Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የደመራ በዓል በመላ ሀገሪቱ ተከበረ

0 879

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የደመራ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እና በመላው ሀገሪቱ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ተከብሯል።

በዓሉ በተለይም በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች፣ ምዕመናን፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ዲፕሎማቶችና የውጭ ሀገር ዜጎች በተገኙበት ነው ከ8 ሰአት ጀምሮ የተከበረው።

2010_meskel_2.jpg

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ ህዝቡ ለሰላም ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

“የህንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ ሁለተኛ ጉብኝት የመልካም ገፅታችን፣ የታላቅነታችን፣ የልምታችን እና የሰላማችን ማሳያ ነው” ብለዋል።

“ሰላማችንን እና አንድነታችንን ጠብቀን እስከተጓዝን ድረስ ፈላጊያችን እና አክባሪያችን ብዙ ይሆናል” ያሉት ብፁዕነታቸው፥ ለሰላም ዘብ በመቆም የሀገሪቱን ልማት ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ባለፉት ሳምንታት በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ድንበር ላይ በተከሰተው ግጭት ምክንያት በጠፋው የሰው ህይወት፣ የአካል ጉድለት እና የንብረት ውድመት ቤተክርስቲያን ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማት ገልፀዋል።

ህዝቡ ከሁሉም በላይ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” የሚለውን የፈጣሪን ድምፅ ዘወትር እንዲሰማ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ሰላም የእድገት ዋስትና በመሆኑ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ያለማመንታት ከበሽታ አምጪ ተግባራት እና ከሁከት በመራቅ የሀገሪቱን ከፍታ በቀጣዮቹ ዓመታት እንዲያረጋግጥ አባታዊ መልዕክታቸውን አቅርበዋል።

2010_meskel_1.jpg

የመስቀል ደመራ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መመዝገቡ የሀገሪቱን መልካም ገፅታ ለመገንባት ከፍተኛ ሚና እያበረከተ መሆኑን የተናገሩት፥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ ናቸው።

ከንቲባው በዓሉ ከሚያስገኘው የቱሪዝም ጥቅም ባሻገር የኢትዮጵያን መልካም ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ሃይማኖቶች ህገመንግስቱ በሰጣቸው ነፃነት የራሳቸውን አስተምህሮና የአምልኮ ስርዓት እያስቀጠሉ ይገኛሉ ነው ያሉት።

መንግስት እና ሃይማኖት የተለያዩ ሆነው በሀገራዊ አጀንዳዎች በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እና መሪዎቿ በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ከመንግስት ጋር እየሰሩ በመሆናቸው ሊበረታቱ የሚገባው ነው ብለዋል።

የሀገራችን ሃይማኖቶች ስለሰላም፣ ስለመቻቻል እና ስለልማት አስፈላጊውን ሚና መወጣታቸውን ጠቅሰው፥ ይህን በጎ ስራቸውን እንዲያስቀጥሉ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

የሃይማኖቶች ነፃነት እና ህልውና የሚረጋገጠው የሰላም፣ የመከባበር እና የመቻቻል መኖር በመሆኑ በሃይማኖት ሽፋን የሚፈፀሙ የፀረ ሰላም እንቅስቃሴዎችን በጋራ መታገል ይገባል ብለዋል።

“እንደ ህዝብ ተከብረን እና እንደ ሀገር ከፍ ብለን መጓዝ የምንችለው ድህነትን ማሸነፍ ስንችል ነው” ያሉት ከንቲባ ድሪባ ኩማ፥ ዜጎች፣ የሃይማኖት ተቋማት እና አባቶች እንዲሁም መንግስት በፀረ ድህነት ትግሉ ላይ በጋራ እንዲረባረቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በፈጣን እድገት እና ለውጥ ላይ የሚገኙት አዲስ አበባ ብሎም ኢትዮጵያ ስኬት ላይ እንዲደርሱ ጠንክሮ መስራት ይገባል ነው ያሉት።

በዘንድሮው የመስቀል ደመራ ስነስርዓት ላይ የተገኙት የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ቅዱስ ባስልዮስ ሁለተኛ በንግግራቸው የመስቀል ደመራ በዓል በዩኔስኮ በመመዝገቡ ደስታቸውን ገልፀዋል።

የሁለቱ አብያተ ቤተክርስቶያናት እህትማማችነት በትውልዱ እንደሚቀጥልም ነው አቡነ ባስልዮስ የገለፁት።

በደመራ በዓሉ ጥንግ ድርብ የለበሱ ካህናት እና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተለያዩ ዝማሬዎችን ያቀረቡ ሲሆን፥ የደመራ መለኮስ ስነስርአት ተከናውኖ የበዓሉ ፍፃሜ ሆኗል።

የደመራ በዓል በአንዳንድ የሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል ነገ ማለዳ እንደሚከበር ይታወቃል።

የመስቀል ክብረ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የባህልና የሳይንስ ተቋም (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡ ይታወቃል።

በምህረት አንዱዓለም

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy