Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፖሊሲዎቻችን ውጤቶች

0 309

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፖሊሲዎቻችን ውጤቶች

                                                                 ደስታ ኃይሉ

መንግስት ባለፉት ዓመታት የነደፋቸው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ እውና እያሰጡንና ሽልማቶችም እያስገኙልን ነው። ሰሞኑን ለትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የአካባቢ ጥበቃና የሲጋራ ቁጥጥር፣ ለመከላከያ ሰራዊታችን የተሰጡ እውቅናዎች…ወዘተ ሽልማቶች የዚህ አባባል ማሳያዎች ናቸው። እነዚህ ሽልማቶች አገራችን የምትከተላቸው ፖሊሲዎች ውጤቶች መሆናቸውን ማንም አይክድም።

 

አገራችን የምታከናውናቸውን ተግባራትና ውጤቶቻቸውን በትክክል መግለፅ መቻላችን የፖሊሲ ውጤቶቻችንን ማስተዋወቅ ችለናል። ከዚህ አኳያ ሁሉንም ተግባሮቻችንን በማስተዋወቅና ዓለምም ተገቢውን እውቅና እንዲሰጠን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ዓይነተኛ ሚና እንደተጫወተ መገንዘብ ይቻላል።

 

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት የአካባቢውንና ጎረቤት ሀገሮችን ለጋራ ጥቅምና ሰላም እንዲሰሩ የሚጋብዝ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሰረት ጥሏል፡፡ ይህ እንደ ቀድሞዎቹ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲዎች የሀገር ውስጥ ጉዳዮችን ቸል በማለትና ወደ ውጭ ያነጣጠረ ሳይሆን፤ በቅድሚያ በሀገር ውስጥ ሰላም በማስፈን በማረጋጋት ላይ ትኩረት በማድረግ  በአካባቢያችን ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂና አስተማማኝ ሠላም እንዲፈጠርና የጋራ ልማትና ትብብር እንዲጠናከር ማድረግ ነው፡፡  

 

የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና ሀገራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ ተልዕኮ አለው፡፡ ፖሊሲው እንደሚያመለክተው ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖረን ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የሀገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ ያረጋግጣል፡፡

 

ደህንነታችንን ለማስጠበቅ ዋናው መሣሪያ ልማትና ዴሞክራሲን በሀገር ደረጃ ማረጋገጥ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ ተመስርቶም ዲፕሎማሲያችን በቂ ጥናት በማካሄድ አደጋዎችን ለመቀነስ፣ ግጭቶች ሲፈጠሩ በድርድር እንዲፈቱ ለማድረግ፣ በዚህ ሂደት ሊፈቱ ያልቻሉትን ለመከላከል አቅም መገንባት ተተኪ የሌለው ሚና እንደሚጫወት የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂው ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡

 

የፖሊሲው አንዱ የትኩረት አቅጣጫ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ነው። በዚህ ስራም ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ጋር የምታደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየጎለበተ መጥቷል፡፡

 

ልማታዊ ዲፕሎማሲውም ተጠናክሯል፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ ከልዩ ልዩ ሀገሮች ጋር ግንኙነቷን በማጠናከርም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የኢንቨስትመንት ፍሰትና ሚዛናዊ የንግድ ትስስር እንዲጨምር እየሰራች ነው፡፡

 

የአገሪቱን የውጭ ግንኙነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስፍራ ለማጎልበትም ባለፉት 25 ዓመታት ሰፊ ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ለሀገሪቱም ሆነ ለአካባቢው የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን የሠላምና የትብብር አድማሱ እንዲሰፋ እያደረገች ትገኛለች፡፡ በምትከተለው በዚህ የትብብርና የሠላም ዲፕሎማሲ መርህ መሰረትም በዓለም ዙሪያ ካሉት አገሮች ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

 

ይህን ፖሊሲ መሰረት በማድረግም ኢትዮጵያ የሌሎችን ጥቅም የማይጎዳ የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲን እየተከተለች ነው። ይህን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም እንዲያውቀው ተደርጓል። አገራችን በዚህ ረገድ መሪ መሆኗን ግልፅ አድርጋለች።

 

ዛሬ የአየር ንብረት ለውጥ የዓለማችን ፈታኝ ሁኔታ ከሆነ ሰነባብቷል። ለችግሩ በዋና ምክንያትነት የሚጠቀሱት፣ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ የበካይ ጋዞች ልቅት መጨመርና የደን ሀብት እየተመናመነ መምጣት መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይገልፃሉ፡፡

ችግሮቹን ለመፍታት የበካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስና የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን መከተል እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤን ማጎልበትና በደን ልማት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ተመራጭ መፍትሄ መሆናቸውን ዓለም የተስማማባቸው ሃቆች ናቸው፡፡ በተለይም በግብርና ምርታማነት ላይ መሰረቱን ለጣለ ኢኮኖሚ የአየር ንብረት ለውጥ ምን ያክል ተፅዕኖ እንዳለው መገንዘብ ያስችላል፡፡

ይህን ሃቅ ቀድማ የተገነዘበችው ኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥ በግብርና ምርታማነት ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቋቋም የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን እየተከተለች ትገኛለች፡፡

ይህ ልማት ህዝቡን ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር፤ ለአካባቢ ተስማሚ መሆኑን በተጨባጭ የተገኙ ውጤቶች ህያው ምስክር ናቸው፡፡ በትግራይ ክልል የተከናወነው የተራቆቱ መሬቶችን በደን የመሸፈንና መልሰው እንዲያገግሙ የማድረግ ስራዎች የዚህ ተግባር ማሳያዎች ናቸው፡፡

በተለይም ወጣቶችን እንደ ደን ቆረጣ ካሉ አካባቢን ከሚጎዱ የገቢ ማስገኛ መስኮች በማላቀቅ ህገ አማራጭ ወደ ሆኑ የገቢ ማስገኛ መስኮች እንዲዞሩ አድርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም በእርሻ ላይ የተመሰረተው ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር ያግዛል፡፡ ቴክኖሎጂው ከፍተኛ ዋጋ የሚያውጡ የሰብል፣ የዛፍ፣ የፍራፍሬና አትክልት ዝርያዎችን የእንስሳት እርባታና ድለባ፣ የንብ ማነብ ስራን አቀናጅቶ በማልማት የገቢ ምንጭን ማሳደግ የሚያስችል ነው፡፡

ክንዋኔው በኢኮኖሚው ላይ ከሚያደርሰው አዎንታዊ ተፅዕኖ ባሻገር፤ በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚያደርሰውን ጫና በመቀነስ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል፡፡ ፊዚካላዊና ሥነ ህይወታዊ የአካባቢ ሥራዎችን በመተግበርም የተጎዱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግም በማድረግ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል የአፈር ለምነትን ለመጨመር እገዛ እያደረገ ነው፡፡

በሌላ በኩልም ቴክኖሎጂው የዕፅዋት እና እንስሳት ዓይነቶች እንዲበራከቱ አድርጓል፡፡ አካባቢውም በተለያዩ ዕፅዋቶች ሲሸፈን የአካባቢው ውበት ስለሚያምር ለህብረተሰቡ የመዝናኛ ቦታን ስለሚያበረክት ንፁህ ከባቢን ለመፍጠር የሚደረገውን ርብርብም የሚያግዝ ነው፡፡

የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ እንዲያገግሙ ለማድረግ በየአካባቢው መልክዓ ምድር ሊተገበር የሚችል ሲሆን፤ ለአካባቢው አየር ፀባይ ተስማሚ የእፅዋት ዝርያ በመምረጥ ተስማሚ የእርከን ዓይነቶችን መለየት እና የገቢ ምንጭ ሊያስገኙ የሚችሉ ስራዎች ተቀናጅተው የሚሰሩበት ሁኔታ በማጤን ህብረተሰቡ የሚጠቀምበትን መንገድ ለማሳየት ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

 

ይህ በማሳያነት ያቀረብኩት ፖሊሲ ተገቢነቱ ብቻ ሳይሆን የአገራችንን ስም ያስጠራ ነው፡፡ ይህና ሌሎች የፖሊሲ ውጤቶቻችን ለአገራችን ሽልማት ማስገኘታቸው ልማታዊው መንግስት የሚከተለው የእድገት መስመር ምን ያህል ትክክለኛ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy