Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉና የህዝቡ ተሳትፎ

0 492

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉና የህዝቡ ተሳትፎ

                                                      ቶሎሳ ኡርጌሳ

ዛሬ በሀገራችን ውስጥ በፌዴራል፣ በክልል፣ በዞን፣ በወረዳና በሌሎችም የአስተዳደር እርከኖች ላይ ላይ የሚገኙና በኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር የተሳተፉ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ማስረጃ እስከቀረበባቸው ድረስ በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበት ቁርጠኛ አሰራር ተዘርግቷል። ትግሉም በያዝነው ዓመት ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መንግስት ገልጿል። ታዲያ ለዚህ ስኬት እውን መሆን የሚችለው፤ ወንጀለኞችን በማጋለጥ የሚታወቀው የሀገራችን ህዝብ በተግባሩና በአስተሳሰቡ ዙሪያ እንደ ሌሎቹ ጊዜያት የላቀ ሚና በመጫወት የዜግነት ግዴታውን ሲወጣ መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም።

በየትኛውም ሀገር ውስጥ ያለ ህዝቡ ተሳትፎ እውን የሚሆን ዘመቻ የለም። ህዝቡ ያልነካቸው ማናቸውም ተግባራት እውን ሊሆኑ አይችሉም። እናም ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት ህዝቡን በሰላማዊ መንገድ የማታገል ሂደትን መከተል ያስፈልጋል።

ህዝቡ እዚህ ሀገር ውስጥ በሚከናወኑ መንግስታዊ ስራዎች የሚያሳየው ያለመርካት ስሜትና በዚህም ሳቢያ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ለሰላማዊ ትግል በር የተከፈተለት መሆኑን ከመገንዘብ የመጣ ነው። ታዲያ ይህን ስሜት በሰከነና በተደራጀ እንዲሁም ለሀገርና ለህዝብ በሚጠቅም ስሜት መምራትና የሚጠናከርበትንም መንገድ መቀየስ ያስፈልጋል። በተለይም ይህን ህዝባዊ ስሜት ለፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ዘመቻው ላይ በማዋል ውጤት ማምጣት የሚቻል ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፈቃዳቸው ያፀደቁት ህገ መንግስት፤ ማንኛውም ዜጋ ጥያቄዎችን በተናጠልም ሆነ በህብረት የሚያቀርብበትን አሰራርና መብት እንዳስቀመጠ በሚገባ ይገነዘባሉ። በተለያዩ ጊዜያትም ይህን መብታቸውን እየተጠቀሙ ዛሬ ላይ ደርሰዋል።

ዳሩ ግን ይህን መብታቸውን በሰላማዊ ትግል የሚያጠናክሩነትን ሁኔታ ማመቻቸትና ለዚህም የህዝቡን ፍላጎት ከፀረ-ሰላም ኃይሎች ድብቅ አጀንዳ ጋር ነጥሎ በመመልከት ሰላማዊ ትግሉን ማጎልበት ከማንኛውም ጊዜ በላይ ጊዜ ዛሬ ትርጉም ያለው ስራ ማከናወን ያስችላል። የጠያቂውን ህዝብ ስሜት በአግባቡ በመገንዘብ የሚያቀርባቸውን ችግሮች በፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ዘመቻው ላይ ማዋል ከተቻለ ውጤቱ የትየለሌ ሊሆን እንደሚችል ግልፅ ይመስለኛል። በአንድ በኩል ዴሞክራሲያዊ መብትን ያጠናክራል፤ በሌላ በኩልም የህዳሴ ጉዟችን ደንቃራ ሆኖ ሊያደናቅፈን የሚችለውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባርን መቅረፍ ያስችላል።

ርግጥ ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማቅረብና ህገ መንግስታዊ መፍትሔ መሻት የዜጎች ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ነው። ታዲያ ይህ ዴሞክራሲያዊ መብት በፅንፈኞች እንዲሁም በፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ሃይሎች ተጠልፎ ህገ ወጥ በሆነ መስመር እንዳይጓዝ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። እንደሚታወቀው ፅንፈኞችና ፀረ-ሰላም ሃይሎች ዛሬ ጠያቂ ለሆነው ህዝብ ያስገኙለት አንዳችም ዓይነት ፋይዳ የለም።

እነዚህ ሃይሎች ሰላሙን አጥቶ የየዕለት ተግባሩን እንዳያከናውን እንዲሁም በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ አማካኝነት በተለይም ባለፉት 10 ዓመታት የተገኙትን ስኬቶች ከማስተጓጎል ውጪ ያመጡለት ነገር የለም። ይህ ሃቅ ከጠያቂው ህዝብ የሚሰወር አይደለም።

በፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ዘመቻው ላይ ይህን ጠያቂ ህዝብ በበለጠ ማሳተፍ የትናንት የልማት ስኬቶችን አቅቦ ከመቀጠል እንዲሁም መጪውን የህዳሴ ጉዞ ለማረጋገጥ ፋይዳው የላቀ ነው። ይህን ደግሞ ጠያቂው ህዝብ በሚገባ ያውቀዋል። እንደሚታወቀው የሀገራችን ህዝብ የዛሬ 15 ዓመት በፊት የተቀጣጠለው የተሃድሶ ንቅናቄ በመንግስት ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራ ፈጣን በሆነ ሁኔታ የተቀየሰና ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደነበር የሚያውቅና ለዚህ ዕውን መሆንም የተንቀሳቀሰ ነው። ለውጥ ማምጣትም ችሏል። የለውጡን ትክክለኛነትና ጥንካሬን ለማረጋገጥም በ50 ዓመት ታሪካችን ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የድርቅ አደጋ አጋጥሞን፤ ይህ ነው የሚባል የውጭ ድጋፍ ሳይገኝ በራስ አቅም መቋቋም መቻሉ ማሳያ ይመስለኛል።

በተለይም በሶስተኛው ሚሊኒየም መባቻ ባሉት 10 ዓመታት ውስጥ በከተሞች ውስጥ የኢንዱስትሪ ልማት መሰረቶችን ማስፋፋት መቻሉ ከህዝቡ የሚሰወር ዕውነታ አይመስለኝም። በተለይም በከተሞች ውስጥ እየተከናወኑ ያሉት የአነስተኛና ጥቃቅን ፕሮግራሞች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው። ምንም እንኳን በከተሞች ያለው የተጠቃሚነት ሁኔታ በተለያዩ ስንክሳሮች ምክንያት የሚፈለገውን ያህል መጓዝ ባይቻልም፣ ከፕሮግራሞቹ በተለይም ወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ብዙ ርቀት መጓዝ እንደተቻለ ህዝቡ በሚገባ ያውቃል።

ከህዝብ የተሰወረ ነገር የለምና ባለፉት 10 ዓመታት ዜጎች ከልማቱ በፍትሐዊ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማህበራዊ መስክ ውጤት የተገኘባቸው ስራዎች መከናወናቸውን የሀገራችን ህዝብ የሚዘነጋቸው አይደሉም።

በተለይ በትምህርት፣ በጤና እና በመሰረተ-ልማት አቅርቦት ዘርፍ የተከናወኑት ወሳኝ ስራዎች ለዚህ አባባል ሁነኛ አስረጅዎች ናቸው። ከእነዚህ ማህበራዊ መስኮች ህዝቡ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን፣ በአኗኗር ዘይቤው ላይም ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ጥረት ተደርጓል። ስኬቶችም ተመዝግበዋል።

እነዚህ ስኬቶች የተገኙት ህዝቡ ባደረገው ርብርብ ነው። ስኬቶቹ በኪራይ ሰብሳቢዎች ምክንያት ግለታቸውን ጠብቀው እንዳይጓዙ እንዲሁም መጪውን ዘመን የከፍታ ማማ ላይ ሆኖ እንዳይመለከት የጠራራ ፀሐይ ግርዶሽ እንዲሆኑበት አይሻም። እናም ይህን ህዝብ በፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር ላይ በበለጠ ሁኔታ ማሳተፍ ውጤቱ የህዳሴውን ችቦ በአስተማማኝ ሁኔታ ማቀጣጠል መሆኑ አያጠያይቅም።

ርግጥ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባርና አስተሳሰብ በአንድ ጀንበር የሚቀረፍ አይደለም። ትግልንና የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ማረም የሚጠይቅ ነው። ሆኖም የልማቱና የህዳሴው ዋነኛ ተዋናይ የሆነው ህዝብ በፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ዘመቻው በቁርጠኝነት እስከተሳተፈ ድረስ ችግሩን መቅረፍ የማይቻልበት ምክንያት አይኖርም።

ሀገራችን በምትከተላቸው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራተጂዎች በሁሉም ዘርፎች የተገኙት መልካም ውጤቶች ለህዳሴ ጉዟችን ፅኑ መሰረት እየጣሉም ናቸው። እናም ፖሊሲዎቹን ተመርኩዞ የተዘጋጀው ሁለተኛው የልማት ዕቅድ የሶስተኛ ዓመት ትግበራ በኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር መጓተት አይኖርበትም። ይህን እውን ለማድረግም ህዝቡን የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ዘመቻው ቀዳሚ ተዋናይ እንዲሆን በነቂስ ማንቀሳቀስ ያስፈልጋል።

በመሆኑም ህዝቡን ባሳተፈ መንገድ ችግሩን ለመቅረፍ የሚደረገው ትግል በዋነኛነት ሀገራችን በቅርብ ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር እንድትሆን ያስችላታል። እናም በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋን በመከላከል ረገድ የህዝቡን ተሳትፎ ማሳደግ የችግሩን መፍትሔ የማግኘት ያህል ዋጋ ያለው መሆኑን መገንዘብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy