Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጽንፈኞች ከሁከትና ብጥብጥ ርቀው አያውቁም!

0 461

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጽንፈኞች ከሁከትና ብጥብጥ ርቀው አያውቁም!

አባ መላኩ

ከፌዴራል ስርዓታችን የተማርነው  ትልቅ ነገር የተለያዩ አስተሳሰቦች፣ ቋንቋዎች፣ ማንነቶች፣ ባህሎች፣ ወዘተ የሚታዩባትን  አገር   አቻችሎ ማስተዳደር  እንደሚቻልና   በአጭር  ጊዜ ውስጥም  ወደ ልማትና ዕድገት ማምራት እንደሚቻል በተግባር አሳይቶናል። እስካሁን  ባለው ሁኔታ  ኢትዮጵያ  አስተማማኝ  ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ  ስርዓት  ማረጋገጥ የቻለችውና ፈጣን  የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ  የቻለችው በዚህ የፌዴራል ስርዓት ብቻ  ነው።

በአገራችን  የሚስተዋሉ    ሁሉም ስኬቶች  መሰረታቸው ይህ የፌዴራል ስርዓት መሆኑን  መገንዘብ  ዋንኛው  ጉዳይ  ነው። የፌዴራል ስርዓታችን አገራችን ባለፉት 26 ዓመታት በስኬቶች  ላይ እንድትረማመድ  አስችሏታል።  አገሪቱን ከብተና ታድጓል፣ የብሄሮች፣ኘ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን እኩልነትን አረጋግጧል፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመዘገብ አድርጓል፣ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና  ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት  እንዲፈጠር  አድርጓል፣ ወዘተ ሁኔታዎችን አመቻችቷል።   አሁን ላይ  የፌዴራል ስርዓታችን ለአገራችን ባስገኘው ጥቅም ሳቢያ  አገራችን ለሌሎች መልካም ተሞክሮን እስከመሆን  ደርሷል።  

አንዳንዶች በጥላቻ ላይ ተመርኩዘው   የአገራችንን የፌዴራል ስርዓት ለማጣጣል  ሲሯሯጡ ተመልክተናል።  ማንም የመሰለውን ሃሳበ መሰንዘር መቻሉ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ቢሆንም ያለበቂ መረጃ  አገርንና ህዝብን ሊጎዱ የሚችሉ አስተያየቶች  መሰንዘር  ግን ተገቢ አይመስለኝም። የግጭቶች መከሰት ተፈጥሮዊና አይቀሬ ነው።  አይደለም  በአገር  ደረጃ በቤተሰብ ደረጃም  ቢሆን  መቼም  ቢሆን  ልዩነት  መፍጠሩ፣  አለምግባባት  መከሰቱ  አይቀርም። ዋናው ነገር ግጭት መቀስቀሱ ሳይሆን ግጭትን መፍታት መፍታት መቻል ነው።  

በአገራችን  የሚታዩ  ግጭቶች  መንስዔ   የፌዴራል ስርዓት  ስለተከተልን  አይደለም። እውነት እውነቱን እንነጋገር ከተባለ  በአንዳንድ  አካባቢዎች   የተከሰቱ  ግጭቶችን  ስንመለከታቸው  መንስዔቸው  አገራችን  የተከተለችው የፌዴራል ስርዓት  ሳይሆን   የተለያዩ  አካላት  የፌዴራል ስርዓቱን  የተረዱበት ሁኔታ ነው።  ባለፉት ሥርዓቶች  የነበሩት  አሀዳዊ ስርዓቶች  /Unitary States/ በአንዳንድ አካባቢዎች  ብቻ ሳይሆን በመላ አገሪቱ  በቀውስ እንድትመታ አድርጓት   እንደነበር  የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።  

አህዳዊው  ስርዓት   ጭቆናን  በማንገስ   በህዝቦች መካከል  ፍትሃዊ የሆነ የሀብትና የስልጣን ክፍፍል  እንዳይኖር   በማድረግ  የማንነት ጥያቄዎችን   በማፈን  አገራችንን ለአስከፊ የዕርስ በርስ ጦርነት ዳርጓት ቆይቷል። አገራችን እነዚህን ችግሮች የተሻገረቻቸው  የፌዴራል ስርዓት መከተል በመቻሏ ነው።  የፌዴራል ስርዓቱ  ለአገሪቱ  የቆዩ ህመሞች  ሁሉ  ሃኪም ሆነ  እንጂ   የግጭት  መንስዔ  አልሆነም።  ግጭት በየትኛውም አገር በየትኛውም ጊዜ ሊከሰት የሚችል ነገር ነው። ይህ ሆኖ ሳለ ትናንሽ ግጭቶች  መከሰት የፌዴራል ስርዓቱ  ውጤት ተደርጎ መታሰብ የለበትም። ግጭቶች  እንዳይፈጠሩ  ማድረግ ዋንኛው  ቁምነገር ቢሆንም  ግጭቶች  ከተከሰቱ ብኋላም  ግጭቶች   እንዳይስፋፉ እንዲሁም በአፋጣኝ እልባት እንዲያገኙ ማድረግ መቻል ደግሞ  ሌላው ጉዳይ ነው።

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት  ግጭትና ያለመግባባት   አይደለም በአገር ደረጃ  በቤተሰብ አባላት መካከልም    ሊፈጠር የሚችል ክስተት እንደሆነ እየታወቀ ጽንፈኛው ሃይልና  አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች በአንዳንድ  የአገራችን አካባቢዎች   የሚከሰቱ ትናንሽ  ጉዳዮችን  በማጎን የፌዴራል ስርዓቱ  የግጭትና  የሁከት ምንጭ   አድርገው ለማቅረብ    ሲሯሯጡ ይታያሉ።  ለጽንፈኛው  ሃይል  ግጭት፣ ሁከትና  ነውጥ  እንዲቀሰቀስ፣ ከተቀሰቀሰም  ብኋላ  እንዲራገብ በማድረግ  የንጹሃን  ህይወት  እንዲቀጠፍ  አካል እንዲጎድል እንዲሁም  ንብረት እንዲወድም  የማይፈነቅሉት  ድንጋይ  የለም።  ግርግር ለሌባ … እንደሚባለው  ጽንፈኛው አካል  የቋመጠላትን  ስልጣን  ላገኝ እችላለሁ በሚል የተሳሳተ  ስሌት  ሁሌም  ከሁከትና  ግርግር  ጀርባ ጠፍቶ አያውቁም።

ሁከትን  በማራገብ፣  ህዝቦችን  ባልተገባ መንገድ በማነሳሳት ህይወት እንዲጠፋ ንብረት እንዲወድም ማድረግ እጅግ የወረደ ተግባር ነው። በዚህ የወረደ ተግባር ላይ  የተሰማራ ማንኛውም አካል  ከተጠያቂነት  ማምለጥ የለበትም።   ለአገራችን መልማትና  ዕድገት   የሚበጃት   ትናንሽ  ነገሮችን  እያነፈነፈ  ህዝቦችን  ለግጭትና  ሁከት የሚቀሰቅስ  ሳይሆን  ህዝብን  ለልማት  የሚቀሰቅስ   አካል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር  ኃይለማሪያም ማንኛውም አካል በፌዴራልም ሆነ በክልል  የመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ  ይህን ግጭት  ያባባሱ  አካላት  ከህግ ፊት ይቀርባሉ  ያሉት ነገር  ተተግብሮ  ማየት እንፈልጋለን።  

የፌዴራል ስርዓታችን  የህልውናችን መሰረት ነው። ማንም ይህን ስርዓት በሚጎዳ  ተግባር ላይ የተሰማራ አካል ከተጠያቂነት እንዲያመልጥ  ማድረግ  የለብንም።  የኢትዮጵያ  ሶማሌ ክልል  ፕሬዚዳንት  እንዳሉት  የኢትዮጵያ  ሶማሌ ህዝቦች  ተጎዱ በማለት  ኦሮሞዎችን ያጠቃ  ሁሉ ሶማሌዎችን አልጠቀመም፤   በተመሳሳይ  ኦሮሞዎች ተጎዱ በማለት   የኢትዮጵያ ሶማሌዎችን  ያጠቃ  ኦሮሞ  ሁሉ  ኦሮሞዎችን ጎዳ እንጂ  አልጠቀማቸውም  ያሉት ንግግር  ልቤ ውስጥ ገብቷል።   ምክንያቱም እነዚህ ሁለት ህዝቦች  አንድ ናቸው።

የኦሮሞና  የኢትዮጵያ  ሶማሌ  ህዝቦች ከልዩነታቸው ይልቅ በበርካታ ነገሮች  እጅግ የተሳሰሩ በኩታ ገጠም አካባቢዎች  የሚኖሩ ህዝቦች  ናቸው።  የአንዱ ህዝብ ጥቅምም ሆነ ጉዳት   የሌላው ህዝብ   የሆነበት ነው።  እነዚህ ሁለት ህዝቦች  በኃይማኖት፣ በባህል፣ በጋብቻ ወዘተ  ተሳስረዋል።  አንዱን ከአንዱ መለየት በማይቻልበት ሁኔታ አንድ ናቸው ማለት ይቻላል።  እንደእኔ እንደኔ  ለእነዚህ  ህዝቦች ግጭት  ዋንኛው ምክንያት  የጽንፈኛው  ሃይል  መርዘኛ ፖለቲካ እንዲሁም ህብረተሰቡና  አመራሩ  ስለፌዴራል ስርዓት  ያላቸው  ግንዛቤ  ያለመዳበር   ይመስለኛል። ከዚህ ባሻገር አንዳንድ ግለሰቦች ለህዝባቸው የተቆረቆሩ እየመሰላቸው ሳያውቁት  እጃቸውን  በግጭት ውስጥ    በማስገባታቸው ይመስለኛል።

ጽንፈኛ አካሎች ለፌዴራል ስርዓታችን አደጋዎች ናቸው።  ትምክህተኛው  ሃይል   የፌዴራል  ስርዓቱን ስኬቶች ለማኮሰስ  ሲል “ይህ የፌዴራል ስርዓት  ህዝቡን ከፋፍሏል፣ አገሪቱን ሊበትን ነው”  ወዘተ በማለት በማለት  ሲቀሰቅስ፤   ጠባቡ  ሃይል  ደግሞ አብረው የኖሩ ህዝቦችን ለመነጣጠል፣ ያለፈው ስርዓቶች አደረሱ የተባለውን በደል አሁን ላይ ለማወራረድ በማለት  አብሮነትን የሚሸረሽር ተግባራትን  ሲፈጽሙ ይታያሉ። የጽንፈኛው ሃይል ብቸኛ  ፍላጎት ህዝቦችን  በማጋጨት   ወደ ስልጣን መሰላል መሰቀል ነው።  እነዚህ ሁለት ጽንፎች ኢትዮጵያንና  ኢትዮጵያዊነትን የተለየ ትርጉም በመስጠት ሁከት ለመቀስቀስ  ጥረት  ቢያደርጉም  አልተሳካላቸውም። አዲሲቷ  ኢትዮጵያ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያዊ ዜግነት  በፍቃደኝነት እንጂ በሃይል የሚጫን  ያልሆነባት አገር ነች።  

 

በስህተት በዚህ ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት   በቀጣይ  ተገቢው  ትምህርት ሊሰጣቸው  ይገባል።  ከዚህ ውጭ ሆን ብለው ግጭት እንዲቀሰቀስ ውይም ግጭቱ እንዲባባስ  ያደረጉ  ማንኛውም አካላት  ተገቢው  እርምጃ  ሊወሰድባቸው ይገባል። በዚህ ግጭት ውስጥ  በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በውስጥም   ይሁን በውጭ ያሉ ማንኛውም አካሎች  ተጠያቂ መሆን መቻል አለባቸው። እነዚህ አካላት ለፌዴራል ስርዓታችን አልፎም ለአገራችን ቀጣይ ህልውና አደጋ በመሆናቸው ሁላችንም ተባብረን  ወደ ህግ ፊት ልናቀርባቸው ይገባል።   መንግስትም ይህን ገቢራዊ እንደሚያደርገው እርግጠኛ ነኝ።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy