Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህዝቡ የሠላሙ ዋስና ጠበቃ ነው!

0 279

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህዝቡ የሠላሙ ዋስና ጠበቃ ነው!

አባ መላኩ

ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ ስለሠላም የዘመረ፣ ስለሠላም የሰበከ፣ ስለሠላም ያቀነቀነ አለ ቢባል እሞግታለሁ። የኢትዮጵያ ህዝብ ስለሠላም እጅግ ብዙ ዋጋ ከፍሏል። መንግሥት ሠላምን በተመለከተ አንድ ርምጃ በወሰደ ቁጥር ህዝቡ የጉዳዩ ባለቤት ሆኖ ቀናኢነቱን በተግባር የሚያረጋግጠውም ለዚሁ ነው። ህዝቡ በየአካባቢው የሠላሙ ባለቤት ሆኖ የሚንቀሳቀሰውም ያለምክንያት አይደለም።

ስለሠላም ሲባል በተደጋጋሚ ጊዜያት አዋጅ ሊወጣ ይችል ይሆናል። ነጋሪት ሊጎሰምም እንዲሁ። በነዚህ ጉዳዮች ብቻ ግን በዘላቂነት ሠላምን ማስፈን አሊያም ሠላምን ማረጋገጥ ይቻላል ተብሎ አይታሰብም።

እነዚህ ጉዳዮች ምናልባት ጊዜያዊ መፍትሄ ሊያመጡ ይችሉ ይሆናል። ዘላቂ ሠላምን እውን ማድረግ የሚቻለው በህዝብ ንቁ ተሳትፎ ነው። ለአገሪቱ ሠላም መረጋገጥ መሠረቱ ህዝቡ ነውና። ይህ በመሆኑም ምክንያት የአገሪቱ ሠላም በአጭር ጊዜ ወደነበረበት እንዲመለስ ኅብረተሰቡ ለሠላም ካለው ፅኑ ፍላጎት እንጂ በአዋጅ ብቻ የሚመጣ አይደለም። ለማሣያ ያህል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በወጣበት ወቅት አፈጻፀሙ ላይ የየአካባቢውን ሠላም በመጠበቅ ረገድ ዜጋው ያሳየው ኃላፊነት ተጠቃሽ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል። ይህም የሚያሳየው የሠላሙ ባለቤት ህዝቡ ራሱ መሆኑን ነው።  

እንደሚታወሰው የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በውጭ ኃይሎችና በውስጥ ተላላኪዎቻቸው ቅንጅታዊ እኩይ ሴራ ሁከት ተፈጥሮ ነበር። ሁከቱን በቁጥጥር ሥር ማዋል እንዲቻልም በህገ መንግሥቱ መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቶ ነበር። አዋጁም በወቅቱ ሠላሙን ተነጥቆ በነበረው የየአካባቢዎቹ ህዝቦች ሙሉ ድጋፍ ስለነበረው አፋጣኝ ምላሽ አስገኝቷል። በአጭር ጊዜ ውስጥም መንግሥት ከህዝቡ ጋር በመሆን የተፈጠረውን ሁከት በቁጥጥር ሥር ማዋል ችሏል። የሁከቱ ተሳታፊ የነበሩ ወገኖችም የተሃድሶ ትምህርት እንዲሰጣቸው ተደርጓል። ሁከት አቀጣጣዮችም የበደሉትን ህዝብ ለመካስ ቃል ገብተው ወደየአካባቢዎቻቸው ተመልሰዋል።

ህዝብ ከሁከት ፈጣሪዎች፣ ከአሸባሪዎችና ከግጭት ቀስቃሽ ኃይሎች ጎን እንደማይቆም ደጋግሞ አረጋግጧል። አጥፊዎችን በማጋለጥ የእርምት ርምጃ እንዲወሰድባቸው ሙሉ አቅሙን ተጠቅሟል። ታዲያ እዚህ ላይ የህዝቡ የማይተካ ሚና አድናቆት ሊቸረው ይገባል። ይህም ማንኛውም አዋጅ ያለ ህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ ተፈፃሚ ሊሆን እንደማይችል የሚያሳየን ቁም ነገር ነው።

ሁሌም ለሚወጡ አዋጆች ሆነ ለሚደነገጉ ህጎችና ደንቦች ተፈጻሚነት በግንባር ቀደም ዋነኛው ተዋናይ ዜጋው ነው። ዜጋው በማንኛውም መመዘኛ ሠላሙን ተፃርሮ አይቆምም። በመሆኑም ለሠላሙ መረጋገጥ ፀረ ሠላም ኃይሎችን ማጋለጥና ለህግ ማቅረብ ተገቢ ይሆናል። አጥፊ ኃይሎች ከድርጊታቸው ተቆጥበው ወደ ሠላማዊ ህይወት ለመመለስ ጽኑ ፍላጎት ሲያሳዩ ህዝብ ድጋፍና እገዛውን ይቸራቸዋል። ይህ ተግባር ኅብረተሰቡ ለዘላቂ ሠላም የቱን ያህል የፀና አቋም እንዳለው ማሣያ ነው።

የየትኛውም አገር ሠላም የሚጠበቀው በህዝብ ፍላጎት እንጂ በጦር ኃይል ብዛት አይደለም። ስለ ሠላም በሚደረጉ ማናቸውም ክንዋኔዎች ውስጥ የህዝቡ ተሳትፎ ግንባር ቀደሙን ሥፍራ ይይዛል። የአገሪቱንና የህዝቦቿን ሠላምና መረጋጋት የማይሹ የውጭ ኃይሎችና ተላላኪዎቻቸው የፈፀሙት ፀረ ሠላም ድርጊት የት ድረስ እንደ ዘለቀ ከህዝቡ የተሰወረ አይደለም። ህዝብ ሁሌም ከማንኛውም ተግባር ቀድሞ ግራና ቀኙን ያያል።  ህጋዊ አካሄዶችን ያጤናል ይፈትሻል። አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖቹን ይመረምራል። ከዚያም ሚዛናዊ ውሣኔን ይሰጣል። የቆየ ልማዱም ነው።  

የወደፊት ዕጣ ፈንታውን የሚወስነው አገሪቱ የምትከተለውን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመስ አጥብቆ በመያዝ ነው። ለዚህም ሲባል ዘወትር ከሠላም ወዳድ ኃይሎች ጎን ይቆማል። የሠላምን ዋጋ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ከምንም በላይ ለሠላም ሲባል ሁሌም በየአካባቢው ለሠላሙ  ዘብ ቆሞ እንዳዜመ ነው።

ዛሬ ህዝቡ በየቀየው ላለው የሠላም ሁኔታ ዋነኛ መሠረት ሆኗል። በየአካባቢው የሚፈጠረው የፀረ ሠላም ድርጊት መልሶ የሚጎዳው ራሱን መሆኑን ጠንቅቆ ስለሚገነዘብ  ለሠላሙ መረጋገጥ ይበልጥ መትጋትን ያውቅበታል። ሠላምን የሚያጎድሉ፣ ልማትን የሚያደናቅፉና ግጭትን የሚያባብሱ መስመሮችን ጠራርጎ በመጣል የሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተፈጻሚ ማድረግና በፀረ ድህነት ላይ የተጀመረውን ዘመቻ በማቀጣጠል ጉዞውን ቀጥሏል። ህዝቡ በሁሉም አቅጣጫ ከልማቱ በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ተፈላጊውን የዕድገት ራዕይ ሰንቆ እየተጓዘ ነው።  

ከዚህም ጋር የተጀመረውን ዕድገት ለማስቀጠልና በዚያውም ልክ ዴሞክራሲው አገር በቀል ፍላጎትን መሠረት ባደረገ መልኩ እንዲጎለብት የተጀመረው ጥረት እንዳለ ሆኖ ይህ ህዝብ በአንዳንድ የተወሰኑ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከመልካም አስተዳደር ችግሮች ጋር በተያያዘ እንዲሁም ፅንፈኛ ኃይሎችና የአገራችንን መለወጥ የማይሹ ቡድኖች በሚያሴሩት ሽረባ  የተከሰተውን ሁከት ለመቋቋም ህዝቡ በባለቤትነት ስሜት የከፈለው መስዋዕትነት በቀላሉ አይታይም። ይህ የህዝቡ ስሜት የመነጨው ከምንም ተነስቶ አይደለም — የሠላምን ዋጋ በምንም ሊለካ እንደማይችል ካለፉት ተጨባጭ ሂደቶች ስለተማረ እንጂ።

በእርግም ከተግባር የበለጠ ትምህርት ቤት የለም። ህዝቡ የሠላሙ ዘብ ነው። ሁከቱን ለመቀልበስ በአገሪቱ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ የህዝቡን ሠላምና ፀጥታ ለማረጋገጥና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል ሲባል ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን ቆሞ ተግባራዊ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል። አበረታች ውሣኔና ርምጃ ነው። በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ህዝቡ የአንበሣውን ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል። በህዝቡ የነቃ ተሳትፎ በአገሪቱ ላይ ተደቅኖ የነበረው አደጋ እንዲቀለበስ ለማድረግ በተደረገው ርብርብ የህዝቡ ሚና ተዘርዝሮ አያልቅም።  

የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፉት 26 ዓመታት ገደማ የተራመዳቸው የልማት ውጣ ውረዶች የሚቀራቸው የተወሰኑ ተጨባጭ ለውጦች ቢኖሩም፤ ከትናንቱ በተሻለ ቁመና ላይ እንደሚገኙ ግን ይታወቃል። እነዚህም ህዝቡን በተሻለ ማማ ላይ እንደሚያወጡት በልማቱ ውስጥ ተዋናይ የሆነው ማንኛውም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ራሱን ዋቢ አድርጎ ማቅረብ ይችላል።  

ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ከተቀረፁ፣ ህዝቡን ከዳር እስከ ዳር የሚያንቀሳቅስ ልማታዊ መንግሥት ካለና በዚሁ መሪ አካል አስተባባሪነት ብሎም በህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ የሚዘወር ሠላም እስካለ ድረስ፤ ሰርቶ መለወጥና ማደግ እንደሚቻል ጠንቅቆ የሚያውቅ ህዝብ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጥሯል። መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ስለሠላሙ መስፈን ድምጹን ከፍ አድርጎ ይዘምራል። በየአካባቢውም የሠላሙ ዋስና ጠበቃ ሆኖ ይንቀሳቀሳል። ይህ የትናንቱ አኩሪ ተግባሩም ወደፊት ተጠናክሮ ይቀጥላል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy