በመላው ሀገሪቱ ለ10 ተከታታይ ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበረውና የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያበስረው የ2010 አዲስ ዓመት አቀባበል የፍቅር ቀንን በማክበር በዛሬው እለት ተጀምሯል።
በዓሉም “በፍቅር የተሳሰረ ዝህብ እናት ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል ነው ተከብሮ የዋለው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በዛሬው እለት አዲስ ዓመት መልካም ምኞት መግለጫን ጨምሮ የከንቲባው ፊርማ ያረፈበት ካርድ እና አበባ በማበርክት በዓሉን አክብሯል።
የመልካም ምኞት መግለጫ ካርድ እና አበባ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከደረሳቸው መካከልም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ አንዱ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በዚሁ ጊዜ፥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ለስጦታው አመስግነው፤ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የመልካም ምኞት መግለጫ ካርድ እና አበባ የደረሳቸው የፌዴራል እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተወካይ ሀጂ ከድር ሁሴን፥ “ይችህ የፍቅር ቀን ኢትዮጵያውያን ዘንድ የጠበቀ ፍቅር እንዲኖረን የምታደርግ የመልካም ቀን ናት” ብለዋል።
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼክ መሀመድ ሸሪፍ በበኩላቸው፥ “መሪዎች ለተመሪዎች እና ተመሪዎችም ለመሪዎች የሚሰጡት ፍቅር ለሀገር እድገት ወሳኝ ነው” ብለዋል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሮ ዳግማዊት መጎስ፥ የከተማ አስተዳደሩ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው የእንኳን አደረሳቹ መርሃግብሮችን ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
“በመልካም ምኞት መግለጫ ፖስት ካርዱ ላይ እንዳስቀመጥነው አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያን ከፍታ እውን የምናደርግበት ነው” ሲሉም ወይዘሮ ዳግማዊት ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፍቅር ቀንን ለትምህርት ሚኒስትር፣ ለሴቶች እና ህጻናት ሚኒስትር ፣ለመንግስት ኮሚኒኬሽን ጎዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር እና ሌሎችም ሚንስትሮች እና የከተማዋ ነዋሪዎች አበባ እና ፖስት ካርድ በመስጠት አክብሮ ውሏል።
በሰርካለም ጌታቸው