ethiopian news

Artcles

የወሰን ግጭቱ፤ ከመንስኤና ውጤቱ አንፃር

By Admin

September 28, 2017

የወሰን ግጭቱ፤ ከመንስኤና ውጤቱ አንፃር

መዝገቡ ዋኘው

 

ሀገራዊ ሰላምን የመጠበቅና የማስጠበቅ ስራና ኃላፊነት በመንግስት ላይ ብቻ የሚጣል አይደለም፤ በዋነኛነት የሕብረተሰቡ ኃላፊነት ነው፡፡ መንግስት ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮች ሲፈጠሩ የአደጋው ስፋትና ጥልቀት አሰሳቢ ሁኖ ሲገኝ ጣልቃ በመግባት ሰላምን በማስከበረ መረጋጋት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ በቅርቡ በሶማሌ ክልልና በኦሮሚያ በወሰን ጉዳይ የተነሳው አለመግባባት ደረጃው እየጨመረ፤ መልኩን እየቀየረ በመምጣቱ የፌደራሉ መንግስት ጸጥታና ሰላምን ለማስከበር የሚገባበትን ሁኔታ ፈጥሮአል፡፡

ጉዳዩ በየእለቱ መልኩን እየቀየረ ከመሄዱ በፊት ችግሩን ለመፍታት የሁለቱን ክልላዊ መንግስታት መሪዎች የፌደራል ሚኒስትሩ ሰብስበው በማነጋገር ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ለማድረግ ጥረት ያደረጉ ሲሆን፤ በሂደቱም ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች ተሰተውለዋል። ዳግም ሁኔታው የተለወጠው በወሰኑ አካባቢ ተደጋጋሚ ግጭቶች በመከሰታቸው ምክንያት ለበርካታ ዜጎች ሕይወት መጥፋትና የዜጎችንም መፈናቀል አስከትሎአል፡፡

ይህን የመሰለው ክስተት የሚያጋጥም ቢሆንም ሊፈታ የሚገባው በሰላማዊ ውይይትና ንግግር ብቻ መሆን ነበረበት፡፡ ይህንን ሁኔታ ሆን ብሎ እንዲባባስና ከመንገድ እንዲወጣ ያደረጉት ግለሰቦች በምንም መልኩ ከተጠያቂነት ሊወጡና ሊያመልጡ አይችሉም፡፡ ለረዥም ዘመናት በፍቅር፣ በመቻቻልና በመከባበር ተጋብቶና ተዋልዶ የአንዱን ቋንቋ ሌላው እየተናገረ የኖረውን ሕዝብ ማባላትና ደም ማፋሰስ ጤነኛ ሰዎች ያደርጉታል ተብሎ አይታመንም፡፡

ቀጠናው ራሱን የቻለ የተለየ ችግር ያለው ከመሆኑም አንጻር በስፋት ሊመረመሩ የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ይሄን ከስሩ የማጣራትና የመፈተሹ በተገኘውም ተጨባጭ ማስረጃ መሰረት እርምጃ የመውሰዱ ግዴታና ኃላፊነተ የፌደራል መንግስት ነው የሚሆነው፡፡ ጉዳዩ አንዱ ሌላኛውን በመወንጀል ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ በእርግጥ ከዚህ ግጭት ጀርባ የክልላዊ መንግስታቶቹ ታጣቂዎች ብቻ ናቸው ወይ ያሉት? የሚለውም በጥልቀት መፈተሸ አለበት፡፡

ለምን ቢባል ቀድሞ በነበሩት ረዥም አመታት እንዲህ አይነቱ የገፋ ችግር አልተከሰትም ነበር፡፡ ጥፋትና ግድያ ፈጸሙ የሚባሉት የሶማሌ ክልል ታጣቂዎች ናቸው ወይንስ የእነሱን ስም በመጠቀም ምናልባትም ዩኒፎርም በመልበስ ሌሎች ኃይሎች (የአልሻባብና የኦብነግ ታጣቂዎች) የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት እንዲፈጠር፤ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዲጠፋ፤ በዚህም ለእነሱ የተደላደለ የመፈንጪያ መሬት ለማግኘት የተጠቀሙበት ስልት ይሆን? ብሎ በምናልባታዊነት መፈተሽም ተገቢ ነው፡፡

ኢትዮጵያን በቀንደኛ ጠላትነት የሚፈርጃትና በእስከአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ የመግቢያ ቀዳዳ ያላገኙት አልሻባብ እና ኦብነግን የመሳሰሉ የሽብር ድርጅቶች አዲስ ስልት ነድፈው እየተጠቀሙበት ቢሆንስ? የሌሎች የውጭ ኃይሎች እጅ በአባባሺነትና በአቀጣጣይነት ከጀርባ ቢኖሩበትስ ብሎ መጠየቅ ለሀገር ሕልውና ሲባል ግድ ይላል፡፡

በዚህ ቀጠና ውስጥ የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት የኢትዮጵያን ፈጣን ልማትና እድገት ለመግታት በተለይም የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ስራ ለማጨናገፍ በስትራቴጂ ደረጃ የረዥም ግዜ እቅድ ነድፈው የሚንቀሳቀሱት ግብጽና ኤርትራ ይህንን የግጭቱን አካባቢ አይጠቀሙበትም ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ይሄንንም መፈተሽ ግድ ይለናል፡፡

ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሶማሌውም ሆነ ኦሮሞው ረዥም  ዘመናት አብረው የኖሩ ከመሆናቸው አንጻር ቀድሞ ይታይ እንደነበረው መጠነኛ አለመግባባቶችና ግጭቶች ቢፈጠሩም በቀላሉ በሽማግሌዎች ሊፈቱ ይችሉ የነበሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የግጭቱ መጠን በገዘፈ ደረጃ መከሰቱ የዜጎችን ሞትና ከመኖሪያቸው መፈናቀልን ማስከተሉ ሲታይ የግድ ከእነዚህ ታሳቢ ግምቶች በመነሳት የእይታ አድማሳችንን አስፍተን መመልከት ይጠበቅብናል፡፡ ለምን ሆነ? ለምን ተደረገ? ገፊ ምክንያቶቹ ምንድናቸው? የሚሉትን ደጋግሞ መመርመር ግድ ይላል፡፡ ያለው  ሁኔታ ከሕዝብ መጋጨት፣ ከሰላም ማጣትና መደፍረስ መጠቀም የሚፈልጉ ኃይሎች ስለመኖራቸው አመላካች ነው፤ በምንም መልኩ ወደዚህ ደረጃ ማደግና መስፋት ያልነበረበት ሁኔታ ነበርና፡፡

በአሁኑ ሰአት ግጭቱን ለመፍታት መንግስት መከላከያና የፌደራል ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል በስፍራው እንዲገባ አድርጎአል፡፡ የማረጋጋት፣ የተፈናቀሉትን የመርዳትና የመልሶ ማቋቋም፣ በሀገር ሽማግሌዎች የማስማማት፣ ከሕዝቡም ጋር በየደረጃው ውይይቶችን በማድረግ ችግሩን ለመፍታት ከፍተኛ ስራ በመሰራት ለይ ይገኛል፡፡

የተከሰተውን ሁኔታ መነሻ በማድረግ በተለይ በሶማሌ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ የተሰጠው እጅግ ኃላፊነት የጎደለው መግለጫ በእርግጥ እነዚህ ሰዎች ክልልና ሕዝብ የሚመሩ ናቸው ወይ የሚለው ጥያቄ የሕዝብ መነጋገሪያ ሁኖ እንዲከርም አድርጎአል፡፡ የሁለቱም ክልሎች ኃላፊዎች የተሸከሙት የሕዝብ አደራና ኃላፊነት እንደመሆኑ መጠን የፌደራል መንግስት ሳይገባም እርስ በእርስ ተገናኝተው ተነጋግረው ችግሩን ሊፈቱት ይገባቸው ነበር፡፡ ይህም ካልተቻለ ጉዳዩን በጨዋነት በስነስርአት ፈትሸው የፌደራሉ መንግስት በጋራ አነጋግሮ የሚፈታው ጉዳይ ነበር የሚሆነው፡፡

በየክልሎቹ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮዎች የወጡት መግለጫዎች ይባስ ጉዳዩን ወደከረረ ጫፍ እንዲነጉድ ያደረጉ ነበሩ፡፡ ይሄንን መሰረትና ዋቢ ያደረገው የውጭው ሚዲያ የተፈጠረውን ችግር የባሰ የማቀጣጠል ሰራ ሰርቶአል፡፡ ይህ አዝማሚያ ሀገሪቱን ወደ ቀውስ ውስጥ ለመክተት በታቀደ መልኩ እየተሰራ ያለስራ ለመኖሩ በግልጽ አመላካች ነው፡፡

ትላልቅ የተባሉትን ሀገራት ለመፍረስና ለመበታተን ያበቁአቸው በትንሹ ሊቆም የሚችለውን ችግር እያሰፉ፣ ሕዝቡን እያነሳሱ፣ ጥላቻ እየዘሩ፣ እርስ በእርሱ እያፉጁና እያባሉት በሚዲያ መሪነት የተጀመረው የማዋጋት ስራ በሕዝብ እልቂት ደም መፋሰስና ስደት በሀገራት መፈራረስ ተደመደመ፡፡ ይህ አይነቱ እኩይ የአቀጣጣይነት ስራ ለሕዝብም ለሀገርም ሕልውና አይበጅም፡፡ ተጎጂው ሕዝብና ሀገር ናቸው፡፡

አለም አቀፉ ሚዲያ እንዲሁም አክራሪው ጽንፈኛ ኃይል መላ ትኩረታቸውን በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ ከወሰን ጋር ተያይዞ በተከሰተው ግጭት ላይ በማድረግ የበለጠ ብጥብጥና ግጭት የሚባባስበትን ሁኔታ ለመፍጠር ሲዳክሩ ከርመዋል፡፡ የበለጠ መተራመስ፣ ግጭትና ደም መፋሰስ እንዲፈጠር ዛሬም በስፋት በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ምንም ተፈጠረ ምን የሀገሩን ሰላምና ደሕንነት ነቅቶ የሚጠብቅ ሕዝብና መንግስት ስላለ የአሰቡትን ሊያሳኩ አይችሉም፡፡

ችግሩን የማጉላት ስራ ዛሬም በተለያየ የውጭ ሚዲያዎች በአክራሪውና ጽንፈኛው ኃይል ድረገጾች እንዲሁም በፌስቡክ አማካኝነት እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ ይህ የሀገርን ሰላምና መረጋጋት የማደፈርስ ስራ ባለቤት ያለው መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ለኢትዮጵያና ለሕዝብዋ በምንም መልኩ አይበጅም፡፡ የመፍትሄው አካል ሳይሆኑ ዋነኛ ተልእኮአቸው ሀገሪቱን ትርምስ ውስጥ መክተት ስለሆነ ሊመከት ይገባዋል፡፡ በሀገር ሕልውና ላይ የተነጣጠረ አደጋም ነው፡፡

ግጭቱ በምንም መልኩ የሁለቱን ክልሎች ወንድማማች ሕዝቦች አይወክልም፡፡ ሁለቱም ሕዝቦች ለዘመናት የዘለቀ የአብሮነትና የመቻቻል እሴት ያላቸው በመሆኑ ግንኙነታቸው በጊዜያዊ ችግር ሳቢያ አይደናቀፍም፡፡

ዛሬም የክልሎቹ ሚዲያዎች ቆም ብለው ራሳቸውን መፈተሽ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕግ ስርአትና መንግስት ባለበት ሀገር ችግሮችን በስርአቱና በአግባቡ መፍታት እየተቻለ እርስ በእርስ መናቆሩ ይህንን ለሚፈልጉት ኃይሎች ጥይት አቀባይ መሆኑ ለሕዝባቸውም ለሀገሪቱም የማይጠቅም መሆኑን ሊያውቁት ይገባል፡፡ የአንድ ሀገር ዜጎች መሆናቸውንም የረሱበት ሁኔታ ታይቶአል፡፡ አንዱ በሌላው ላይ የጠለቀ ጥላቻ እንዲያድርበት የማድረጉ ተግባር መጨረሻው የከፋ ጥፋትና ውድመትን ከማስከተል ውጪ የረባ ፋይዳ የለውም፡፡ ለሀገርም ለሕዝብም የሚበጅ አይደለም፡፡ ለሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦችም ሆነ ለመላው አገራችን የማይበጅ የጥፋት መንገድና እጅግ አደገኛ አዝማሚያ በመሆኑ በፍጥነት ሊገታ ይገባዋል፡፡

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተነሳውን ግጭት በመቀስቀስና በማባባስ እንዲሁም የዜጎችን አካል በማጉደልና የሰው ሕይወት በማጥፋት የሚጠረጠሩ ግለሰቦችም ሆኑ የፀጥታ ኃይሎች ለድርጊታቸው ተጠያቂ እንደሚሆኑ መጠራጠር አይገባም፡፡

በአብዛኛው የሕዝብ መገናኛ ብዙሐን በተለያየ ደረጃ የፌዴራል ስርአቱንና የሕዝቦችን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ በሕዝቦች መካከል ጥርጣሬ የሚፈጥሩና ግጭትን የሚቀሰቅሱ መግለጫዎችንና ዘገባዎችን ከማሰራጨት ሊቆጠቡ ይገባል፡፡ ይህ እያቆጠቆጠ በመምጣት ላይ የሚገኘው አደገኛ አዝማሚያ ጋዜጠኝነት ከሚጠይቀው ስነምግባር፣ ከመገናኛ ብዙሀንና ከመረጃ ነጻነት ሕጉ እንዲሁም ከአለም አቀፍ ሕጎችም ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጻረር በመሆኑ ጥንቀቄ ሊያደርጉበት ይገባል፡፡

የሚዲያ ባለሞያዎች ጉዳዩ በቀጥታ ከሀገራዊ ደሕንነትና ሰላም ጋር የተገናኘ በመሆኑ ይህም በሕጎች ላይ በግልጽ ሰፍሮ የተቀመጠ ስለሆነ ሊያጤኑት ግድ ይላል፡፡ ችግሩ መንገድና አቅጣጫ ስቶ ቢሄድ ጥፋት፣ እልቂትና ውድመት ቢከሰት ዜጎቹም የራሳችን ወንድሞች፤ ሀብቱም ንብረቱም የእኛው፤ የምንጎዳውም የምናዝነውም የምንጸጸተውም እኛው ነን፡፡ የሚደሰቱና የሚጨፍሩት ደግሞ ጠላቶቻችን ናቸው፡፡ ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል እንዲሉ፡፡ ይሄን የጥፋት ድግስ ሰብረን ለማቆም መረባረብ የሁሉም ዜጋ ቀዳሚ ስራ መሆን ይገባዋል፡፡

ባጠቃላይ ይህን በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች ከወሰን ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ግጭት ለመቆጣጠር፤ የቀድሞውን ሰላምና መረጋጋት ለማስፈንና አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ ልዩ ልዩ ተግባራት በመንግስት በኩል እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ከኃይማኖት አባቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር የጋራ ውይይት እየተደረገ ነው ሲሆን፤ ተፈናቃዮችን መልሶ የማቋቋም፤ ሕዝባዊ ውይይቶችን የማካሄድና ሌሎች የማረጋጋት ተግባራት በስፋት እየተሰሩ፤ የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎችም የሕዝቡን ሰላም በመጠበቅና በማረጋጋት ሥራ ላይ ተሰማርተው ሕግና ደንብ እያስከበሩ መገኘታቸው የሚያበረታታ ሲሆን ለስኬቱም አጠቃላይ ህዝቡ ከጎናቸው ሊቆም ይገባል፡፡