ethiopian news

Artcles

የፌዴራል ስርዓቱና የሰንደቅ ዓላማችን

By Admin

September 07, 2017

የፌዴራል ስርዓቱና የሰንደቅ ዓላማችን

                                                        ታዬ ከበደ

ኢትዮጵያ በፌዴራል ስርዓቷ አማካኝነት እውን ያደረገችው ሰንደቅ ዓላማ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መገለጫ እንዲሁም የሀገራችን ብሩህ ተስፋን የሚያንፀባቅር ነው። የአገራችንን ሰንደቅ ዓላማ ከፌዴራላዊ ስርዓቱ ጋር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ነው ማለት ይቻላል። እናም መጪውን የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ስናስብ ስለ ባንዴራው የህዝቦች መገለጫነት ማውሳት ተገቢ ይመስለኛል።

ሰንደቅ ዓላማችን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የመሰረቱት ዲሞክራሲያዊ አንድነት ምልክት ነው። ድህነትንና ኋላቀርነትን ለመዋጋት የሚደረገው ትግል የሚጠናከርበትም ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ያለፉት ጨቋኝና አምባገነን ስርዓቶች የሀገራችንን ህዝብ በእጅጉ ጎድተውታል፡፡ ስርዓቶቹ ለስልጣናቸው ሲሉ የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎቶች በማፈን የራሳቸውን ወንበር ሲያደላድሉ ኖረዋል። የህዝቡን ተስፋ አሟጠው በመውሰድ ተስፋ ቢስ አድርገውታል።

ስልጣንን በዘር ግንድና በኢ-ዴሞክራሲያዊ መንገድ ተቆናጠው ህዝቡን አላላውስ ብለውት በድህነት አረንቋ ውስጥ እንዲዳክር ከማድረጋቸውም በላይ፣ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ አንገቱን ደፍቶ እንዲሄድ ማድረጋቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።

ምስጋና ለሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መራር ትግል ይሁንና ዛሬ ይህ ታሪክ ዳግም ላይመለስ ጓዙን ጠቅልሎ ተሰናብቷል። ህዝቦች በራሳቸው ፈቃድ ተስማምተው ባፀደቁት ህገ-መንግስት ሰላማቸውን፣ ልማታቸውንና ዴሞክራሲያቸውን ያለ ገደብ እያጣጣሙት ነው።

እርግጥ ዛሬ ላይ እየጎለበተ የመጣው የዴሞክራሲ ባህል እየተገነባባት ያለች ሀገርን ለመመስረት እልህ አስጨራሽ ትግልንና የህይወት መስዋዕትነትን ጠይቋል፡፡ ይህ በታሪክ ሁሌም የሚወሳ ሀቅ ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ በምትከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት አያሌ ድሎችን ማስመዝገብ ችላለች። ሕዝቦቿም የውጤቶቹ ተቋዳሽ ለመሆን በቅተዋል። ይሁንና የቀድሞው ሥርዓት ተመልሶ ይመጣ ዘንድ ጨለምተኞቹ ሠላሙን አግኝቶ ኑሮውን ለመለወጥ የሚጣጣረውን ዜጋ ወደ ኋላ ለመጎተት የማይቀበጣጥሩት የለም። ተግባራቸው  ግን ትርጉም የለውም።

ሰንደቅ ዓላማ ምንነት ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ጥልቅ ትርጉሞች አሉት። አንድም ከታሪካችን ጋር የሚያይዘው ዕውነታ ስላለ፣ ሁለትም ከብዝሃነታችን ጋር ያለው ቁርኝት ከፍተኛ ስለሆነ ነው። ከታሪክ አኳያ ስንነሳ፤ ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን  የሀገራችንን የግዛት አንድነት ለማስከበርና ሀገራቸውን ከውጭ ወራሪዎች ለመታደግ እንደ አንድ ሰው በመሆን በዱር በገደሉ ያካሄዱትን ተጋድሎ ዕውን ያደረጉት በሰንደቅ ዓላማው ስር ሆነው ነው። የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከብዝሃነታችን አኳያም ስንመለከት፤ በሰለጠነው የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የመሰረቱት የዴሞክራሲያዊ አንድነታቸው መገለጫ መሆኑን ለመገንዘብ አይከብድም።  በልዩነታችው ውስጥ ያለው አንድነታቸው ሁነኛ ማሳያም መሆኑ እንዲሁ።

እንደሚታወቀው የሀገራችን ህዝቦች በሰንደቅ ዓላማው ስር ሆነው አንዱ የሌላውን ማነነት እንዲያውቅ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩ ስራዎችን አከናውነዋል። በተለይም ያለፉት ፊውዳላዊና ጨቋኝ ስርዓቶች በህዝቦች መካከል ጥለዋቸው ያለፉት ቁርሾዎችና ጠባሳዎች እንዲሽሩ፣ የመፈቀቃቀድና የወንድማማችነት መንፈስ እንዲጎለብት፣ ልዩነታቸው ተጠብቆ በሚያስተሰስሯቸው እጅግ የበዙ ታሪካዊና ነባራዊ ጉዳዩች ላይ እንዲያተኩሩ የሚያደርጉ ስራዎችን ገቢራዊ አድርገዋል።

የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት ፈጣን ልማትንና የጋራ ተጠቃሚነትን ከማስገኘት አኳያ ያለው ፋይዳም የገዘፈ ነው። በቡድንም ይሁን በግል አሊያም በሀገር ደረጃ የሚሰራ ማናቸውም ጉዳይ ያለ አንድነት ዕውን ሊሆን አይችልም። አዎ! በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ አንድነት ሲኖር ፈጣን ልማትና የተሻለ አቅም መፍጠር ይቻላል። አንድነት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የህዝቦች ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ የሚችለው እኩልነትና መፈቃቀድ ሲኖር ነው። የሀገራችን ህዝቦች አንድነት ህገ-መንግስታዊ መሰረት ያለው እንዲሁም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፅኑ ፍላጎትንና እምነትን መሰረት ያደረገ ነው። የዚህ ዕውነታ ነፀብራቅና የብዝሃነታችን ጥላና ከለላ ደግሞ ሰንደቅ ዓላማው መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም።

ይህ ሃቅ አንዳንድ ወገኖች ይህን በልዩነት ውስጥ ያለን የህዝቦችን ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ለብተና እንደሚዳርግ በማስመሰል ያስሙ የነበሩትን ልፈፋ መና ያስቀረ ነው ማለት ይቻላል። እንደሚታወቀው ከሩብ ክፍለ ዘመን በፊት (ዛሬም ቢሆን)፤ ሀገራችን ተበታትና ማየት የሚሹ ሃይሎች በህገ-መንግስቱ ላይ የሰፈረውንና በአንቀፅ 39 ላይ የሚገኘውን “የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስመገንጠል” የሚለውን ፍፁም ዴሞክራሲያዊ አንቀፅ ገልብጦ በማየት “ኢትየሎጵያ አበቃላት፤ መበታተኗ የሚቀር አይደለም” ሲሉ የጥንቆላ ትንበያን ሲያሰሙ ነበር። ግና ይህ ሟርታቸው ሊሰምር አልቻለም። በተግባር የታየው የዚህ ተቃራኒ ነውና። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ሀገራችን የምትከተለው ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ስርዓት መሆኑ አይካድም።

ይሁንና በቅርቡ ይህን በልዩነት ውስጥ ያለን አንድነት ያጠናከረውን ፌዴራላዊ ስርዓት ለመቀልበስ አሸባሪዎችና ፀረ-ሰላም ኃይሎች ሁከትና ብጥብጥን ለመፍጠር ሞክረዋል። ፕሬዚዳንቱም በንግግራቸው ላይ “የሀገሪቱን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የመቀልበስ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች በሀገራችን ጥቅም ላይ አፍራሽ እንቅስቃሴ እያደረጉ ናቸው” በማለት ሃቁን ገልፀዋል።

እርግጥ እነዚህ ኃይሎች ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ ከሚያደርጓቸው ተግባራት ውስጥ አንዱ ሰንደቅ ዓላማውን ያለመቀበል ነው።ህ ፍላጎታቸው በተለያዩ ወቅቶች ተረጋግጧል። አንዳንዶቹ ሰንደቅ ዓላማውን ሲቀዱ፣ ሌሎቹ ደግሞ ለሰንደቅ ዓላማው ምንም ዓይነት ዕውቅና ሳይሰጡ ቀደምት ስርዓቶች ይጠቀሙበት የነበረውንና መሐሉ ላይ ኮከብና ጨረር የሌለውን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሌጣ ሰንደቅ ዓላማን ብቻ ይዘው ሲወጡ ተስተውሏል።

እነዚህ ኃይሎች የፌዴራሉን ሰንደቅ ዓላማ ያለመቀበላቸው ምክንያት ግልፅ ይመስለኛል። ይኸውም ልዩነትን የሚፈታ ስርዓት እያለ፣ ልዩነትን በኃይል በማስፈፀም እነርሱ ወደሚፈጉት የቀደምት ስርዓቶች እንድንመለስ ስለሚፈልጉ ነው። ይህ ፍላጎታቸው ግን ኢ-ዴሞክራሲያዊ ነው። ባለንበት የሰለጠነ ዘመን ልዩነትን በመቻቻልና በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት መሞከር እንጂ በአስገዳጅ ኃይል ለመፍታት መሞከር ስለማይቻል ነው።

ሰንደቅ ዓላማውን ዕውን ያደረጉት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ናቸው። የስርዓቱ መገለጫ የሆነው ይህ ሰንደቅ ዓላማ ያለ እነርሱ ፍላጎትና ፈቃድ በሰንደቅ ዓላማው ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ሊደረግበት አይችልም። ያለ ህዝቦች ይሁንታ ማንኛውንም ነገር ለመፈፀም መሞከር የእነርሱን ሉዓላዊ ስልጣን መጋፋት ነው።

ይህ ደግሞ ጥቂቶች በፍፁም “እኔ አውቅልሃለው” የሚል ፀረ-ዴሞክራሲያዊ መንገድ እየተመሩ እጅግ የሚበዛውን ህዝብ መብት በማን አለብኝነት በኃይል ለመንጠቅ መሞከር ነው። ዳሩ ግን እንዲህ ዓይነቱ የለየለት የጉልበተኞች መንገድ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊሰራ አይችልም።