ethiopian news

Artcles

ግጭትን ማባባስ ከባድ ዋጋ ያስከፍላል!

By Admin

September 27, 2017

ግጭትን ማባባስ ከባድ ዋጋ ያስከፍላል!

ዳዊት ምትኩ

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሊ አንዳንዳንድ አካባቢዎች ህዝቦችን የማይወክል ጊዜያዊ ግጭት ተፈጥሮ እንደነበር እናስታውሳለን። በአሁኑ ወቅት ፌዴራል መንግስትና ሁለቱ ክልሎች የተፈጠረውን ጊዜያዊ ግጭት በዘላቂነት ለመቅረፍ ጥረት እያደረጉ ነው። በተቃራኒው በኩልም የጥበትና የትምክሀት ሃይልና ነገር ቀጣይ ሚዲያው ግጭቱን ለማባባስ ፀረ ሰላም እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ነው።

ያም ሆኖ ሁለቱም አካላት ግጭትን ማባባስ የዜጎችን ህይወት ከመቅጠፍ፣ ሰላምና መረጋጋታቸውን ከማናጋት በስተቀር ምንም ዓይነት ጥቅም እንደሌለው ማወቅ አለባቸው። የሁለቱም ክልል ወንድማማች ህዝቦች ከጠባቦች ጠብ አጫሪ ፍላጎቶች ራሳቸውን በማራቅ ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ይኖርባቸዋል።

ግጭት በዓለም ላይ ባሉ ማህበረሰቦች ውስጥ የሚከሰት ጉዳይ ነው። የሰው ልጅ ማህበራዊ መስተጋብር እስካለ ድረስ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ውስጥ መኖሩ አይቀሬ ነው። ለነገሩ የሰው ልጅ ከራሱ፣ ከቤተሰቡ፣ ከማኅበረሰቡ አሊያም ከተፈጥሮ ጋር መጋጨቱ ትናንት የነበረ፣ ዛሬም ያለና ነገም የሚኖር ክስተት ነው።

እንኳንስ በአንድ ቤተሰብ፣ ቀዬ፣ መንደር፣ አካባቢ፣ አገር፣ አህጉርና ዓለም ውስጥ የተለያዩ የተፈጥሮ ፀጋዎችን በጋራ እየተጠቀመ “አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ” በሚል መተሳሰብ ውስጥ የሚኖረው የሰው ልጅ ቀርቶ፤ ወንዝ ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ግዑዛን ድንጋዩችም ቢሆኑ በተፈጥሮ ዑደት መዘውር ሂደት ውስጥ ሊጋጩ ይችላሉ። እናም ግጭት ባህሪያዊ የተፈጥሮ ህግ ነው።

ዋናው ቁም ነገር የግጭቱን መንስዔ አጥርቶ ከማወቁ ላይ ነው። መንስዔው ምናልባትም ዓለማችንን በአያሌው እየፈተናትና እየናጣት ያለው የተፈጥሮ ሃብቶች እጥረት ወይም በህዝቦች መካከል ለዘመናት ተጠብቆ የቆየውን በሰላም አብሮ የመኖር እሴትን ጥቂቶች ከራሳቸው ጥቅም አኳያ በመመዘን የሚፈጥሩት ፍላጎት ሊሆን እንደሚችል አያጠያይቅም።

ታዲያ ይህን እውነታ ወደ አገራችን በተለይም ወደ ከሁለቱ ተጎባራች ክልሎች አኳያ ስንመለከተው ግጭቱ በታጣቂዎችና በግለሰቦች ግላዊ ፍላጎት ምክንያት ለሁለተኛ ጊዜ አገርሽቷል። በዚህም ምክንያት በሁለቱም ወገኖች ውስጥ ያሉ ትጥቅ የያዙና ጥቂት የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት ሃይሎችና ግለሰቦች በድንበር ማካለል ሰበብ ሰላምን አውከዋል። በዚህም ሳቢያ የፌዴራል የፀጥታ ሃይሎች በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገቡ ምክንያት ሆነዋል።

ይሁን እንጂ እንደ እኛ ባለ ራሱን በራሱ በሚያርምበትና የአሠራር ስርዓት በተዘረጋበት ፌዴራላዊ ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች ውስጥ ከድንበር ማካለል ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችል ግጭት ሊኖር አይችልም። ሁሉም ነገር መፍትሔ አለው።

ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓቱ በአጎራባች ክልሎች ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት የሚከተለው የራሱ መንገድ አለው። አገራችን ለፌዴራላዊ የመንግሥት ሥልጣን አወቃቀር ጀማሪ በመሆኗና ባለፉት ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ሥርዓቶች ውስጥ የግፍ ቀንበር ተጭኖበት የነበረው የአገራችን ህዝብ ከፌዴራላዊ ሥርዓቱ ለጋነት አኳያ ያለው ግንዛቤ በሚፈለገው መጠን ያልዳበረ በመሆኑ በተለያዩ አካባቢዎች ሊፈጠሩ የሚችሉ ተግዳሮቶች መኖራቸው አይቀርም። ሆኖም ተግዳሮቶቹ ሥርዓቱ ራሱን በራሱ እንዲያርም እንዲሁም ከችግሮቹ ትምህርትና ተሞክሮ በመውሰድ እንዲጎለብት የሚያስችለው ነው።

እርግጥ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓቱ በአጎራባች ክልሎች ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት የሚከተለው የራሱ መንገድ አለው። ለነገሩ አገራችን ለፌዴራላዊ የመንግሥት ሥልጣን አወቃቀር ጀማሪ በመሆኗና ባለፉት ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ሥርዓቶች ውስጥ የግፍ ቀንበር ተጭኖበት የነበረው የአገራችን ህዝብ ከፌዴራላዊ ሥርዓቱ ለጋነት አኳያ ያለው ግንዛቤ በሚፈለገው መጠን ያልዳበረ በመሆኑ በተለያዩ አካባቢዎች ሊፈጠሩ የሚችሉ ተግዳሮቶች መኖራቸው አይቀርም። ሆኖም ተግዳሮቶቹ ሥርዓቱ ራሱን በራሱ እንዲያርም እንዲሁም ከችግሮቹ ትምህርትና ተሞክሮ በመውሰድ እንዲጎለብት የሚያስችለው እንጂ፤ አቶ ኢስማኤል በአገም ጠቀም የአፃፃፍ ዘዴ እንደገለፁት በብሔር ላይ የተመሠረተ

ፌዴራላዊ ሥርዓቱ መቼም ቢሆን ለግጭት መንስኤዔ ሊሆን አይችልም። ሥርዓቱ ለአገራችን ህዝቦች የመቻቻልና የአብሮነት ዋስትና እንጂ የልዩነትና የግጭት መንስዔ አይደለም። በራሳቸው ፈቃድ አንድ የጋራ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት ቃል ገብተው ህገ መንግሥቱን ዕውን ያደረጉት የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ናቸው። ስለሆነም የአገራችን ህዝቦች በራሳቸው ሙሉ ፈቃድ የመሠረቱትን ፌዴራላዊ ሥርዓት መልሰው የግጭት ምክንያት ሊያደርጉት ይችላሉ ብሎ ማሰብ ጤናማ ምልከታ አይሆንም።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ከግጭት የሚሰንቁት ምንም ዓይነት ተስፋ የላቸም። ተስፋቸው የተመሠረተው ከሠላም፣ ከልማትና ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ነው። ከግጭት የሚጠቀም ህዝብ ባለመኖሩም እነዚህን ተስፋዎች በማይነቃነቅ ፅኑ መሠረት ላይ ለማኖር አስተማማኝ ሰላም መፍጠር የግድ ነው።

በመሆኑም ለበርካታ ዓመታት በሠላም የኖሩት የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝቦችም እንደ ማንኛውም ህዝብ ጥቅማቸው ያለው ከሠላም እንጂ ከግጭት አለመሆኑን ይገነዘባሉ።

ስለሆነም በሁለቱ ክልላዊ መንግሥታት ህዝቦችም መካከል ግጭት የሚፈጠርበት መሠረታዊ ሁኔታ ሊኖር አይችልም። በሁለቱም ወገኖች ውስጥ ጥቂት በአመራር ላይ ያሉ ግለሰቦች አሊያም ታጣቂዎች የራሳቸውን ፍላጎት ለማራመድ በድንበር አካባቢዎች ግጭት መፍጠራቸው ለዘመናት በፍቅር አብረው የኖሩትን የሁለቱን ተጎራባች ህዝቦች ፍላጎት የሚወክል አይደለም።

የትኛውም የህበረተሰብ ክፍል ከሚፈጠረው ግጭት ተጠቃሚ አይሆንም። የሚያስከፍለው ዋጋም ከባድ ነው። ግጭት በልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግሥት መሪነት በልማት ላይ ሌት ተቀን በመሳተፍ ህይወቱን ለመለወጥ የሚያስበውን የየክልሎቹን ህዝቦች የሥራ ሞራል የሚሰልብ ነው። ኢንቨስትመንታቸው የውጭ ባለሃብቶችን እንዳይስብም ማነቆ ይሆናል።

የአገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት ውስጥ ክልሎቹ ሊወጡት የሚገባቸውን የተናጠልና የአብሮነት ሚናን ያቀጭጫል። በሁለንተናዊ አገራዊ ለውጥ ላይም እንቅፋት ይሆናል። እንዲህ ዓይነቶቹ ከድንበር መካለል ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ዘላቂ ጥቅሞችን የሚያኮሰምኑ ግጭቶችን ዘላቂ በሆነ መንገድ መዝጋት ይገባል። አላስፈላጊ በመሆኑም የሁለቱም ክልል ህዝቦችም ይሁኑ የሚመለከታቸው አካላት በህገ መንገስቱ መሰረት ተገቢ መፍትሔ ለመስጠት ጊዜ ሊወስዱ አይገባም። ግጭትን በማባባስ ላይ የተሰለፉ ወገኖችን በአፋጣኝ አጣርቶ ህግ ፊት ማቅረብም ያስፈልጋል።