Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዴሞክራሲያዊ የህዝቦች አንድነት

0 322

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዴሞክራሲያዊ የህዝቦች አንድነት

 

አባ መላኩ

 

በማህበራዊ ድህረ ገፆችና በግል ጋዜጦች የሚወጡ አንዳንድ አስተሳሰቦች ምንጫቸው  ከትምክህተኛ እና ጠባብነት ካምፖች ነው። ይዘታቸውም ሲፈተሽ የተለያዩ መሠረተ ቢስ ወሬዎችን በማራገብና የህዝቡን ሠላም በማናጋት በአቋራጭ ሥልጣን መያዝን ግብ አድርገው መንቀሳቀስ ነው። አስተሳሰቦቹ መሠረተ ቢሶችና የማይጠቅሙ የሚያደርጋቸው ነጥብ አነሰም በዛም እንደየአቅማቸው የአገራችን ህዳሴ ጉዞን በማደናቀፍ አሉታዊ ተጽዕኖ ስለሚኖራቸው ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት አስተሳሰቦች በአደባባይ ወጥቶ መጋለጣቸው አስፈላጊ ቢሆንም በልካቸው የልማታችንና የመልካም አስተዳደር ሥራዎቻችን ጎታች መሆናቸው አይቀርም፡፡

 

እርግጥ ነው፤ በአንድ አገር ለህዝቦች ብልፅግና እና መልካም አስተዳደር የአስተሳሰብ ልዩነቶችና ሐቀኛ ክርክሮች አስፈላጊ ነገሮች ናቸው፡፡ አስፈላጊ የሚሆኑት ግን በሥነ አመክንዮ የተደገፉና ለሰፊው ህዝብ ወገንተኝነት ያላቸው እስከሆኑ ድረስ ብቻ ነው፡፡

 

አንድ ሐሳብ ወይም ተግባር በበቂ ምክንያት ካልተደገፈና ለህዝቡ ጥቅም ከሌለው ዋጋ አይኖረውም። ሊኖረውም አይችልም፡፡ በብዛት በትምክህተኛው ርዝራዥ ኃይሎችና በዚህ ኃይል በተደናገሩ ጥቂት ዜጎች ከሚራገቡት አስተሳሰቦች “የጎሣ ፖለቲካ፣ የግዛት አንድነት፣ አንድ አገር፣ ብሔራዊ ቋንቋ…” ወዘተ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

 

በሌላ በኩል መጠኑ ይለያይ እንደሆነ ነው እንጂ ሁሉንም ህዝቦች ሲጎዳ የኖረው ገዥ መደብ ሆኖ ሳለ አንድ ህዝብ በሌላ ወንድም ህዝብ ላይ የፈፀመው ጭቆና እንደነበረ አስመስሎ በማቅረብ በህዝብ መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ሠላምና ዴሞክራሲ ለማናጋት ከጠባብነት አስተሳሰብ ካምፕ የሚመነጩ የጥፋት ጥሩምባዎች ሲነፉ ይደመጣል።  

 

በመሠረቱ ጠባብነት ራሱን ችሎ የተፈጠረ ሳይሆን ከትምክህተኝነት ራሱን ለመከላከል የተቆፈረ ምሽግ ነው፡፡ ከፍ ሲል የተገለፁትን ነጥቦች አንድ በአንድ ከማየታችን በፊት ስለአገራችን ታሪክ በአጭሩ መፈታተሽ ይጠቅማል፡፡

 

የኢትዮጵያ ታሪክና የህዝቦቿ ግንኙነት በጎና መጥፎ ገፅታዎች አሉት፡፡ በጎ ገፅታዎች የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ያዳበሯቸው እሴቶችና ገድል ናቸው፡፡ ህዝባችን በረዥም ጊዜ ሂደት የምንነትና የእምነት መወራረስ ፈጥረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በተለያዩ ጊዜያት አገራችንን ለመቆጣጠር ብሎም ለመቀራመት የመጡትን የውጭ ወራሪዎች በጋራ ተዋግቶ ድል በማድረግ አገራችንን ከባዕድ ገዥዎች ከመጠበቅ ባሻገር ከባዕድ ገዥዎች የማይሻሉ የውስጥ አምባገነኞችን ታግለው አስወግደዋቸዋል፡፡

 

በሌላ በኩል የገዥ መደቡ በህዝቦች ግንኙነት ላይ መጥፎ አሻራ ጥሎ አልፏል። በህዝቦች ላይ ይደርስ በኖረው ብሔራዊ ጭቆና ምክንያት ዛሬ ማስታወስ ባያስፈልግም መጠነ ሰፊ ጥፋቶች ደርሰዋል። ማስታወስና መተንተን ባያሻም የታሪክ ዋና ጥቅም የትናንትናን አውቀህ ጥፋቶቹን በማረም የዛሬና የነገ ህይወት ማስተካከል ስለሆነ ታሪካችንን ማወቁ ይበጃል፡፡

 

በአንድ የታሪክ አጋጣሚ በትረ ሥልጣን የጨበጠው ትምክህትኛው ኃይል የአገሪቱን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነታቸውንና ኢትዮጵያዊነታቸውን ለማጎልበት ሲጠይቁና ሲታገሉ ከማስተናገድ ይልቅ በራስ መነፀር ብቻ እንዲያልፉ  በርከት ያሉ ቅድመ ግዴታዎችን ሲያስተናግዱ ኖረዋል፡፡ ከዚህ አልፎ አንዳንድ  ወገኖቻችን አፅመ ርስታቸው በሆነው አገር “መጤ” ወይም “ከወንዝ የወጣ” ሌሎች ደግሞ “በኢትዮጵያ የሚገኙ” እየተባሉ በአገራቸው ጉዳይ ያገባናል እንዳይሉ ተደርገው ቆይተዋል። ገዥ መደብ ሥልጣኑን ዘለዓለማዊ ለማድረግ በማሰብ ሌሎች ብሄሮችና ብሄረሰቦችን በራሱ አምሳል ብቻ ለመቅረፅ ያረቀቀውና ይታገልለት የነበረው ፖሊሲ ምክንያት ህዝብን እርስ በርስ በማጋጨት የጥርጣሬ መንፈስ ከፈጠረ በኋላ ከፋፍሎ ይገዛ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ የገዥ መደብ “እኛን ምሰል ፖሊሲና ስትራቴጂው” ለረዘም ያለ ጊዜ ብሔራዊ ጭቆናን መፊጠርና ማስቀጠል በመቻሉ፤ በህዝቦች መካከል ልዩነትና ጥርጣሬ እንዲኖር በማድረግ አገራችንን ለከፍተኛ እልቂትና የመበታተን ጫፍ አድርሶ የነበረ በመሆኑ ፖሊሲው በከፊል የተሳካ ነው፡፡ በዘመነ ገዥ መደብ ግዴታ እንጂ መብት የሚባል አልነበረም፡፡ መብት ከሌለ ደግሞ እኩልነት አይኖርም፡፡ እኩልነት ከሌለ ደግሞ የጋራ ተጠቃሚነት አይታሰብም፡፡ እኩልነትና የጋራ ተጠቃሚነት በሌሉበት ሠላም ሆነ ልማት አይኖርም፡፡ የዘመኑ ሀቅ የነበረው ተወልዶ ሌላን መምሰልና ሰርቶ ለገዥ ማስረከብን የተሰላቸ ህዝብ ለመብቱ ፍለጋ በ1960ዎች ጫፍ እስከ ጫፍ ተነስተዋል፡፡ ጥያቄው ስለህዝብ ሉዓላዊነትና ስለሃብቱ እኩል ተጠቃሚነት የነበረ ቢሆንም የግብረ መልሱ ቋንቋ ኃይል ብቻ ስለነበር ሠላም ጠፍቶ ልማት አይታሰቤ ሆኖ ቆይቷል፡፡

በኃይል አንድነት አይመጣም፡፡ ሊመጣም አይችልም፡፡ አብሮነት የህዝብ ምርጫ እንጂ የገዥዎች ይሁኝታ አይደለም፡፡ በገዛ አገራቸው ሠላም፤ ልማትና ዴሞክራሲ ቀርቶ በየአካባቢያቸው አሰቃቂ ግፍ የደረሰባቸው ብሔሮችና ብሔረሰቦች ነፃ አውጭ ግንባር ቢፈጥሩ ንቃተ መብታቸው ማደጉን እንጂ አብሮነት አለመፈለጋቸውን አያሳይም፡፡ ንቃተ መብታቸው አደገ ሲባል ያኔ የገዥ መደብ ዘመን ከነበረ አንድነት መለያየቱ እጅግ የተሻለ ስለነበር ነው፡፡ መለያየቱ የተሻለ ነበር ማለት ግን ከመለያየት የበለጠ አማራጭ አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ ትምክህተኛው ገዥ መደብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አስወግዶ በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተና ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ያለው የህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት አይደርስ ይመስል የነበረው ግን የተደረሰ የብልሂ አማራጭ ነው፡፡ ይባስ ብሎ ትምክህተኛው ኃይል መልሶ ቢነግስ እንኳ ራሱን ብቻ ይወክላል እንጂ ኢትዮጵያንም ሆነ ኢትዮጵያዊነትን ሊወክል አይችልም፡፡

 

አንድ ህዝብ እንደ ህዝብ ራሱን መተካት አለበት፡፡ አንድ ህዝብ እንደ ህዝብ ራሱንና ህይወቱን ማጣት የለበትም፡፡ ለዚህም ነው ረገጣ የበዛባቸው የኢትዮጵያ ህዝቦች የየራሳቸውን ነፃ አውጭ ግንባር የመሠረቱት፡፡ ግንባሮቹ የተለያየ ዓላማ ነበራቸው፡፡ መገንጠልን የመረጡ ግንባሮችም ሆነ አብሮነትንና ኢትዮጵያዊነትን ሳይፈልጉ ቀርቶ ሳይሆን ለብዙ አሥርት ዓመታት መብታቸው በሙሉ ስለተነፈጉ ነው፡፡ አንድ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር ስላልመሠረተ የተለየ የኢትዮጵያ አንድነት ፍቅር ነበረው ማለት አይደለም፡፡ ሊኖረውም አይችልም፡፡ ያ ነፃ አውጭ ግንባር ያልመሠረተ አካል ለጊዜው የነበረው ማህበረ ፖለቲካዊ አደረጃጀት ግንባርን ለመመሥረት አላስቻለውም አሊያም በተነፃፃሪም ቢሆን መብቱን አላጣም ማለት ነው፡፡ ጭቆናን ለማስወገድ ነፃ አውጭ ግንባር ሳይመሠረት በራሱ መንገድ የታገለም አለ፡፡

 

ነፃ አውጭ ግንባሮችን ሲመሠርቱ የተለያየ ዓላማ ነበራቸው፡፡ በብዙዎች ሲደገፍና ሲታገሉለት የነበረ ዓላማ የመገንጠል አማራጭ ሆኖ በአንዳንዶች ሲራመድ ኖሯል። ከሻዓቢያ ውጭ የመገንጠል ጥያቄ የነበራቸው ነፃ አውጭ ግንባሮች ሁሉ አልተሳካላቸውም፡፡ ምክንያቱም ብሔራዊ ጭቆናን መገርሰስ እንጂ መገንጠል ህዝብ የሚመርጠው አማራጭ አልነበረም፡፡ በኢሕአዴግ የታመነበትና በሂደት በሌሎች ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች የተደገፈው ሁለተኛው አማራጭ ሁሉንም ጭቁን ህዝቦች ነፃ አውጥቶ ሠላምና ዴሞክራሲያዊ የህዝቦች አንድነት ማረጋገጥ እንዲሁም በየደረጃው ዜጎች የሚሳተፉበት ተመጣጣኝና ቀጣይነት ያለው የልማት ተጠቃሚነት የሚል ነበር፡፡

 

የህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነትና እኩል ተጠቃሚነት ሲከበር በህዝብ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ለህዝቦች አንድነት ሲባል በአገራችን ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ጀምሮ የሰዎች የበላይነትና የብሔር ጭቆና ታሪክ ከመሆናቸው ባሻገር አስተማማኝ ሠላም፣ ታዳጊ ዴሞክራሲና ህዝቡ በየደረጃው ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚሆንበት ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ምጣኔ ሃብት ሊገነባ ችሏል። ዛሬ በተባበረ የህዝቦች ክንድ ህዳሴያችን እውን ሆኗል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy