Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለሰብአዊ መብቶች መከበር የላቀውን ስፍራ የሰጠ ፌደራላዊ ስርአት

0 457

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለሰብአዊ መብቶች መከበር የላቀውን ስፍራ የሰጠ

ፌደራላዊ ስርአት

ስሜነህ

 

መንግሥት ሰብዓዊ መብትን ለማሻሻል የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችንና የዴሞክራሲ ተቋማትን አቋቁሟል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋማት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዚህች ሃገር የመብቶች ፍረጃና ቅደም ተከተል ሳይቀመጥ የጋራና የግል መብትም ሆነ ሌሎች መብቶች ሳይነጣጠሉ ተደጋግፈው የሚጠበቁበት ስርአት በመዘርጋቱ ለሰላም፣ ለልማትና  ለዴሞክራሲ ሥርዓቱ ጠንቅ የነበሩ ምክንያቶች ከስመዋል።

ለሰብዓዊ መብት መከበር እንቅፋት ከሚሆኑ ችግሮች መካከል የመልካም አስተዳደር አለመስፈን አንዱ በመሆኑ በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለማስወገድ ከህዝቡ ጋር በተደረገ ውይይት ውጤት ማስመዝገብ የሚያስችል ስርአትና አሰራር ተዘርግቷል። አሁን በአገራችን ያለው ሁለንተናዊ እድገት ከሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ውጪ የተሣካ ሊሆን እንደማይችል የሃገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ተመልክቶ መደምደም ይቻላል። ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ የሠብአዊ መብት ስምምነቶችን በመቀበል እና በማጽደቅ የአገሪቷ የህግ አካል ሆነው እንዲተገበሩ በማድረግ በዓለም ከሚገኙና “የበለፀጉ” ከሚባሉት አገሮች ባልተናነሠ ሃላፊነቷን በመወጣት ላይ መገኘቷም ይታወቃል።  

የሰብአዊ መብት ጉዳይ  ከሕገ መንግስቱ በዋናነት ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያለመ ነው። አንደኛው ለዘመናት የግጭት ምክንያት የሆነውን ስልጣንና ሃብት በማእከልና በጥቂጥ ሃይሎች መከማቸት የፈጠረውን ችግር ለመመለስ ሕገ መንግስታዊ ዋስትና ያለው የፌዴራል ሥርዓት ማለትም ስልጣንና ሃብት በፌዴራልና በክልሎች መካከል መከፋፈሉ እንዲሁም የህዝቦች የማንነት ጥያቄ ለመመለስ ህዝቦች ራሳቸውን የማስተዳደር መብት የሚቀበል መሆኑ  ነው፡፡ ዋና መነሻውም ህዝቦች ራሳቸውን ማስተዳደር ከቻሉ የራሳቸውን ማንነት፣ ቋንቋ እምነትና  ታሪክ ለማሳደግና ወደ ቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይችላሉ የሚል ነው፡፡

የመንግሥት ሥልጣን ምንጩ ሕዝብ /ዜጎች/ እንደሆኑና መንግስትም ከሕዝብ ላገኘው ሥልጣን የዜጎችን መብት የማክበር ግዴታ እንዳለው የሚያስገነዝብ  ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ ይህ ጽንሰ ሃሳብ ወደ ኋላ የሕዝቦች ራሳቸውን የማስተዳደር መብት በሚል መልኩን ቀይሮ አሜሪካውያን በ1776 ከእንግሊዝ ነፃ ለመውጣት እንዲሁም በፈረንሳይ አብዮት ዓይነተኛ መሳርያ ሆኖ የተለያዩ ቅኝ ገዥና ንጉሳዊ ሥርዓቶችን በማንኮታኮቱ በሕዝብ የተመረጡ መንግሥታት ብቅ እንዲሉ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ሰብአዊ መብት የሚለው አስተሳሰብ ወደ ፖለቲካ መድረኩ ብቅ ማለት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሰዎችን ከተገዢነት ወደ ሙሉ ዜግነት እንዳሸጋገሩና ነፃ እንዳወጡ ብዙ ፀሐፊዎች ይስማሙበታል፡፡

ሌላው ሰብዓዊ መብቶች ባንድ አገር እንዲፈፀሙ ቀዳሚው ኃላፊነት በአገሪቱ ፍ/ቤቶች፣ ሰብአዊ መብት ኮሚሽኖች፣ እምባ ጠባቂና ለሌሎች ተመሳሳይ አገራዊ ተቋሞች የተሰጠ መሆኑ ነው። እዚህ ላይ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ ሰብአዊ መብቶች የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ የሚጎናፀፋቸው መብቶች (Natural law conception) ናቸው ወይስ መብቶች መብት ሊሆኑ የሚችሉት በሕግ በተለይም በሕገ መንግሥት እውቅና ሲያገኙ የሚለው ብዙ ፀሀፊዎችን ለብዙ ዘመን ያከራከረ መሆኑ ነው፡፡

ሰብአዊ መብቶች ከስማቸው ጭምር መረዳት እንደሚቻለው ሰው ሰው በመሆኑ የሚጎናፀፋቸው ቢሆኑም ሕጋዊ (ሕገ መንግስታዊ) እውቅና ካልተሰጣቸው ተፈፃሚ የመሆናቸው ጉዳይ አከራካሪ በመሆኑ በርከት ያሉ ተመራማሪዎች መሠረታዊ መብቶች (Fundamental Rights) ለመባል ሕገ መንግሥታዊ እውቅና የግድ ይላል የሚለውን ሚዛን የሚደፋ መሟገቻ ስናጤን በሃገራችን ለሰብአዊ መብቶች የተሰጠው የላቀ ህገመንግስታዊ ቦታ ትክክል መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ በርግጥም ይህ መከራከሪያ ሚዛን የሚደፋ መሆኑን ካለፉትና ህገ መንግስታዊ ዋስትናን ከነፈጉት ስርአቶች በመማር ሃገራችን የሰብአዊ መብትን ጉዳይ በነቢብ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ይረጋገጥ ዘንዳ ህገመንግስታዊ ዋስትናን የመስጠቷን ተገቢነት ልብ እንድንል ያደርጋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ሌላም ጉዳይ አለ፡፡ የትኛውም ዓይነት መብት በዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ሰነድም ይሁን ባንድ አገር ሕገ-መንግስት ሲካተት የመጀመርያውና ቀዳሚው ዓላማ እንዲከበር እና እንዲፈፀም የሚል ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ የአስፈላጊ ተቋሞች መኖርንና ሥልጣንና ኃላፊነታቸውን መወጣትን ይጠይቃል፡፡ አለበለዝያ መብቶች በወረቀት ላይ የሰፈሩ ጌጦች ይሆኑና ዜጎችም በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዳይኖራቸው እንዲሁም ከዛ በከፋ መልኩ የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት እንዳይኖር ምቹ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡

ይህ ሲባል ግን መብቶች ፍፁምና ገደብ የሌላቸው ናቸው ብለው እንደሚዘምሩት የከሰሩ ፖለቲከኞች መታሰብም  የለበትም፡፡ ሁሉም ዓለምአቀፍ ሰነዶችና አብዛኞቹ ሕገ-መንግሥቶች መብቶች ላይ የተወሰነ ገደብ ሊኖራቸው እንደሚችል ማመናቸውና መቀበላቸው ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ሌላውና ከሰብአዊ መብቶች ጋር ተያይዞ ዴሞክራሲያዊ ስርአቱ የሚሞገትበት አጀንዳና ተገቢም የሚሆነው መመዘኛ የፍትህ ስርአቱ ነው።

ይህ የፌደራላዊ ስርአት እውን ከመሆኑ አስቀድሞ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የተናጋና የማንኛውም ዜጋ በህይወት የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ በእርስ በእርስ ጦርነቱ ምክንያት ዋስትናውም ያልተረጋገጠ ሆኖ የቆየ መሆኑ ይታወሳል።  የህግ የበላይነት የሚባል ነገር ፈጽሞ ሊታሰብ የማይችልበትና ንጉሱ ወይም ደርጉ የማይገሰሱና ለህዝብም ሆነ ለህግ ተጠያቂነት የሌላቸው ፈላጭ ቆራጭ መንግስታት የነበሩ መሆኑም በተመሳሳይ። ራሳቸውንም ከህግ በላይ አድርገው የሚቆጥሩና ህዝቡን ወደሁለተኛ ደረጃ ዜግነት በማውረድ ፍትህና ርትእ መጓደል የስርአቶቹ መለያ ባህርይ እንደነበር በአገዛዞቹ በግፍ የተጨፈጨፉት ንፁሃን ዜጎች ህይወት በታሪካችን ጥቁር ነጥብ ጥሎ ያለፈ ክስተት ነው።   

ይህ የፌደራላዊ ስርአት በዋናነት ከህግ በላይ የሆኑትን ኢዴሞክራሲያዊ መንግስታት በማስወገድ በምትኩ ለመረጠው ህዝብና ለህግ ተጠያቂነት ያለውን የዴሞክራሲያዊ ስርአት መሰረት ጥሏል። በዴሞክራሲያዊ መንግስት የተቀረጹት ህጎች ሕገመንግስቱን እና ሌሎች ከሱ የሚቀዱ ህጎች በማንኛውም ባለስልጣን ወይም ህግ ወይም ልማዳዊ አሰራር እንዳይጣስ የሚከላከልና የሚጠብቅ የፍትህ ስርአት በአገራችን እንዲገነባ አስችለዋል።  

የመጨረሻው የስልጣን ባለቤት ህዝቡ በመሆኑ በህዝቡ ይሁንታ የጸደቁትን ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ተግባራዊ የማድረግ፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር፣ በጥቅሉ የህግ የበላይነት የነገሰባት አዲስ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሂደት የፍትህ አካላት ሚና ከፍተኛ ነው። ፈጣን የኢኮኖሚ እድገቱን ተከትሎ ዜጎች በውል ህግ አሰራር ላይ የተመሰረተ ግልፅ የቢዝነስ ግንኙነት እንዲፈጥሩና ኢንቨስትመንት እንዲቀላጠፍ የፍትህ አካላት ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው።  

በዚህ በኩል በፌዴራል፣ በክልልና ከዚያ በታች በሚገኙት አስተዳደር አካላት ህዝቡን የፍትህ ተደራሽ በማድረግ ባለፉት 26 አመታት፣ በተለይ ደግሞ ከተሃድሶ ንቅናቄ ወዲህ በርካታ ለውጦች ተመዝግበዋል። በዚህም መሰረት በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዓመታት ጊዜ ውስጥ በተደረጉ ጥረቶች ከዓለም አቀፍ ሕጎች፣ ከአገሪቱ ሕገ መንግስትና ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር የተጣጣሙ ብቻ ሳይሆን ለሰብአዊ መብቶች የላቀውን ስፍራ የሰጡ የህግ ረቂቆች እንዲዘጋጁ ተደርጓል። ለሃምሳ አመታት ስራ ላይ የቆየውን የወንጀል ህግ የወቅቱ የህብረተሰብ የእድገት ደረጃ እና ቴክኖሎጂ እድገት ጋር ተያይዞ በመስፋፋት ላይ የሚገኙትን (ጠለፋ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ሽብርተኝነትና አክራሪነት፣ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ኮምፒውተር መረጃ ስርቆት ወዘተ) በተያየዥ የተከሰቱና የሚከሰቱ ወንጀሎችን ለመከላከል በሚያስችል መልኩ የህግ ማሻሻያ ተደርጓል።

የሴቶችንና ህጻናትን ጉዳይ የሚመለከቱ የተለዩ የዳኝነትና የፍትህ አሰራርና አደረጃጀቶችን በመዘርጋት የህብረተሰቡን የፍትህ ጥያቄ ለመመለስ ጥረት ተደርጓል። ይሁን እንጂ ዘርፉ ለበርካታ ዘመናት በልምድና በኋላቀር አሰራር ሲመራ የቆየ በመሆኑ የተለያዩ ተከታታይ የሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውና ለውጥም መመዝገቡ ባይካድም አሁንም ድረስ ዘርፉ ለኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ድርጊት የተጋለጠ ሆኖ ቆይቷል። በታራሚዎች አያያዝና የተፋጠነ ፍትህ አሰጣጥ ሂደት የሚታዩ በርካታ ውስንነቶች አሉ። በቀጣይ እነዚህንና ሌሎችንም ለኪራይ ሰብሳቢነት አሰራር የተጋለጡ ጉዳዮችን ለይቶ መፍታትና በየደረጃው ለፍትህ አገልግሎት ጠያቂው ተደራሽና ተአማኒነት ያላቸውን ፍትሃዊና ተገማች ውሳኔዎችን በማስቻል ሊጠናከር ይገባል።

በጥቅሉ ሲታይ ከጀማሪ ዴሞክራሲ ስርአቱ በህብረተሰብ ደረጃ የህግ የበላይነትን የሚሸረሽሩ ኋላቀር አመላካከቶችና ፍላጎትን በሃይል የማስፈጸም ዝንባሌ አሁንም ያልተቀረፈ ቢሆንም፤ አዳዲስ አሰራሮችና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ችግሩን ለመፍታት የተደረገው ጥረት ሊበረታታ የሚገባውና በህዝብ ተሳትፎ የምንፈልግበት ደረጃ ላይ የሚደርስ መሆኑን ያለመጠራጠር ለመቀበል የሚያስችል ፌደራላዊ ስርአት ተዘርግቷል ብሎ ለመውሰድ ይቻላል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy