ህገ-መንግስቱ በማናቸውም የመንግስት አካላት ብቸኛ ውሳኔ ሊሻሻል እንደማይችል በማስቀመጥ አንዱ የሌላው የበታች እንዳይሆን ይከላከላል።

የክልሎች ሃሳብ በፌዴራል ምክር ቤቶች እንዲወከሉ በማድረግም በፌዴራል የጋራ ጉዳዮች ውሳኔ አሰጣጥ ላይ እንዲሳተፉ አድርጓል። ህግ- መንግስትን የመተርጎም ስልጣን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በመሰጠት፤ በህገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ኮሚሽን የውሳኔ ሃሳብ አቅራቢነት የሚወሰንበትን ስርአት ህገ-መንግስቱ ዘርግቷል።

በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት የተመሰረተው ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም በመሆኑ በግዛት ላይ የሰፈሩ ብሔራዊ ማህበረሰቦች የራሳቸውን ጉዳይ በሚመለከት የራስ አስተዳደርና የጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ አስተዳደር ስልጣን እንዳላቸው ያረጋግጣል።

ሌላኛው የህገ መንግስቱ የተለየ ባህሪ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን መሰረት ያደረገ ፌዴራላዊ የፖለቲካ ስርዓትን ማጎናፀፉ ነው። ይህም የፖለቲካዊ ስርዓቱ ዋልታና ማገር ነው ማለት ይቻላል። ያለመፈቃቀድ አንድነት ሊኖር ስለማይችል፤ እንዲህ ዓይነቱ በህዝቦች ፈቃድ ላይ ብቻ የተመሰረተ አካሄድ የህገ መንግስቱን ጥንካሬ የሚያሳይ ነው።

ህገ መንግስት የመንግስት ስልጣን ይዘት ምን እንደሚመስል፣ ስልጣን እንዴት እንደሚደራጅና እንደሚከፋፈል፣ በስልጣን አካላት መካከል ስለሚኖረው ግንኙነት፣ በመንግስትና በዜጎች በህዝብ መካከል ስለሚኖረው ትስስር፣ መንግስት ሊከተላቸው ስለሚገቡ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መርሆዎች የሚገልፅና በሌሎች ወሳኝ የህዝቡን ህይወት የሚነኩ ጉዳዩች ላይ የሚያጠነጥን ሰነድ ነው። እናም ህገ መንግስቱን በማክበር የሚፈጠሩ ማናቸውንም ችግሮች በዚያው  ማዕቀፍ ውስጥ ለመፍታት ያስችላል።

በመሆኑም የህገ መንግስቱን የበላይነት ማረጋገጥ ማለት የህገ መንግስቱ ባለቤቶች የሆኑት ሕዝቦችን ፈቃድና ፍላጎትን ዕውን ማድረግ ነው። ህገ መንግስትንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓትን በስራ ላይ የማዋል ሚና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ዋነኛ አካል አካል በመሆኑ፤ የህገ-መንግስቱ መከበር የሁሉም ዜጎች፣ የመንግስት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሌሎች የዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ተዋንያንን ፍላጎት ማረጋገጥ ነው። ስለሆነም ከዚህ አኳያ ምንም እንኳን እስካሁን ድረስ የተከናወኑት ተግባራት ውጤታማ ናቸው። እነዚህ ሁኔታዎች ህገ መንግስቱ ምን ያህል የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዋልታና ማገር እንደሆነ የሚያሳዩ ይመስሉኛል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy