Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የ“ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ” እመርታ

0 1,420

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የ“ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ” እመርታ

                                                         ዘአማን በላይ

በያዝነው ወር ላይ የዓለም የቱሪዝም ቀን ይከበራል። ይህ የቱሪዝም ዘርፍ በበርካታ ህዝቦች ዘንድ “ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ” በመባል ይታወቃል። ከእኛ ሀገር አኳያ “ጭስ አልባው ኢንዱስትሪው” ባለፉት ስርዓቶች ይህን ያህል ገቢ የሚያስገኝ ዘርፍ አልነበረም።

ከደርግ ውድቀት በኋላ ግን የኢፌዴሪ መንግስት ሀገሪቱ ከቱሪዝም የምታገኘውን ጥቅም በተገቢው ሁኔታ ለመጠቀም የመንግስት አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶችን እንደ አዲስ ለማዋቀር በወጣው አዋጅ ቁጥር 471/98 መሰረት ስራውን በበላይነት የሚመራው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን በአዲስ መልክ በመዋቀር ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም በተሻለ ሁኔታ ለማግኘት እንዲቻል አድርጓል። ሀገሪቱ በተቀናጀ ሁኔታ የምትመራበት የቱሪዝም ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂን ረቀቅ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በ2001 ዓ.ም በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።

በዚህም ሳቢያ በዘርፉ በተለያዩ መንገዶች ሲካሄዱ የነበሩትን ጥረቶች ወጥ በሆነ መንገድ የመንግሥትን፣ የግል ባለሃብቱን፣ የመስህብ አካባቢ ማኅበረሰብን እንዲሁም የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ተግባርና ሃላፊነትን የሚያረጋግጥ ፖሊስና ስትራቴጂን በመመርኮዝ  ወደ ስራ ተገብቷል።

ፖሊሲውና ስትራቴጂው ዘርፉን በመሰረተ ሰፊ የልማት አቅጣጫ ስለ መምራት፣ ነባርና አዳዲስ የቱሪዝም መስህቦችንና ምርቶችን ስለ ማልማት፣ ለሴክተሩ ልማት ወሣኝ የሆኑ የመሰረተ ልማት አውታሮችና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ስለ ለማስፋፋት ያብራራል።

ከዚህ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ የቱሪዝም ገበያ ፉክክር ውስጥ ብቁ ተወዳዳሪ ስለ መሆን፣ የሀገሪቱን ተጠቃሚነት ስለ ማረጋገጥ እንዲሁም በሴክተሩ በከፍተኛ ደረጃ የሚታየውን የአቅም ውስንነት ስለማስወገድ አስፈላጊነት በመስጠት እንዲደራጅ ተደርጎ ውጤት ማምጣት የቻለ ነው።

ምንም እንኳን ከደስርግ ውድቀት ማግስት “ጭስ አልባ ኢንዱስትሪውን” ለመምራት በርካታ ተግባሮች ቢከናወኑም፤ በተለይ ባለፉት 10 ዓመታት ፖሊሲውንና ስትራቴጂውን በመመርኮዝ ሀገሪቱ ከ“ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ መጠቀም የሚገባትን ጥቅም በተቀናጀ ሁኔታ እንድታገኝ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል። አጥጋቢ ውጤትም ተገኝቷል። በተለያዩ ወቅቶች የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ከ2003 እስከ 2007 ድረስ ተፈፃሚ በሆነው በቀዳሚው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወቅት ዘርፉ የተጠናከረ እንዲሆን ጥረት ተደርጓል።

በዚህም የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ የብዝሃ ባህል፣ የቅርስና የተፈጥሮ መስህቦች ዘላቂነት ባለው መልኩ በመጠበቅ፣ በማልማትና በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ ዘርፉ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያ ልማትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት ተገቢውን አስተዋፅኦ ማበርከት የሚያስችሉ ስራዎች እንደተከናወኑ መረጃዎች ያስረዳሉ።

በሌላ በኩልም በመተግበር ላይ ባለው በሁለተኛው የዕድገትን ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘርፉ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው። በዚህም ዘርፉ ለፈጣንና ቀጣይ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ዕድገት ጉልህ ሚና እንዲጫወት የማድረግ ዕቅዶች ተይዘው በርከታ ስራዎች ተከናውነዋል።

ባህላዊ የተፈጥሮ ቅርሶችና እሴቶችን በማልማት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት እንዲሁም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጉልህ ድርሻ እንደኖራቸው የማድረግ ተግባር ትኩረት ተሰጥቶት ተሰርቷል። እመርታዎችም ተገኝተዋል።

ሌላው ቀርቶ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በነበርንባቸው 10 ወራቶች ሳይቀር ዘርፉ ይህ ነው የሚባል ጉልህ ችግር ሳይስተዋልበት የቱሪስት መናኸሪያችን ተጠናክሮ መቀጠሉ የእመርታው አመላካቾች ናቸው ማለት ይቻላል። ርግጥ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች በነበሩ ሁከቶች ምክንያት በደፈናው ‘ምንም ችግር አልተፈጠረም’ ማለት አይቻልም። ሆኖም ኢንዱስትሪው ለሀገራችን የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ከመጉዳት አኳያ ጉልህ የሆነ ጉዳት አልነበረውም።

እንዲያውም እኔ እስከማስታውሰው ድረስ ዘርፉ በአዋጁ ወቅት ያለ አንዳች ሳንካ አስተዋፅኦ ማበርከቱ ሲገለፅ ነበር። ይህም የሀገራችን የቱሪዝም ልማት በአስቸጋሪ ወቅቶች ውሰጥ ሆኖም ልማትን የሚያረጋግጥ መሆኑን የሚያመላክት ነው።

ያም ሆኖ ከተጀመረ ሶስተኛ ዓመቱን በያዘው በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ “ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ” ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲያድግ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እንቅስቃሴ ተደርጓል። የባህል ኢንዱስትሪዎች ምርቶች ተስፋፍተውና ደረጃቸው ተሻሽሎ በዓለም አቀፍ ገበያ እንዲገቡ ለማድረግም ጥረት እየተደረገ ነው።

የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ መገለጫን “Land of origions” (ቀደምት ምድር) ወደሚል ስያሜ በመቀየር ዘርፉ የዓለም መስህብነቱን ጨምሮ ከፍ እንዲል ለማድረግ ተችሏል። ከዘርፉ ልማት አጠቃላይ እመርታ በተለይ ሴቶችና ወጣቶች ግንባር ቀደም ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑና ባህላዊ እሴቶችና የተፈጥሮ መስህቦች ለሀገሪቱ መልካም ገጽታ ግንባታ የበኩላቸውን አሰተዋፅኦ እንዲያደርጉ በመደረግ ላይ ነው። ይህም እስከ ዕቅዱ ፍፃሜ (እስከ 2012 ዓ.ም) የሚቀጥል ይሆናል።

የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መገኛ የሆነችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ባህልን፣ ቅርስንና የተፈጥሮ መስህቦችን ቀጣይነት ባለው መልኩ በመጠበቅና በማልማት እንዲሁም የህዝቦችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማጎልበት የባህልና ቱሪዝም ዘርፉ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ብሎም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መጎልበት ተገቢውን አስተዋፅኦ እንዲያበርክትም በመደረግ ላይ ነው።

በዚህም የሁሉም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህላዊ እሴቶች፣ ተፈጥሯዊ መስህቦቻችንንና ቅርሶቻችንን በመመዝገብና በመጠበቅ እንዲሁም እንዲታወቁና እንዲለሙ በማድረግ ለህዝቦች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲውሉ እየተደረገ ነው።

የሀገሪቱ ባህላዊ እሴቶች ጎልብተው በህዝቦች መካከል መተማመንና መከባበርን እንዲጠናከርና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲያግዙ የማድረግ ግብን ያነገበው ይህ ዘርፍ፤   ባህላዊና ተፈጥሯዊ መስህቦቻችንና ቅርሶቻችንን እንዲለሙ ብሎም ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሚና እንዲኖራቸው በማድረግ መካከለኛ ገቢ ያለው ህብረተሰብ የመፍጠርን ብሔራዊ ራዕይ ለማሳካት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱም ግብ መጣሉን መረጃዎች ያመለክታሉ። የህዝቦች ባህላዊ መገለጫዎች የሆኑ የተለያዩ ስርዓቶችና መስህቦች በዓለም አቀፍ ደረጃ ታውቀው እንዲመዘገቡ እየተደረገ ነው።   

የኢትዩጵያን ብርቅዬ ተፈጥሯዊ መስህቦችና ባህላዊ ቅርሶች ለጥናት፣ ለምርምርና ለቱሪዝም አገልግሎት እንዲውሉ በማድረግ ለሀገራችን ዕድገት አስተዋፅኦ እንዲኖራቸው የማድረግ ስራዎችም እየተከናወኑ ነው። የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ በተለይ የውጭ ምንዛሬን በማስገኘትና የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና የሚጫወትበት ደረጃ ላይ እንደደርስ እየተሰራ ከመሆኑም በላይ፤ ባለፉት 10 ዓመታት ገቢራዊ የሆኑ ስራዎች ካለፉት ጊዜያት እጅግ የላቀ ተግባራት እውን የሆኑበትና እመርታም የተገኘበት ነው። ይህም እመርታ በቀሪዎቹ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዓመታት ተጠናክሮ ቀጥሎ ለኢትዮጵያ ከፍታ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ በእነዚህ ዓመታት የተገኙት “የጭስ አልባው ኢንዱስትሪው” ውጤቶች አመላካቾች ይመስሉኛል።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy