Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፀረ-ሙስና ትግሉ ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል…

0 290

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፀረ-ሙስና ትግሉ ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል…

                                                     ቶሎሳ ኡርጌሳ

መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን የጀመረው የፀረ-ሙስና ትግል በሀገራችን ውስጥ ልማታዊ አስተሳሰብ የበላይነት እንዲይዝ የሚደረግ ትግል አካል ነው። ታዲያ ይህ ትግል  በመንግስት ደረጃ ይጀመር እንጂ፤ ዋነኛ ባለቤቱ ህዝቡ መሆኑንም በተለያዩ ወቅቶች ተመልክተናል። ይኸውም የዛሬ 15 ዓመት ገደማ በተካሄደው ኪራይ ሰብሳቢነትን፣ ጥገኝነትንና የመንግስት ስልጣንን ለራስ ጥቅም የማዋል ተግባርን የመታገል ተሃድሶ ውስጥ በዋነኛነት መንገስትና ገዥው ፓርቲ ጉዳዩን ቢያቀጣጥሉትም ህዝቡ የማይተካ ሚና እንደነበረው እናስታውሳለን።

ይህ ተሃድሶ ሀገራችንን አሁን ላለችበት የዕድገት ጎዳና ያበቃት ነው ብዬ አስባለሁ። በወቅቱ በአንድ በኩል ስልጣንን የኢኮኖሚያዊ ሃብትና የብልፅግና መሳሪያ በማድረግ ፀረ-ዴክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት በሚሹ ወገኖች፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስልጣን የሃብት ምንጭ እንዳይሆን፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ እንዲያብብና እንዲዳብር ብሎም የጥገኝነት አስተሳሰብ የበላይነት እንዳያገኝ በሚተጉ ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ግምገማና የመድረክ ትግል መካሄዱን እናስታውሳለን።

ታዲያ በወቅቱ ተፈጥረው በነበሩት በእነዚህ ሁለት ፅንፍ አመለካከቶች ዙሪያ በተካሄዱ ግምገማዊ የሃሳብ ፍጭት፤ ስልጣን የጥቂቶች የሃብት ማካበቻ እንዳይሆን እንዲሁም ዴሞክራሲና ዴክራሲያዊ አንድነት እንዲጎለብት ብሎም የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ውስጥ የበላይነት እንዳያገኝ የታገለው ወገን ነጥሮ በመውጣት ተሃድሶው ግቡን መትቷል፤ ውጤትም አምጥቷል።

እንደ እውነቱ ከሆነ በወቅቱ እንዲህ ዓይነቱ የተሃድሶ ርምጃ ባይካሄድ ኖሮ ሀገራችን የምትመራባቸው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም ስልቶች ባልተነደፉ ነበር። ያኔ አቆጥቁጦ የነበረው ፀረ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብም በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ ጋር አብሮ ባልከሰመ ነበር። እናም ተሃድሶ ሲባል እንዲያው ለይስሙላ አሊያም ለታይታ ሲባል ብቻ የሚከናወን ሳይሆን ይህን መሰሉን ለውጦች እውን የሚያደርግ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል።

መንግስት ትናንትም ይሁን ዛሬ ያከናወናቸውና የሚያከናውናቸው ተሃድሶዎች ተጨባጭ ውጤቶችን ያመጡ ናቸው። መንግስት በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው የተሃድሶ ሂደት የመንግስት መዋቅሮችን የህዝቡን እርካታ በሚፈጥሩ መንገድ እያከናወነ ነው። ሙሰኞችን ለህግ በማቅረብ በፈፀሙት ጥፋት ልክ እንዲቀጡ በማድረግ ሂደት ውስጥ ህዝቡ እያከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

ይህ ሁኔታም ከዚህ ቀደም በነበሩ የተሃድሶ መንገዶች የተከናወኑ ተግባራትን የሚያጠናክርና ይበልጥ የሚያሰርፅ ነው። መንግስት ለያዘው ቁርጠኛና ውጤት ሊያመጣ የሚችለው ጥልቅ ተሃድሶ ሁሉም የበኩሉን ጠጠር ቢወረውር የሚፈለገው ለውጥ ሊመጣ ይችላልሚና መወጣት ሲችል ነው።

ርግጥ በየትኛውም ዴክራሲያዊ ሀገር ውስጥ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ነባራዊ ክስተት ነው። ምንም እንኳን በሀገራችንም መንግሥትና ህዝብ በመገንባት ላይ የሚገኙት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ገና ለጋ ቢሆንም፤ እንደ ጀማሪ ዴሞክራሲያዊ ሀገር ከዚህ ነባራዊ ክስተት የፀዳንና ጉድለቶች የሉብንም ብሎ ለመናገር አይቻልም።

ለነገሩ የኢፌዴሪ መንግስትና እርሱን የሚመራው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ከህዝቡ ጋር በመሆን በየጊዜው በሚወስዷቸው በርካታ ርምጃዎች የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቦች በመጠኑም ቢሆን እየቀረፉ ቢሆኑም፤ የሚፈለገው የአስተሳሰብ ለውጥ ተገኝቷል ማለት አይቻልም።

እንዲያውም አስተሳሰቦቹ እየገነገኑ ጫፍ ላይ እየወጡ ይመስላሉ። በአመዛኙ ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሙስናን የሚፀየፍና እንደ ነውር የሚያይ የመንግስት ስራ አስፈፃሚን ብሎም ህዝብን በተሟላ ሁኔታ መፍጠር አልተቻለም።

በሰጪም ይሁን በተቀባይ መካከል ያለው አስተሳሰብ አንድና ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል። ይህ የሆነውም ካለፉት ስርዓቶች ይዘናቸው የመጣናቸው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ቅሪት አስተሳሰቦች ብሎም ልማቱ የፈጠራቸው አንዳንድ ሁኔታዎች አስተዋፅኦ በማድረጋቸው  መሆኑ አያጠያይቅም።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ሁሉም ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ የመንግስት ስራ ፈፃሚዎችና ከሙስና ጋር ግንኙነት ባለቸው ግለሰቦች ላይ የተወሰዱት የአስተዳደራዊና ህጋዊ ርምጃዎች መንግስት በፀረ-ሙሰና ትግሉ ላይ ምን ያህል ቁርጠኛ አቋም እንዳለው የሚያሳዩ ናቸው።

ይህ የመንግስት ቁርጠኛ አቋም መንግስት ዛሬም እንደ ትናንቱ ቃሉን የማያጥፍና ሁሌም የሚያካሂደው የፀረ ሙስና ትግል  በውጤት የሚታጀብና ለዚህም ህዝቡ ከፍተኛ ሚና እንዲጫወት ያደረገው መሆኑን ያሳየ ተግባር ነው። መንግስት ትናንትም ይሁን ዛሬ ያከናወናቸውና የሚያከናውናቸው የፀረ-ሙስና ዘመቻዎች ግባቸውን የሚመቱት ህዝቡን ያሳተፉ በመሆናቸው ነው።

መንግስት በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው የፀረ ሙስና ትግል የመንግስት መዋቅሮችን የህዝቡን እርካታ በሚፈጥሩ መንገድ እያከናወነ ነው። ይህ ሁኔታም ከዚህ ቀደም በነበሩ የተሃድሶ መንገዶች የተከናወኑ ተግባራትን የሚያጠናክርና ይበልጥ የሚያሰርፅ ነው።

መንግስት በቁርጠኝነት የያዘው ይህ የፀረ ሙስና ትግል በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ መረጋገጥ መቻል አለበት። ኪራይ ሰብሳቢዎችንና መዝባሪ ሙሰኞችን ህዝቡ በሚገባ ያውቃቸዋል። ትናንት ምን እንደነበሩና ዛሬ የት እንደደረሱ ከህዝብ የሚሰወር አይደለም። ህዝቡ የከፈለው ግብር እነማን ኪስ ውስጥ ያለአግባብ እንደገባ ያውቃል።

ህዝቡ በኪራይ ሰብሳቢነትና በሙስና ላይ የሚሳተፉ ወገኖችን ከ…እስከ በሚባል መልኩ አብጠርጥሮ ያውቃቸዋል። እነማን ከማን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው፣ የትስስር ሰንሰለታቸው እስከየት ድረስ እንደሆነ፣ በምን ዓይነት ቁርኝት እንደሚጠቃቀሙ ለህዝቡ ግልፅ ነው። ርግጥ ኪራይ ሰብሳቢዎችና ሙሰኞቹ ከሌላ ፕላኔት የመጡ ሳይሆኑ ከህዝቡ ውስጥ የተገኙ በመሆናቸው ህዝቡ የአውራ ጣቱን ያህል በሚገባ ያውቃቸዋል።

እናም የፀረ ሙስና ትግሉ ግለቱን ጨምሮ ትናንት ከነበረበት ወደ ተሻለ ከፍታ እንዲሸጋገር የህዝቡን ሚና ማንም ሊተካው አይችልም። ህዝብ በልማት ላይ ተሳትፎ ሀገራዊ ዕድገት እንደሚያመጣው ሁሉ፤ የፀረ ሙስና ተግባርን በመታገል በሀገሩ ውስጥ ልማታዊነትን ሊያነግስ ይችላል።  

ርግጥ እየተካሄደ ላለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ምስጋና ይግባውና በአሁኑ ወቅት የተፈጠረው ህዝብ ጠያቂ ሆኗል። ይህ ህዝብ በሁሉም የሙስና ተግባር ፈፃሚዎች ላይ ‘ለምን?’ የሚል ጥያቄን እያነሳ ነው። መብትና ግዴታውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ህዝብ እየተፈጠረ ነው።

ታዲያ በየትኛውም ሀገር ውስጥ መብቱንና ግዴታውን በማወቅ የሚጠይቅ ህዝብ በተፈጠረ ቁጥር መንግስት ስራዎቹን በጥራትና በተጠያቂነት መንፈስ ለማከናወን ይገደዳል። ይህም የህዝቡ ጠያቂነት በዚሁ ሁኔታ ከተጠናከረ የፀረ ሙስና ትግሉ ግለቱን ጠብቆ እንዲሄድ ከማስቻል ባለፈ፤ ልማታዊ የፖለቲካ አኮኖሚ በኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ መቃብር ላይ እንዲያብብና የሀገራችን ህዳሴ ቅርብ እንዲሆን ማድረጉ አይቀሬ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy