የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሃላፊ ዶናልድ ያማማቶ ጋር ተወያዩ።
በውይይታቸውም በሁለትዮሽና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገዋል።
ዶክተር ወርቅነህ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለው የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት የበለጠ እንዲሰፋ ኢትዮጵያ እንደምትፈልግ ገልፀዋል።
አያይዘውም ሁለቱ ሀገራት በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን የትብብር እንቅስቃሴ የበለጠ ለማጠናከር ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን ጠቁመዋል።
ያማማቶ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ እና አሜሪካ ግንኙነት መጠናከር የማዕዘን ድንጋይ ናት ብለዋል።
አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር የነበረውን የጠበቀ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ዝግጁ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በተያያዘ ዜና ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከኩዌት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ ሳባህ አል-ካሊድ አል-ሃማድ አል-ሳባህ ጋር በኒውዮርክ ተገናኝተው በሁለትዮሽ እና በባህረ ሰላጤው ሀገራት ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
ሼክ ሳበህ አል-ካሊድ ኢትዮጵያ ለተያያዘቸው የልማት እንቅስቃሴ ኩዌት ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል ገብተዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ የኩዌት ጠንካራ አጋር ሆና እንደምትቀጥል ነው ያነሱት ሚኒስትሩ፥ በቅርቡ በባህረ ሰላጤው ሀገራት የተፈጠረው ችግር እንዲፈታ ለተጫወተችው ሚና ምስጋና አቅርበዋል።
የሁለቱን ሀገራት የጋራ የሁለትዮሽ ስብሰባ በአዲስ አበባ በቅርቡ ለማካሄድ ሚኒስትሮቹ መስማማታቸውን፥ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።