ዳር እስከ ዳር የሃገር ፍቅር ቀን
ዳር እስከ ዳር የሃገር ፍቅር ቀን
ዮናስ
ኢትዮጵያ አዲስ አቅጣጫ በያዘችባቸው የመጀመሪያ ዓመታት በአገራችን የፖለቲካዊ መልክዓ ምድር ላይ ከባድ ልዩነትና ተጠራጣሪነት ሰፍኖ እንደነበረ አያከራክርም፡፡ ኢትዮጵያ ብዙኅነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማስተዳደር መቻሏና ይህም በብዙሃኑ ህዝቦቿ ላይ የፈጠረው የእርስ በርስ መተማመን በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ተፈጥሮ የነበረውን ጥርጣሬና ስጋት ቀስ በቀስ እያረገበው መሄዱም በተመሳሳይ፡፡ መብታቸው የተከበረ ማህበረሰቦች በአንድነት ከመኖር የተሻለ አማራጭ ሊወስዱ እንደማይችሉ በተግባር መታየቱን ተከትሎ የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል ድረስ መከበሩ የመበታተን ቁልፍ እንዳልሆነ ታይቷል።
ያልተማከለው ፌዴራላዊ አስተዳደር ሁሉም ህዝቦች ያላቸውን ፀጋ በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑና በፌዴራላዊ ስርዓቱ ላይ በጎ አመለካከት እንዲያዳብሩ መንገድ ከፍቷል። መንግስት ሁሉም ክልሎች በየራሳቸው ፍጥነት እያደጉ፣ ነገር ግን ደግሞ በአቅም ልዩነት ምክንያት የሚፈጠረውን ያልተመጣጠነ እድገት ለማካካስ በማሰብ የሚሰጣቸው እገዛዎች፣ በተለይ በዳር አካባቢ የሚገኙ ታዳጊ ማህበረሰቦችን ከመቼውም ጊዜ በላቀ ኢትዮጵያዊ ገመድ እርስ በርስ እንዲተሳሰሩ አድርጓቸዋል።
በዚህ ላይ አገሪቱን ከጫፍ ጫፍ የሚያስተሳስር የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማት መስፋፋቱና ይህንንም በተናጠል ሳይሆን በጋራ ለመጠቀም የሚቻልበት እድል መስፋቱ፣ በዴሞክራሲ ላይ የተመሰረተውን አገራዊ ገመድ በጠንካራ የኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት አውታር ማጠንከር አስችሏል ። ይህንኑ የበለጠ ለማጠንከርና በጽኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ጷግሜ 3 የሃገር ፍቅር ቀን ተብሎ ተሰይሟል። ባለፉት 10 አመታት የተመዘገቡት ድሎች ካለሃገር ፍቅር የማይመጡ ነበርና።
ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የበለጠ ደግሞ ካሳለፍናቸው 10 አመታት ወዲህ በተሰሩ ተግባራዊና የአስተምህሮ ስራዎች በአገራችን ህዝቦች ዘንድ በልዩ ልዩ መሰረታዊ ጉዳዮች ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ብሔራዊ መግባባት ተፈጥሯል።
ህገ መንግስታችን የዴሞክራሲና የሰላም፣ የፍትህና የእኩልነት ዋስትና እንደሆነ በተነፃፃሪ የተሻለ መግባባት ተፈጥሯል። የሚገነባው ሥርዓት የገበያ መሆን እንዳለበትና ሰዎች ሰርተው የመጠቀም ህጋዊ ዋስትና ሊያገኙ እንደሚገባቸው ተመሳሳይ መግባባት ተፈጥሯል። በዚህ ላይ ድህነትና ኋላቀርነት ዋነኞቹ ጠላቶቻችን እንደሆኑ፣ ስለዚህም ደግሞ በፍጥነት መልማትና የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንዳለብን አጠቃላይ የጋራ ግንዛቤ ተይዟል።
የህግ የበላይነት መከበር እንዳለበትና ዜጎች ሁሉ በህግ ፊት እኩል እንደሆኑ ቢያንስ ቢያንስ ለመግባቢያ መነሻ የሚሆን ግንዛቤ በዚህ 10 አመት ተይዟል። እዚህ ላይ ከፈጣኑ እድገት ጋር ተያይዘው የተከሰቱ ነባርም ሆኑ አዳዲስ የስርዓት ችግሮችም እንደዚሁ ከሞላ ጎደል ስለሃገር ፍቅር የጋራ ስምምነት የተያዘባቸው እና ሊታረሙ ከሚገቡ ነጥቦች መካከል የተሰመረባቸው አጀንዳዎች ናቸው።
ኪራይ ሰብሳቢነት መጥፎ እንደሆነና ብዙኀኑን ህዝብ እንደሚጎዳ ከሞላ ጎደል በብዙኀኑ ህዝብ ዘንድ ስለሃገር ፍቅር ስምምነት እየተፈጠረ ነው። በዚህ ላይ ሰላማዊና የተረጋጋ ህብረተሰብ የመሆናችን አስፈላጊነት በጥልቅ የሚታመንበት ሆኗል። ዜጎች ከአመፅ ይልቅ ሰላማዊ በሆነ መንገድና በድርድር መብትና ጥቅሞቻቸውን ማስፋት እንዳለባቸው የሚታመንበት መሆኑም የሃገር ፍቅር አንዱ መገለጫ ነው።
በእነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ብሔራዊ መግባባት የተፈጠረ መሆኑ እንደተጠበቀ ይህ ግን በፅኑ የፖለቲካ ኢኮኖሚ መሰረት ላይ የተገነባ ባለመሆኑ አሁንም የመዋለልና ወደፊትና ወደኋላ የመመለስ አዝማሚያዎች መታየታቸው ሊሰመርበት የሚገባ እና ስለሃገር ፍቅር ሊታረም የሚገባው ጉዳይ ነው።
ኪራይ ሰብሳቢነት መጥፎ እንደሆነ የሚቀበለው ህዝብ ትንሽ በማይባል ደረጃ በዚሁ ዝንባሌ ሲለከፍ እየታየ ስለሆነ። የህግ የበላይነትና ሰላማዊ የትግል አግባብን የተቀበለው ህብረተሰብ፣ አልፎ አልፎ ፍላጎቱን በሃይልና በግጭት መንገድ ለማሳካት ሲንቀሳቀስም በተመሳሳይ እየታየ ስለሆነ። በተለይ ደግሞ አስፈጻሚው አካል ብቃት ባለው መንገድ የማይመራውና ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ በሆነው አቅጣጫ የማያስጉዘው በሚሆንበት ጊዜ፣ ከብሔራዊ መግባባት አኳያ የተሻለ ርቀት የሄድንባቸው ጉዳዮች ሳይቀሩ ወደኋላ የመመለስ አዝማሚያ የሚታይባቸው እስከመሆን ደርሰዋልና ስለሃገር ፍቅር ቀን ሊታረሙ ከሚገባቸው ያሳለፍናቸው 10 ዓመታት ተግዳሮቶች ናቸው።
ይህም ሆኖ ባሳለፍነው 10 ዓመት በተለየ ኢትዮጵያ በህገ መንግስቱና የህግ የበላይነት ማስከበር ላይ፣ በልማትና በህዝብ ተጠቃሚነት አጀንዳዎች ላይ እንዲሁም በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት ግንባታ መሰረታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ በተነፃፃሪ የተሻለ ብሔራዊ መግባባት የፈጠረች አገር ሆናለች።
ባሳለፍነው አመት በየደረጃው የተደረገው ጥልቅ ተሃድሶም ስለሃገር ፍቅር ህዝቡን ያሰተሳሰረ ገመድ ሆኗል። ምክንያቱም ተሃድሶው አንጥሮ ያወጣው ጉዳይ ዴሞክራሲ የሕልውናና የልማት አጀንዳ መሆኑ ላይ ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ማድረግን ስለሆነ። የብዝሃነት ምድር በሆነችውና ልማቷ በሕዝቦቿ በጎ ፈቃድና ፍላጎታቸው በሚያፈሱት ጉልበት ላይ በተመሰረተው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የሕልውና ጉዳይ መሆኑ ያለማቅማማት እንዲታመን ያደረገ ጥልቅ ተሃድሶ ነበርና። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መብትና እኩልነት መረጋጥ፣ የቡድንና የግለሰብ መብቶች የሚከበሩበት ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ከልባዊ ዴሞክራሲ ውጪ ዕውን መሆን እንደማይችል ጥልቅ ተሃድሶው አድምቆ አስምሮበታልና። የሀገራችን ዴሞክራሲ ለፕሮሲጀር ሳይሆን ከልባዊነትና ከሕዝባዊ ወገንተኝነት የሚመነጭ፣ ለሕዝብ ጥቅም የሚቆም እርግጠኛ ዴሞክራሲ መሆኑና ሊሆንም እንደሚገባው በግልፅ ተቀምጧልና ስለሃገር ፍቅር ሊጠናከር ይገባዋል።