ይህ ዕቅድ ቀድሞ ይሳካል ባይ ነኝ
ይህ ዕቅድ ቀድሞ ይሳካል ባይ ነኝ
ወንድይራድ ኃብተየስ
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በመተግበር በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃም በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ አገር ለመሆን በቅታለች። ህብረተሰቡ ከአካባቢ ጥበቃና ተፋሰስ ልማት ስራዎች ቀጥተኛ ተጠቃሚ መሆን በመቻሉ አሁን ላይ ለአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ቀስቃሽና ጎትጓች አያስፈልገውም። አርሶና አርብቶ አደሩ በየዓመቱ ለበርካታ ቀናት ለተፋሰስ ስራ ነጻ አገልግሎት ይሰጣል። በዘንድሮው ክረምት ብቻ በአገራችን በሁሉም አካባቢዎች በአስርት ቢሊዮን የሚቆጠር ችግኞች በመተከል ላይ ናቸው። በእርግጥ የተተከሉ ችግኞች ሁሉ ይጸድቃሉ ባይባልም በርካቶቹ ግን እንደሚጸድቁ ከዚህ በፊት ያለው ተሞክሮ ያሳያል። አርሶና አርብቶ አደሩ በበጋ ያከናወኗቸው የተፋሰስ ልማት ስራዎች አፈርን ከመከላት በመከላከል ላይ ናቸው። ኢትዮጵያ በ2025 አገራዊ የደን ሽፋኗን 20 በመቶ ለማድረስ በእቅድ ይዛ በመስራት ላይ ነች። እንደእኔ እንደኔ አሁን ላይ ባለን አፈጻጸም ይህ እቅድ ቀድሞ ይሳካል ባይ ነኝ።
ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት የአረንጓዴ ኢኮኖሚው ትልቁን ድርሻ አበርክቷል። አገራችን ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በበርካታ አካባቢዎች በተካሄዱ የተፋሰስ ልማት፣ ችግኞችን መትከል፣ ልቅ ግጦሽን መከላከል፣ ደኖችን መንከባከብ፣ ወዘተ በመቻሉ የደን ሽፋናችን ቀድሞ ከነበረበት ሶስት በመቶ አካባቢ ወደ 15 በመቶ በላይ ማድረስ ተችሏል። በአሁኑ ሰዓት በተለይ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል አግጠው የነበሩ በርካታ ተራሮች ወደ አረንጓዴነት በመለወጥ ላይ ናቸው። ምንጮች በማገገም ለመስኖ በመዋል ላይ ናቸው። የበርካታ አካባቢዎች የተፈጥሮ ስነምህዳሩ እጅጉን ተሻሽሏል። የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በተመለከተ ህብረተሰቡን ባለቤት ማድረግ ስለተቻለ የታሰበው ለውጥን ማሳካት ተችሏል።
ከአዲሱ ዓመት መቀበያ ከሆኑን ኩነቶች መካከል አንዱ የአረንጓዴ ልማታችንን የምንዘክርበት ቀን አንዱ ነው። ጳጉሜ 1 ቀን 2009 ዓ ም “የአረንጓዴ ልማት ጠበቆች ነን” በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል። እውነት ነው እንደ ኢትዮጵያ ያለ ለአረንጓዴ ልማት የታገለ አገር ያለ አይመስለኝም። ታላቁ መሪ ለአረንጓዴ ልማት መረጋገጥ ከአገር ቤት አልፈው በአፍሪካ እንዲሁም በዓለም ዓቀፍ መድረኮች ትልቁን ሚና ተጫውተዋል። በርዕቱ አንደበታቸው ዓለም ስለሚኖርባት ምድርና እየገጠማት ስላለው የአየር ንብረት እንዲያጤነው አርድገዋል።
የታዳጊ አገራት ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ በግብርና ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ ለአየር ንብረት ለውጥ በቀላሉ ተጋላጭ ነው። በመሆኑም ይህን ተጋላጭነታቸውን መቀነስ ካልቻሉ ከድህነት መወጣት አይችሉም። አገራችን የአደንጓዴ ልማት ስትራቴጂን ነድፋ መተግበር በመጀመሯ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ ችላለች። ይህ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት ያደረገው ደግሞ በግብርናው ዘርፍ ላይ ነው። በመሆኑም የግብርናውን ዘርፍ የሚፈታተን ማንኛውም ነገር ከኢትዮጵያ ህይወት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል መንግስት ስትራቴጂ ነድፎ በመተግበር ላይ ነው። በዚህ ስትራቴጂም አገራችን ተጨባጭ ለውጦችን በማስመዝገብ ላይ ነች። ለአብነት የረሃነትን መስፋፋትን በእጅጉ ቀንሳለች፣ የአፈር መከላትን ተከላክላለች፣ ለዜጎች ተጨማሪ የስራ እድል መፍጠር ችላለች፣ የምግብ ዋስትናን በአገር ደረጃ ተረጋግጧል፣ በአጠቃላይ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ስለአረንጓዴ ልማትና የአየር ለውጥ ያላቸው አቋም ዓለምን እጅግ ያስገረመ ነበር። የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ በአንድ አካባቢ ታጥሮ የሚቆም ችግር አይደለም። በአንዱ ጥፋት ሌላውም ተቀጪ ነው “አይጥ በበላ ዳዋ…” እንደሚባለው ነው። ታዳጊ አገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ያላቸው አስተዋጽፆ ይህን ያህል አይደለም። ነገር ግን ኢኮኖሚያቸው በግብርና ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ በአየር ንብረት ለውጥ ለሚመጣ ጉዳት ተጋላጭነታቸው እጅግ ከፍተኛ ነው። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ለአየር ንብረት ስምምነቶች ቁብ ባይሰጡትም በርካታ የዓለም አገራት ግን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ያላቸውን ጠንካራ አቋም በድጋሜ አረጋግጠዋል። እኛ ኢትዮጵያዊያን ማንም ደገፈውም ተቃወመውም ከአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂያችን የሚያነቃንቀን ነገር አይኖርም። ምክንያቱም ይህን ስትራቴጂ በመከተላችን ያገኘነውን ጥቅም በተጨባጭ አይተነዋል። በአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂያች ሳቢያ ባከናወናቸው አካባቢ ጥበቃና የደኖችን ልማት ስራዎቻችን ወደ አቀድነው የኢኮኖሚ ስርዓት የሚያደርሰን መሆኑን የመጣንበት መንገድ አረጋግጦልናል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ በሚያደርገው መዋቅራዊ ሽግግር የኃይል ፍላጎታችን እጅጉን አድጓል። ዛሬ ላይ ከ4300 ሜጋ ዋት በላይ ሃይል እያመነጨን የሃይል እጥረቱ ግን እጅግ ከፍተኛ ነው። የኃይል አቅርቦት እና የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ነገሮች ናቸው። የአገራችን ዕድገት የሚፋጠነው እንዲሁም ኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ የሚያደርገው የኃይል ፍላጎታችን ማሟላት ስንችል ብቻ ነው። የኢፌዴሪ መንግስት በአገራችን የሚስተዋለውን የሃይል አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ በርካታ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ነው። የአገራችን የሃይል አቅርቦት ሙሉ ለሙሉ ለአካባቢ ተስማሚ ናቸው።
የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂያችን እኛን ብቻ ሳይሆን ጎረቤት አገራትንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። በታላቁ የህደሴ ግድብ ከደለል ለመታደግ በተከናወኑ በርካታ የአካባቢ ጥበቃ ተግባራት ጎረቤት አገራትን ከድንገተኛ ጎርፍ እንዲሁም ከደለል ይታደጋቸዋል። ከዚህም ባሻገር የወንዙ ፍሰት ዓመቱን ሙሉ ተመጣጣኝ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ የወንዙን ዘላቂ ህይወትም አስተማማኝ ያደርገዋል።
በአካባቢ ጥበቃ ስራ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ መሆን በመቻሉ አሁን ላይ የአካባቢ ነዋሪዎች ጉትጎታና ቅስቀሳ አያስፈልጋቸውም። አርሶና አርብቶ አደሩ በየዓመቱ ለአካባቢ ጥበቃ ስራ ጊዜ ሰጥቶ ሁሉም በነቂስ ወጥቶ በፍቃደኝነት በመተግባር ላይ ይገኛል። በዚህም በበርካታ የአገራችነ አካባቢዎች በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች በርካታ ወጣቶችና ሴቶች ተጨማሪ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። ከዚህ ባሻገር ምርትና ምርታማነት በማደጉ የአገሪቱ የግብርና ውጤት እጅጉን ተሻሽሏል። በዚህም የአርሶ አደሩ ገቢ በጣም ተሻሽሏል።
በትግራይ ክልል በተከናወነ ውጤታማ የአካባቢ ጥበቃ ስራ አገራችን በዓለም ዓቀፍ መድረክ በአካባቢ ጥበቃ ስራ የወርቅ ተሸላሚ እንድትሆን አስችሏታል። ይህ ታላቅ ስኬት ነው። በትግራይ ምስራቃዊ ዞን በክልተ አውለአሎ ወረዳ “የአብረሃ ወአፅብሃ” ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪዎች እጅግ የተጎሳቆለ መሬትን ወደ ለምነት መቀየር ችለዋል። ይህ አካባቢ እጅግ የተጎሳቆለና ለምነቱን ያጣ መሬት የነበረ ሲሆን ነዋሪው ለዘመናት በእርዳታ የኖረ ህዝብ ነበር። ይሁንና የአካባቢው ነዋሪዎች ከ30 ዓመት በላይ የተፋሰስ ልማትን ማካሄድ በመቻላቸው አካባቢያቸውን ወደምድረ ገነትነት መቀየር ችለዋል፡፡ ይህ ነው ተምሳሌትነት! ሁላችንም ኮርተናል። ይህን መልካም ተሞክሮ ወደሁሉም የአገራችን አካባቢዎች እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ልናሰፋው ይገባል። የአሁኑ ትውልድ ውጤታማ የሆንበትን ይህን የአካባቢ ጥበቃ ስራ አጠናክረን በማስቀጠል የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይኖርብናል። በአገር ደረጃ ማሳካት የተቻለውን የምግብ ሰብል ምርት በቤተሰብ ደረጃ ለመድገም የአካባቢ ጥበቃ ስራችንን ማጠናከር አማራጭ የሌለው ነገር ነው።