Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለሰንደቅ ዓላማው ክብርና ፍቅር እንስጥ!

0 330

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለሰንደቅ ዓላማው ክብርና ፍቅር እንስጥ!

ዳዊት ምትኩ

አዲሱ ትውልድ የዛሬ 23 ዓመት ገደማ የኢትዮጵያ ህዝቦች በህገ መንግስታቸው ላይ ያሰፈሩት የሰንደቅ ዓላማ መርሆዎችን ማወቅ ይገባዋል። አውቆም ለሰንደቅ ዓላማው ክብር ሊቸረው ይገባል። ዛሬ በመላው አገራችንና በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ከፍ ብላ የምትውለበለበው ሰንደቅ ዓላማችን ውድ የህዝብ ልጆች በከፈሉት የህይወትና የአካል መስዋዕተነት የተገኘች ናት። እናም ትውልዱ ሊያከብራትና ፍቅርም ሊያድርበት ይገባል። ይህን አለማድረግ ትናንት ሰንደቅ ዓላማውን ለማስገኘት ማናቸውንም ዓይነት መስዕዋትነትን የከፈሉ የህዝብ ልጆችን ውለታ እንደ መርሳት የሚቆጠር ይመስለኛል።

በህገ መንግስቱ አንቀፅ ሶስት ላይ ሰንደቅ ዓላማውን አስመልክቶ የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሃል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በመሃሉ ብሔራዊ አርማ (ኮከቡና ጨረሮቹ) እንደሚኖሩት በግልፅ ተቀምጧል። ህገ-መንግስተን ተከትሎም በዚህም በ1988 ዓ.ም. በቁጥር 16/1988 “የሰንደቅ ዓላማና አርማ አዋጅ” እንዲወጣ መሰረት ጥለዋል—ደማቸውን ዋጅተውና አጥንታቸውን ከስክሰው ሰንደቅ ዓላማውን ላስረከቡን ውድ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ልጆች ክብርና ምስጋና ይግባቸውና።

ታዲያ ይህን ዕውነታ በሚገባ የተገነዘቡት የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች የሰማዕታቱን አደራ ተቀብለው በተለይም ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በሰንደቅ ዓላማው ጥላ ስር ተሰባስበው አያሌ ሀገራዊ ተግራትን ፈፅመዋል። ዙሪያ መለስ ዕድገትን እያስመዘገቡም ዛሬ ላይ መድረስ ችለዋል። ሰንደቅ ዓላማውን የማንነታቸው መገለጫ በማድረግም በአንድነትና በእኩልነት ዘልቀዋል።

የኢፌደሪ ሰንደቅ ዓላማ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብዝሃነት መገለጫ ነው። አደሲቷ ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም ሃይማኖቶችና ቋንቋዎች የሚገኙባት ናት። ባለፉት ዓመታት ይህን ልዩነት እንደ ጥንካሬ በመውሰድ የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት የተፈጠረው ብሎም ብጥብጥና ሁከት ውስጥ እንዳትገባ ማድረግ የተቻለው ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚችልና ዘለቂና ቀጣይነት ያለው ልማት ማረጋገጥ ስለተቻለ መሆኑ እሙን ነው። ለዚህም ደግሞ ዋስትናው ህገ-መንግስቱ ነው።

እርግጥ በህገ-መንግስቱ ሳቢያ ሁሉም ዴሞክራሲያዊ መብቶች (የግልና የቡድን) በተቀናጀ መልኩ አንዱ የሌላውን በሚደግፍ አኳኋን ተመልሰዋል። በዚህም ብዝሃነትን ለማስተናገድ ችግር የነበሩ በርካታ ጉዳዩች ሊመለሱ ችለዋል። ይህም የሀገሪቱ ልማት ላለፉት 14 ዓመታት ያለ አንዳች ሳንካ ፈጣንና ተከታታይ በሆነ መንገድ እንዲቀጥል አድርጓል።

እርግጥ ባለፉት ዓመታት ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ትሩፋት ሊገኝ የቻለው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግስት እየተመሩ ብዝሃነታቸውን የጥንካሬያቸው ምንጭ አድርገው በሰንደቅ ዓላማው ስር ተሰባስበው ሌት ተቀን በመስራታቸው መሆኑን ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም።

በአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ልዩነቱን የጥንካሬው መሰረት አድርጎ በመቁጠር በ‘ባንዴራው’ ስር ተጠልሎ ድህነትን ለማሸነፍ ላለፉት ዓመታት ታግሏል። የትግሉ ባለቤትም በመሆን ላይ ይገኛል። ለዚያውም ከዓለም በፈጣን ዕድገት ከቻይና እና ከህንድ ቀጥሎ የልማት ተምሳሌታዊ ማማውን ጫፍ ላይ ሰቅሎ። እናም ድሉን ይበልጥ ለማጠናከር የሚችልበትን በዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ከአንዴም ሁለቴ ተልሞ ወደ መከከለኛ ገቢ የመገስገስ ራዕዩን ተያይዞታል—ነገሩ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንዲሉት ነውና።

አበው “ለብልህ አይነግሩትም” እንዲሉ፣ በሁሉም የልማት ዘርፎች ከጫፍ እሰከ ጫፍ በመንቀሳቀስ በ‘ባንዴራው’ አጊጦና አሸብርቆ የትናንት የውርደት ምንጩ የሆነውን ድህነት ዛሬ ላይ ድል በመንሳት ወደ ፊት እየገሰገሰ ነው። ብዝሃነቱ የድሉ ምንጭ እንጂ የልዩነቱና የመፋለሱ ምክንያት እንዳልሆነ ላለፉት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዓመታት በተግባራዊ ክንዋኔው ያረጋገጠው ይህ ህዝብ፤ ነገም ይህን ጥንካሬውን አጠናክሮ መቀጠሉ አጠያያቂ አይሆንም።

ይሁንና ከዚህ የህዝቡ ፍላጎት ውጪ በሆነ መንገድ በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፆች ፀረ-ሰላም ሃይሎችና እዚህ ሀገር በተጨባጭ በመምጣት ላይ ያለውን ለውጥ የማይፈልጉ የውጭ ሃይሎች በሰልፍ ሰበብ የሀገራችን ሰንደቅ ዓላማ ለማኮስመን ጥረት እያደረጉ ነው። ይህ ደግሞ የህዝቦች አንድነትና እኩልነት የሆነውን መሰረታዊ ጉዳይ አለመቀበል በመሆኑ ከህገ መንግሰቱ ጋር የሚጣረስ ነው። ተቀባይነትም ሊኖረው አይችልም።

እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ የሀገራችን ህዝቦችና ሃይማኖቶች አንድነትና እኩልነት መገለጫ በመሆን ዜጎች በስሩ ተሰባስበው ዛሬ ላይ ለተገኘው ሁለንተናዊ ለውጥ መሰረት ነው። ስለ ሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት ሲነሳ፤ ጉዳዩ አንድነት ፈጣን ልማትንና የጋራ ተጠቃሚነትን ከማስገኘት አኳያ ያለው ፋይዳም ከግምት ውስጥ ገብቶ ይመስለኛል።

ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚገነዘበው በየትኛውም ሀገር ውስጥ በቡድንም ይሁን በሀገር ደረጃ ከአንድነት ውጪ የሚከናወን ምንም ዓይነት ነገር የለም። እርግጥ አንድነት ሲኖር ፈጣን ልማትና የተሻለ አቅም መፍጠር እንደሚቻል አያጠራጥርም።

አንድነት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የህዝቦች ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ የሚችለው እኩልነትና መፈቃቀድ ሲኖሩ ይመስለኛል። አዲሱ ትውልድ ይህን እውነታ መገንዘብ አለበት።

አዲሱ ትውልድ በሰንደቅ ዓላማው መሃል ላይ ያለውና የሀገራችንን ብሔረሰቦች በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነትን የሚያንፀባርቀውን አርማን መንካት ማለት የእነርሱን ህልውና መካድ መሆኑን ማወቅ ይኖርበታል። በሀገራችን የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጁ ቡድኖችን ይዞ በአደባባይ መውጣት ክልክል መሆኑንም ማወቅ አለበት።

ይህን መሰሉን ህልውናን የሚክድ ተግባር የሀገራችን ህዝቦች ሊቀበሉት አይችሉም። ተግባሩም ከእነርሱ ፍላጎት ውጪ በፀረ-ሰላም ኃይሎች አማካኝነት የግል ፍላጎትንና ጥቅምን ማዕከል በማድረግ የሚናወን በመሆኑ ተቀባይነት የለውም።

ህዝቦች በራሳቸው ፈቃድ እውን ያደረጉት ስርዓት ላይ የተጋረጠውን ኢ-ዴሞክራሲያዊ አደጋ ስለሆነ በደማቸው እውን ያደረጉትን ስርዓት ለማስጠበቅ እንደሚታገሉ መገንዘብ አለበት።

በመሆኑም አዲሱ ትውልድ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከፊውዳሎችና ከአምባገነኖች ጋር የታገሉት ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን ዕውን ለማድረግ በመሆኑ፤ በጥቂት ኢ-ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሳቢያ የታገሉላቸውን መብቶቻቸውን አሳልፈው ሊሰጡ የሚችሉበት ምክንያት እንደሌለ ማወቅ አለበት። ምንም እንኳን አዲሱ ትውልድ ስለ ሰንደቅ ዓላማችን ግንዛቤ ቢኖረውም የሚያደርጋቸውን ማናቸውንም ተግባራት በሰንደቅ ዓላማው ስር ሆኖ መፈፀም እንደሚኖርበት መዘንጋት አይኖርበትም። በዚያኑ ልክም ለሰንደቅ ዓላማው ክብርና ፍቅር ሊቸር ይገባዋል።        

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy