Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዶክተር ነገሪ ሌንጮ፤

0 662

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

• ከወሰን ጋር ተያይዘው የተፈጠሩት ግጭቶች ውስጣዊ ችግሮች ናቸው

• በዓላት ላይ የፖለቲካ አጀንዳ ማራመድ የህዝቡ ፍላጎት አይደለም

• ከተለቀቀው ተዘዋዋሪ ፈንድ የቀረው ገንዘብ ዘንድሮ ይለቀቃል አሉ!

ከወሰን ጋር ተያይዘው በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶች በውስጣዊ ችግር ሳቢያ የተከሰቱ መሆናቸውን አምኖ በየደረጃው ያለው አመራር ውስጡን ሊፈትሽ ይገባዋል ሲሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አስታወቁ፡፡ ህዝባዊ በዓላት ህዝቦች በሰላምና በአንድነት የሚያከብሯቸው እሴቶቻቸው መሆናቸውንም ገለጹ፡፡

ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ትናንት በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ይከሰቱ የነበረ ሲሆን፣ በቅርቡ ደግሞ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ብሄራዊ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ወራትን ያስቆጠረ ግጭት ተፈጥሯል፡፡

ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እየተፈታ ነው ተብሎ ሲጠበቅ ወደ ከፋ ችግር አምርቶ የዜጎች ህይወት እንዲያልፍ ምክንያት መሆኑን እና ዜጎች ከአካባቢዎቻቸው መፈናቀላቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ይህን መሰሉ ግጭት የፌዴራል ሥርዓቱን ዓላማና መርህ እንዲሁም የህዝቦችን ዘላቂ ፍላጎትና ራዕይ የሚቃረን መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በውስጣዊ ችግር ሳቢያ ዜጎችን ለሞትና ለመፈናቀል የሚያደርስ ግጭት በተደጋጋሚ ሲከሰት ማየት እጅግ አሳዛኝ ነው ያሉት ዶክተር ነገሪ፤ ድርጊቱ በአፋጣኝ መቆም አለበት ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡ አዋሳኝ አካባቢው ሰፊ ድንበር እንደመሆኑ አልፎ አልፎ የሚታዩ ትንኮሳዎች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ በህገ ወጥ ድርጊቱ እየተሳተፉ የሚገኙ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አስጠንቅቀዋል፡፡

ከወሰን ጋር በተያያዘ የተፈጠሩት ችግሮች ትክክለኛ መንስኤዎች ምን እንደሆኑ ወደፊት ተጣርቶ እንደሚገለጽ በመጠቆም፤ የዜጎችን ህይወት እስከመቅጠፍ የደረሱት ሁኔታዎች አመራሮቹ ሊያስቀሯቸው የሚችሉ እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ‹‹የችግሩን መንስኤ ወደ ውስጥ ለመመልከት፣ ችግሩንም ለዘለቄታው ለመፍታት መረባረብ ይገባናል›› ብለዋል፡፡

እንደ ኃላፊ ሚኒስትሩ ገለጻ፤አዋሳኝ ክልሎች ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች እየሰሩ ሲሆን፣ የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት እየሰሩ ናቸው፡፡ በቀጣይ የሰላም ኮንፈረንስ ይካሄዳል፡፡

ሆን ብለው አደናጋሪ መረጃዎችን በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች በመልቀቅ ግጭቶችን ለማባባስ አልመው የሚሰሩ አካላት ከአፍራሽ ተግባራቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በተያያዘ ዜና አምና በኢሬቻ በዓል አከባበር ወቅት የተፈጠረው አሳዛኝ ክስተት መቼም መደገም እንደሌለበትም ኃላፊ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡ህዝባዊ በዓላት የሰላምና የአንድነት መገለጫዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፣‹‹ፈጣሪን በማስታወስና በማመስገን በሚከበሩ በዓላት ላይ የፖለቲካ አጀንዳ ማራመድ የህዝቡ ፍላጎት አይደለም›› ሲሊም ተናግረዋል፡፡

‹‹ዛሬ ደመራ፣ ነገ የመስቀል በዓል ይከበራል፡፡ መስከረም 21 ቀን 2010 .ም ደግሞ የኢሬቻ በዓል ይከበራል›› ያሉት ዶክተር ነገሪ፣በዓላት የሚከበሩት ፈጣሪን ለማስታወስ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ህዝቦች በሰላምና በአንድነት የሚያከብሯቸው የሰላምና የአንድነት እሴቶቻቸው መገለጫዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ዶክተር ነገሪ፤ የኢሬቻ በዓል የኦሮሞን ህዝብ ወግና ባህል በጠበቀ መልኩ እንዲከበር፤ አባገዳዎች አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን፣ ሥነ ሥርዓቱ በሚካሄድበት ቦታ የነበረውን የአደጋ ተጋላጭነት ስጋት ያስወገዱ ተግባሮች መከናወናቸውን፣ በመንግሥት በኩል አስፈላጊ ዝግጅቶች እየተደረጉ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

እንደ ኃላፊ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የመስቀል እንዲሁም የገዳ ሥርዓት አንድ አካል የሆነው የኢሬቻ በዓላት በዩኔስኮ ቋሚ ቅርስነት ተመዝግበዋል፡፡ በዓላቱ የአንድ የተወሰነ ህዝብ ወይም አገር ልዩ በዓል መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የውጭ አገር ዜጎችን የሚያሰባስቡ በመሆናቸው ህዝባዊ መድረኮቹን በአግባቡ መጠቀም ይገባል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዶክተር ነገሪ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ አጠቃቀም ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች በወጣቶች ላይ መጉላላት እየደረሰ መሆኑ ግንዛቤ እንደተያዘ ገልጸዋል፡፡ወጣቶች ተደራጅተው ቁጠባ ከጀመሩ ከስድስት ወራት በኋላም ብድር ያተለቀቀላቸው እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ዶክተር ነገሪ ገለጻ፤ ከተዘዋዋሪ ብድር ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ክፍተት በመሙላት ዘንድሮ መንግሥት በተሻለ መልኩ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ባለፈው ዓመት ከተለቀቀው ተዘዋዋሪ ፈንድ የቀረው ገንዘብ ዘንድሮ ጊዜውን ጠብቆ ይለቀቃል ብለዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥር 50 መድረሱንም ጠቁመው፤ ከተቋማቱ የሚወጡ ተማሪዎችን ሥራ ለማስያዝ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ይሰራልም ብለዋል፡፡

ዘላለም ግዛው

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy