Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“የውሸት ወሬን ያጣ፣ ወደ ፅንፈኛው ሚዲያ ይምጣ!”

0 494

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“የውሸት ወሬን ያጣ፣ ወደ ፅንፈኛው ሚዲያ ይምጣ!”
ዘአማን በላይ
ነገሩ አስገራሚ ነው። ነጋ ጠባ ባተሌ ሆነው በኢትዮጵያና በህዝቦቿ ላይ አሉባልታን በመንዛት የሚታወቁት፣ እነርሱ በበለፀገ ሀገር ውስጥ ሆነው በጥራት የበለፀገ አይስክሬማቸውን እየላሱ፣ የሀገራችንን ህዝብ በቅንፈት አጀንዳ ለማዘናጋት እየጣሩ፣ የዚህችን ከድህነት አዙሪት ቀለበት ለመውጣት የምትታትር ሀገርንና የህዝቦቿን የተነሳሽነት ወኔን ለመስለብ እንዲሁም በዚህ እኩይ ሴራቸው የልመና አኮፋዳቸውን ለመሙላት የሚራወጡ ፅንፈኞችና ሚዲያዎቻቸው የማይወረውሩት የውሸት ጦር የለም።
ግና በነገር አንካሴያቸው ላይ የተሰካው የውሸት ጦራቸው የትም የሚዘልቅ አይሆንም። ለዚህ አባባሌ በአስረጅነት ሁለት ምክንያቶችን ማንሳት እችላለሁ። አንደኛው እዚህ ሀገር ውስጥ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በሚገባ የሚረዳ ህዝብ ያለ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ እንደ ማንኛውም ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠሩ ነባራዊ ችግሮችን የመፍታት ብቃትና አቅም ያለው ህገ መንግስታዊ ስርዓት መኖሩ ነው። ዛሬ ህዝቡ ዕንፈኞቹና ሚዲያዎቻቸው የውሸት ቋቶች መሆናቸውን ከመገንዘብ ባለፈ፣ ለእነርሱ የፈጠራ ድርሰት ጆሮውን ማዋስ አይሻም። የቅጥፈት ልፈፋቸው ሰላሙን፣ ልማቱንና ዴሞክራሲያዊ መብቱን እንዲያጣ ከማደረግ በስተቀር የፈየደለት ምንም ነገር እንደሌለ ተገንዝቧል።
በሌላ በኩልም በህዝቡ ይሁንታ በተደረገ ምርጫ ሀገሪቱን ላለፉት 26 ዓመታት የመራውና በመምራት ላይ የሚገኘው የኢፌዴሪ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ማንኛውም ሀገር ሊፈጠሩ የሚችሉ ጊዜያዊ ችግሮችንና ተግዳሮቶችን የመፍታት ብቃትንና ክህሎትን ያዳበረ ነው። አዲሲቷ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት ችግሮችና ተግዳሮቶች ከመፈጠራቸው አሊያም ከተፈጠሩም በኋላ ቢሆን የሚፈታበት አሰራር አለው።

የሀገራችን ፌዴራሊዝም ራሱን በራሱም የሚያርም ተራማጅ (Progressive) ስርዓት ነው። እዚህ ሀገር ውስጥ የሚፈጠሩ አሊያም ሊፈጠሩ የሚችሉ ማናቸውም ችግሮች ከስርዓቱ በላይ ሆነው አያውቁም። ሊሆኑም አይችልም። በኢኮኖሚም ይሁን በፖለቲካ ልቀዋል የሚባሉት ምዕራባዊያን እንኳን ሽብርተኞች እየፈጠሩባቸው ያለውን ችግር መቋቋም ተስኗቸው፤ እዚህ ሀገር ውስጥ በመተግበር ላይ የሚገኘው ፌዴራላዊ ስርዓት በህዝቦች በጎ ፈቃድና ይሁንታ የተገነባ በመሆኑ ይህን መሰሉን ችግር ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመቋቋም ችሏል። በእኔ እምነት ይህን የገዘፈ ችግር መቋቋም የሚችል ስርዓትና ህዝብ መኖሩ፣ ምንም ዓይነት ተግዳሮት ከህገ መንግስታዊ ስርዓቱ በላይ ሊሆን እንደማይችል ጥሩ ማሳያ ነው። ይህን እውነታ ህዝቡ በሚገባ ይገነዘባል። እናም የፅንፈኞቹና ሚዲያዎቻቸው ጩኸት ገደል ማሚቶ የሌለው ከንቱ የበረሃ ላይ ልፈፋ ነው።

ያም ሆኖ ፅንፈኞቹና ሚዲያዎቻቸው ውሸት ‘የዕለት እንጀራቸው’ ነውና ልፈፋቸውን አያቋርጡም። ለስራቸው ከተለያዩ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች የሚቀበሉት ገንዘብ ‘ላምጪው እንዲከፈል ህግ ያስገድዳል’ ተብሎ ስለሚሰጣቸው የቅጥፈት ዲስኩራቸውን ከመንዛት አይቆጠቡም። ጉዳዩ በህዝቦች ስቃይ ደመወዝ መብላት ስለሆነ ይህን ‘ዳቧቸን’ ላለማጣት ይቀባጥራሉ።
እንደ እውነቱ ከሆነ ፅንፈኞችና በራሳቸው የምናብ ዓለም የፈጠሯቸው አሊያም እንዲፈጥሩ ትዕዛዝ የሰጧቸው የኢትዮጵያን መዳከም የሚሹ ኃይሎችን ለማስደሰት የሚነዟቸው የውሸት ልፈፋዎች ሀገራችን ውስጥ ያለን ነባራዊ ሁኔታን አያመላክቱም። ግልብ ዲስኩሮች ናቸው። አዳንዶቹ ለማረጋገጥ የሚያስቸግሩ እጅግ ገጠራማ የሀገሪቱን አካባቢዎች እየጠቀሱ ‘እገሌ የሚባል አካባቢ ህዝብ ከመንግስት ኃይሎች ጋር እየተዋጋ ነው’ እስከማለት የሚደርሱ ዓይን ያወጡ ነጭ ውሸቶች ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ‘አገሌ የሚባል የመንገስት ሹም እንዲህ አደረገ’ የሚል ተራ አሉባልታ ናቸው።

እነዚህ ዓላማቸው ውሸትን ፈጥሮ እዚህ ሀገር ውስጥ ትርምስ መፍጠር በመሆኑ፣ ቢሾፍቱ አሊያም አዲስ አበባ ወይም በክልል ከተሞች ውስጥ በአንዱ አካባቢ የሚገኝ ግለሰብ በሰላም ህይወቱን እየመራ በፅንፈኞቹና በሚዲያዎቹ ቤቱ እንደጋየ፣ በመንግስት የፀጥታ ሃይሎች ታፍኖ እንደተወሰደ አሊያም ማረሚያ ቤት ገብቶ እንደተደበደበ ተደርጎ ሊነገር ይችላል። ይህ ምንም አይደንቅም። ለእነርሱ ተራ ገንዘብ ማግኛ ዘዴ ነው።

ምናልባትም ግለሰቡ ‘ኧረ ቤቴ አልተቃጠለም፣ ማታም የትም ሳልሄድ ተኝቼ ነው ያደርኩት’ ቢል፣ ፅንፈኞቹ ‘የለም፣ ቤትህ ተቃጥሏል፣ አንተም ታፍነህ ተወስደህ ተደብድበሃል’ ሊሉት ይችላሉ። እነርሱ ምን ተዳቸው! እዚህ ሀገር ውስጥ በህይወት ቆሞ የሚሄድ ግለሰብን ገድለው፣ መቃብሩን ካስቆፈሩ በኋላ ሊቀብሩትም ይችላሉ። ‘ሀገር ጃርት ያበቅላል’ እንዲሉ አበው፤ የውሸት እሾሃቸውን በሀገራችን ሰላማዊና ታታሪ ህዝብ ላይ ለመሰካት ያሰፈሰፉ አለብላቢቶች ናቸው። እነዚህ ጉዶች ለፈጠሩት የልቦለድ ዓለም ሰው ቀበራ ለይስሙላ እንኳን ‘በስም መመሳሰል ነው’ የሚል ይቅርታ የሚጠይቁ አይደሉም። በሰለጠ ሀገር ውስጥ የሰየጠኑ ልቦለዳዊ ድርሰት አነብናቢዎች ናቸው።

ውሸት ለመደስኮር ዓይናቸውን በጨው ታጥበው ‘ዓይናችሁን ጨፍኑና እናሞኛችሁ’ የሚሉ ጊዜ ያለፈባቸው ተላላኪዎች ናቸው።
እነዚህ ተላላኪ ፅንፈኞችና ሚዲያዎች ሐሰትን ፀንሰው፣ በተንኮል ማህፀናቸው ውስጥ አርግዘው እንዲሁም “ኢሳት”ን በመሳሰሉ፣ እንደ ፌስ ቡክ ዓይነት ማህበራዊ ሚዲያዎችና መጦመሪያ ገፆች ላይ አቀነባብረው ይገላገሉታል። ከዚያም የስራቸውን ግብር ከፍለው ለሚያሰሯቸው አካላት ሪፖርት ያደርጋሉ። ከፋዮቹም የተላላኪዎቹን ስራ ልኬታ ‘ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ትርምስ ፈጥሯል?፣ ምን ያህልስ ሰው እንዲሞት አድርጓል?’ በሚል መስፈርት ከገመገሙ በኋላ “ስራቸውን” (‘ሴራቸውን’ ቢባል ሳይሻል አይቀርም) ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት አሊያም ለአንድ ዓመት እንዲቀጥል ቡራኬያቸውን ሊሰጡ ይችላሉ። ራሳቸውን “ኢሳት” አሊያም ባለ ሜንጫው “ኢትዮጵያዊው አይኤስ” የሚባለው “ጃዋር” እመራዋለሁ የሚለው “ኦኤምኤን” የአየር ላይ ቆይታ እድሜያቸውን የሚያራዝሙት በዚህ ሁኔታ ነው።

እናም እድሜያቸው እንዳያጥር በህይወት ያለን ሰው ‘ሞተ’፣ የወደቀን ‘ተሰበረ’፣ በግል ፀብ ምክንያት የቆሰለን ‘በመንግስት የፀጥታ ሃይሎች ተገደለ’…ወዘተርፈ እያሉ ቢለፍፉ ምንም የሚያስገርም ነገር የለውም— ነገረ ስራቸው ‘በሆድ- አደርነት’ ተሰልፎ ህይወትን ለማቆየት በህዝብ ደምና አጥንት መነገድ ነውና። ታዲያ እዚህ ላይ የልፈፋቸው አልፋና ኦሜጋ እነርሱ ሳይሆኑ የላኳቸው ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። የእነርሱ ተግባር ሀገርን ለጨረታ አቅርቦ በሃራጅ ለባዕዳን መሸጥ ብቻ ነው። ምንኛ አሳፋሪ ባንዳነት ነው ጃል?! ምንስ ዓይነት ትንሽነት ነው?!…

ታዲያ “ይሉሽን ባልሰማሽ፣ ገበያ ባልወጣሽ” እንዲሉ አበው፤ የፅንፈኞቹና ሚዲያዎቻቸው ነገር “የውሸት ወሬን ያጣ፣ ወደ ፅንፈኞች ሚዲያ ይምጣ!” እንደተባለላቸው የሰሙ አይመስሉም። እንደ አቡነ ዘ-በሰማያት የሚደጋግሙት የ‘ሞተ፣ ተቆረጠ፣ ተፈለጠ’…ዲስኩራቸው አንዳንዴ ውሸትን ለመስማት የሚፈልጉ ሰዎች መዝናኛ እየሆነ ነው። ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ ፅንፈኞችን አሊያም ሚዲያዎቻቸውንና የፌስ ቡክ ገፃቸውን (‘ፈስ ቡካቸውን’ እንበለው ይሆን?) በውሸታምነት ከተፈደጁ ሰነባበተዋል። አብዛኛው ህዝብ “ኢሳት”ንና አምሳያ ወንድሞቹን “እነርሱን ተዋቸው” ማለቱ እየተለመደ መጥቷል። ታዲያ ‘ይህ ሁኔታ እንዴት ሊፈጠር ቻለ?’ ብሎ ለሚጠይቅ ሰው ምላሹ ቀላል ይመስለኛል። ይኸውም እዚህ ሀገር ውስጥ ያለው ህዝብ ሚዛናዊ፣ ነገሮችን በምክንያታዊነት የሚመለከት እንዲሁም በየትኛውም ሀገር ውስጥ እንደሚፈጠሩት ችግሮች ሁሉ፤ ሀገሬ ውስጥ የሚፈጠሩ ማናቸውንም ጊዜያዊ ችግሮች በመንግስት ብልህና በሳል እንዲሁም ትዕግስት የተሞላበት አመራር የሚፈቱና ምላሽ የሚያገኙ ናቸው ብሎ ስለሚያምን ነው።

ይህም ፅንፈኞቹና ሚዲያዎቻቸው የሚቀርጿቸው የውሸት አጀንዳዎች ምን ያህል ከህዝቡ ንቃተ-ህሊና በታች መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። የውሸት ወሬያቸው ምን ያህል ህዝቡን የማይመጥን እንዲሁም ተላላኪዎቹ ዛሬም እንደ ትናንቱ በአሮጌ የቅጥፈት ባቡር ላይ ተሳፍረው በዘመነው የሉላዊነት ዘመን ህዝቡን ለማደናገር ፍላጎት እንዳላቸው የሚያጋልጥም ነው። ለነገሩ ይህን ትንሽነት ይዘው የሚቧችሩት ለባዕዳን የሚላላኩት እነዚህ ፅንፈኞች “የውሸት ወሬን ያጣ፣ ወደ ፅንፈኛው ሚዲያ ይምጣ!” የተባሉትስ ለዚሁ አይደል?…

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy