Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፌዴራሊዝም ሰላምን ለማረጋገጥ ፅኑ መሰረት ጥሏል!

0 442

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፌዴራሊዝም ሰላምን ለማረጋገጥ ፅኑ መሰረት ጥሏል!

                                                              ቶሎሳ ኡርጌሳ

አዲሲቷ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት ሰላምንና መረጋጋትን በማረጋገጥ ረገድ የኢትዮጵያን ከፍታ እየጨመረ ነው። ስርዓቱ በህግ ተደግፎ ስራ ላይ ከዋለበት ካለፉት 22 ዓመት በላይ የሀገሪቱን አስተማማኝ ሰላም በፅኑ መሰረት ላይ ማኖር ችሏል። የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን የዘመናት ጥያቄዎችንም ሊመልስ በቅቷል።

የሀገራችን ፌዴራሊዝም ከዛሬ 26 ዓመት በፊት በአንድ ወገን የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታን ባላገናዘበ መልኩ የችግሮቹ መፍትሔ መገነጣጠል ነው ብሎ የሚያምን አስተሳሰብን፤ በሌላ በኩልም የሀገሪቱ መፍትሔ የሆነውን የፌዴራሊዝም ሥርዓት እንደ መበታተን አደጋ በመቁጠር ባረጀ እና ባፈጀ የአንድነት ስም የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ መብት ብሎም መፈቃቀድን ላይ የተመሰረተ አንድነታቸውን ለመድፈቅ የሚሞክሩ ኃይሎችን የተዛቡ አስተሳሰቦችን ማረም የቻለ ነው። እንዲያውም ሀገሪቱን ወደ ማያባራ ቀውስ ውስጥ ለመክተት አልመው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም አደብ ያስገዛ ነው።

በሀገራችን እውን መሆን የቻለው አስተማማኝ ሰላም ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ኃይማኖት የመከተል፣ በቋንቋቸው የመናገርና የመጻፍ እንዲሁም ባህላቸውንና እሴቶቻቸውን በነፃነት የመግለፅ መብቶቻቸውን ማረጋገጥ ችሏል። ይህም የዚህ ፅሑፍ ማጠንጠኛ የሆነውን ሰላም በመመለስ ለትግላቸው እውቅና በመስጠት ጥያዌዎቻቸውን መመለስ ችለዋል።

በሀገራችን ዕውን እየሆነ ያለው ስርዓት ሰላምን ማረጋገጥ በመቻሉ፤ በማህበራዊ መስተጋብሮች ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል አብሮ ለመጓዝና የማንነት ልዩነቶችን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሳሪያ ሆኗል። ይህ አብሮነትም ዜጎች የጋራ ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ፌዴራሊዝም የጎላ ሚና እንደሚጫወት እምነትን አስይዞ በአዲስ የአስተሳሰብ መንፈስ ወደ ልማት ጎዳና መትመም እንዲችሉ አድርጓቸዋል።  

እናም ስርዓቱ እነዚህን ሁሉ ውጣ ውረዶችን አልፎ ሰላምን ዕውን ያደረገ፣ ልማትን ያረጋገጠና በዚህም የህዝቦችን ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነትን ዕውን ያደረገ እንዲሁም ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታን መገንባት ችሏል። ይህ ሲሆን ግን ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም። ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩት ሁከትና ግጭቶች ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ይመስሉኛል።

ያም ሆኖ ህዝቡ በሰላሙ ላይ ስለማይደራደር ለግጭት ኃይሎች የሚሆን ምቹ ምህዳር እንዳይኖር አድርጓል። ምንም እንኳን በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ አንዳንድ ግለሰቦች የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና የማይፈልጉ፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ አልፎ ደግሞ ድብቅ የጥፋት ኃይሎች ፖለቲካዊ ተልዕኮ ይዘው የሚነቀሳቀሱ ሆነዋል።

በዚህም በመልካም አስተዳደርና በሙስና ህዝቡን ሲያማርሩት እንደነበር የሚታወቅ ነው። እነዚህ ሃይሎች የፈጠሩት ምሬት ከትምክህትና ከጥበት አራማጆች አጀንዳ ጋር ተዳምሮ የሀገራችንን ሰላም ማወኩ የቅርብ ጊዜ ትውሰታችን ነው።

እንደሚታወቀው በትምክህትና ጠባብነት አስተሳሰብ የተጠመቁ ኃይሎች ከሁሉ በላይ የቋንቋ፣ የባህልና የማንነት ብዝሃነትን አጥብቀው ይጠላሉ። የትምክህት ኃይሉ የእኔ ብሔር ብቻ ልዕለ ኃያል ነው ብሎ ያምናል። እንዲሁም ቋንቋዬ፣ ባህሌና ማንነቴ ከሌላው የሚበልጥና የተለየነው ብሎ ከማሰብ በተጨማሪ ‘ሁሌም ለመግዛት የተፈጠርኩ ነኝ’ በማለት የሚያምን ነው።

በአንፃሩም ሌላውን ብሔርና ዜጋ ተራ እና ርካሽ፣ ለመመራት እንጂ ለመምራት ያልተፈጠረ፣ ቋንቋው፣ ባህሉና ማንነቱ የወረደ አድርጐ የመቁጠር አባዜ የተጠናወተው ነው። የህዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነትንም የመቀበል ተፈጥሮ የለውም። እናም በተቻለው መጠን ብዝሃነትን ደፍጥጦ የራሱን አስተሳሰብ፣ ቋንቋና ባህል በሌላው ላይ ለመጫን ቀዳዳዎችን በሙሉ ሲጠቀምባቸው ተመልክተነዋል።

የትምክህት ሃይሉ ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ብሔርተኝነትን የማይቀበል፣ ከህዝቦች አንድነት ይልቅ የግዛት አንድነት የሚያሳስበው ኃይል ነው። ከህዝብ ይልቅ ተራራና ወንዝ የሚናፍቅ ፀረ ህዝብ አመለካከት የተጠናወተውም ነው። የዚህ አስተሳሰብ ተቃራኒ የሆነው ጠባብነትን የተላበሰው ኃይል ደግሞ ሁሉንም ለእኔ እና ለእኔ ብቻ ብሎ የሚያስብ ነገሮችን ሁሉ በጠባብነት መነፅር የሚመዝን የዚህ ዓለም ዕውነታ የሆነውን ብዘሃነትን ተቀብሎና ተቻችሎ መኖርን የእሬት ያህል ቆጥሮ የሚጎመዝዘው ነው። ኋላ ቀርነት መገለጫ ነው ሊባልም ይችላል።

ታዲያ ሁለቱም ሃይሎች ምንም ዓይነት መሰረታዊ አንድነት ባይኖራቸው (እንዲያውም አንዱ ሌላኛውን በጎሪጥ የሚያየው መሆኑ እየታወቀ) በሌለ ማንነታቸው በአንቀልባ በመተዛዘል በይስሙላ ፍቅር እፍ…ክንፍ ሲሉ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም።

በዚህም ሀገር ቤት ያለውን ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙ ችግሮችን ተንተርሰው የተፈጠረውን የህዝብ ጥያቄ ጠልፈው ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመራ አድርገውታል።

ዳሩ ግን መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን ለግጭት መንስኤ የሆኑትን ውስጣዊ ጉዳዩችን በማረምና በችግሩ ፈጣሪዎች ላይም ርምጃ በመውሰድ ጭምር ጉዳዩን በቁጥጥር ስር በማዋል የተፈጠረውን ጊዜያዊ የሰላም እጦት መቀልበስ ችሏል።    

ርግጥ በማንኛውም ሀገር ከችግሮችና ከተግዳሮቶች ነፃ ሊሆን አይችልም። ምንም እንኳን ስርዓቱ እነዚህን ውጣ ውረዶችን ተሻግሮ ሀገራችንንና ህዝቦቿን ዛሬ ላይ ላሉበት አስተማማኝ የሰላም ቁመና ቢያበቃትም፤ አሁንም ቢሆን ከችግሮችና ከተግዳሮቶች የነፃ ነው ማለት አይደለም።

በአንድ በኩል ስርዓቱን የሚመሩት ሰዎች በመሆናቸው ከአቅም ውስንነትና ከሌሎች ነባራዊ ጉዳዩች ጋር ተያይዞ ከችግሮችና ከተግዳሮቶች ነፃ ሊሆኑ አይችሉም። በሌላ በኩልም ችግሮችና ተግዳሮቶች ነባራዊ ክስተቶች ናቸው።

እናም ዋናው ነገር ችግሮቹና ተግዳሮቶቹ መሰረታዊና አላላውስ የሚሉ እንዳይሆኑ የማድረግ ጉዳይ ነው።  ታዲያ ከዚህ አኳያ ፌዴራላዊ ስርዓቱ ችግሮችንና ተግዳሮቶችን በመፍታት ራሱን በራሱ የማረም አቅምና ብቃት ያለው በመሆኑ ይህንኑ እውን ሲያደርግ ዛሬ ላይ ደርሷል።

ሀገራችን ውስጥ እየተተገበረ ያለው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከዚህ ቀደም ያጋጠሙትን ውጣ ውረዶችን እየፈታና ችግሮችን እያረመ የመጣ በመሆኑ እነዚህ ተግዳሮቶች እየፈታ ነው።

ዛሬ ስርዓቱን ተግዳሮቶች እያጋጠሙት ቢሆንም፤ የችግሮቹ አራማጅ ኃይሎች የዘመናት ጥያቄያቸውን በህገ መንግስቱ ያረጋገጡት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባለመሆናቸው፤ ከመንግስት ጋር ሆነው በስርዓቱ አማካኝነት ተግዳሮቶቹን እየፈቱ ቀጥለዋል።

ከሚሌኒየሙ መባቻ ጀምሮ በነበሩት አስር ዓመታት በሀገራችን የተገኘው ሁለንተናዊ ለውጥ ፌዴራላዊ ስርዓቱ ራሱን በራሱ እያረመና አስተማማኝ የስራ ድባብን መፍጠር የሚችል ሰላም እውን ከማድረጉ ጋር የተያያዘ ይመስለኛል። ታዲያ በዚህ ረገድ የስርዓቱ ባለቤቶች የሆኑት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የአንበሳውን ድርሻ መጫወታቸው ሊዘነጋ የሚችል አይደለም።

በዚህ መሰረትም ከሚሌኒየሙ ወዲህ ባሉት አስር ዓመታት ውስጥ ምንም እንኳን ብቅ ጥልም የሚሉ ችግሮች ቢኖሩም፤ እጅግ የገዘፉ ስኬቶች መመዝገብ ችለዋል። ሌላው ቀርቶ በመዲናችን የሚታዩትን የልማት እመርታዎች ብቻ በመመልከት ሀየትኛውም አካል ይህን እውነታ ሊያረጋግጥ ይችላል።

ያም ሆኖ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚሌኒየሙ መባቻ የተጀመረው የልማት ግስጋሴ በእነዚህ የመጀመሪያው አስር ዓመታትም ተጠናክሮ ሳይስተጓጎል ቀጥሏል። ይህ ሂደትም መጪው ዘመን የኢትዮጵያን የልማት ጉዞን ከፍታ እውን የሚያደርገው ይሆናል።

ርግጥ የሀገራችን ህዝቦች ነገም ይሁን ከነገ በስቲያ ሌሎች ችግሮችና ተግዳሮቶች ቢያጋጥማቸውም ዋስትናቸው ዴሞክራሲያዊ ፌደራላዊ ስርዓቱ በመሆኑ በህግ አግባብ እንደሚፈቱት በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ውጣ ውረዶችን ተሻግሮ ሰላምን ይበልጥ አስተማማኝ እንደሚያደርጉም እንዲሁ። በዚህም በተግዳሮቶች ውስጥ ስኬቶችን እንዲያስመዘግቡ እድል ይፈጥርላቸዋል። ፌዴራሊዝም አስተማማኝ ሰላምን በፅኑ መሰረት ላይ የሚያኖር የፖለቲካ ስርዓት መሆኑን ዛሬም ይሁን ነገ እንደ ትናንቱ የሚያረጋግጡበት ይሆናል።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy